ማርያም ወንዝ የተሰኘው ሥፍራ እንኳንስ የሰው ልጅ ሌላ ፍጡር ይኖርበታል ተብሎ አያታሰብም። የፅዳቱ መጓደል ቆሼን ጭምር ያስንቃል።በቆሻሻ የተዋጠውና የተበከለው ይሄ ወንዝ መነሻው ቁስቋም ማርያም ሽሮ ሜዳ አካባቢ በላይ ሲሆን ቀጨኔ መድኃኒዓለምን መዳረሻው አድርጎ ወደታች ይወርዳል።ቦታው የሚጠቃለለውና የሚጠራው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 23 ውስጥ ነው።
የወንዙ ውሃ በቆሻሻ ከመበከሉ የተነሳ የተቃጠለ የፍሬን ዘይት በመምሰል ወደ ጥቀርሻነት ተለውጧል።ሆኖም በዚህ አካባቢ የወንዙን መጥፎ ሽታ ተቋቁመው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ።መኖራቸውን እንኳን ማንም በቅጡ የማያውቀው የህብረተሰብ ክፍሎች የአዲስ አበባ አንዱ ገመና ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል።
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን የሚገፉት በልመና ነው።ኑሮዬ ብለው በወንዙ ዳር ዳር ሰፍረው ለሚኖሩትና በልመና ለሚተዳደሩት የኔ ቢጤዎች የማርያም ወንዝ ሁሉም ነገራቸው ነው።ጎህ ሳይቀድ በድቅድቅ ጨለማ ለልመና ከቤታቸው ሲወጡ የመጀመሪያ ስራቸው በወንዙ ውሃ ፊታቸውን ማበስ ነው።መጠኑ ከፍ በሚል ጊዜ በእጃቸው እየጨለፉ ፤ሲቀንስ ደግሞ በዙሪያው ባገኙት ነገር እየጠለቁ ዓይናቸውን አበስ አበስ ያደርጉበታል።በተለይ ዕጣ ፈንታቸው ነገር ዓለሙን ያስረሳቸው አንዳንድ አዋቂዊችና ህፃናት ሙሉ በሙሉ ፊታቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል። አንዳንዶቹ እንደሚናገሩትም ቤት በሚውሉበት ጊዜ ለምግብ መሥሪያ ይጠቀሙበታል።
በወንዙ ዳርቻ የተደረደሩት ቤቶች በአሮጌና ቁርጥራጭ ላስቲክና ቆርቆሮዎች ተለጣጥፈው የተሰሩ ናቸው።አብዛኞቹ ቤቶች ከ10 እስከ 30 በመሆን የኔቢጤዎች በሕብረት ተጨናንቀው የሚኖሩባቸው ናቸው።ለቤቶቹም በወር ከ200 እስከ 500 ብር ይከፍላሉ። የኔ ቢጤዎቹ ሌሊት ወጥተው በልመና ከሚያገኙትን ገንዘብ ለዕለት ጉርሳቸውና ለቤት ኪራይ ያውሉታል።
የማርያም ወንዝ የኔ ቢጤዎች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ከመኝታቸው ይነሳሉ።አንዱ ሌላውን የመቀስቀስ ኃላፊነትም አለበት።በዚህ ጊዜ በአካባቢው ጫጫታና ሁካታ ይበረታል ።ህጻናትና ታዳጊዎችም በብዛት አይነስውራንን ስለሚመሩ የሌሊቱ ትዕይንት አካል ናቸው።
በተለይ ሴቶች ደካማ እናቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና በክራንች ወይም በዱላ የሚሄዱትን ይደግፋሉ። ቤት የሚቀር የለም። እጅ እግር የሌላቸው ሁሉም ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው ቢቻል በሸክምና በእዝል ባይቻል በኪራይ ዊልቼር ለልመና ይወጣሉ። ጉዳተኞቹን መሸከምና ማዘሉም ለመንደራቸው ነዋሪዎች ሌላ በድርድር ዋጋ የሚቆረጥለት የገቢ ምንጭ ነው።
በተለይ ጉልበት ያላቸው ጎረምሶች ከልመናው ባሻገር እጅ እግር የሌላቸውን ጨምሮ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውን በማጓጓዝ ነው የቤት ኪራይ የሚከፍሉትና የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑት።ከአምስት እስከ ሰላሳ የሚደርሱ የቤተሰብ አባላት እርስ በእርስ እየተዛዘሉ፣ እየተመራሩና እየተደጋገፉ ጨለማው ሳይገልጥ መንደራቸውን ለቅቀው ይወጣሉ።
‹‹እናት›› እያሉ በቁልምጫ የሚጠሯት 31 ቁጥር አውቶቡስን ጨምሮ የሽሮ ሜዳ መስመር አውቶቡስ ሹፌሮች ጨለማው ሳይገልጥ እያሳፈሯቸው ይከንፋሉ። በአራቱም የአዲስ አበባ ማዕዘናት ይሰማራሉ።ቦሌ ወደ ጉምሩክ፣ ካራማራ ሆቴል፣ ሩዋንዳ ማዞርያ፣ ሳሪስ አቦ ፣ መገናኛ፣ 22 ቺቺኒያ አካባቢ፣ መስቀል አደባባይ፣ መርካቶ የልመና መዳረሻ ሥፍራዎቻቸው ናቸው።
አቶ መርጋ ዲሳሳ በእንዲህ ዓይነቱ የልመና ሥራ ተሰማርተው ከሚገኙ የማሪያም ወንዝ መንደር ነዋሪዎች አንዱ ናቸው።አውቀውት ባይነግሩንም ዕድሜያቸው በግምት ወደ 75 ዓመት የሚጠጋ ይመስላል። ሁለት እጅ የላቸውም፤ እንደነገሩን እግር ቢኖራቸውም አይታዘዝላቸውም።
በብዛት ቦሌ አካባቢ ነው የሚለምኑት። መገናኛም ይቀመጣሉ። አልፎ አልፎ መርካቶ የሚወጡበት ጊዜም አለ። የንግስ በዓላት ቀንም በየአድባራቱ በመገኘት ምጽዋት ይጠይቃሉ። በአነዚህ አካባቢዎች በብዛት የሰው እንቅስቃሴ በመኖሩ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኛሉ፤ መጠኑን ባይገልፁትም ለሚሸከማቸው ሰው ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው፤ፈጣሪያቸውንም አመስግነው ወደ ማደርያቸው ማርያም ወንዝ ይመለሳሉ።‹‹እናት›› የሚሏት አውቶቡስ እንደወሰደቻቸው ወደ ማደርያቸው ትመልሳቸዋለች።
ሌላው የ67 ዓመቱ አዛውንትና ምስካየ ህዙናን መድኃኒዓለም አካባቢ ሲለምኑ ያገኘናቸው አቶ አዳነ ቢልልኝም የዚሁ መንደር ነዋሪ ናቸው። በሕክምና ሰበብ ከክፍለ ሀገር መጥተው ነው አዲስ አበባ ሰምጠው የቀሩት። ዘበኝነት ተቀጥረው በቅጡ 30 ዓመት ያልሞላት ልጃገረድ አግብተው የራሳቸው ጎጆ በመቀለስ ሁለት ልጆች ወልደው ይኖሩ ነበር።
ሆኖም ምስካየ ህዙናን መድኃኒዓለም አካባቢ አስፋልት መንገድ ሲያቋርጡ መኪና ገጫቸው። በአደጋው ታፋቸውና ትከሻቸው ክፉኛ ተጎዳ። ባለመኪናው የካቲት 12 ሆስፒታል ወስዶ ጥሏቸው ጠፋ።በቂ ህክምና ባለማግኘታቸውም መንቀሳቀስ ተሳናቸው፤ ለብዙ ጊዜም የአልጋ ቁራኛ ሆኑ። የዘበኝነቱን ሥራም በዚህ ምክንያት ተዉት። ልመናም መተዳደርያቸው ሆነ።
ልጆቻቸው ሴቷ 20 ዓመት ወንዱ ደግሞ ስምንት ዓመቱ ነው። በብዙ ትግል ዘንድሮ ትንሹን ልጃቸውን ቅድመ መደበኛ ትምህርት አስገብተውታል። ትልቋ ስምንተኛ ክፍል ከደሰረች በኋላ አቋርጣለች። ሰው ቤት ልብስ እያጠበችም ሆነ ጉሊት ቢጤ እየሰራች እራሷንና እነሱን ታስተዳድር ነበር። ሆኖም አሁን አእምሮዋ በመታወኩ ሥራውን ካቆመች ዓመታት አልፏታል። በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ የሚተዳደረው አቶ አዳነ ለምነው በሚያመጡት ገንዘብ ነው። ከዚሁም ላይ ሌሊት ወጥተው ማታ ለሚገቡባት የላስቲክ ጎጆ 300 ብር ይከፍላሉ።
ሌላዋ የማርያም ወንዝ ነዋሪ ወይዘሮ የሺሀረግ ወርቁ ናቸው።ወይዘሮ የሺሀረግ እንዳወጉን ከደራ ተፈናቅለው ከመጡና በአካባቢው መኖር ከጀመሩ ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። ሦስት ልጆች የነበሯቸው ቢሆንም የየራሳቸውን እንጀራ ፍለጋ በየአቅጣጫው በመበተናቸው ብቻቸውን ነው የሚኖሩት። ሆኖም ብቻቸውን እንደሚኖሩ ይግለፁ እንጂ በጠባቧና በደካማዋ የላስቲክ ቤት ወለል ላይ የሚያድሩት አምስትና ስድስት ሆነው በሕብረት ነው። በግላቸው በወር የሚደርስባቸው ኪራይም 500 ብር ነው።
በዕለቱ ምስካየ ህዙናን መድኃኒዓለም ደጃፍ እናግኛቸው እንጂ ይሄን ለመክፈልና የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይለምናሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ሀገራቸው ሳሉ ወድቀው እጃቸው ስለተሰበረ የራሳቸውን ልብስ ማጠብ እንኳን አለመቻላቸው ነው።
በአጠቃላይ የማርያም መንደር ነዋሪዎቹም ሆኑ ከዚያ እየተነሱ በአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ ለልመና የሚሰማሩ ዜጎች የመንግስትንም ሆነ የሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችን ትኩረት ይሻሉ።
በሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ቢሮ የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ከማል እንደሚሉትም ችግሩን ለመፍታት በጀት ተመድቦለት የማህበረሰብ አቀፍ ክብካቤ ጥምረት የሚል ፕሮጀክት ተቀርጿል። ከመጪው ጥቅምት ጀምሮም በይፋ ስራ ይጀምራል። ሆኖም በአካባቢውም ሆነ በከተማዋ ባለሀብቶች ከክፍለ ሀገር እያመጡ የሚለምኑባቸውና ሌሎችም ልመናን ባህል ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ስለተረጋገጠ እነዚህ ተለይተውና የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ እንደሚተገበር ነግረውናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም