
በሀገር ውስጥ ንግድ ላይ በተሠማሩ፤ ከውጭ በሚያስገቡ እና ወደ ውጭ በሚልኩት ላይ አተኩሮ ይሠራል። አምራቾችም ሆኑ ነጋዴዎች በንግድ ላይ የሚገጥማቸውን እንቅፋት የማስወገድ ሥራን ያከናውናል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር። የሚኒስቴሩ የፕሮሞሽን ባለሙያ መሠረት ጌታሁን ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተቋቋመባቸውን መሠረታዊ ዓላማዎች የሀገሪቱን ንግድ ይከታተላል፤ ይደግፋል ሲሉም ይገልጻሉ።
ይኸው መሥሪያ ቤት ንግድን መደገፍ እና ማሳለጥ ዋነኛዎቹ ዓላማዎቹ መሆናቸውን በመጠቆም፤ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በንግድ ትስስሩ ላይ ከሀገር አልፎ ሀገሪቷን ከሌሎች ሀገሮች ጋር ለማስተሳሰር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ ከሚሠራባቸው መንገዶች መካከል ኪጋሊ ላይ እአአ በ2019 ፊርማው የተካሄደው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አንደኛው ነው። ይህንንም እአአ በ2060 ለማሳካት ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አፍሪካውያን እየሠሩ ናቸው። ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም የሚጠበቅበትን እየተወጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአህጉር ደረጃ ስምምነት እየተደረገ ነው። ይህን ተከትሎ በ55 ሀገራት ገበያ እየተፈቀደ ነው። እየመጣ ያለውን በመረዳት በስፋት ለመሳተፍ ነጋዴዎች ራሳቸውን ማብቃት፤ አምራቾችም በጋራ መሥራት፤ ጥራታቸው የተረጋገጠ ምርቶችን ማምረት እና ብዛቱንም መጨመር አለባቸው።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ከብዙዎቹ የንግድ ስምምነቶች ከፍ ባለ መልኩ አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው እንዲገበያዩ የሚመቻችበት መንገድ ነው። አፍሪካውያን በሙሉ በኢኮኖሚ እንደ የሚያስተሳስር ጠቅሰው፣ ከብዙዎቹ የንግድ ግንኙነት እና ስምምነቶች ይልቅ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማደግ እና መስፋት የሚችል ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ሌላው ‹‹ምርቶቻችንን የምንላላክበት የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት አለ፡፡›› የሚሉት የፕሮሞሽን ባለሙያዋ፤ ኢትዮጵያ ከሃያ ሀገራት በላይ የንግድ ስምምነት ተፈራርማ፤ ምርቶቿን ወደ ውጭ ትልካለች ይላሉ።
የፕሮሞሽን ባለሙያዋ፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በስፋት እየተሠራበት ያለው፤ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ሀገራትን ማስተሳሰር (ኮሜሳ) ሥራ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ኮሜሳ የቀጣና ገበያ መሆኑንም አመልክተው፣ 10 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ እንዳለውና 21 ሀገራት አባል እንደሆኑበትም ይጠቅሳሉ።
ኮሜሳ ሲመሠረት ኢትዮጵያ አባል አልነበረችም። ይህ ከሌሎቹ ሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ስምምነቶች ለየት የሚል፤ የአባል ሀገሮቹም ብዛትም ከፍ ያለ መሆኑን፤ ከዚህ በተጨማሪም በአባል ሀገሮቹ መካከል አስር በመቶ የታሪፍ ቅናሽ ለማድረግ ሀገሮች ስምምነት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያም አባል ለመሆን መብቃቷን አስገንዝበዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአብዛኛው አፍሪካውያን ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ አነስተኛ ነው። ኮሜሳን የመሳሰሉት የመገናኛ ስምምነቶች አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው የሚያደርጓቸው የንግድ ልውውጦች እንዲጨምሩ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው። በየሀገሩ ኤግዚብሽኖችን በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ሥራ የሚሠራው የአባል ሀገራቱ አምራቾች እና ሻጮች፤ ዕድሉን አውቀው ወደ ንግድ ልውውጥ እንዲሠማሩ ለማድረግ ነው።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኮሜሳ አባል ሀገሮች በተደጋጋሚ በየሀገሮቹ ኤግዚብሽኖችን በማካሔድ እርስ በርሳቸው ንግድ እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ከኮሜሳ አባል ሀገራት ጋር የኢትዮጵያን ምርት እና ሥራዎችን የማያያዝ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
የፕሮሞሽን ባለሙያዋ፤ ለእዚህ በማስረጃነት በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሔደውን የኮሜሳ ኤግዚብሽን ያቀርባሉ። ኤግዚብሽን በመዘጋጀቱ ዕድሉ መኖሩን የማስተዋወቅ ሥራ ከመሠራቱ ባሻገር፤ ኢትዮጵያውያን ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ኢትዮጵያውያንም የአፍሪካውያን እህት እና ወንድሞችን ምርት እንዲያውቁ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ያለቀላቸው ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ ውስን እሴት ተጨምሮባቸው ለግብዓት መሆን የሚችሉ ምርቶች ኤግዚብሽኑ ላይ መቅረባቸውን ጠቁመው፣ ለእዚህም በተወሰነ መልኩ የተዘጋጀ ቆዳን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ጫማ እና ቦርሳ እንዲሁም ሌሎች የቆዳ ምርቶችን ለመሥራት የሚፈልጉ አፍሪካውያን ግብዓቱን ማግኘት የሚችሉበት ዕድል መመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያንም ከሌሎች የኮሜሳ አባል ሀገሮች የታሪፍ ቅናሽ የተደረገባቸውን ያለቀላቸው ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ ለተጨማሪ ምርት የሚሆኑ ግብዓቶችን ማግኘት ይችላሉ። ይህንን አጉልቶ ማየት ከተቻለ ኤግዚብሽኑ በራሱ ትልቅ ዕድል መሆኑን ማመን አዳጋች አይሆንም፡፡
ከኮሜሳ ጋር በመተሳሰር ኤግዚብሽኑ ሀገር ውስጥ መካሄዱ በራሱ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ የሚኖረው ጠቀሜታ ቀላል እንዳልሆነም ተናግረዋል። ዕድሉ መኖሩንም ለዜጎች በማስተዋወቅ በእንደዚህ ዓይነት መድረኮች ላይ አፍሪካውያን እህት እና ወንድሞች የኢትዮጵያን ምርት እንዲያውቁ እና እንዲሸምቱ ከመንግሥት ባሻገር አምራቾች እና ነጋዴዎችም የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ምርቶች በማሰባሰብ በቴክኖሎጂ ገዢ እና ሻጭን የማገናኘት ሥራ የሚያከናውኑ ወጣቶች ተሳትፈዋል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም በቀጣይም መንግሥት የሚሠራውን እና የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ ብቻ ከመጠበቅ በመውጣት፤ ዜጎች ምርታቸውን ለአፍሪካ ገበያ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ በተመለከተ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ከእነርሱ ሥራ ጋር ተባብረው የሚሠሩ እና ውጤታቸውም ጎን ለጎን ሊታይ የሚችል ሀገሮች እና ተቋማት እንዳሉም ገልጸው፣ ቻይናን በአብነት ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያውያን በቻይና ገበያዎች የመሳተፉ ዕድል አላቸው። ቻይና ከአፍሪካ ጋር የንግድ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር፤ ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ትገኛለች። ይህ አፍሪካን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ከተቋማት አንፃር ተቋማት በቻሉት አቅም እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ በሀገር ውስጥ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ ሥራ እንዲፈጥሩ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ድጋፍ ያደርጋል። ወደ ኢንዱስትሪ ሲገቡ ደግሞ አነስተኛ እና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ልማት ኢንተርፕራይዝ ይደግፋቸዋል። በደረጃ ሲያድጉ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል።
እንደ የፕሮሞሽን ባለሙያዋ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲ ያልገቡትም ቢሆኑ፤ ከወረዳ ጀምሮ የጥቃቅን እና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዝ እንደየሥራ ፍላጎታቸው ሥልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል። እንደየዘርፋቸው ከፋይናንስ አንፃር የብድር አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ሥራ ላይ ከሆኑ ማሽን የሚያገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ የማመቻቸት ሥራ ይሠራል።
በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የኮሜሳ ሕብረት አባል ነች። ሥራውም የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ተልዕኮ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሕብረቱ አባልነት ጉዳይ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፡፡
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ እና የኢንዱስትሪ ጉዳዮችን በመያዝ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገሮች ጋር በትብብር እንድትሠራ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጣናው ሀገሮች ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያድግ እና በእነዚህ የቀጣናው ሀገራት መካከል ጤናማ ቀጣይነት ያለው የንግድ እና የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሳለጥ ማድረግ ዋነኛ ሥራው መሆኑን ጠቁመዋል።
የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ ኮሜሳ ዋና ዓላማው የቀጣናውን አባል ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር ማጠናከር ነው ይላሉ። በተለይ የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ ማሳለጥ መሆኑን አስታውቀዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በእነዚህ ሀገሮች መካከል ያለውን የነፃ የንግድ ቀጣና ግንኙነት በፕሮሞሽን ባለሙያዋ የተገለፀውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ውጤታማ ለማድረግ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በቀጣናው ውስጥ ያሉትን ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እንደተባለው ሁሉ፤ ከዚሁ ከኮሜሳ ጋር ተያይዞ የኮሜሳ አንዱ ክንፍ የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን መኖሩን ያስረዳሉ።
ፌዴሬሽኑ የሴቶችን እና የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ በቀጣናው ያሉ ሴቶች እና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተመለከተ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
በፌዴሬሽኑ ሴቶች እና ወጣቶች በቀጣናው ኢኮኖሚ ላይ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ይሠራል። ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚያግዝ ሲሆን፤ በተለይ የሴቶች እና ወጣቶች ምርቶች እና አገልግሎቶች ከገበያው ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ሥራ አስፈፃሚው አቶ ወንድሙ እንዳብራሩት፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሥራ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካውያን ጋር ለመተሳሰር እና ተገቢውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ የወጣቶች፣ የሥራ ፈጣሪ ሴቶች አጠቃላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ንግዱን በዕውቀት በቴክኖሎጂ እንዲሁም ዘመኑ በደረሰባቸው የመረጃ መረቦች አማካኝነት ግብይት መፈፀም አለበት። ባለሀብቱ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የራሱ ድርሻ አለው፤ የነጋዴ ሴቶች እና የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችም ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።
ለንግዱ ማኅበረሰብ በተለያዩ ጊዜያት ክህሎት መፍጠር፤ አዳዲስ የሥራ አማራጭ ሃሳቦችን በዕውቀት ደረጃ ማስረፅ ብቻ ሳይሆን፤ ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በቀጣይነት በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ተቋማቱ አንድ ሀገር ውስጥ በመሆናቸው እንደ አንድ ተቋም ሁለቱም ተቋማት ተቀናጅተው ይሠራሉ የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ አንደኛው ክህሎት በማዳበር የንግዱን ማኅበረሰብ፣ በተለይም ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እና ሴቶች ላይ ሲሠራ፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ደግሞ የንግድ እና የኢንቨስትመንትን ሥርዓት በማሳለጥ እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።
በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች እና የኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች በማሕቀፎች ውስጥ ጎልተው መውጣት ይጠበቅባቸዋል። እንደ ኮሜሳ ዓይነት ማሕቀፎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ በማመልከት፤ መጫወት የሚገባቸውን ሚና ተጫውተው ለራሳቸው እና ለሀገራቸው የተሻለ ጥቅም እንዲያስገኙ እንዲሁም ተጠቃሚነታቸውም በጋራ ተጠቃሚነት መንገድ ላይ እንዲመሠርቱ ያስችላል ብለዋል።
የራስን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ በእኩል የመጠቀም መሠረት ላይ የተቋቋመ የንግድ ግንኙነት ሲፈጠር፤ ተቋማት የየራሳቸውን ድርሻ ሲጫወቱ እና እነዚህ ሲደማመሩ ሀገራዊ ውጤቱ ትልቅ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና ቅምሻ በሚል ኤግዚብሽኑ ላይ የተሳተፈችው ቤዛዊት ፈቃደ በበኩሏ፤ የሁለቱንም ሃሳብ በመደገፍ፤ የሀገራት ስምምነቶች፤ ኮሜሳን በመሳሰሉ ማሕቀፎች እና ግንኙነቶች ገበያ እና ገበያተኛውን ለማገናኘት በተለይም ወጣቶችን እና ሴቶችን፤ አምራች እና ነጋዴዎችን ለማግኘት እና ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብላለች፡፡
የሰሞኑን የኮሜሳ ኤግዚብሽን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ እና ወደ ውጭ የሚላኩ በተለይ የቆዳ ምርቶችን፣ የቅባት እህሎችን እና ቡናን የመሳሰሉትን የኢትዮጵያን ምርቶች ምርቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ በመጠቆም፤ በንግድ ከማስተሳሰር ጎን ለጎን የኤግዚብሽኖች መዘጋጀት ሀገርን እና የሀገርን ምርት ለማስተዋወቅ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ገልፃለች።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ እንደ አአአ በ1994 ታኅሣሥ ወር የተመሠረተው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ /ኮሜሳ/ በአፍሪካ ትልቅ የሚባል ምጣኔ ሀብታዊ ተቋም ነው። 21 አባል ሀገሮችን ያቀፈ ሲሆን፣ በእነዚህ ሀገሮችም 390 ሚሊየን ሕዝብ ይኖራል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም