የኑሮ መሠረቱን የግብርና ሥራን ያደረገው አርሶ አደር ከልጁ ባልተናነሰ ለእንስሳቱ እንክብካቤ ያደርጋል፤ ለመሬቱ፣ ለሰብሉና ለአካባቢው ልማት ይጨነቃል፤ ይጠበባል። እንዲህ እንደ ሰብል አልሚው አርሶ አደር ሁሉ በማዕድን ልማት ሥራ ላይ የተሰማራው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብም ለማዕድን ልማቱ ተመሳሳይ ስሜት አለው።
የክልሉ የማዕድን ክምችት አብዛኛው ህዝብ በማዕድን ልማት ሥራ ላይ እንዲያተኩር እንዳደረገው ይገለጻል። በዚህ ዘርፍ የተሰማራው የማህበረሰብ ክፍል አድካሚ የሆነውን የማዕድን ቁፋሮ ያለማቋረጥ በማከናወን በሚያገኘው ማዕድን ሽያጭ ገቢ ነው የሚተዳደረው።
በአየር መዛባትና በተለያየ ምክንያት በሰብል ላይ በሚከሰት ጉዳት በቂ ምርት እንደማይገኝ ሁሉ በማዕድን ቁፋሮውም በለስ የማይቀናባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ እንዳልሆኑም ማእድን አምራቾቹ ይጠቁማሉ።የማዕድን ቁፋሮው በሳይንሳዊ ጥናትም ሆነ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አይደለም፤ በግምት የሚካሄደበት ወቅትም አለ።በዚህ የተነሳም የቁፋሮ ሥራው ውጤታማ የማይሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። አልሚው መተዳደ ሪያው አድርጎ በመያዙ ልፋቱን ሳይቆጥር ሙከራውን በመቀጠል ሲቀናው ያገኘውን ማዕድን ሸጦ በገቢው ኑሮውን ይመራል፡፡
በዚህ ረገድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ ወረዳ በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ የተሰማሩትን አቶ አህመድ መሐመድን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።አቶ አህመድ ገቢያቸውና መተዳደሪያቸው የወርቅ ማዕድን ልማት ሥራ ነው።ይህን ስራ በግላቸው ጀምረው ነበር።ይሆናል ብለውም ከሌሎች አልሚዎች ጋር በማህበር ተደራጅተውም ለተወሰነ ጊዜ በጋራ በመሥራት ውጤቱን አይተዋል።
በጋራ መሥራት ጥሩ ቢሆንም እኩል ለመንቀሳቀስ ያለው ቁርጠኝነት ግን አልተመቻቸውም፤ በማህበር መሥራቱን ትተው ከቤተሰባቸው ጋር ወደ መስራት ገቡ። የሚያመርቱትን ወርቅ ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁምነገር አብቅተዋል፤ በኑሮአቸው ላይም መጠነኛ የሆነ መሻሻል ማምጣትም ችለዋል።ይሁንና የአመራረት መንገዱ ባህላዊ በመሆኑ በልማቱ ሥራ ላይ ለረጅም ጊዜ የቆዩትን ያህል ለውጣቸው ከፍተኛ ሆኖ አላገኙትም።
በአቅም ውስንነት አብዛኛው አምራች በባህላዊ መንገድ ነው የሚያለማው።በግላቸው የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ተከራይተው ለመስራት ጥረት አድርገዋል።ነገር ግን ለኪራይ የሚያወጡትን ገንዘብ ለእለት ኑሮአቸው ለማድረግ ሲሉ በባህላዊ መንገድ ማልማቱ ላይ ያተኩራሉ።በባህላዊ መንገድ አልምተው የሚያገኙት የወርቅ መጠን አነስተኛ ስለሚሆን ከሽያጩ የሚገኘው ገቢም አነስተኛ ነው።ይህ ደግሞ የእለት ኑሯቸውን ከማሟላት ያለፈ አይሆንም።
የአመራረት መንገዱ አለመዘመኑ ብቻ አይደለም የእሳቸው ችግር።ግብይቱም በማእከል አለመከናወኑ የልፋታቸውን ዋጋ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።ከአልሚው ይልቅ በመካከል ላይ ሆኖ የሚደልለው ተጠቃሚ እየሆነ ነው።ይህ ደግሞ አልሚውን ብቻ ሳይሆን የአገር ጥቅምንም እያሳጣ ነው ሲሉ አቶ አህመድ ይጠቁማሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በኪሎግራም ለብሄራዊ ባንክ ገቢ እንዲደረግ ከተተመነው በታች ያለው የወርቅ ማዕድን ግብይት አስተማማኝ ወይንም ህጋዊ የሚባል አይደለም።የንግድ ፈቃድ ኖሯቸው በህጋዊ መንገድ የሚቀበሉ ነጋዴዎች ቢኖሩም የተለየ የመገበያያ ቦታ አለመኖሩ ግብይቱን ለህገወጥነት አጋልጦታል።የግብይት ማዕከል ቢኖር ግን ችግሩን ይቀርፈዋል የሚል እምነት አላቸው።በዚህ ረገድ መንግስት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ አቶ አህመድ መረጃው አላቸው።ግንባታው ተፋጥኖ ወደተግባር ቢገባ ጥሩ ነው የሚል አስተያት ሰጥተዋል፡፡
አቶ አህመድ በዚህ አጋጣሚ በሥራው ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግርና መንግሥት ቢያስተካከል ያሉትንም ሲገልጹ እንዳሉት።የወርቅ ማዕድን ልማት ሥራ ከአመት አመት አይቋረጥም።ለልማቱ የበጋው ወቅት ከከረምቱ የተሻለ ነው።በክረምት ሰፊ ልማት ለማከናወን ጭቃው አያመችም።
በጋው ምቹ ቢሆንም፣ የራሱ ችግር አለው፤ በሚፈለገው መጠን ውሃ ለማግኘት ስለሚያስቸግር በምርት ሂደት ላይ መጓተት ይፈጥራል።ለወርቅ ማጠቢያ የሚሆን ውሃ በቦቴ በግዥ ከሩቅ ማጓጓዝ የግድ ይሆናል።በእዚህ ወቅት ለአንድ ቦቴ ውሃ እስከ ስምንት ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፤ ይህም ከፍተኛ ወጪ ነው።
በአካባቢው የጉድጓድ ውሃ ለማውጣትም ዘመናዊ የመቆፈሪያ መሳሪያ ያስፈልጋል።የገንዘብ አቅም ባለመኖሩ ይህን ለማሟላት አልተቻለም።
ሌላው ለሥራቸው እንቅፋት የሆነባቸው ድንጋዩንና ማዕድኑን ለመለየት ለሚያስፈልገው የመፍጫ ማሽንና ድንጋዩን ከጉድጓድ ውስጥ ለማውጣት ለሚረዳው መሳሪያ ማንቀሳቀሻ የሚውል የነዳጅ አቅርቦት ዋጋ መናር ነው።አቶ አህመድ ከነጋዴ አንድ ሊትር ነዳጅ ለመግዛት ከአንድ መቶ ብር በላይ ማውጣት ተገደዋል።
ችግሩንም ለሚመለከተው ክፍል በማሳወቅ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ የመጣ ለውጥ የለም።አቶ አህመድ መንግሥት እንዲህ ያለውን ህገወጥነት እንዲከላከልም ጠይቀዋል።
በ2014ዓ.ም በአካባቢያቸው በነበረው አለመረጋ ጋትና የፀጥታ ችግር ምክንያት በወርቅ ማዕድን ልማቱ ላይ እንቅስቃሴያቸው ዝቅተኛ እንደነበር የጠቀሱት አቶ አህመድ፣ በተለይ በ2014 በጀት አመት ማብቂያ ላይ ለተወሰኑ ጊዜያቶች የወርቅ ማዕድን ልማት ሥራው ተቋርጦ እንደነበርም ያስታውሳሉ።መስተጓጎሉ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ።ለማዕድን ልማት ሥራ ሰላምና መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡እሳቸው ሰላምን የማረጋገጡ ተግባር ከተከናወነ በተያዘው በጀት አመት ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋ አድርገዋል።በተለይ ደግሞ ለልማቱ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ማግኘት ከቻሉ ውጤታማነታቸው የበለጠ እንደሚሆንም ነው ያስታወቁት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሐመድ አምራችና ገዥን ማገናኘት የሚያስችል ማዕከል ማቋቋም ከተቻለ ህገወጦችን በቀላሉ መከላከል ይቻላል ሲሉ ይገልጻሉ። እስካሁን የማዕድን ግብይቱ ለክትትልና ቁጥጥር በሚያስቸግር ልቅ በሆነ ሁኔታ በየመንደሩና ተገቢ ባልሆነ ቦታዎች እየተከናወነ ይገኛል።
ማዕድንን የኑሮ መሰረቱ ያደረገው በዘርፉ ላይ የተሰማራው ማህበረሰብም በዚሁ መንገድ ግብይቱን ማካሄዱን ለምዶታል። ጥቅምና ጉዳቱን ለይቶ አልተገነዘበም። ይህ ክፍተት ለህገወጥ ማዕድን አዘዋዋሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፣ የአምራቾችን የልፋት ዋጋ እያሳጣ፣ መንግሥትም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ እያረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ናስር ገለጻ፤ ችግሩን ለመፍታት የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል።በጊዜያዊነት ወይንም በአጭር ጊዜ በተቀመጠው መፍትሄ በክልሉ የማዕድን ልማት በሚከናወንባቸው ኩሙሩክ፣ መንጌና አሶሳን ጨምሮ በአራት ወረዳዎች ለቁጥጥር ምቹ የሆኑ ቦታዎች በመለየት ግብይቱ በአንድ ስፍራ እንዲከናወን ተመቻችቷል።በዚህ ምቹ ሁኔታም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሚዛን ሳይዙና በተለያየ መንገድ ለመገበያየት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን ተከታትሎ ለመከላከል ተችሏል።በአንዳንዶች ላይም ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል።
በዘላቂነት ደግሞ ማዕድን ሚኒስቴር የግብይት ማዕከል ለመገንባት አቅዷል።አቶ ናስር በእቅዱ መሠረት ግንባታው ተከናውኖ ወደ ሥራ ከገባ በተጠናከረ ቁጥጥር ችግሮችን በመፍታት ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል ነው የሚሉት።
ማዕከሉ ለብሄራዊ ባንክ የሚቀርብ ወርቅ ለማዘጋጀት የሚያስችል መሳሪያና ትክክለኛ ሚዛን የሚከናወንበትን አሟልቶ የሚይዝ ሲሆን፣ ደረጃውን ያሟላ ተግባር ለማከናወን ይረዳል።በተጨማሪም ተለዋዋጭ የሆነውን ገበያ ነጋዴው በመቆጣጠር አምራቹ ከዓለም ገበያ በታች በሆነ የመገበያያ ዋጋ እንዳይጎዳ ማድረግ ያስችላል።
ክልሉ የግንባታ ቦታ በማመቻቸት፣ ማዕድን ሚኒስቴር ደግሞ የግንባታ ወጭውን በመሸፈን በ2015 በጀት አመት ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው የወርቅ ማዕድን መገበያያ ማዕከል የሚገነባውም በሸርቆሌ፣ ኩምሩክና መንጌ ወረዳዎች እንደሆነም አቶ ናስር ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ናስር ማብራሪያ፤ በክልሉ ወርቅ አምራች በሆኑ ወረዳዎች በማህበር ተደራጅተው በልማቱ ላይ የሚሳተፉ ማህበራት ከ200 ይበልጣሉ፤ በእያንዳንዱ ማህበር ውስጥ ያሉት አባላት ቁጥር የተለያየ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አባላትን የያዙ ናቸው፡፡በአጠቃላይ የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ የተመሰረተው በማዕድን ልማት በመሆኑ በግለሰብ ደረጃና በማህበር ተደራጅተው በልማት ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ናስር በባህላዊ መንገድ ከሚካሄደው የወርቅ ማምረት ስራ በተጨማሪ ባለሀብቶች በልማቱ ለመሰማራት ፍቃድ መውሰዳቸውን ይጠቅሳሉ፤ ባለሀብቶቹ ወደ ሰፋፊ የልማት ቦታዎችን ከልለው ቢይዙም ወደ ልማቱ አልገቡም።በርካታ አመታትን በእዚህ መልኩ ያስቆጠሩ ኩባንያዎች በክልሉ ተሰማርተዋል።በማምረት ሂደት ላይ የሚገኙ የተወሰኑ እንዳሉም ጠቅሰው፣ ሥራቸው ግን በኩባንያ ደረጃ የሚገለጽ አይደለም ይላሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ክልሉ በባህላዊና በአነስተኛ የወርቅ አምራቾች የተመረተ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ እያስገባ ይገኛል። ኩባንያዎቹ የሥራ ፈቃድ ያገኙት ከፌዴራል መንግሥት በመሆኑ ክልሉ እርምጃ መውሰድ አይችልም።ችግሩን በማሳወቅ መፍትሄ እንዲሰጠው የማሳወቅና የማሳሳብ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።ወደ ልማት እንዲገቡ የፌዴራል መንግሥትም የሁለት አመት ጊዜ የሰጣቸው ቢሆንም፣ የተሰጣቸውን ጊዜ አልተጠቀሙበትም።
ዋና ዳይሬክተሩ ክልሉ ስለጉዳዩ ለፌዴራል መንግሥት ማሳወቁንና ማሳሰቡን አላቋረጠም።ኩባንያዎቹ ወደ ሥራ የማይገቡ ከሆነ የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ቁርጠኛ የሆኑ አነስተኛ አምራቾች ድጋፍ ተደርጎላቸው በኩባንያዎቹ የተያዙ ቦታዎች ለልማት የሚውሉበት ሁኔታ እንዲመቻችም ክልሉ ሀሳብ አቅርቧል ሲሉ ይገልጻሉ።ማዕድን ሚኒስቴርም ባለሙያዎችን በመላክ የጥናት ሥራ ማካሄዱን ጠቅሰው፣ ጉዳዩንም አይቶ መፍትሄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አቶ ናስር ኩባንያዎች ለሥራ የሚያስፈልጓቸውን የተለያየ መሣሪያዎች ከውጭ በግዥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደገጠማቸው እንደሚገልጹ አቶ ናስር ጠቅሰው፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ለችግሩ በምክንያትነት አንደሚያነሱም ይገልጻሉ።
የሥራ ፈቃድ ወስደው የልማት ቦታዎችን ከልለው የያዙበት ጊዜና ምክንያት ብለው ያነሷቸው ጉዳዮች ደግሞ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች መሆናቸውንና አሳማኝ እንዳልሆኑም አቶ ናስር ይናገራሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኩባንያዎቹ የተሰማሩት በመተከል፣ አሶሳ፣ ከማሺና በሌሎችም አካባቢዎች ነው።ኩባንያዎቹ ወደልማቱ ከመግባት ይልቅ ለጥናት የሚወስዱት ጊዜ እጅግ ይረዝማል። ወደ ሥራ ገብተው ቢሆን የሚለማው ማዕድን መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ አነስተኛና ባህላዊ ማዕድን አምራቾችንም በማነቃቃት ጥቅማቸው ከፍ የሚልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅ ማዕድን በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም፤ በእምነበረድ በተለይም ሰማያዊ ቀለም ባለው እምነበረድ እንዲሁም የድንጋይ ከሰል፣ ግራናይት ማዕድናትም ይገኛሉ።እንደ አገር የተከሰተው የፀጥታ ችግር በልማቱ ላይ መቆራረጥ እያስከተለ ነው።
ይህም ችግር አልሚው ማህበረሰብ እንዲፈናቀልና ለተረጂነት እንዲጋለጥ አድርጎት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ናስር፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በተገኘው አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በአብዛኛው ቦታ የልማቱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ። ክልሉ በሁሉም ዞኖች የሚገኘውን የማዕድን ሀብት እንዲለማ እያረገ እንደሚገኝም ነው የሚገልጹት፡፡
በተለይም በተያዘው 2015 በጀት አመት የወርቅ ማዕድን ልማትን በማጠናከር በአመት ከ30 ኩንታል በላይ ወርቅ ብሄራዊ ባንክ ለማስገባት መታቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።ለዚህም ክልሉ ፀጥታው የተረጋገጠ እንዲሆን፣ ለአምራቾች የመሳሪያ ማንቀሳቀሻ የሚውል ነዳጅ አቅርቦት በተለይም አነስተኛ አምራቾች ከባለሀብቶች ጋር ተቀናጅተው ነዳጅ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ግብረሃይል በማቋቋም እስከ ቀበሌ ድረስ ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ህገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎችን የመከላከል ሥራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አስታውቀዋል።እስከ ሁለት መቶ ሄክታር የሚሆን የማዕድን ልማት ሥፍራዎች ለአዳዲስ አልሚዎች ፍቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በ2014 በጀት አመት 23 ኩንታል ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማስገባቱንም አስታውሰዋል።የፀጥታ ችግር ባይኖርና አልሚዎቹ ለማሽን ሥራ የሚጠቀሙበት ነዳጅ በአቅርቦትም በዋጋም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ቢቀርብ ኖሮ የወርቅ ምርቱ ከፍተኛ ይሆን እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
መንግሥት በዘርፉ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ቢሆንም፣ በክትትልና ድጋፍ በእቅድ የተያዙ ሥራዎች ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ ሥራዎች እንደሚቀሩ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውን መረጃ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።የፌዴራል መንግስቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የወርቅ ልማት የመደገፍ የቤት ሥራ እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም