– ዶክተር ትሁት አስፋው ኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለቅስቀሳና ለማህበራዊ ድጋፍ ፕሬዚዳንት
ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ነው የተወለዱት፤ ያደጉትና የተማሩት ግን አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቤተልሄምና አብዮት ቅርስ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል። እንደተመረቁ ሞርጌጅ ይባል በነበረ ባንክ በተማሩበት ሙያ ተቀጥረው ለሶስት ዓመታት አገለገሉ። በመቀጠልም ሴፍ ዘ ችልድረን ኖርዌይ በተባለ ድርጅት ጅማ ተመድበው ሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ኬር ኢትዮጵያ በተባለ ድርጅት ከ10 ዓመት በላይ አገልግለዋል።
በዚሁ ድርጅት አማካኝነት ኖርዌይ ተልከው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት ተምረዋል። ከኖርዌ ተመልሰው በላካቸው ተቋም ውስጥ ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ደግሞ የውጭ ነፃ ትምህርት እድል ተወዳድረው ካናዳ ለ ስነ ፆታ እና ብዝሃ-ሕይወት ዘርፍ ለአምስት ዓመታት ተምረው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አገኙ። በሙያቸው እዛው ካናዳ ውስጥ ስራ አግኝተው ቀሩ። ከ21 ዓመታት በላይ በቆዩባት ካናዳ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ማዕድን ቁፋሮ ሲሰሩ በተፈጥሮ ሃብትና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ምን አይነት እክል እንደሚፈጥሩ ጥናት በማድረግና ለሚመለከተው አካል ምክረ-ሃሳብና የፖሊሲ ግብዓት በመስጠት ረገድ ከፍተኛ እውቅና የተቸሩ ኢትዮጵያዊ ሴት ናቸው።
በተጨማሪም እንደ ኤች. አይ.ቪ እና ቲቢ በተባሉ ተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ብዙ ጥናቶችን አካሂደዋል። በዚያው በሚኖሩበት አገር ውስጥ ሚኒስትሮች የፖሊሲ አማካሪ ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታ ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ግጭት እንዲሁም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪም ለቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ በማሰባሰብ ለህዝብና ለአገራቸው ያላቸውን አጋርነት በተግባር አረጋግጠዋል። በተለይም በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚያሳትፍ ህጋዊ ድርጅት እንዲቋቋም እንግዳችን መሰረት ስለመጣላቸው ይነሳል። በዚህ ድርጅት አማካኝነት አሁንም ድረስ ተከታታይነት ያለው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በዚህ የድጋፍ ስራቸውና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ኢትዮ-ካናዳውያን ኔት ወርክ ለቅስቀሳና ለማህበራዊ ድጋፍ ፕሬዚዳንት ዶክተር ትሁት አስፋው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
‹‹ህዝቡ ሰላም ማግኘት የሚችለው የአሸባሪው ሕወሓት አመራሮች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው››
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ክልል ጉጂና በአማራ ክልል ዘጌዬ ማህበረሰብ ዙሪያ ስላጠኑት ጥናት በጥቂቱ ይንገሩንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ትሁት፡- ልክ ነሽ፤ የማስተርስ ዲግሪዬን ጉጂ ማህረሰብ ላይ ነው የሰራሁት። ከአንዲት ፊላንዳዊ አጥኚ ጋር በመሆን ለአራት ወራት ከማህበረሰቡ መሃል በድንኳን ተቀምጠን ያካሄድነው ጥናትና እዚያ የቆየንበት ጊዜ ዛሬ ድረስ የማይጠፋ ደስ የሚል ትዝታ አለኝ። የጉጂ ህዝብ ምን አይነት ጨዋና ሰው አክባሪ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ የቻልኩት በዚያ ጊዜ ነበር። የሚገርምሽ እኛ ድንኳን ውስጥ በምናድርበት ጊዜ የአካባቢው አባቶች ‹‹ልጆቻችን አንድ ነገር ቢሆኑ የእኛ ስም ነው የሚጠፋው›› ብለው አራት ወር ሙሉ ሳይታክቱ ተራ በተራ እየጠበቁን ነበር የሚያድሩት። አሁን ድረስ ሳስበው የማህበረሰቡ ቅንነት ያስገርመኛል።
የጉጂ ማህበረሰብ እንደሚታወቀው አርብቶ አደሮች ናቸው፤ ከአካባቢያቸው ካለው ከጌዲዮ ህዝብ ጋር ብዙ ጊዜ በዚህ በተፈጥሮ ሃብት በግጦሽ መሬት የተነሳ ግጭት አለ። እናም የእኔ ጥናት የግጭት አፈታት ባህላቸው ምን ይመስላል በሚል ነበር ጥናት ስናደርግ የነበረው። አባ ገዳዎችንና ህዝቡን ቁጭ ብለን እናወያይ ነበር። በጥቅሉ የህዝቡን የግጭት አፈታት ማህበራዊ እሴቶች ምን እንደሚመስል ነው ያጠናነው። እግረ መንገዴንም ኦሮምኛ ቋንቋ መልመድ ችዬ ነበር። በነገራችን ላይ አፋርም ላይ ተመሳሳይ ጥናት አጥንቻለሁ።
የዶክትሬት ዲግሬዬን ደግሞ በአማራ ክልል ባህር ዳር ጣና ሃይቅ ላይ ባለችው ዘጌዬ ደሴት ላይ ነው ያጠናሁት። ይህች ደሴት በጣም የሚያስደንቅ የተፈጥሮ ታሪክ ያላት ስትሆን፤ የህብረተሰቡም አመጣጥ አስገራሚ ነው። ጫካው ከየት መጣ? ቡናው እንዴት ሊበቅል ቻለ? የሚል ነበር አንዱ ጥናቴ። የሚገርመው ቡና ከደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ የሚበቅል ቢሆንም ዘጌዬ ጫካ ውስጥ ቡና እና የተለያዩ ፍራፍሬዎች አሉ። በጣም አስደናቂ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ያለባት ደሴት ናት። ጥናታችን ከደሴቷ የተፈጥሮ ሃብት ባሻገር የሕብረተሰቡ ማህበራዊ ህይወታቸው ዙሪያ በተለይም በሴቶች ላይ የሚደረገው ጫና፤ ኑሯቸውን እንዴት እንደሚገፉ የመሳሰሉት ጉዳዮች ነው ያጠናነው። እዚያም የግጭት አፈታትና የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ሚና ዙሪያ አጥንቻለሁ። በተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ በጣም የተወደደና እውቅና የተቸረው ጥናት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራውን በማስተባበር በአገሩ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረጉን ስራ የጀመሩበት አጋጣሚ ምን ነበር ?
ዶክተር ትሁት፡- እንደምታስታውሽው የዛሬ ሁለት ዓመታት ገደማ ሙዚቀኛ ሃጫሉ መገደሉን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ በተለይ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በዝተው ነበር። እኛ ካናዳ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የችግሩ ተባባሪ ሆነን እንጂ የመፍትሔ አካል ለምን መሆን አልቻልንም? በሚል ውይይት ጀመርን። ለህዝባችን ድምፃችንን ማሰማት አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን። በመቀጠልም የሰላም ውይይት ማካሄድ አለብን ብለን ዲያስፖራውን የሚያሳትፍ ማህበር አቋቋምን። ይሁንና በኮቪድ ምክንያት ውይይታችንን በዙም ነበር የምናካሂደው የነበረው። እኔ ደግሞ ጉጂ ማህበረሰብ ውስጥም ስለኖርኩኝ እንዲህ አይነቱ የመገፋፋት ባህል ከየት መጣ የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኝ ስለነበር እንዲህ አይነቱ ፀያፍ ልምድ ለማስወገድ ማህበረሰቡን የማንቃትና የመፍትሄ ሃሳብ የማፈላለግ ስራ እሰራ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‹‹እኔም የወንድሜ ጠባቂ ነኝ›› እንዳሉት እኛም የሚገድለውም ሆነ የሚገደለው ህዝብ የእኛም ወገን በመሆኑ ዝም ማለት የለብንም፤ ለማስቆም የየበኩላችን ለመስራት ወስነን መንቀሳቀስ ጀመርን። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ባለሙያዎችን እየጋበዝን የውይይት መድረክም እናዘጋጅ ነበር። ከእነዚህም መካከል ‹‹የጥላቻ ንግግሮችና አደጋው›› የሚለውን ነገር ከነሩዋንዳ ከመሳሰሉት አገራት ተሞክሮ በመውሰድና አገራችንንና ህዝባችንን እንዴት መታደግ እንደምንችል እንመክር ነበር። እንደምታውቂው ሩዋንዳ መግደል ከመጀመሩ በፊት አንዱ ሌላውን ህዝብ ‹‹በረሮ›› የሚል ስያሜ ነበር ሲሰጣቸው የነበረው። ሰውን ያህል ፍጡር ‹‹በረሮ›› ብለን ካመንን ለመጨፍለቅም ሆነ ለመግደል አይከብደንም። ስለዚህ ይሄ በጣም ከባድ ነገር ነው ብለን በዚያ ላይ ትምህርት እንዲሰጥ አድርገናል። ሰው ሁሉ ውስጡ በጣም ተጎድቶ ስለነበር እየመጣ ያዳምጣል፤ ይወያያል፤ በአጠቃላይ ብዙ ሰው ነበር የሚሰባሰበው። እዚህም ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የግኑኝነት አግባብ ፈጠርንና እየጋበዝናቸው በውይይቱ ላይ ይሳተፉ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለን የሰሜኑ ጦርነት ሲነሳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረገው ጥሪ ከመላው ካናዳ ብዙ ሰዎች ተሰባስበን ሩቅም ብንሆን ለወገኖቻችን ማድረግ በምንችልበት ጉዳይ መከርን። ከዚህ ቀደም አሜሪካ ያሉ ድርጅቶች ጠንካራ ቢሆኑም ካናዳ ግን ብዙ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። ስለሆነም እኛም አንድ ማድረግ አለብን ብለን ተነሳን። በነገራችን ላይ ካናዳ
በርካታ ኢትዮጵያዊ ነው የሚኖረው። ስለዚህ ጠንከር ብለን መውጣት አለብን ብለን እንደድርጅት ተቋቋምን። በዚህ መሰረት ኢትዮጵዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለቅስቀሳና ለማህበራዊ ድጋፍ በሚል ድርጅት አቋቋምን ። እኔም የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ሆኜ ተመረጥኩኝ። ሌሎችን ሰዎች አሰባስበን በመላው ካናዳ 11 ቅርንጫፍ ከፈትን።
መጀመሪያ ለመከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ እናድርግ ብለን ገንዘብ ሰብስበን ላክን። ከዚያ ለሚቆስሉ የመከላከያ ሰራዊት አካላት የሚሆን የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ለመላክ መዘርዝር አዘጋጅተን ከመላው ካናዳ አሰባሰብን። እስካሁን ጠቅላላ ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚወጣ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ልከናል። ይህንንም ያደረግነው ከጤና ጥበቃ ጋር በቅርበት በመስራት ነው። በቀጣይ ደግሞ ለተፈናቀለው ህዝብ ገንዘብ እየተሰበሰበ በጠቅላላ በሁለት ዓመት ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው ያሰባሰብነው። ያንንም ስናደርግ ደግሞ ለህዝቡ ለራሱ በቦታው እየተገኘን ነው የሰጠነው። የጀመርነው ከአፋር ክልል ነው፤ ክልሉ እንደሚታወቀው በጦርነት በከፍተኛ ደረጃ ከተጎዱ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል እንደመሆኑ ምግብና ልብስን ጨምሮ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገንላቸዋል።
በተመሳሳይ አማራ ክልል በወሎ፣ ጎንደር፣ ባህርዳርና ደብረብርሃን በጣም ብዙ ተፈናቃዮች ያሉባቸው አካባቢ ድጋፍ አድርገናል። በመቀጠልም ቁስለኞችን ሆስፒታል ድረስ በመሄድ እየጎበኘን ድጋፍ እናደርግ ነበር። የእኛ አባላቶች እንዳውም ጎንደር ላይ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር የገና በዓልን አብረው ነው ያከበሩት። እኛ ደግሞ በደብረብርሃን በኩል ሄደን እዛ ያሉትን ቁስለኞች ስንጎበኝ መተኛ አልጋ አጥተው ሲንከራተቱ ተመለከትን፤ እናም ከአሜሪካ ትራንስፖርት እየከፈልን በሁሉም ሆስፒታል አልጋ እንዲመጣ አድርገናል። ሰራዊታችን በጦርነቱ መጎዳታቸው አንሶ ደግሞ እንዴት መተኛ አልጋና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ ያጣሉ? በሚል ቁጭት በከፍተኛ መናሳሳት ህዝቡ እየተረባረበ እርዳታ ስናደርግ ቆይተናል።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የአጣዬን ታሪክ እንደ ሚታወቀው በሸኔ ቡድን ብዙዎቹ ቤታቸው ተቃጥሎ ነበር። ቤቱ እንደተቃጠለ ወዲያውኑ በዙም ስብሰባ ጠራን፤ ሻማ ከማብራትና ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ የተጎዱ ወገኖቻችንን መደገፍ አለብን ብለን ተነሳን። በዚያ መሰረት 160 ሺ ዶላር በአንድ ምሽት ነው ያዋጣነው። የተቃጠለባቸው ወገኖች ‹‹ስምንት ቤት ስሩልን›› ቢሉም በጉልበታቸው ራሳቸው በማገዛቸውና ወጪ መቆጠብ በመቻሉ ለአስር አባወራ ቤት መስራት ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት የቤቶቹ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን በጥቅሉ ቤቱን ለማሰራት በ180 ሺ ዶላር ወጪ አድርገናል።
በሌላ በኩል ከኮምቦልቻ ከ20ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ሃርቡ ከተማ ላይ ከምዕራብ ወለጋ በሁለት ዙር ተፈናቅለው የመጡ 65ሺ ወገኖችን ጎብኝተን ነበር። በአዲስ ዓመት በዓልን ደግሞ 5ሺ500 ተፈናቃዮች በሬ አርደን አብረን አሳልፈናል። እነዚህ ወገኖቻችን መልሰው የሚቋቋሙበትን ስራ እንዲሰራ ከመንግስት ጋር ውይይት ጀምረናል፤ ከአማራ ልማት ማህበርም ጋርም እየተወያየን ነው። በነገራችን ላይ የአጣዬውን ቤት የገነባነው ከዚሁ ማህበር ጋር ሆነን ነው። አሁን ስንመለስ ደግሞ ሪፖርት ለዲያስፖራው አቅርበን በተከታታይ እነዚህ ወገኖቻችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታም እገዛ ለማድረግ እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በተደጋጋሚ ለሰላም የተዘረጉለቱን እጆች መስበሩ ከምን የመነጨነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ትሁት፡- እስካሁን እንዳያነው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አምባገነንነቱንና ለህዝብ የማያስብ መሆኑን ለአለም ያስመሰከረበት ጊዜ ነው። እኔ በጣም የሚያሳዝነኝ ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ሁሉ ህዝቡ ተገዝቶላቸው፤ የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ አድርገዋል፤ ግን ይህ አልበቃ ብሏቸው መላአገሪቱ ለማተራመስ የዚን ያህል ርቀት መሄዳቸው ነው። እንዳውም አመስግነው መደበኛ ህይወታቸውን መቀጠል ይችሉ ነበር፤ ምክንያቱም ማንም አልጠየቃቸውም ነበር።
ግን ‹‹እኛ ይህችን አገር ካልገዛን መጥፋት አለባት›› በሚል አመለካከት ትግራይ መሽገው መከላካያ ሰራዊታችን ላይ ያደረሱት ግፍ ታሪክ የማይረሳው ነው። ያም ሆኖ ደግሞ አገሪቱ ሰላም ትሁን፤ ህዝቡ የሰላም አየር ይተንፍስ ተብሎ መከላከያ ከትግራይ ከወጣ በኋላ ከትግራይ አልፈው አማራና አፋር ክልል ድረስ በመውረር ያደረጉት ጭፍጨፋ በጣም የሚያሳዝን ነው።
በዚህ ሁሉ ምንም ለሰላም ፍላጎት እንደሌላቸው አሳይተዋል። እኛ ካልገዛን የአገሪቱ ህዝቡ ሁሉ ይጥፋ የሚል አቋም ነው ይዘው ግፍ የሚፈፅሙት። ረጃጅም እጆቻቸው ከአማራም፤ ከአፋርም ክልል አልፈው በኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች ደርሰዋል። በተለይ ከሸኔ ጋር ጥምረት እያደረጉ ባሉት እንቅስቃሴ ከጥፋት ውጭ ምንም አጀንዳ እንደሌላቸው በግልፅ አሳይተዋል። በመሰረቱ ለትግራይ ህዝብ እንኳን ምንም እንደማያስቡ እያየን ለሌላ ለማን ያስባሉ ተብሎ ይገመታል?። እናም መንግስት ይህንን ጦርነት እንዲጨርሰው ነው የእኔ ፍላጎት። ምክንያቱም ተመልሰው በየቦታው እየሄዱ እያደረጉ ያሉትን ጥፋት እንዲቀጥሉ የሚፈቀድላቸው ከሆነ አይደለም ለመንግስት ለእኛ ራሱ ህዝብን እርዱ ለማለት ያስቸግረናል። ስለዚህ መንግስት የሰላም ማስከበር ስራውን የሚከፈለውን ሁሉ ከፍሎ መጨረስ አለበት።
በእርግጥ የውጭ ጫና እንዳለ እናውቃለን፤ ግን ደግሞ የውጭ ተፅዕኖውን ተቋቋሞ ጦርነቱን ዳር ማድረስ ይገባል። የውጭ ጫናውን በሚመለከት እኛም የምንሰራው ስራ አለ። ያለውን የተሳሳተ መረጃ በማስተካከል፤ ካናዳ ላለው ጠቅላይ ሚኒስትር በመፃፍ፤ የካናዳ ምክር ቤት ሁሉ እየቀረብን እውነታውን እንዲገነዘቡ አድርገናል። በዙምም እየቀረብን ስለነባራዊ ሁኔታ እናብራራለን፤ በዚህም የሕወሓት ትክክለኛ ማንነት እንዲጋለጥ አደርገናል። አንዳንድ የዓለም መንግስታት በጭፍን አሸባሪውን ሕወሓትን እየደገፉ መሆኑ ግልፅ ነው። ግን ወያኔዎች አሸባሪ መሆናቸውን በምክር ቤቱም የተረጋጋጠ ነገር ነው። የሚገርመው እኮ የአሜሪካ መንግስትም ከዚህ በፊት ‹‹ሽብርተኛ›› ብሎ ፈርጆአቸው ነበር፤ አዲስ ነገር አይደለም። መልካቸውንም ሆነ ባህሪያቸውን አልቀየሩም፤ ስለዚህ ህዝቡ ሰላም ማግኘት የሚችለው የሕወሓት አመራሮች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው። እንዲህ አይነቱ ነገር በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ እንዳይደገም ትምህርት መሆን አለበት።
ሌላኛው ነገር እነሱ ለ30 ዓመታት የዘረጉት በጎሳ የተከፋፈለ ህዝብ እንዲጋደል ያደረጉት ስርዓት መቅረት አለበት። ይህንን ደግሞ በተደጋጋሚ ለመንግስት አቅርበናል። ወደፊት ማየት የምንፈልጋት ከዚህ በፊት የነበረው አይነት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው በነፃነት የትኛውም ክፍለአገር ማንንም ሳይፈራ የትም ቦታ ንብረት አፍርቶ፤ ልጆቹን በፈለገው ቋንቋ አስተምሮ መኖር የሚችልባት ኢትዮጵያን ነው። ማንኛውም ቋንቋ ቢበዛ በግሌ ችግር የለብኝም፤ ግን ሰው ነፃነቱ ተከብሮ፤ ሰብአዊነቱ ተከብሮ መኖር የሚችልባትን ኢትዮጵያ ለማምጣት በመጀመሪያ ጎሰኝነት ወይም ማንነት ላይ ያነፃፀረ ፅንፈኝነት ከመሰረቱ ወይም ከምንጩ መድረቅ አለበት። ይህን የክፋት ምንጭ ማድረቅ ይገባል። ይህንን ከተደረገ በኋላ ህዝቡ አዕምሮ ላይ መሰራት አለበት። እኛ በውጭ አገራት በስደት እየኖርን ጥቁር ሆነን ከነጮች ጋር መብታችን ተከብሮ ነው ያለው። እነሱ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ተምረን፤ እነሱ የሚሰሩበት መስሪያ ቤት ሰርተን፤ እነሱ የሚያገኙትን ጥቅም እያገኘን ነው የምንኖረው። ስለዚህ እዚህ አገርም የዜግነት መብቱ የሁሉም ሰው በሚኖርበት ቦታ መጠበቅ አለበት።
ይህንን ለማምጣት ደግሞ አጥፊዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው፤ ፍትህ መኖር አለበት፤ ያለፍትህ ሰላም አይኖርም። በወለጋ፤ በቤኒሻንጉል ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው። ምክንያቱም አገር እያተራመሰ ያለው ወያኔ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የወያኔ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ በአጠቃላይ ወያኔ የዘረጋው መዋቅር መፍረስ አለበት። አሁን እኮ እየታጨደ ያለው 30 ዓመት የተዘራው ጥላቻ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ፤ ህዝቡም ተረባርቦ ያንን ስርዓት ‹‹አንፈልገውም›› ማለት አለበት። ጥላቻን አልፈልግም ሊል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት የሚያደርገ ውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የተቀበሉና የተወዛገቡ የአለም መንግስታትን እውነታውን ለማሳየት ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ትሁት፡- እስካሁን ባየነው የሌላ አገራት መንግስታት እያደረጉ ያሉት መንግስት ላይ ጫና መፍጠር ብቻ ነው። እኔ እነዚህ መንግስታት የኢትዮጵያን ሁኔታ በትክክል አይረዱም አልልም፤ ብዙ የሚረዱበት መንገድ አለ፤ እያወቁ ግን እነሱን የሚያዩዋቸው እንደተጎዱ እንደተበደሉ ነው። ምክንያቱም የእነሱ ተላላኪዎች በየአለም አደባባዩ የዘር ጭፍጨፋ እንደተደረገባቸው አድርገው ስለሚጮሁ ነው። የመከላከያ ሰራዊታችንን በጨፈጨፉ ማግስት ‹‹ትግራይ ጄኖሳይድ›› ብለው የጀመሩ ሰዎች ናቸው። እነሱ በውሸት የተካኑ ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት በአቋሙ መቆም አለበት ብዬ ነው የማምነው። ደግሞስ እድል ስንት ጊዜ ነው የሚሰጣቸው? የእርዳታ እህል ዘርፈው ወዲያው ኃይላቸውን አጠናክረው ለውጊያ ነው የወጡት፤ ይህም የአደባባይ ሚስጥር እንደነበር የሚታወስ ነው።
እንዲህ አይነቱን በክፋት የሰለጠነ ቡድን እንዴት አድርጎ ነው ወደ ሰላም ጠረጴዛ ማምጣት የሚቻለው? እስካሁን ድረስ እኮ ለሰላም ውይይት ሳይሆን ለጦርነት ሲዘጋጁና ወረራ ሲያካሂዱ ነው የቆዩት። እናም የሰላም ፍላጎቱ እንደሌላቸው ግልፅ ነው። ለሰላም ድርድር ሰው አዘጋጅተናል ቢሉም እነሱ ከውስጥ ለጦርነት እየተዘጋጁ ነበር። ይህ አልበቃ ብሎ ሰላም እንፈልጋለን ብለው መደራደሪያ ያቀርባሉ። መደራደሪያ እያቀረቡ የሰላም ውይይት እፈልጋለሁ ብሎ ነገር የለም። እናም ሃያላን አገራት ለሚባሉት መንግስት የተደረገውን ጥረት በደንብ እንዲገነዘቡ ማድረግና በአቋሙ መፅናት አለበት። እኛም ደግሞ በውጭ ያለነው በፍፁም ሰላም እየተባለ እንደገና ጦርነት እየለኮሱ ህዝብ የሚያልቅበት ነገር ሊደገም አይገባም የሚል አቋም ነው ያለን።
መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ፈፅሞ መለሳለስ የለበትም ብለን ነው የምናምነው። ይሄ ጦርነት ማለቅ አለበት፤ ሌላ መንገድ የለውም። ይሄ የወያኔ የሽብርተኛ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሰበር አለበት። የትግራይ ህዝብም ነፃ መውጣት አለበት። ምክንያቱም በዋናነት እያለቀ ያለው የትግራይ ወጣት ነው። አሁንም ከህጻን እስከ አዛውንት ለጦርነት ክተት ቅስቀሳ እያደረገ ነው። ስለሆነም ይህ ቡድን ለትግራይ ህዝብም አይጠቅምም፤ ይህ ቡድን ሰላም ያመጣል ብሎ የሚያምን የትግራይ ህዝብ አለ ብዬም አላምንም። በግድ ተገዶ በሃይል ነው የተያዘው። በነገራችን ላይ በታሪክም ብናይ የትግራይ ህዝብ በግድ የተያዘው በወያኔ ብቻ ነው። ባለፉት ዓመታትም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ከነጭራሹ አልነበረም፤ እነሱ ናቸው ህዝቡን አንቀው የያዙት። የትግራይ ህዝብም መናገር አለበት። በውጭ ያለው የትግራይ ተወላጆች ስለወያኔ ክፋት መናገር መቻል አለባቸው። ለምንድን ነው የሚሸፋፍኑት? መንግስት ግን ፀንቶ ጦርነቱን አጠናቆ ህግ ለጣሱ፣ ለገደሉ፣ ክፋት ላደረጉ ፍትህ ሊሰጥ ይገባል። የሕግ የበላይነት መከበር አለበት። የእኔ አቋም ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት በተደጋጋሚ ይሄ ጦርነት የተልዕኮ ጦርነት እንደሆነ ይገልፃል፤ በተለይ የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ የታሪካዊ ጠላቶች እጅ እንዳለበት ያነሳል። ለመሆኑ ከዚህስ አኳያ ምን አይነት የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይገባል?
ዶክተር ትሁት፡- ይሄ በጣም ግልፅ ነው፤ እንዳነሳሽው የውጭ ሃይሎቹ የሚፈልጓት አገር ደካማ ኢትዮጵያን ነው። በእነሱ ላይ ጥገኛ የሆነች፤ ሁልጊዜ የእርዳታ እህል እየለመነች የምትኖር ኢትዮጵያ ነው የሚፈልጉት። ይህንን ደግሞ በተለያየ መልኩ ግልፅ አድርገውልናል። ስለዚህ ከእነዚህ ሰዎች የምንጠብቀው ነገር የለም። ግብፅ የራሷ ፍላጎትና አጀንዳ አላት። ለዘመናት 80 በመቶ በላይ ውሃ ተጠቅማ በርሃ የሆነ መሬቷን ማልማት ችላለች። ኢትዮጵያ ግን የራስዋን ውሃ እንኳን እንዳትጠቀም ሲያደርጉ ነው የኖሩት። እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ሞኝ መሆን አይገባውም። ኢትዮጵያ ምንም አይነት ወዳጅ ከውጭ አገራት አሉኝ ብላ ማመን የለባትም። ለኢትዮጵያ ህዝቧ ነው ያላት። ህዝቡ ደግሞ አንድ ሆኖ መቆም አለበት። አንድ ሆነን ከቆምን ማንኛውንም የውጭ ሃይል መመከት እንችላለን።
ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የ‹‹በቃ›› ወይም ‹‹No more›› እንቅስቃሴው ነው። ይህ እንቅስቃሴ ሲጀመር የሚሳካ አይመስልም ነበር፤ ግን አለም ሁሉ ፀጥ ነው ያለው፤ ይልቁንም ሃያላኑ ወደ ልመና ነው የገቡት። ይህ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን በሙሉ ነው ያነሳሳባቸው። ዲያስፖራው ለአገሩ ‹‹ሆ›› ብሎ ሲቆም ማንም ሊከላከለው አልቻለም። ምንም እንኳን የሕወሓት ውሸት ከአገር አልፎ አለምን ያዳረሰ ቢሆንም ዘመቻውን ማስቆም አልቻሉም። እና አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ሌላ ወገን ይደርስልናል ብለን ማሰብ የለብንም፤ ለኢትዮጵያ ያለነው እኛው ነን። በጎሳ፤ በቋንቋ ተለያይተን ብንበታተን ለሌሎች መብል ነው የምንሆነው። ለሌላው መጠቀሚያ ነው የምንሆነው። ለነግብፅ እፎይታ ነው የምንሆነው። ሱዳንም ብትሆን እኛ ብንበታተን ደስታውን አትችለውም። ይህንን ሁላችንም ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል።
ሁልጊዜ እንደምንናገረው ሁላችንም በጎሳ በማባላቱ በእኛ ይብቃ፤ የሚቀጥለው ትውልድ እፎይ ማለት አለብን። ትምህርት ቤት ሄዶ ሳይፈራ በሰላም መመለስ አለበት፤ እናት ልጆቼ በሰላም ይመለሳሉ ወይ ብላ መጨነቅ የለባትም። እኛ ወደዚህ ስንመጣ እንኳ የምኖርበት መንግስት ‹‹ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ በመሆንዋ አትሂዱ›› ብሎን ነበር። ሆኖም አሻፈረን ብለን ለወገኖቻችን አለኝታ መሆናችንን ለማረጋገጥ ነው የመጣነው። በአጠቃላይ የውጭ አገራት መንግስታት ለእኛ ምንም አያደርጉልንም፤ ስንጠነክር ይወዱናል፤ ስንዳከም ደስታቸው ነው። ስለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልዩነቶቻችንን አስወግደን ለህዝባችንና ለአገራችን መቆም አለብን የሚል ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት ወንጀለኞች መፈታ ታቸውን ተከትሎ መንግስትና አገር ሲደግፉ የነበሩ አንዳንድ የዲያስፖራ አባላት ቅር ተሰኝተው እንደነበር ይታወሳል። ለመሆኑ በአገር ማኩረፍ ይቻላል? ሁሉንም ዲያስፖራ እንደ «በቃ» ዘመቻው ሁሉ አሁንም በአገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ትሁት፡- እንዳልሽው አሸባሪው ሕወሓት እስረኞች ሲፈቱ ትንሽ የማይባለው ዲያስፖራ ቅር ተሰኝቶ ነበር፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ድንገተኛ ነበር፤ በርካታ ዲያስፖራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በብዙ ደስታ ነበር የመጣው፤ በድንገት እነዚያ ሰዎች ሲፈቱ በጣም አዝነው ተመልሰው የሄዱም አሉ፤ በዚያ ወቅት በቤተ መንግስት እኛ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እየሠራን ነበር። ወደ 800 ሺ ዶላር አካባቢ አሰባስበን ነበር፤ ለአንድ እራት አንድ ሺ ዶላር የከፈሉ ነበሩ። እናም ያ ነገር ሲከሰት እኛ ላይ ራሱ ከፍተኛ ቁጣ ነበር የተነሳብን። የማሰባሰቡን ስራ እንድንሰርዘው ሁሉ ተጠይቀን ነበር። ሆኖም ‹‹በአገር አይኮረፍም›› እያልን ከፍተኛ የማረጋጋት ስራ በመስራት በሂደት የነበረው ቁጣና ኩርፊያ እየቀነሰ ሄዷል።
ዶክተር አብይም ሰብስበውን ማብራሪያ ሰጥተውን ነበር፤ ብዙውን ነገር ተቀብለነዋል። ያልተቀበልነው ነገር ሊኖር ይችላል፤ እሱ ምንም ማለት ግን አይደለም፤ ከዚያ በኋላ ግን አኩርፈን ህዝባችንን አለመደገፍ ትክክለኛ መንገድ ነው ብዬ አላምንም። በእርግጥ ስራችን ቢዳከምብንም እኛ የምንችለውን ያክል እየሰራን ህዝቡንም እየቀሰቀስን ነው ያለነው። አሁን ህዝቡ ህዝባችን ነው። የብዙ ሰው ልብ ያለው እዚህ ነው፤ ዲያስፖራ ማለት ባንዲራ አቅፎ ቁጭ ብሎ የሚያለቅስ ህዝብ ነው። እውነቴን ነው የምልሽ እኔ ራሴ እንዲህ አይነት የአገር ፍቅር እንዳለኝ እዚህ ሆኜ አይገባኝም ነበር። ስትወጪ ነው የባሰ የምትጓጊው፤ እናም ብዙ ዲያስፖራ ህዝቡን አገሩን ይወዳል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከራሳችን ነገር መውጣት መቻል አለብን። መንግስትም ቢሆን በህዝብ የተመረጠ ነው፤ ይሄ መንግስት ደግሞ በደንብ አላገለገለንም ሲል ህዝቡ ራሱ ያወርደዋል። ስለዚህ ይህንን ህዝብ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ከምንርቀውና ከምንበታትነው ተስፋ ልንሆነው ነው የሚገባው። ይሄ ጊዜ እንደሚያልፍ ተረድተን አብረን እንሁንና ህዝቡን እናበርታው።
በመንግስትም ሆነ በሚዲያ በኩል ትክክለኛው መረጃ ውጭ ላለው ማህበረሰብ የማድረስ ችግር አለ። ችግሮች ሲፈጠሩ ቶሎ ምክንያቱን በማስረዳት ግርታንና ቅሬታን ማስወገድ መቻል አለባችሁ። ይህንን ስታሳውቁ የተቆጣው ህዝብ ምልስ ይላል። ዝም ሲባል ግን ቁጣው እየባሰ ነው የሚሄደው። ያም ቢሆን ግን መፅሓፍ ቅዱስ እንደሚለው ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይር ሁሉ ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይቀይርም።›› የትም ብንሄድ ለአገራችን ያለን ፍቅር አይቀየርም። አሁንም አብረን እንቆማለን እንጂ ወደኋላ አንመለስም።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ዶክተር ትሁት፡- በዚህ ጦርነት ምክንያት ከየቀየው የተፈናቀለው ህዝብ ጉዳይ ያሳስበኛል። ለዚህ ህዝብ ከምንም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ጥሩ ነገሮች መሰራታቸው ደስ ይላል፤ ግን እዛ ጋር መሬት ላይ የፈሰሰ ህዝብ ስመለከት ደስታዬ ግማሽ ይሆንብኛል። መንግስት፤ የሁሉም ክልል መሪዎችና ህዝብ ተባብሮ እነዚህን ዜጎች ህይወት መታደግ አለበት። ወደተረጋጋ ኑሮ የሚመለስበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ እናንተ የመገናኛ ብዙሃን አካላት ሃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል። በዚህ ዓመት ማንም እናት ስታለቅስ፤ ማንም ልጅ ሲሳቀቅ ማየት የለብንም። የእኛም ጉጉት አገራችን ሰላም ሆና፤ ህዝባችን እፎይ ብሎ ማየት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
ዶክተር ትሁት፡- እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
በማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም