ሰሞኑን የዓመቱ የትምህርት ስራ በመላው ኢትዮጵያ ተጀምሯል:: ከ34ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድም ጀምረዋል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዚህ ዓመት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን በመከላከል በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እንደሚሠራ አሳውቋል:: ይህ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ መግለጫ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የሚመለከት ነውና ዛሬ ስለ እሱ ልናወጋ ወደድን::
ወደ ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት በመጀመሪያ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የግብረ-ገብ እና የዜግነት ትምህርት እንዲሁም ለሥራ እና ክህሎት ሥልጠና ስለተካተተ መንግስትን ደግ አደረግክ በርታ ልለው እወዳለሁ:: ተማሪዎች ጭንቅላታቸው፤ እጃቸውም፤ ልባቸውም የሚሰራ ሆነው እንዲያድጉ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው:: በተለይም ሁሉም ሰው ዩኒቨርሲቲ ሊገባ እንደማይችል ከተረዳን ትውልዱ እጁን እንዲፈታ ማድረግ እና የራስን ተሰጥኦ እንዲፈልግ ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነው::
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ የትምህርት ቤቶች አካባቢ ጸጥታ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው:: በተለይም በከተሞች አካባቢ ይህ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው:: እንዴት ተደርጎ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚችልም ለማወቅ ከባድ ነው:: የሆነ ሆኖ ትምህርት ቤቶች ከሁከት የጸዱ መሆን አለባቸው የሚለው ጉዳይ አከራካሪ አይደለም:: በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ አንድ ትምህርት ቤት ዙሪያ ከትምህርት ስራው ጋር የሚቃረን ሌላ በርከት ያለ የንግድ ተቋም ይፈለፈላል ቢባል ማጋነን አይሆንም:: በትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ባር፤ ከጀርባው ሺሻ ቤት፤ ከጎኑ ጭፈራ ቤት፤ ከፍ ብሎ ጫት ቤት፤ እልፍ ብሎ ማሳጅ ቤት፤ ከዛ ደግሞ ፔንስዮን ወዘተ እያለ ይቀጥላል:: እነዚህ የንግድ ተቋማት ተማሪዎችን ወደ ደንበኝነት ከመሳብ አንስቶ ለሌሎች ሱሶች (ሲጋራ፤ ጫት፤ ሺሻ) እስከማለማመድ ብሎም ሴት ተማሪዎችን ለወሲብ ንግድ እስከ መመልመል የሚደርሱ ናቸው:: ለእነሱ ትምህርት ቤቱ የገበያ ምንጭ ነው:: ለትምህርት ቤቱ እነሱ አደጋዎች ናቸው::
እስኪ በአይነ ልቡናችን የምናውቃቸውን ትምህርት ቤቶች እናስታውስ:: ለምሳሌ ያህል ዳግማዊ ምኒሊከን፤ ጥቁር አምበሳን፤ ቦሌ ሁለተኛ ደረጃን ወዘተ… እናስታውሳቸው:: እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው ከ10 የሚበልጥ መጠጥ ቤት 500 ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ይዘዋል:: ተማሪው እነዚህን መጠጥ ቤቶች፤ የሚከፍቱትን ሙዚቃ፤ የሚያወጡትን ጠረን እና ሌሎችም ሳቢ ሁኔታዎች ተቋቁሞ ነው ትምህርት ቤት መግባት የሚገባው:: ይህን ስበት መቋቋም የሚችሉ ይኖራሉ:: ነገር ግን ብዙው ተማሪ ወጣት ነውና ከእድሜም ከብስለት ማነስም ሰንብቶም ቢሆን በዚህ ወጥመድ ውስጥ መግባቱ አይቀርም:: ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን እና ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል::
እንዲያው ብዙ ርቀት ሳንሄድ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ የሚሆን አዲስ ዘመናዊ ተቋም ማዘጋጀቱ ችግሩ ምን ያህል እንደደረሰ አመላካች ነው:: ተቋሙ የተስፋፋበት ዋነኛ ምክንያት እድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላ ከባድ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈው የሚገኙ ወጣቶችን ለማረም ተብሎ ነው:: አብዛኞቹ ወጣቶች ወደዚህ የገቡበት አንደኛው ምክንያት ትምህርት ቤት ብለው በወጡበት ወቅት የለመዱት ሱስ ገፊ ምክንያት ሆኖባቸው ነው:: ስለዚህም በነዚህ ልጆች ወንጀል ላይ በትምህርት ቤቶቻቸው ዙሪያ ያሉ መጠጥ ቤቶች፤ ጫት ቤቶች፤ ሺሻ ቤቶች እና ሌሎች ድርሻ አላቸው ማለት ነው:: ከዚህም ባለፈ ዛሬ ላይ በተለያዩ የግል፤ የመንግስት እና የሀይማኖት ተቋማት በወጣቶች ላይ የሚሰራው ስራ መነሻ ምክንያቱ ወጣቶች በሱስ እየተጠለፉ እንደሆነ መታየቱ ነው::
በአንድ ወቅት በአንድ የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰራ የተማሪ ማማከር ባለሙያን ባናገርኩበት ወቅት የተረዳሁት እውነታውም እነዚህ በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማት ቁጥራቸው እየጨመረ እና በተማሪዎች ላይ ያላቸው ተጽእኖም እያየለ እንደመጣ ነው:: በዚህም የተነሳ ትምህርት ቤት ብለው ወጥተው ሺሻ እና ጫት ቤት የሚውሉት ተማሪዎች ቁጥር እየበረከተ እንደመጣ፤ ብዙ ተማሪዎች እዚያው ትምህርት ቤት በር ላይ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን እንደሚቀይሩ እና ወደነዚህ ቦታዎች እንደሚገቡ፤ ብዙ ተማሪዎች በተላመዱት ሱስ የተነሳ ክፍል ውስጥ ተረጋግተው ትምህርት መስማት እንደማይችሉ እና ብዙ ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ መጸዳጃ ክፍል ሲጋራ እና ሌሎች አደንዛዣ እጾችን ሲጠቀሙ እንደሚያዙ፤ በሚያሳዩት ባህሪ የተነሳ ከመምህራኖቻቸው ጋር እስከ ድብድብ የደረሰ ጠብ ውስጥ የገቡ ተማሪዎች መኖራቸውን፤ አንዳንድ ተማሪዎችም በሱስ የተነሳ ትምህርት እስከ ማቋረጥ ብሎም ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ እስከመሆን እንደደረሱ ወዘተ ነግሮኝ ነበር::
በእርግጥም እነዚህ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማት በተማሪዎች ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የተወሰኑትን ብንጠቅስ አንደኛው በተማሪዎች ላይ የውጤት ማሽቆልቆል፤ ከትምህርት ቤት መቅረትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ አለመሆን እንዲሁም ትምህርት ማቋረጥ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ናቸው:: ሁለተኛው ጉዳት የአካላዊ ጤና መዛባት ነው:: አብዛኛውን ጊዜ በከተሞች አካባቢ የሚታዩት አደጋዎች ለምሳሌ ያህል የመኪና አደጋ እንዲሁም እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በወጣቶች ላይ የሚከሰቱት በሱስና አደንዛዥ ዕፅ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች ናቸው::
በሌላ መልኩ በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ከሱስ ነጻ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸሩ ለተለያዩ የአእምሮ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው:: ለምሳሌ ድብርት፤ አስቸጋሪ ጠባይ፤ የስብዕና መቃወስ፤ እራስን ለማጥፋት ማሰብና መሞከር እንዲሁም ማጥፋት ተጠቃሽ ናቸው:: ጉዳቱን በማህበራዊ መልኩ ስናየው ደግሞ ወጣቶቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ሁሉ ሱሳቸውን ለማስታገስ የሚጠቀሙበት ሲሆን ያን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ወደ ወንጀል ሊሰማሩ ይችላሉ:: እንዲህ እንዲህ እያልን በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ መጠጥ ቤቶች ልጆችን ለምን አይነት ችግር እንደሚጋብዙ መዘርዘር እንችላለን::
ስለዚህም ዘላቂው መፍትሄ በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ተቋማትን ማጽዳት መሆን አለበት:: ከዚህም ባለፈ ግን በዚህ ዙሪያ ለተማሪም ለወላጅም ለሌላውም ግንዛቤ መፍጠር እና በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል:: አዋኪ ነገሮችን የማጽዳት ስራው የሌሎችን ሰርቶ የመኖር መብት የማይጋፋ እንዳይሆን፤ እንቅስቃሴውም ትምህርት ቤትን ብቻ ሳይሆን መኖሪያ አካባቢዎችን ያማከለ እንዲሆን ማድረግ ስለሚስፈልግ ስራው በህግ የተቃኘ፤ በስትራቴጂ የሚመራ እና ዘለቄታ ያለው ሆኖ መሰራትም አለበት::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም