ጉራጌ ብቻውን አያድግም፤ ሲያደግም አንተን ይዞህ ያድጋል።አገር ሆኖ ሰፍቶ ያለውን አካፍሎ ከሌለው ላይ አጉርሶ ወንድም እህት አባት ሆኖ አብሮህ ያድጋል።ከታዋቂዎቹና አንጋፎቹ ጋዜጠኞች ጀርባ አንድ ገመና ሸፋኝ ታታሪ ወጣት ነበር።አሁን ያ ወጣት የአንድ ታዋቂ የጉራጌ ባህላዊ ሬስቶራንት ባለቤት ሆኗል።
አንጋፋ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ መድረክ ላይ የእሱ ውለታ እንዳለባቸው ሲናገሩ ማድመጥም የተለመደ ነው።በእነሱ ትዝብት እንደውም የዚህ ታታሪ ወጣት ውለታ ተከፍሎም የሚያልቅ አይደለም።ሁሌም በየመድረኩ ስለዚህ ወጣት ሲጠየቁ ወደኋላ በመመለስ የሆነውንና ይደረግ የነበረውን በምን ሰዓት ምን ዓይነት ውለታ ይውልላቸው እንደነበር መናገር የሁሉም ደስታ ነው። ውለታውን ሲያወሩ ደግሞ ትልቅ አክብሮትን ፍቅራቸውም ከፊታቸው ላይ የሚነበበው ብዙዎቹ ላይ ነው፡፡
ወጣቱ ጠንክር ቴኒ አሁን ላይ በጥረት የአንድ ታዋቂና ትልቅ የጉራጌ ሬስቶራንት(ቶቶት) ባለቤት ሆነዋል።ጠንክር እዚህ ለመድረሱ ብዙ ጥረዋል፤ ለፍተዋል፤ ከሊስትሮነት ተነስተውም ያሰቡበት ደርሰዋል።በዚህ የስራና የኑሮ ውጣውረድ ጊዜ ውስጥ ደግሞ በርካቶች ተቸግረው እንዳይቀሩ ባላቸው አቅም እያበደሩም እየሰጡም ተስፋ ሆነዋቸዋል።ይህንን ስራቸውን ደግሞ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
ታዋቂውና አንጋፋው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ስለእሳቸው ሲናገር ከሰማሁት ውስጥ “ጠንክር ማለት የልብ አውቃ ውስጥ አዋቂ ደራሽ ነው፤ ጠንክር ካለ ችግር የለም፤ ባሻህ ሰዓት ያበድርሃል ደመወዝ ስትቀበል ጠብቆ ያስከፍልሃል” ነበር ያለው፡፡
ሌላው አንጋፋ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ስራ ባለሙያ ሳምሶን ማሞ ደግሞ “ምን ጊዜም ሲቸግረኝ ቀድሜ የማደርገው ነገር ጠንክር በስራ ቦታው ላይ መኖሩን ማረጋገጥ ነው። ምክንያቱም ጠንክር ካለ አበዳሪ አለ፤ ከዛ ችግር ይወገዳል ማለት ነው ” እያለ ስለጠንከር የክፉ ቀን ወዳጅነት ፈጥኖ ደራሽነት ይናገራል። እነዚህ ብቻም አይደሉም የትልቁ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የስራ ባልደረቦች አብዛኞቹ የጠንክር ጥገኞች ነበሩ ቢባል ምንም ማጋነን አይሆንም። ይህ ወጣት ጋዜጠኞቹ የመንግስት ደመወዝተኛ ሆነው እሱ ደግሞ እነሱን ጨምሮ የሌሎች አላፊ አግዳሚዎችን ጫማ በመጥረግ ከሚያገኙት ገቢ እንዳይቸግርቸው ያበድሯቸው የነበረ መሆኑ ነው ትልቁ ሚስጥሩ፡፡
ለዚህ የማይዘነጋ ውለታቸው ደግሞ እንኳን ሰዎቹ የኢትዮጵያ ሬዲዮም አልዘነጋውም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ሬዲዮ ጣቢያው የተመሰረተበትን 85ተኛ ልደት በዓሉን ሲያከብር ጠንክር ቴኒን የጋዜጠኞቻችን ባለውለታ በማለት በይፋ ማመስገኑ ነው።
ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ብዙ ትዝታ አለኝ የሚሉት አቶ ጠንክር “……አገር ቤት ሆኜ ሬዲዮ ስሰማ ጋዜጠኞቹ ይመስሉኝ የነበረው ቦታ ጠቧቸው የሚጨናነቁ ሰዎች አልያም ደግሞ ሰይጣኖች ነበር፤ ነገር ግን ምነው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ አልም ነበር፤ የሕይወት አጋጣሚ ሆኖ ግን እኔ ከአገሬ በመጣሁ በሶስተኛው ወሬ ስራ የጀመርኩት የኢትዮጵያ ሬዲዮ በር ላይ ሆኖ አረፈው” ይላሉ፡፡
‹‹ስራ በጀመርኩ በሶስተኛ ወሬ ደግሞ ብርሃኑ ገብረማርያም ቃለምልልስ አድርጎልኛል።እዛ በር ላይ ጫማችንን ይጠርጋል ብለው እንዳቸውም ንቀውኝ አያውቁም፤ እንዲያውም በጣም ያከብሩኛል፤ ሰርግ ይጠሩኛል፤ አራስ እመርቃለሁ፤ የተቸገረ እረዳለሁ፤ የሌለው ይበደራል፤ ሲያገኝ ይመልሳል በጠቅላላው በጣቢያው ሰራተኞች ተወድጄ ተከብሬ እንደ አንድ የስራ ባልደረባቸው አክብረውኝ ነው እዚህ ያደረሱኝ›› በማለት ጠንክር መነሻቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ጠንክር ቴኒ ከወይዘሮ አጸደ ተስፋዬና ከአቶ ቴኒ ጉያ አብራክ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ነው ወልደታቸው። ብላቴናው ጠንክር አገር ቤት እያሉ እንደ እኩዮቻቸው ከብት ጠብቀዋል፤ ጭቃ አብኩተው ከእኩዮቹ ጋር ተጫውቷል ፤ ብቻ በአገር በወንዙ ለልጅ የሚሆኑ ነገሮችን ሁሉ አከናውነዋል።ጠንክር በአገር ቤት ከእኩዮቹ ጋር ከሚያደርጉት መስተጋብር ቤተሰቦቻቸው ለማገዝ ላይ ታች ከሚለው ስራ አረፍ ሲሉ ደግሞ ልማዳቸው የነበረው ሬዲዮ ማድመጥ ነበር።ብቸኛ የነበረውን የኢትዮጵያ ሬዲዮ አብዝቶ ከማዳመጥ የተነሳም የሰዎቹ አድናቂ እንዲሁም ብተዋወቃቸው እያሉ ዘወትር የሚመኙ ወጣትም ነበሩ፡፡
ጉራጌ ስራ ልምዱ ለውጥም ህልሙ እንደመሆኑ አብዛኛው የጉራጌ ማህበረሰብ አገር ቤት የሚቆየው ጫንቃው ለስራ ዝግጁ እስከሚሆን ድረስ ብቻ ነው። ጠንክርም በአገር ቤት ለመቆየት የቻሉት እንደ እኩዮቹ ወይም የአገሩ ልጆች ጫንቃቸው ስራን መሸከም እስከሚችል ጊዜ ብቻ ነበር።ለስራ መድረሳቸውን እርግጠኛ ሲሆን ግን በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ማምራትና ስራ ሰርቶ ራሳቸውን መቻል ብሎም መለወጥ እንዳለባቸው በመወሰን አዲስ አበባ ገቡ፡፡
ገና በዛ ለጋ እድሜያቸው ሰፊዋን አዲስ አበባ ሲቀላቀሉ ዛሬ ላይ ያለው ማንነት ይመጣል ብለው ባያስብም ጠንክሮ ከተሰራ ግን ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ ጠንቅቆ ያውቁም ነበር። በመሆኑም አዲስ አበባ ገብቶ የሊስትሮ ሳጥኑን አንስቶ ስራን ሀ ብሎ የጀመረው ድሮ ይመኘው ከነበር የሬዲዮ ጋዜጠኞች መዋያ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ (ከቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ) በራፍ ላይ ሆነ፡፡
አቶ ጠንክር እየሰሙ ካደጉት ጣቢያ በራፍ ላይ ለእግራቸው ጫማ ሳያደርጉ የሰዎችን ጫማ ማሳመር ጀመሩ።በዚህ ውስጥ ልጅነታቸው ብሎም የገጠሩ ኑሯቸው ተደማምሮ ለስራው እንግዳ ለአገሩ ባዕዳ ቢሆኑም የሰዎች ካልሲ እያበላሹ፤ ቀለም እያባከኑና አንዳንድ ተግሳጾች እየደረሱባቸውም ቢሆን ስራቸውን በትጋትና በብቃት ማከናወኑን ግን ተያያዙት፡፡
ስራ ቢበዛባቸውም በሰሩት ገንዘብ ገቢ ቢያገኙም አገር ቤት ሆነው የጀመሩትን ትምህርት ከመማር ግን ያገዳቸው ነገር የለም፤ ምክንያቱም ገና ከጅምራቸው መድረሻቸው የታያቸው ብልህ ወጣት ስለነበሩ።በዚህም ቀን ቀን በ15 ሳንቲም የሰዎችን ጫማ ሲንከባከቡ ብሎም እዚህም እዚያም ሲላላኩ ይውሉና ማታ ደግሞ ለነጋቸው የሚሆናቸውን ሰንቅ ለማግኘት ከአስኳላው ዘልቀው እውቀትን ሲቀስሙ ያመሻሉ። ባለራዕይው ወጣት ጫማ መጥረግ ብቻውን ያሰቡበት እንደማያደርስ የተረዱም ይመስላሉ። በመሆኑም ከጫማ መጥረግ ስራቸው ጎን ለጎን ሌላ ስራንም መፍጠር እንዳለባቸው አሰቡ፤ በዚህም እዛው ጫማ የሚጠርጉባት ጥግ ላይ እንደ ሶፍትና ማስቲካ ያሉ ነገሮችን በመያዝ ሱቅ በደረቴ አይነት ንግድን ጀመሩ፡፡
ነገን ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ ጠንክሮ መስራትን አላማቸው ያደረጉት አቶ ጠንክር ሁለቱንም ስራቸውን በትጋት እየሰሩ የማታ ትምህርታቸውንም አጠናክረው እየተማሩ ለስምንት ያህል አመታት በስኬት አሳለፉ።በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ከላይ እንዳነሳነውም እሳቸውም እንደሚናገሩት በተለይም ለማስታወቂያ ሚኒስቴር (የኢትዮጵያ ሬዲዮ )ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ለችግራቸው ፈጥኖ ደራሽ አለሁ ባይ በመሆን ብዙ ውለታን ውለዋል።ይህ አለኝታነታቸው ደግሞ በተቋሙ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በሰራተኞቹ ዘንድ እንደ ወንድም፤ እንደ ቤተሰብ እንዲታዩ በሃዘን በደስታውም አብረው እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡
የሊስትሮ ስራ፣ ሱቅ በደረቴ እንዲሁም የማታ ትምህርት በዛብኝ ያላሉት ጠንካራው ጠንክር ከእነዚህ ሁሉ ስራዎች ጎን ለጎን ሰዎች ከምግብ ጀምሮ የሚፈልጉትን ነገር ከዚህ አምጣልን፤ ወደዚህ ውሰድልን ሲሏቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ይላላኩም ነበር።ይህ መላላካቸው ደግሞ በተለይም አሁን ለተሰማሩበት የንግድ ስራ ትልቅ መንገድ እንደከፈተላቸው እሳቸውም በአንደበታቸው ይናገራሉ፡፡
በመሆኑም በ1988 ዓ.ም የጀመሩት መላላክ በተለይም ምግብ ቤቶች ጋር እየሄዱ ምግብ ማምጣት ጥሩ የስራ ፍላጎት አሳደረባቸው፤ በየትኛው ዘርፍ ቢሰማሩም ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዛውም አመላከታቸው።በመሆኑም “ምግብ አምጣለን” እያሉ የሚልኳቸው ሰዎች በመበራከታቸው ብልጡ የንግድ ሰው በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉት አይነት ነገር እግረ መንገዳቸውን ገበያውን ማጥናት የት ምን ማደረግ አለብኝ የሚለውን በምን ብሰማራ ነገን ብሩህ አደርጋለሁ የሚለውን ማየት ጀመሩ፤ እውነትም ይህ ልፋታቸውና ድካማቸው ብሎም
ብልህነታቸው ታክሎበት የዛሬውን ጠንክርን እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆናቸው፡፡
ስራ ወዳዱ የብዙዎች ገመና ከታች የሆኑት አቶ ጠንክር ምን ቢያምራቸው ገንዘብ ማጥፋት ላይ ቁጥብ ናቸው።በዚህም ሊስትሯቸውን ብሎም ሱቅ በደረቴያቸውን እንዲሁም ለሚልኳቸው ሁሉ እየተላኩ አልበላም፤ አልጠጣም፤ አልዘንጠም ብለው ባጠራቀሙት ገንዘብ ምግብ ቤት የመክፈት ፍላጎት አደረባቸው።ፍላጎትን ወደተግባር ለመለወጥ ምንም የማይሳናቸው ግለሰቡም ያጠራቀሙትን 6ሺ ብር በመያዝ የምግብ ቤት ስራን ‹‹ሀ›› ብለው ጀመሩ፡፡
ወትሮም የሰው ፍቅር የስራ ፍላጎት የነበራቸው አቶ ጠንክር “ማሜ ምግብ ቤት” ብለው በከፈቱት ምግብ ቤት ውስጥ እንደ አዲስ ገበያ ፈላጊ እንደ ጀማሪ ነጋዴ አልተቸገሩም፤ ይልቁንም በደህና ቀን ያፈሯቸው ወዳጆቻቸው ለውጣቸውን ሲያዩ እጅግ ተደሰቱ፤ በሌላው ቀን ከሚመገቡበት ምግብ ቤት ንቅል ብለው የእሳቸውን ቤት መቀላቀል ጀመሩ፤ በዚህ ደግሞ ከፍ ያለ የስራ ሞራልና መበረታት ለበለጠ ስኬትም አበቃቸው፡፡
በስድስት ሺ ብር መነሻ ገንዘብ የተጀመረው “ማሜ ምግብ ቤትም” በመጀመሪያው የስራ ቀኑ ብቻ 49 ብር ሰራ ፤ ይህ ለታታሪውና ለስራ ሰው የምግብ ቤት ባለቤት ጥሩ መነሳሳትን ፈጠረ፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ደንበኞች በጣም በመብዛታቸው ለምሳ የተዘጋጀው ምግብ ገና 6 ሰዓት ላይ አለቀ።እሳቸውና ሁለት ሰራተኞቻቸውም የሚመጡትን ደንበኞች ፍጹም ተደስተው እንዲሄዱ ከፍ ያለ ትጋትን ያሳዩ ነበር።በወቅቱ ምግብ ቤቱ ላይ መጥተው የሚመገቡት ሁሉ በምግቡ ጣዕምና በመስተንግዶው ረክተው ከመሄዳቸውም በላይ በባለቤቱ ስራ ወዳድነትና ለውጥ ፈላጊነት ተደሰቱ።
ይህ ምግብ ቤት ስራው ጠንክሮ የደንበኞቹም እርካታ በተጀመረው መልኩ ቀጥሎ የስድስት ወር የልደት በዓሉን ለማክበር በቃ።በዚህን ጊዜ በጣም የሚገርመውና የባለቤቱን ትጋት የሚያሳየው ደግሞ ምግብ ቤቱ በእሳቸውና ሁለት ሰራተኞቻቸው ቢጀመርም ስድስተኛ ወሩ ላይ 17 ሰራተኞችን ያስተዳድር ነበር።ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙዎችን ያስደነቀ ሆኗል፡፡
አቶ ጠንከር ቴኒ ገንዘብን በቁጠባ መጠቀም ላይ ጽኑ እምነት አላቸው።እያንዳንዱ ገንዘብን ሳንቲም እሳቸው ጋር ሲደርስ ላቅ ያለ ዋጋ አለው።በዋዛ ፈዛዛ የሚባክን አምስት ሳንቲም የለም።ሱስ የለባቸውም በጠቅላላው ገንዘብን የሚያውሉት ነገ ይቀይረኛል ብለው ለሚያስቡት ስራ ብቻ ነው።ይህ ደግም በእጅጉ የጠቀማቸው አካሄድ ነው፡፡
አቶ ጠንክር ስራ መስራት ብቻውን ዋጋ እንደሌለውና የሰሩት በአግባቡ መጠቀም በተለይም ቁጠባ ትልቅ ዋጋ ያለውና ከፍ ያለ ቦታ ላይ የሚያደርስ ስለመሆኑ አብዝተው ይመክራሉ።
ተወልደው እዚህ እስከሚደርትሱበት ጊዜ ድረስ የጊዜና የገንዘብ አጠቃቀም የገባቸውና ምንም ዓይነት ብክነት ያላሳዩት አቶ ጠንክር ቴኒ የከፈቱትን ምግብ ቤት በየጊዜው የተለያዩ ተጨማሪ ምግቦችን እያካተቱ ቤቱንም ለእንግዶቻቸው በሚመጥን ሁኔታ እያዘጋጁ ዓመታትን አስቆጠሩ።በእነዚህ ዓመታት እርሳቸው ጥሩ የሚባል ገንዘብን ያገኙበት ከመሆኑም በላይ ለበርካታ ወገኖችም የስራ እድልን በመክፈት የብዙዎችን ጓዳ ሲሞሉ ሰዎች ሰርተው በሚያገኙት ገንዘብ ቤተሰባቸውን መርተው እንዲኖሩም ሲያስችሉ ነው የኖሩት፡፡
ማንም ሰው ትልቅ ሆኖ አልተፈጠረም ትልቅም ትንሽም የሚያደርገው ስራና ስራ ብቻ ነው።ለዚህ ማሳያው ደግሞ የአቶ ጠንክር ቴኒ የሕይወት መንገድ ይመስለኛል።ትላንት ከጋዜጠኞች ጀምሮ የብዙዎችን ጫማ ጎንበስ ብለው ያጸዱ ነበር፤ ያኔም ቢሆን ግን በቻሉት መጠን ባላቸው ነገር ለብዙዎችም የሚደርሱም ነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው፤ በትጋትና በጥረታቸው ሕይወታቸውን ስኬታማ ከሚባል ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል።ይህ ደግሞ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምሳሌ የሚሆን ነው።አቶ ጠንክር ከዚህም ባሻገር የጠንካራ ሰራተኝነትና የጥረት ውጤትም ናቸው፡፡
የጥንካሬ ተምሳሌት የሆኑት አቶ ጠንክር አሁን አቅሙም ገንዘቡም እንዲሁም የሰውም ተቀባይነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል፤ ከዚህ የተነሳም በ2001 ዓ.ም ፊታቸውን ከፍ ወዳለ ነገር ለማዞር ወሰኑ፤ የብዙዎች መዝናኛ እንግዳ መቀበያ ሰርግ ልደት ምርቃት ሌላም ሌላም የደስታ ሁነቶችን ማስተናገጃ የሆነውን “ቶቶት የባህል ምግብ አዳራሽ” እውን አደረጉ፡፡
ይህ የባህል ምግብ አዳራሽም አገርን የመወከል በተለይም የስራ ወዳዱን የጉራጌን ማህበረሰብ የማስተዋወቅ አቅም ያለውን የባህል ምግብ አዳራሽ ላለፉት 14 ዓመታት እየመሩ እዚህ ደርሰዋል፡፡
አቶ ጠንክር የባህል ምግብ ቤት በመክፈታቸው ከ 202 ያላነሱ ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ፤ ራሳቸውን እንዲችሉ ቤተሰብ መስርተው አገር እንድትቀጥል እንዲያስችሉም የራሳቸውን ሚና በመወጣት ላይ ናቸው፡፡
አቶ ጠንክር እንደ ብዙዎቹ አሰሪዎች ሰራተኛን ራሳቸው ጋር ዘላለም እንዲቆይ አይፈልጉም፤ አይመክሩምም፤ ከባዶ ተነስተው ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ የሆኑ ሰውም በመሆናቸውም ሰራተኞቻቸው በሚሰሩት ስራ ቤተሰባቸውን ከመምራትና ከማስተዳደር ባሻገር ሰፋ ያለ እቅድን ይዘው ነገን ለማሳመር ብሎም የራሳቸውን ስራ አስበው በዛ መልክ እንዲጓዙ ሁሌም ይመክራሉም።አንዳንዶቹም ይህንንን ህልማቸውን አሳክተውላቸዋል፡፡
አቶ ጠንክር አላማዬ ተሳክቷል፤ በቃኝ ብለው አይቆሙም ሁሌም አዲስ ነገር ያስባሉ።በሌላ በኩል ደግሞ የማገኘው ገንዘብ የእኔና የቤተሰቤ ብቻ ነውም አይሉም፤ ከዛ ይልቅ በተወለዱበት አካባቢ የሚጎድሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ ናቸው።በዚህም አካባቢያቸው ላይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመቀናጀት መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ስራ ላይ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላሉ።
በሌላ በኩልም የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራት ለወጣቶች የንግድና የፈጠራ ስራ ላይ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡም ሰው ናቸው፡፡
የስራ ፈጠራ እንዲሁም የጥንካሬ ተምሳሌት የጥሩ ስብዕና ባለቤት ብሎም ለሌሎች የስራ እድል ፈጣሪ በመሆናቸውም ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው የበጎ ሰው ሽልማት ላይ ቀርበው አሸናፊ ለመሆን ችለዋል፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም