አዲስ አበባ፡- ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ ቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አብራሪዎች በአምራቹ ቦይንግም ይሁን በአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ እንደነበሩ የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ማመላከቱ ተገለፀ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የምርመራ ሂደት ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ሂደትና አሰራርን ተከትሎ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምርመራ ሂደቱን አደጋው የደረሰበት አገር በቀዳሚነት እየመራ የአውሮፕላኑ አምራች አገር፣ የአውሮፕላኑን ንድፍ (ዲዛይን) የሠራው አገር እና እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች አካላትም በዓለም አቀፍ ሕጉ መሰረት ተሳትፈውበታል ያሉት ሚኒስትሯ ምርመራው ያለምንም ችግር መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
የመርማሪ ቡድኑ በአውሮፕላኑ አደጋ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ተመስርቶ ያስቀመጣቸው እውነታዎችና ምክረ ሐሳቦች፤ አውሮፕላኑ መብረር የሚያስችል ሰርተፍኬት ያለው መሆኑ፣ አብራሪዎቹ ይሄንን በረራ ማድረግ የሚያስችላቸው ተገቢው የምርመራ ብቃት ያላቸው መሆኑ፣ አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛው መስመር ለመብረር በሚያስችለው ሁኔታ ላይ መሆኑ እና አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በአምራቹ ቅደም ተከተል መሰረት ማከናወን መቻሉን መርማሪ ቡድኑ ማረጋገጡን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
የመርማሪ ቡድኑ መሪዎችና አባሎች አውሮፕላኑ በሰላም ተንደርድሮ የተነሳ እንደነበር ማወቃቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በረራው ከተጀመረ በኋላ በተደጋጋሚ የአውሮፕላኑ አፍንጫ መደፈቅ ሲያሳይ አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በአምራቹ የተሰጠውን የበረራ ቅደም ተከተል ተከትለው አውሮፕላኑን በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ከአውሮፕላኑ የመረጃ ሳጥን የተገኘው መረጃ ከውጭ አካል በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰበት ጥቃት እንደሌለም ጠቁሟል፡፡ የአደጋው ሙሉ ሪፖርት በዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ እንደሚወጣም ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
ሙሐመድ ሁሴን