በሕይወት ጉዞ ውስጥ መውለድ መክበድ፤ ዘር መተካት ያለና ወደፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አይነት ቤተሰባዊ ትስስሩ የጠበቀበት አገር ማግባትና መውለድ የሕይወት አንዱ ግብ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ወጣቶችን ፕሮግራማቸው ባይሆን እንኳን ‹አግቡ አግቡ› የሚለው ጉትጎታ የሚበዛው። የኢትዮጵያውያን ሰርግ በብዙ አጃቢዎች ደምቆ ወደ ሶስት ጉልቻ የሚሸኘው። ጋብቻ በተፈፀመ በዓመቱ ደግሞ ውለዱ እንጂ የሚለው አስተያየት ይከተላል። አንድ ከተወለደ በኋላ ደግሞ ‹ምነው ብቻውን ወይም ብቻዋን አስቀራችሁ ድገሙ ድገሙ እንጂ ልጅ ፀጋ ነው› የሚሉ አስተያየቶች ከዚህም ከዚያም ይወረወራሉ።
በገጠር አካባቢ ደግሞ ‹ልጅ በልጅነት› በሚል ልማድ ገና በአስራዎቹ አጋማሽ ጎጆ ቀልሰው የልጆች እናትና አባት መሆን የሕይወትን መንገድ በአፍላነት መቀላቀል የተለመደ ነው። የዛሬ ባለታሪካችን አፍላነታቸውን በእናትነት ያሳለፉ በልጆቻቸው የተካሱና ድካማቸውን የረሱ አይነት እናት ናቸው። ማረፊዬ ጧሪዬ ባሉት የልጅ ልጃቸው ያላሰቡት ነገር ቢከሰትም ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ በደስታ ያሳለፉ እናት ነበሩ።
ወይዘሮ ልክየለሽ እንግዳ ይባላሉ። ደርበብ ቀላ ሞንደል ያሉ ወይዘሮ ናቸው። ወይዘሮዋ በልጅነታቸው ተድርው አምስት ልጆችን አፍርተዋል። ተወልደው ካደጉባት ብሎም ለወግ ማእረግ ከበቁባት የወሎዋ አማራ ሳይነት በ1977 ዓ.ም ድርቅ የተነሳ ከቤታቸው ወጥተዋል። ከትውልድ ቀያቸው ርቀው አዲስ አበባን ከረገጡባት ቀን አንስቶ ከባለቤታቸው ጋር በመተጋገዝ ሀብት ንብረት አፍርተዋል። ልጆቻቸውን አስተምረው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል። በመከባበርና በመተጋገዝ ያሳለፉትን የትዳር ዘመናቸውን ሲያስታውሱ በደስታና በስስት እንባቸው አይናቸው ላይ ይሞላል። ልጅን በስነ ምግባር ማሳደግ የሚያውቁት ባለቤታቸው ጨዋና በኑሮ የተሳካላቸውን ልጆች ማሳደግ ችለዋል።
በመኖር ሂደት ውስጥ ሞት አይቀሬ ነውና የሚወዷቸውን የልጅነት ባላቸው በሞት ተለዩዋቸው። በጊዜ ልጆቻቸውን ድረው ኩለው ከባለቤታቸው ጋር ብቻ ቀርተው የነበሩት እናት፤ ሀዘኑና ብቸኝነቱ በጣም ጎዳቸው። ያኔ ቤቱ ጭር ሲል ብቸኝነት አፍ አውጥቶ ሊውጣቸው ሲነሳ ከልጆቻቸው ተማክረው አንድ ነገር ይወስናሉ። የመጀመሪያ ልጃቸው ቴዎድሮስ ጫኔ የመጀመሪያ ልጅ የሆነውን ህፃን ሮቤል ቴዎድሮስን ወስደው ለማሳደግ ወሰኑ። ቤታቸውን ከብቸኝነት ድባብ አውጥቶ ዳግም ነፍስ እንዲዘራ ያደረጋቸውን ልጅ ከልባቸው ወደዱት። ልጁም ከአያቱ ጋር በእንክብካቤ ማደግ ጀመረ።
ቅምጥሉ የአያት ልጅ
ከወለዷቸው ልጆቻቸው በላይ የሚንሰፈሰፉለት ህፃን ሮቤል በአያቱ እጅ ቅብጥ ብሎ አደገ። ትምህርት ቤት ሲወስዱትና ሲመልሱት አዝለውት ነበር። ምንም እንኳን ቢከብዳቸውም የፍቅራቸው ማየል ያንን እንዲያደርጉ ያስገድዳቸው ነበር። አቅሙ ሲጠነክርና እግር ሲያወጣ በላ አለበላ ተጨንቀው፤ የእንቅልፉ መብዛቱ እሳቸውን እንቅልፍ ነስቷቸው፤ ወጥቶ እስኪገባ ልባቸው ደጅ ውሎ ደጅ እያመሸ ለቁም ነገር ይበቃላቸው ዘንድ ተመኙ።
ምኞታቸውንም ለማሳካት ለልጅ ልጃቸው አለ የተባለውን ጥሩ ነገር በሙሉ አደረጉለት። ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈልበት ትምህርት ቤት አስተማሩት፤ ውድ የተባለውን ልብስና ጫማ መግዛት ብቻ በአጠቃላይ አንድም ነገር ሳይጎድልበት እንዲማር አደረጉ። ይህ ሁሉ ቢሆንም የልባቸው መሻት ሳይሆን ቀረ።
እርሳቸው ሮቤል ተምሮ ከልጆቻቸው በላይ የሚጦራቸው የአይናቸው ማረፊያ እንዲሆናቸው ቢመኙትም በትምህርቱ ከአስረኛ ክፍል በላይ መቀጠል አልቻለም። ይባስ ብሎ በሱስ ውስጥ ተነከረ። የጫት፤ የመጠጥና የሲጋራ ሱሰኛ ሆነ። ሲወጣ ሲገባ አያቱን ሳንቲም አምጡ በማለት ያስቸግራቸው ያዘ። የለኝም ያሉት ቀንም መቀነታቸውን ሲፈታና ቦርሳቸውንም ሲፈትሽ መገኘቱ የተለመደ ተግባር እየሆነ መጣ።
ወጣቱ የተከፈለለትን ዋጋ ያህል ውጤት ሳያመጣ ከመቅረት አልፎ፤ ባልታሰበ አቅጣጫ ሄዶ አግድም አደገ ተባለ። ምግባረ ብልሹ ከሚባሉት ወጣቶች አንዱ የሆነው ይህ ወጣት ከአያቱ ቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ቴዎድሮስ፤ የሮቤል አባት የልጅ ልጃቸውን እንዲወስድላቸው ተማፀኑ።
ለልጁ ባእድ የሆነው አባት
ወትሮም ልጁ ተነጥሎት እንዲያድግ ያልፈለገው አባት እናቱን ላለማስቀየም የመጀመሪያ ልጁን መስጠቱ ሁሌም ይቆጨው ነበር። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ ነገር ሆኖበት የበኩር ልጁ እንደ አይን ሲጠፋበት ዝም ብሎ ከመመልከት ውጭ የሚያደርገው ነገር አጣ። ከስር ከስር ተከታትሎ መንገድ ያላሳየው ልጅ እንዴት ሆኖ ሊገራው እንደሚችል ሲያስብ ግራ ገብቶታል።
እናቱም ማንም ስለልጄ አያገባውም በማለት አሞላቀው ቅጣትን ሳያውቅ፤ የለም አይቻልምን ሳይለምድ ያሳደጉትን የልጅ ልጃቸውን ከመስመር ሲወጣ አባቱ እንዲወስድላቸው መጠየቃቸው ቢያሳዝነውም የወለደ አይጥልም ሆኖበት ልጁን ወደ ቤቱ ወስዶ ከተቀሩት ልጆቹ ጋር እንዲኖር ለማድረግ ሞከረ።
ወጣት ሮቤል ግን ስርአት አልበኝነቱ በስርአት የሚተዳደረው ቤተሰብ ውስጥ እንዲኖር አላስቻለውም። ወላጅ እናቱም ሆኑ እህት ወንድሞቹ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ለሳምንታት ከታገሉ በኋላ በገዛ ፈቃዱ ከአባቱ ቤት ወጥቶ አያቱ ጋር ተመለሰ።
ጭቅጭቅ ነገሰ
ለሁለት ሳምንታት አረፍ ያለው የአያቱ ቤት ዳግም በሮቤል መምጣት መበጥበጥ ጀመረ። ሲወጣ ሲገባ አያቱን መገላመጥ ብሎም ያልተገባ ቃላትን መሰንዘር ጀመረ። አልፎ ተርፎ “ከዚህ ቤት ውጣ ካልሽኝ አጠፋሻለሁ” በማለት ዛተ ማስፋራትን ያዘ።
ወይዘሮ ልክየለሽ በእጃቸው ያደገ ልጅ የከፋ ነገር ያደርስብኛል ብለው ባያስቡም እሳቸውን በድፍረት መናገሩ ራሱ አንጀታቸውን ያቆስለው ጀመር። የጎሪጥ የሚተያዩት አያትና የልጅ ልጅ ግንኙነታቸው ከቀን ወደ ቀን እየተበላሸ የነበራቸው ፍቅር ጠፍቶ በጠላትነት ይተያዩ ጀመር።
የሰባ ዘጠኝ ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት ወይዘሮ ብቸኝነታቸውን ያስረሳቸው ዘንድ ያሳደጉት የልጅ ልጃቸው ቤታቸውን ሲኦል ሲያደርገው ከማዘን በቀር ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። ልጃቸው ቴዎድሮስም “አግድም አደግ አድርገሽ ያሳደገሽውን ልጅ እንዴት ላቃናው?” በማለት ችላ ብሏቸዋል። ምንም ቢሆን ግን ባህሪው የሆነ ቀን ሊቀየር ይችላል ከማለት በስተቀር አያቱ ላይ ክፉ ነገር ያደርጋል ብሎ ያሰበ አንድም የቤተሰቡ አባል አልነበረም።
ክፉ ቀን
ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወጣት ሮቤል ቴዎድሮስ አያቱ መኝታ ቤት በመግባት ከቤት ኪራይ ያገኙትን ገንዘብ ይዞ ወጣ። ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናናበት አምሽቶ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ቤት ተመለሰ። ጤፍ እገዛበታለሁ ብለው ያስቀመጡትን ብር ከቦታው ያጡት ወይዘሮ ልክየለሽ በጣም ተናደው የልጅ ልጃቸውን ሲጠብቁ ይወላሉ። እስከ ውድቅት ድረስ ቢጠብቁትም ባለመመለሱ አዝነው ይተኛሉ። በጠዋት ጥሩ ስራ እንደሰራ ሰው ቁርስ እያለ ሲደነፋ ንዴታቸውን መቆጣጠር ይሳናቸውና
ከቤታቸው እንዲወጣ በሃይለ ቃል ይናገሩታል። ያኔ ዙሪያ ገባውን ቃኝቶ ምቹ ሁኔታን ስላላገኘ ቂም ይዞ ከቤት ወጣ።
ከዛ ግን አድብቶ እና አስልቶ ማንም ሰው ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ወንጀል ፈፀመ። የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ነሐሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቀጠና 5 ወጣት ማዕከል አካባቢ ነበር፡፡ ተከሳሽ ሮቤል ቴዎድሮስ የ79 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ከአባቱ እናት ጋር ይኖር ነበር። በልጁ ያልተገባ ባህሪ ምክንያት ቤታቸውን ጥሎላቸው እንዲወጣ የተናገሩት ሲሆን “ከቤት ውጣ ብላኛለች” በሚል ምክንያት ከወትሮው በቀነሰ መጠን መጠጥ ቀማምሶ ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት ወደ ቤት መጣ።
እንደመጣ አያቱን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቁጭ ብለው አገኛቸው። ከጠዋት ጀምሮ ማድረግ ያለበትን ሲያስብ የዋለው ወጣት ወይዘሮ ልክየለሽን በተቀመጡበት ጭንቅላታቸውን በመዶሻ ደጋግሞ በመምታት ሕይወታቸው እንዲያልፍ አደረገ።
በእጃቸው በልቶ በእጃቸው ጠጥቶ ጀርባቸውን ተፈናጦ በአያት እጅ በቅንጦት ያደገው ወጣት የበላበትን ወጪት ሰበረ። ለጥሩ ብለው ያሞላቀቁት ልጅ አጥፊያቸው ሆነ። አድጎ ይጦረኛል ያሉት፤ የማታ ምርኩዜ ብለው የሚጠሩት የልጅ ልጃቸው መጥፊያቸው ይሆናል ብሎ አንድም ቀን ያሰበ ሰው አልነበረም። ግን ያልታሰበው ሆነ። እሱም አልወጣም ካለው ቤት በፖሊስ ተይዞ ወጣ። እርሳቸውም ሰላም ካጡበት ቤታቸው ወደ ዘለዓለም ማረፊያቸው ተሸኙ። ዳግም ላይመለሰ ሁለም ነገር በቅፅበት ተጠናቀቀ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
የወይዘሮ ልክየለሽን የድረሱልኝ ጩኸት ሰምተው የመጡት ተከራዮች ፖሊስ በመጥራት ልጁ በቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉ። ፖሊስም ቀድሞ የነበረውን የልጁና የአያቱን ግንኙነት፤ ወንጀሉ የተፈፀመበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በሚመለከት ከአይን ምስክሮች ቃል ተቀበለ። በመቀጠል ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ልኮ ክስ እንዲመሰረትበት አደረገ፡፡
ውሳኔ
አቃቤ ህግ ያቀረበውን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ የክስ መከላከያውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቷል፡፡ “ከቤት ውጣ ስትለኝ ተናድጄ ነው” ከማለት በስተቀር ተከሳሹም ወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበለም።
የተከሳሽ ሮቤል ቴዎድሮስን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት ግለሰቡ በበቀል ሰሜት ተነሳስቶ፤ የአያቱን ነፍስ ለማጥፋት አቅዶና ተዘጋጅቶ ወንጀሉን በመፈፀሙ ጥፋተኛ መሆኑን ተረጋግጧል። ለዚህም ወጣቱ ከጥፋቱ እንዲታረም ሲል በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2014 ዓም