ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ረጅም ዓመታትን ከኖሩባትና ዜጋዋ ካደረገቻቸው ሲውዲን ወደ አገራቸው ተመልሰው «አዲስ የልብ ህክምና ማዕከልን» ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር አቋቁመው ሀገራቸውን በሙያቸው ማገልገል የጀመሩት በ 1998 ዓ.ም ነው፡፡ ከ6 ዓመት በፊት «የህክምና መሳሪያዎችን ያለቀረጥ አስገብተዋል» በሚል ታስረው ከ4 ዓመት በላይ ፍርድ ሳያገኙ ተንገላትተው በመጨረሻ 4 ዓመት ከስምንት ወር ቢፈረድባቸውም ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ብለው ክሱን ውድቅ አድርጎ በነጻ ተሰናበቱ፡፡
በኋላም እርሳቸው ታመው ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ቂሊንጦ እስር ቤት የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ በመምራት እንደገና በሽብርተኛነት ተከስሰው ተጨማሪ ወራትን በእስር አሳልፈው በድምሩ ከአምስት ዓመት ከሦስት ቀን ታስረው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከእስር ተለቀቁ፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም በዜግነት ስዊድናዊ ስለሆኑ የስዊድን መንግሥት ከእስር እንደተለቀቁ ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ወሰዳቸው።
የደረሰባቸውን በደል በማሰብ ብዙዎች ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለሱ ገምተው ነበር፡፡ ዶክተር ፍቅሩ ግን እርዳታቸውን የሚጠብቁ ወገኖቻቸውን ለመተው አልፈቀዱምና ከአምስት ሳምንት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ በያዝነው ወርም ከስውዲን ሀገር የልብ ሀኪሞች ቡድን ይዘው በመምጣት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው የልብ ማዕከል ለስድስት ኢትዮጵያውያን ነጻ የልብ ህክምና ሰጥተዋል፡፡
«ከኢትዮጵያ ከሄድኩ ከአምስት ሳምንት በኋላ መመለሴ ብዙ ኢትዮጵያውያኖችንና የስዊዲን መንግሥትንም ገርሟቸዋል» የሚሉት ዶክተር ፍቅሩ በተለይ ደግሞ የስዊዲን ህዝብ ምንድን ነው ይሄ ሰውዬ አብዷል ? እስከ ማለት መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም «በመሰረቱ በሀገርና በህዝብ ላይ ቅያሜ የሚባል ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ ሀገሬ የኔ ነች ካልክ ከህዝብም አንተ አንዱ ከሆንክ እንዴት አድርገህ በራስህ፣ በመኖሪያህና በሀገርህ ትቀየማለህ ? ውጭ ሀገር መኖር የበለጠ ሀገርህን እንድትወድ እንጂ እንድትጠላ አያደርግህም፡፡
ስለዚህ አገሬን እንዴት እተዋለሁ ? እንዴት እቀየማለሁ ? እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ስዊዲን ሀገር ኖሬ የሲዊዲን ዜግነት ቢኖረኝም ኢትዮጵያዊነቴን የሚፍቀው የለም ይላሉ። ዶክተር ፍቅሩ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው የልብ ህክምና ማዕከል ስለሰጡት ነጻ ህክምና ሲገልጹ፣ እነዚህን ሀኪሞች ይዘን የመጣነው በአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታልና በታዝማ ሜዲካልና ሰርጂካል ስፔሻላይዝድ ማዕከል ተባባሪነት እስከ 15 የሚደርሱ ሰዎችን ለማከም ነበር፡፡ ነገር ግን ከውጭ የምናስገባው የህክምና ቁሳቁስ አይገባም ተብሎ ኮንቴይነሩ ጅቡቲ ሁለት ወር ሲቀመጥ ሐኪሞቹ ቀድመው መጡ፡፡ ከመጡ አይቀር በሚል ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የካርዲያክ ሴንተር ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊሞቱ የሚችሉ ስድስት ታማሚዎችን ልባቸውን ቀደን ሰው ሰራሽ «ቫልቭ» እንዲገባላቸው አድርገናል ብለዋል፡፡
ላለፉት አሥር ዓመታት ነጻ የልብ ቀዶ ጥገና እና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባሮች ሲያከናውን የቆየው የልብ ማዕከል ኢትዮጵያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሔለን በዶክተር ፍቅሩ አስተባባሪነት የመጣው የሐኪሞች ቡድን በሦስት ቀናት ውስጥ ስድስት የልብ መጥበብ ችግር ያለባቸው ታካሚዎች ዋጋው ውድ የሆነውን ሰው ሰራሽ ቫልቭ በማስገባት የተሳካ ቀዶ ጥገና ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከሲዊዲን ከመጣው ቡድን ጋር የእውቀት ሽግግር ማድረግ መቻሉን ፤ አንዳንድ እገዛዎች እንደተደረገላቸው ፤ ወደፊትም በጋራ በመስራት ህብረተሰቡን ለማገልገል መስማማታቸውንና ዶክተር ፍቅሩ ወደፊትም ማዕከሉን ከጎናቸው በመሆን በተለያየ መንገድ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶክተሩ ለዚህ ማዕከል ከዚህ በፊትም አልፎ አልፎ ተመሳሳይ እገዛ አድርገው እንደሚያውቁ ገልጸው፣ አንድ ታካሚ ልብ ውስጥ የምናስገባው የአንድ ሰው ሰራሽ ቁስ ዋጋ ብቻ ስልሳ ሺ ብር ነው፡፡ይህ ድጋፍ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
ከዚህ በኋላ ዶክተሮች ከሲዊዲን ሲመጡ ሰባት ቀናት አዲስ የልብ ህክምና ማዕከልና ታዝማ ፣ 3 ቀናት ደግሞ በልብ ይህን ተቋም ለመርዳት እንዲሰሩ እናደርጋለን፡፡ የህክምና መሳሪያዎችንም አሟልተንላቸዋል፤ ወደፊትም እናሟላላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም ማዕከሉ ለድሃ ህዝብ በነጻ ህክምና የሚሰጥ ስለሆነ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ህክምናውን ካገኙት ስድስት ታካሚዎች አንዷ የሆነችው ያስሚን ሁሴን፣ ህክምናውን ለማግኘት ሁለት ዓመት ወረፋ ጠብቃለች፡፡
ቤተሰቧችዋ እሷን ለማሳከም በሌለ አቅማቸው እንደምንም ብለው ውጭ ሀገር ሄደ እንድትታከም ሲጥሩ ቆይተው ቅዳሜ ወደ ውጭ ልትበር ተዘጋጅታ ረቡዕ ዕለት ተደውሎላት ይህን ዕድል ማግኘቷን ሲነገራት እስካሁን ድረስ ለማመን መቸገሯን እንቧ እየተናነቃት ተናግራለች፡፡ እንደ ዶክተር ፍቅሩ ገለጻ በየዓመቱ በልብ ህመም ምክንያት የሚሞተው ኢትዮጵያዊ በኤች አይቪ ኤድስና በወባ ከሚሞተው በላይ ነው፡፡ ተማረ የሚባለውን ህዝብ አርባ በመቶ የሚጨርሰው ይህ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው፡፡ ትልቁ ኃላፊነታችን መሆን ያለበት በሽታው እንዳይመጣ መከላከል ነው፡፡ «ስዊዲን ሀገር እንደኔ ያሉ ብዙ ሐኪሞች አሉ ፤ እኔ ለኢትዮጵያ ነው የማስፈልጋት» የሚሉት ዶክተር ፍቅሩ «ሲዊዲን ሀገር አክሜው ስወጣ በበለጠ መንገድ ለምን አልሰራኸኝም ብሎ የሚገላምጠኝ ታካሚ አለ፡ ፡ እዚህ እኮ አነጋግሬው ስወጣ ምስጋናና ትልቅ ክብር የሚሰጠኝ ታካሚ ነው ያለው፡፡
ይህን ስሜት ማንም አያገኘውም ፤ደስታ ስለሚሰጠኝ ለራሴም ስል ነው እዚህ መሆንን የምመርጠው » ብለዋል፡፡ በአዲስ የልብ ህክምና ማዕከል በክፍያ ስለሚሰጠው የልብ ህክምና ሲገልጹ፣ ለምሳሌ «ቫልቭ » የሚገባለት የልብ ታማሚ አሜሪካን ሀገር 60ና 70 ሺህ ዶላር ያወጣል፡፡ ታይላንድ ደግሞ 25ና 30ሺህ ዶላር ፡፡ «ፔስ ሜከር» ለምንለው የልብ ህክምና ለምሳሌ ኬንያ 18ና 20 ሺህ ዶላር ይከፈላል፡፡ እነዚህ ዋጋዎች ከመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች ውጭ ናቸው፡፡
አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል «ቫልቭ» ለሚገባለት ታካሚ ትልቁ የሚባለው ክፍያ ከ10 ሺህ ዶላር በታች ነው፡፡ «ፔስ ሜከር» ስንሰራ የምናስከፍለው ከ ሦስት ሺህ 500 ና አራት ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡ መሳሪያዎቻችንና ለህክምና የምናውላቸው ቁሶቻችን ግን ከአውሮፓና አሜሪካ የሚመጡ የተመረጡና ጥራት ያላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ሀኪሞቻችንም ስዊዲን ሀገር የተማሩና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ዋጋችን ከውጪው ዓለም ጋር በፍጹም ሊነጻጸር የሚችል አይደለም ብለዋል፡፡
በዓይነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር የልብና የልብ ነክ ህክምናዎች ፣ የምርምርና የስልጠና መስጫና የማገገሚያ ማዕከል የያዘ 25 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፕሮጀክት ቀርጸን ሁሉ ነገር አልቆ መሬት እንዲሰጠን ጠይቀናል የሚሉት ዶክተሩ፣ መሬት ካልሰጡን ምንም ማድረግ አንችልም ቦትስዋና እና ጋና ሁሉን ነገር እናቀርባለን እኛ ጋር ኑ እያሉ እየለመኑ ነው፤ እኔ ደግም እዚሁ ሀገሬ ላይ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡ለሀገሬ የገባሁትን ቃል ጠብቄ ህይወቴ እስካለ ድረስ በሞያዬ ላደርግ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
የትናየት ፈሩ