በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።አርሶ አደሩ ዝናብ ጠባቂ ብቻ ከመሆን እንዲወጣ እየተደረገ ባለው ርብርብ ለመስኖ እርሻ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ከመስኖ እርሻም በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ላይ ርብርብ መደረጉን ተከትሎ ውጤት እየታየ ነው፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳን በወንዝ እና ሀይቅ አካባቢዎች መስኖ በዋናነት አትክልትና ፍራፍሬ እየተመረተ የቆየ ቢሆንም፣ ዋና ዋና ሰብሎችን በመስኖ በብዛት ለማምረት፣ በተለይም ስንዴን ለማምረት መጠቀሙ በስፋት ያልተገበረ አሰራር ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡
መንግስት ለመስኖ ልማት በሰጠው ትኩረት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴርን አቋቁሟል፡፡ ሚኒስቴሩም የመስኖ መሰረተ ልማቶችን በመገንባቱ ስራ ተጠምዷል፡፡ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በቅርቡ የአምራችነት ቀን በተከበረበት ወቅት እንዳሉት፤ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሶሶ የሆነውንና ሰፊ የሰው ኃይል በመያዝም ድርሻ ያለውን የግብርና ሥራ በመስኖ መደገፍ ግዴታ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ መስኖ ለልማት እንዲውል በብዛት የመስኖ መሠረተ ልማት እንዲከናወን መንግሥት ጥረት አድርጓል፡፡
በ2013-2014 የምርት ዘመን የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን የመስኖ አገልግሎት ጥቅም ላይ መዋል አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የቆላና የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ይጠቀሳል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ የግብርና ሥራ በመስኖ እንዳይደገፍ ማድረግ በግብርና ምርታማነት ላይም ሆነ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በስንዴ ልማት ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብም የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት እንደ አገር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ በላቀ መልኩ ለመወጣት ወደ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሆን የእርሻ ማሣ በመስኖ እንዲለማ ለማስቻል ዝግጁ ነው፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተልእኮውን ይወጣል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የተጀመረው በቆላማ አካባቢዎች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ተስፋፍቷል፡፡ በሁሉም የአየር ንብረቶች ላይ ወንዞችን በመጥለፍና በመሳሰሉት መንገዶች ልማቱ እየተካሄደ ነው፡፡ በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት ብቻ ከ600 ሺ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በተካሄደ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማግኘት ተችሏል፡፡ በተገኘው የስንዴ ምርትም አገሪቱ የአገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎቷን ማሟላትና ለስንዴ ገዥ ይወጣ የነበረንም የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ችላለች፡፡ ልማቱ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ተቋማትን ትኩረት ሳይቀር መሳብ ችሏል፡፡
መንግስት የመስኖ እርሻዎችን ለማስፋፋት መስራቱን ቀጥሏል፤ በአገሪቱ በተያዘው 2015 በጀት አመት በበጋ መስኖ የሚታረሰውን መሬት ወደ አንድ ሚሊየን በማድረስ 40 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እቅድ ተይዟል፡፡ በዚህም የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ወደ ጎረቤት አገሮች ለመላክ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ክልሎችም የየራሳቸውን እቅድ አዘጋጅተው በበጋ መስኖ ልማቱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ብቻ በቅርቡ እንዳስታወቀው አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት አቅዷል፡፡ በክልሉ ለመስኖ ስራው የሚያስፈልጉ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች የማቅረብ ስራም እየተከናወነ ነው፡፡
በየክልሎቹ ስንዴ በመስኖ የማልማት ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎችም እየተካሄዱ ናቸው፡፡ የመስኖና ቆላማ
አካባቢዎች ሚኒስቴርም የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታዎ ችን በተለያዩ ክልሎች እያካሄደ ነው፤ ከእነዚህ ፕሮጀክቶቹ አንዱ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የሚገነባው ነው፡፡
የወላይታ ዞን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስኖ ምቹ ከሚባሉ አካባቢዎች መካከል የሚጠቀስ እንደመሆኑ የግድቡ መገንባት በርካታ ፋይዳዎች ይኖሩታል። ዞኑ በመስኖ ሊለማ በሚችል ለም የወል እና የአርሶ አደር ማሳ የታደለ ነው፡፡ በአካባቢው ወይቦ፣ ጋሞ፣ ሻፋ፣ ሶኬ፣ ቁሌ እና ዎተሬን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ የማይደርቁ ብዙ ወንዞች ይገኛሉ፡፡ ይህም አካባቢውን ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ ያደርገዋል፡፡
አካባቢው ለመስኖ ልማት የሚሆን መሬት እና ውሃ የታደለ ቢሆንም፣ እስካሁን በመስኖ የለማው መሬት መጠን በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በዞኑ ለመስኖ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ጥረቶች አንዱ በቆላማ አካባቢዎችና መስኖ ልማት ሚኒስቴር ባለፈው በጀት ዓመት ግንባታው የተጀመረው የወይቦ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ነው፡፡
ወይቦ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በሁለት ነጥብ 44 ቢሊየን ብር በጀት፣ በባለግርማ ሞገሱ ወይቦ ወንዝ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታው በኅዳር 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ በሰኔ ወር 2017 እንዲጠናቀቅ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦለታል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የኮሙ ዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ከፍ ያለ ፋይዳ የሚያስገኝ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እየተገነባ ያለው በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ወረዳና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ መካከል ነው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በአራት ቀበሌዎችና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ ደግሞ በሰባት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ለመስኖ ምቹ የሆነ መሬት እያላቸው በዓመት ዝናብ በመጠበቅ አንድ ጊዜ እያመረቱ ያሉ አርሶ አደሮች ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ ያስችላቸዋል፡፡
እንደ አቶ ብዙነህ ገለፃ፤ ፕሮጀክቱ ሦስት ሺህ 371 ሄክታር መሬት ለማልማት ያስችላል፡፡ ከዚህ ውስጥም አንድ ሶስተኛው ፈሮ በሚባለው የመስኖ ዘዴ (በትንንሽ የመስኖ ቦዮች አማካኝነት) የሚለማ ነው፡፡ ቀሪው ሁለት ሶስተኛው ደግሞ በዘመናዊው የርጭት ዘዴ እንዲለማ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም ፕሮጀክቱን ከሌሎች ፕሮጀክቶች ልዩ ያደርገዋል፡፡
የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የግድቡ ርዝመት 660 ሜትርና ከፍታው ደግሞ 33 ሜትር ነው፤ በ630 ሄክታር መሬት ላይ ውሃው ወደ ኋላ የሚተኛ ሲሆን፣ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው:: ይህም ውሃው በአካባቢው ከመስኖ ባሻገር ለሌላ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲውል እድል ይፈጥራል፡፡
ይህ ውሃ ከመስኖ ግብርና በተጨማሪ ለቱሪስት መስህብነትና ለዓሳ ምርት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የወይቦ ፏፏቴ የቱሪስት መስህብ እየሆነ ይገኛል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከፏፏቴው ጋር በመሆን አካባቢውን ይበልጥ የቱሪስት መዳረሻ ያደርገዋል፡፡
ፕሮጀክቱ እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ ባሻገር የአካባቢውን ኢኮኖሚ የማነቃቃት እድል ስለሚኖረው ለሚገነባበት አካባቢ ህዝብ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ግንባታው እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅትም ቀላል የማይባል ጥቅም እያስገኘ ነው፡፡ ለ185 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ተጨማሪ የስራ እድሎችን የመፍጠር አቅም አለው፡፡
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ ወይቦ ፕሮጀክት ሁለት ሎቶች አሉት፡፡ ሎት አንድ ግድብ እና ተያያዥ ስራዎችን ያካትታል፤ ይህም በደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እየተገነባ ይገኛል፡፡ ሎት ሁለት ደግሞ ከመስኖ መሬት መዋቅር ዝግጅት ጋር ይያያዛል። ይህም የሚገነባው ክሮስ ላንድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) በመቀናጀት ነው፡፡ ሎት አንድ ስድስት በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የሎት ሁለት አፈፃፀምም ተመሳሳይ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ አካል የደቡብ ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
አቶ ብዙነህ፤ ፕሮጀክቱን እያጋጠሙ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል የስራ ተቋራጩ የአቅም ውስንነት እና ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም የልማት ተነሺዎች የተጋነነ የካሳ ክፍያ መጠየቅ እና የዲዛይን ማሻሻያ በማስፈለጉ የዲዛይን ማሻሻያ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት ሆነዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የሎት አንድን አፈፃፀም ወደ 20 በመቶ እንዲሁም የሎት ሁለትን ደግሞ ወደ 41 በመቶ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ ፕሮጀክቱን ለማፋጠን ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። ለችግሮቹ የመፍትሄ አማራጮች ተቀምጠውለት በዚያው መሰረት ክትትል እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡
የወሰን ማስከበር ስራዎች እና የመስኖ ግንባታው ጎን ለጎን እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ የልማት ተነሺዎች ከቦታው የሚለቁት ተቋራጩ እና አማካሪው ለመስኖ ፕሮጀክት የሚውለውን ቦታ ካዩት በኋላ ነው፡፡ ካሳ ተከፍሎ የማስነሳት አሰራር እንደሚተገበርም ጠቁመዋል፡፡
ካሳ ከፍሎ መነሳት ያለባቸውን ነዋሪዎችን አስነስቶ ተቋራጩንና እና አማካሪን ወደ ቦታው የማስገባት ሁኔታ ከአሁን በፊት እንዳልተለመደ የሚያነሱት አቶ ብዙነህ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያቱ የመስኖ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ አርሶ አደሩ መሬቱን መጠቀም አለበት የሚል እሳቤ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት በቅድሚያ የተወሰኑ አርሶ አደሮችን በማስነሳት ግንባታው እንደተጀመረና በሂደት ሌሎች አርሶ አደሮችን የማስነሳት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የወሰን ማስከበር ጉዳይ ሳይጠናቀቅ የሚጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የወሰን ማስከበር ችግር በተደጋጋሚ ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል፡፡ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ቀድሞ በማጠናቀቅ የፕሮጀክቶች ግንባታ ቢጀመር ከወሰን ማስከበር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ይቻላል፡፡ የወሰን ማስከበር ጉዳይ ሳይጠናቀቅ ግንባታው የሚጀመር ከሆነ ግን የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመፍታት አደጋች ይሆናል፡፡
እንደ መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ ለፕሮጀክቱ ሌላኛው ተግዳሮት እየሆነ ያለው ጉዳይ የተቋራጩ የአቅም ውስንነት ነው፡፡ አገር በቀል ተቋራጮችን ለማበረታታት ፕሮጀክቶች ለአገር በቀል ተቋራጮች መሰጠታቸው የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ የልምድ እጥረት ያለበት እንደመሆኑ ለግንባታዎች ተግዳሮት ሲሆን ይስተዋላል። በመሆኑም የተቋራጮችን አቅም የማጠናከር ስራዎች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
የትኛውም ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ በአጠቃላይ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ መሳለጥ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ በቅርቡ ፕሮጀክቱን የጎበኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ አሳስበዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የዞኑ እና የወረዳው መንግሥት በቅርበት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋሉ ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቱ ግንባታ በተባለው ጊዜ እንዲጠናቀቅ መሃንዲሶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ፕሮጀክቱ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ፋይዳ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም