ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት ካለፉት ዓመታት በተሻለ በወጪ ንግድ አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። ይህም በወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያው መሆን ችሏል። በወጪ ንግድ አበረታች ውጤት ካስመዘገበችባቸው ዘርፎች መካከል ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የግብርናው ዘርፍ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአጠቃላይ በወጪ ንግዱ ለተገኘው ከፍተኛ ገቢ የግብርናው ዘርፍ 72 በመቶ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 በመቶ እንዲሁም የማዕድን ዘርፉ 14 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል። ከግብርናው ዘርፍም ቡና በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ በማስገኘት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሽ ለመሆን በቅቷል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወጪ ንግዱ ለተገኘው ስኬት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ላኪዎችን ከወራት በፊት መሸለሙ ይታወሳል። በዚህም ከ28 ሚሊየን ዶላር በላይ በወጪ ንግድ ገቢ ያስገኙ ላኪዎችን ሸልሟል፤ እውቅና ሰጥቷል። በወቅቱም ቡና ለተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ መጠቀሱ ይታወሳል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከአንድ ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የተገኘ ሲሆን፣ ገቢውም በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያ ወይም ከፍተኛው ሆኗል። ባለፈው ሳምንት ‹‹ቡናችን ለአብሮነታችንና ለብልጽግናችን‹‹ በሚል መሪ ቃል የቡና ቀን ለሁለት ቀናት በፓናል ውይይት እና በቡናና ሻይ ዘርፍ ለተገኘው ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅናና የሽልማት መርሀ ግብር በማካሄድ በተከበረበት ወቅትም እንዲሁ የቡናው ዘርፍ ስኬት ከፍ ብሎ ተነስቷል።
በመድረኩ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ከአንድ ሺ 500 በላይ በቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎች እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራል መንግስትና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል። በቡናው ዘርፍ ለተከናወነው ውጤታማ ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ 267 ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ከተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ እውቅናና ሽልማት ተቀብለዋል።
በመድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ባለ ዝግጅት ጥሩ ለሰሩ እውቅና መስጠት፣ ስራቸውን ድካማቸውን ልፋታቸውን ማወቅ፣ ማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል። በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደ አገር ከተገኘው የውጭ ምንዛሬ 72 ከመቶ የሚሆነው ከግብርና የተገኘ መሆኑን ፕሬዚዳንቷም ጠቅሰዋል። ከዚህም ውስጥ 35 በመቶ ከቡና የተገኘ መሆኑንም አመልክተዋል።
በአስር አመቱ መሪ እቅድ ለግብርና በተሰጠው ትኩረት የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ኑሮ እየተለወጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛሬ ያየሁት በተለይ የግሉ ዘርፍ በአገራችን እንዲያድግ በር የሚከፍት ነው ሲሉም ተናግረዋል። የግሉ ዘርፍ ለብዙ አመታት እንዳያድግ ተደርጎ መቆየቱን አስታውሰው፣ ያለግል ዘርፍ የአገር እድገት እንደሌለና የግሉን ዘርፍ መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በዚህ ሀብቷ ግን ብዙ እንዳልተጠቀመችበት ነው ያመለከቱት። ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ታችኛው የአመራር እርከን የቡና ዘርፉን በቅርበት በመከታተል ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንደ አገር የተመረጡ 10 አገራዊ የልማት ፕሮግራሞች ውስጥ ግብርናው ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት፣ የስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ የልማት መስኮች መሆናቸውን አብራርተዋል። ቡና አልሚ አርሶ አደሮች የድካማቸውን ማግኘት እንዲችሉ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንዳሉት ደግሞ፣ የቡናን ገቢ ለማሳደግ አሰራሮችንና ደንቦችን በማሻሻል ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል። ለአብነትም ከ470 ሺ ሄክታር በላይ በሆኑ የቡና ማሳዎች ላይ የሚገኙ የቡና ዛፎች ታድሰዋል (ተጎንድለዋል)። የቡና ስርአተ ትምህርት በመቅረጽ፣ የቡና ቅምሻ ማእከል በማቋቋም የቡና እሴትን ለመጨመር ተሰርቷል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዓለም የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ጉጉት እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተመልክቶ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አንድ ኪሎ ቡና 47 ሺ ብር የተሸጠበት ሁኔታ ለቀጣይ ስራ እንደሚያነሳሳም ነው ዶክተር አዱኛ የጠቆሙት።
ሽልማቱም ጥሩ ቡና በመላክ በተሻለ ዋጋ ጥሬ ቡና የሸጡ፣ ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ሴት ቡና ላኪዎች፣ እሴት የተጨመረበት ቡና በመላክ ከፍተኛ ገቢ ያሰገኙ ላኪዎችን ያካተተ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በቡናው ዘርፍ ይህን ያህል ስኬት እንዲመዘገብ በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ከልማቱ ጎን ለጎን ለግብይቱም ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። የግብይት ሰንሰለት ማሳጠር እንዲሁም ህገወጥ ግብይትና ኮንትሮባንድ ንግድ ለመካላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባሮች በዘርፉ ለተመዘገበው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የቡናና ሻይ ባለስልጣን መጽሄት ይዞት በወጣው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ መልእክትና ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ እንደተገለጸውም፤ ባለስልጣኑ ከተቋቋመ ባለፉት አምስት አመታት /አንዱ አመተ መዋቅር የመዘርጋት እና የሰው ሀይል የማደራጀት ተግባሮች የተከናወኑበት በመሆኑ/ የዘርፉን ችግሮች ነቅሶ ከማውጣት አንስቶ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች የማውጣት እንዲሁም ስትራቴጂ የመንደፍ ስራዎች ተከናውነዋል።
የቡናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል በንቅናቄ በተደራጀ፣ በተናበበ እና በተቀናጀ መልክ መስራት በመቻሉ በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ከ470ሺ ሄክታር መሬት በላይ መሬት ላይ የነበረ ያረጀ፣ በቂ ምርት የማይሰጥ እና ጥራቱ የተጓደለ ቡና ለማደስ ተችሏል። ይህን በማከናወን ሂደት በአርሶ አደሩ በኩል የነበረውን አመለካከት ለመቀየር እስኪቻል ድረስ ስራው ፈታኝ ነበር። እነዚህ እየታደሱ ያሉ ቡናዎች ሙሉ በሙሉ ፍሬ መስጠት ሲችሉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጡ ይታመናል።
በቡና ግብይቱ በኩልም ውጤታማ እና ሰፋፊ ተግባሮች ተከናውነዋል። ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ብሎ ለማናገር ባያስደፍርም የነበሩትን ውስብስብ እና አስቸጋሪ አሰራሮችን መልክ የማስያዝ እና ህግ እና መመሪያ የተከተለ አሰራር በመዘርጋት በኩል ስኬታማ ተግባሮች ተከናውነዋል ለማለት ይቻላል። በተለይ ህገወጥነትን በቴክኖሎጂ በተደገፈ ሁኔታ በመቆጣጠር የተሄደበት ርቀት አበረታች ነው።
ዋና ዳይሬክተሩ የቡና ግብይቱን አስመልክቶ ለመጽሄቱ እንዳሉት፤ አማካይ የቡና ዋጋ ከዓለም የገበያ ሁኔታ ጋር በማጣጣም እየተሰራ ባለው ስራ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ አድጓል። ከዚህ ቀደም አንድና ብቸኛ የነበረው የግብይት አማራጭ እንዲሰፋ በመደረጉ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። አገሪቷ የምታገኘውም ገቢ ጨምሯል። በርካታ አርሶ አደሮችን ሚሊየነር እያረገ የሚገኘው ባለልዩ ጣእም የቡና ቅምሻ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን እንዲመጣ በማድረግ ሶስት ጊዜያት በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ ተችሏል።
በባለስልጣኑ በ2014 በጀት አመት 280 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል የሚለውን እቅድ መሰረት በማድረግ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ነገር ግን እጅግ በሚገርም እና በሚያስደስት ሁኔታ እናሳካዋለን ብለን ካቀድነውም በላይ በመጠንም ሆነ በገቢ ታሪካዊ የሚባል ስኬት አስመዝግበናል ያሉት ዶከተር አዱኛ፣ አገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ 300 ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ አቀፍ ገበያ በማቅረብ አንድ ቢሊየን አራት መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝታለች ሲሉ አብራርተዋል።
አምራቹ ከቡና ግብይቱ የሚያገኘውን ድርሻ ለማሳደግም ተሰርቷል። አነስተኛ ቡና አምራች አርሶ አደሮች በቀጥታ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከአቅራቢዎች ወይም ከላኪዎች ጋር በትስስር የሚሸጡበትን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ የአርሶ አደሩንም ሆነ በየደረጃው የሚገኘውን ተዋናይ በስፋት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የቡና ጥራት 25 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፤ አጠቃላይ የቡና የወጪ ንግድ መጠን 18 በመቶ እንዲያድግም ተደርጓል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስን ወደ አገሪቱ አምጥተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ውድድሩ በባለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ታሪካዊ የሚባልና ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
ምርትን ከገበያ ዋጋ በታች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳነስ ባሻገር ጤናማ የግብይት ስርአት እንዳይኖር በማድረግ የዘርፉን እድገት እየተፈታተነ የመጣውን ችግር ለማቃለል የኮንትራት አስተዳደር መመሪያ በማዘጋጀት ተግባራዊ ሆኗል። በዚህም የአንድ ቶን ቡና ዋጋ በአማካይ ከ2ሺ 800 ወደ 3ሺ900 ዶላር ማሳደግ ተችሏል። ህገወጥ የቡና ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚያስችል ሶፍትዌር በማበልጸግ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ህገወጥ ንግዱንም ለመቀነስ ተችሏል።
ውጤቱ እጅግ የሚያስደስት ቢሆንም፣ አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ገና ብዙ መስራት እንደሚገባ እና ተወዳዳሪ ሆኖ ሌሎች በቡናው ዘርፍ ትልቅ ደረጃ የደረሱ አገሮች ካሉበት ተርታ ለመሰለፍ ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተጨማሪ የቤት ስራ የሰጠ አጋጣሚ ነው። በመሆኑም ገና እንደሚቀረን እና በጣም አብዝተን መድከም እንዳለብን ይሰማኛል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ያስገነዝባሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም በከፍተኛ ውድድር ላይ ናት። ሁሉም ቀድሞ ለመገኘት ይሮጣል፤ አንደኛው ሌላኛውን ጥሎ ለማለፍ ይሽቀዳደማል፤ ይህ እንደ ቡናው ዘርፍ ሲታይ ልክ እንደ እኛ ቡና አምራች የሆኑ፣ ነገር ግን ቀድመን ለዓለም ያስተዋወቅነውን ቡና እነሱ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና የግበይት ዘዴ እንዲሆንም አማራጫቸውን በመጠቀም፣ እሴት የማይጨምሩ ሰንሰለታቸውን በመበጣጠስና በዋጋ የመደራደር አቅማቸውን በማሳደግ ቀድመውን አልፈውን ሄደዋል። በሄክታር መሬት የሚያገኙበት ቡና እኛ ከምናገኘው ምናልባትም እስከ ሶስት እጥፍ የሚበልጥ ነው። በመሆኑም በጣም ብዙ ከረጢት ቡና በገበያው ለመርጨት ያስችላቸዋል። እንግዲህ ቆም ብለን እና ራቅ አድርገን ማሰብ የሚገባን ገበያውን እንዴት ሰብረን እንግባ? እንዴት እንቆጣጠረው? የሚለው ላይ ነው።
በዚህ ሁኔታ ለዘመናት የተጠቀምንበትን እና ኮሜርሻል የሆኑ ቡናዎቻችን ብቻ እየላክን ተጠቃሚ እንደማንሆን፣ ከቁጥ ቁጥ ገቢም እንደማንላቀቅ፣ በጥናት ተገነዝበናል ይላሉ ዶክተር አዱኛ። ከዚህ ወጣ ብለን አይናችንን ከፈት አድርገን የስፔሻሊቲ ቡና ገበያን ማማተር ይኖርብናል፤ አብዛኛው ቡና ገዢዎቻችን የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ከተለመደው የቡና ቃና ወጣ ብለው ማጣጣም ይፈልጋሉ ሲሉ ይጠቁማሉ።
ሌሎች ቡና አምራች ተወዳዳሪዎቻችን በተለመደው ሁኔታ ቡናቸውን በገፍ ሲያቀርቡ እኛ የተለየ ጥራት፣ ቃና እና ደረጃ ያለውን ቡናችንን ብናቀርብ ገበያውን ሰብረን ለመግባት ያስችለናል፤ በብዛት ስንልክ የነበረውን ኮሜርሻል ቡና መጠን ወደ ስፔሻሊቲ ቀይረን /ዳይቨርት አድረገን/ መጠቀም ይኖርብናል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም