ማህሌት አብርሃም እንዲህ ትላለች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሰሯቸው መልካም ነገሮች ለእኔ ወደ ተለያዩ አገራት ሄደው ሀገሪቷ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት ያደረጉት እንቅስቃሴ አንዱ ነው። በመገናኛ ብዙሃን እንደሰማሁት ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ያግዛል የሚል ዕምነት አለኝ።
ሌላው ዶክተር ዐብይ ጥሩ ነገር ሰርተዋል ብዬ የማስበው አገርን ሲበድሉ የነበሩ ወንጀለኞች እንዲጋለጡና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረጋቸው ነው። እስከዛሬ ድረስ ሳይታወቁ ብዙ አሰቃቂ ወንጀሎችን የሰሩ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ መደረጋቸው በአገራችን ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን የሚያደርግ በመሆኑ ዶክተር ዐብይን የሚያስመሰግን አሪፍ ሥራ ነው።
ይሁን እንጂ የእርሳቸውን ወደስልጣን መምጣትና በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ ግጭቶችና ሁከቶች ተፈጥረዋል። ግጭቱን በሚፈጥሩ አካላት ላይ ምንም እርምጃ እየተወሰደ አይደለም። ሰዎች እየተደበደቡ ከቦታቸው ሲፈናቀሉና ንብረታቸውን ሲዘረፉ ከዛም አልፎ ሲገደሉ በዝምታ ነው የታለፈው። ህግ አስከባሪዎችም ኃላፊነታቸውን በሚገባ አልተወጡም። ይሄ መደገም የለበትም። በጣም በአፋጣኝ ሊስተካከል ይገባል።
አሁን ላይ ለውጥ አለ የሚባለው በላይኛው አካል ላይ እንጂ እንደ እኔ አረዳድ ታች ላይ የሚታይ ለውጥ የለም። በአመራር ደረጃ ያለውን ለውጥ እናደንቃለን። ህዝቡ ላይ ካልተሰራ የአመራር ለውጥ ብቻውን ዋጋ የለውም። ታች ላይ በደንብ መሰራት አለበት።
ወጣቶችን በተመለከተም በዶክተር ዐብይ የሥልጣን ጊዜ ለውጦች አይቻለሁ። እኔ ባለሁበት አካባቢ የወጣቶችን ችግር ለመፍታት ብዙ እየተሰራ ነው። ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ እና ብድር ተመቻችቶላቸው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። እየተደረገ ያለው ድጋፍ ያለስራ ተቀምጦ የነበረውን ወጣት እያነቃቃው ይገኛል። ቤተሰቡን እንዲያግዝና ለሀገሩም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የሚያደርግ አሪፍ ጅምር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ።
ኩመላ ፉፊ ደግሞ በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በህይወት ዘመናችን እናያለን ብለን አስበናቸው የማናውቃቸውን ብዙ ለውጦችን አይተናል። በፖለቲካ ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው በውጭ አገር ይኖሩ የነበሩ በርካታ ምሁራን ተመልሰዋል። ይህም በቀላሉ ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ነበር። ለህዝብና ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን ነገር በመናገራቸውና በመጻፋቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ወንጀለኛ ተብለው በየእስር ቤቱ ሲማቅቁና ሲሰቃዩ የነበሩ አብዛኞቹ ከእስር ተፈትተዋል።
በዜጎች ላይ በርካታ አሰቃቂና ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈጸሙበት የነበረው፣ሥርዓቱን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች በግፍ የሚሰቃዩበትና የሚገደሉበት የማዕከላዊ እስር ቤት ተዘግቷል። በህይወቴ ማዕከላዊ ይዘጋል ብዬ አንድም ቀን አስቤው አላውቅም፤ በአገሪቱ የመጣው ለውጥ ይህንም አሳይቶኛል። በጣም ደስ ብሎኛል።
በአጠቃላይ ለውጡ ዓለም ሁሉ የመሰከረለት ነው። ለውጡ በፈለጉት መልኩ ያልሄደላቸውና ያልተዋጠላቸው አካላት ሊኖሩ ይችላሉ። የዲሞክራሲ ባህላችንም ገና ያላደገና ልምምድ ላይ በመሆናችን በለውጡ ሂደት ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮችና ተግዳሮቶች ሊገጥሙ ይችላሉ።
አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ አለመግባባቶችና ሌሎችም ችግሮች የዚህ ውጤት ናቸው። ለዲሞክራሲ ባህል አዲስ ከመሆናችን የተነሳ እንዲህ ዓይነት ነገሮች በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙና የሚጠበቁ በመሆናቸው ያን ያህል የሚያሰጋ ሁኔታ አይታየኝም። እንዲያውም ለውጡን በሥርዓት መጠቀም ያልቻልነው እኛ ነን እንጂ የመንግሥት ችግር ነው ብዬ አላምንም።
እኛ ወጣቶችም ከለውጡ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም አግኝተናል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የፈለግነውን ፖለቲካዊ አመለካከት በነጻነት እንድናራምድና የፈለግነውን ፖለቲካ ፓርቲ ያለፍርሃት እንድንደግፍ ዕድል ፈጥሮልናል።
ከዚህ በፊት እኮ አንድ የምትደግፈውን ተፎካካሪ ፓርቲ አርማ ይዞ መውጣት እኮ ያሳስራል። ሃሳባችን በነጻነት እየገለጽን ነው፤ ይኼ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ለወጣቱ ትልቅ ፋይዳ ነው ያለው። ይህ እንዲሆንም ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፤ ዝም ብሎ በቀላሉ የመጣ ለውጥ አይደለም።
አምቦ ከተማ የሚኖር ወጣት “ጣና ኬኛ” ብሎ የባህር ዳር ወንድሙን ችግር እንደ ራሱ ችግር አይቶ አንድ ላይ ተባብሮ የሀገሩን ችግር የሚፈታበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በኢኮኖሚም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ባይባል እንኳን ለወጣቱ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቢሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። በቀጣይም ወጣቱ ከዚህ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም ለዶክተር ዐብይ ያለኝን ፍቅር የምገልጽበት ቃላት ያንሰኛል። በዚሁ ይቀጥልልን፤ ይበርታልን።
ህይወት ተስፋዬ በበኩሏ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ከተመረጡ ብዙ ለውጦችን አይተናል። ለምሳሌ በሰላም ግንባታ በኩል ለ20 ዓመታት ያህል በጠላትነት ስንተያይ ከቆየነው ከኤርትራ ጋር እንድንታረቅ ያደረጉት ጥረት ያስመሰግናቸዋል። የአሰብን ወደብ በጋራ እንድንጠቀም የሚያስችል ሥራም የሰሩ በመሆናቸው በቀጣይ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብዬ አስባለሁ። ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያለንን ግንኙነትም የበለጠ ለማጠናከር ወደ ብዙ አገሮች ሄደው የተለያዩ ስምምነቶችን እየፈረሙ ይገኛሉ። ይሄ በጣም ትልቅ ሥራ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ሰላም ያለው አዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው። በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኞቹ ያለው ሁኔታ ግን በጣም አሳሳቢ ነው። ሰላም የለም፤ በየቦታው ደም ይፈሳል፣ ግጭትና ፀብ ነው የሚታየው። በጣም የሚያሳዝን ነገር እየተፈጠረ ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሌሎች የውጭ አገራት ጋር ሰላም ለመፍጠር በስፋት ጥረት እንደሚያደርጉት ሁሉ በሀገር ውስጥም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል። እኛ ሰላም ሳንሆን ከማንም ጋር ሰላም ልንሆን አንችልም። ከዚህ በተረፈ ያለው ነገር በጣም የሚያበረታታ ነው።
ሱራፌል ዓለሙ ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሪፍ አሪፍ ነገሮችን አሳይተውናል። ለአብነትም መገናኛ ብዙሃን ከበፊቱ በተሻለ ትክክለኛ መረጃዎች በነጻነት የሚዘግቡበትና ለህዝቡ የሚያደርሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ወጣቶችም ስሜታዊ ሳንሆን ከለውጡ ጋር ተባብረን መስራት አለብን። ምክንቱም የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ የሚፈልግ ኃይል በመካከላችን ክፍተት ይፈልጋል።
ስለሆነም ይህን ተገንዝበን በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዛውን እርስ በእርስ የሚያባላ የሀሰት ወሬ በስሜት ሳንከተል ከዶክተር ዐብይ ጋር አንድ ላይ ተባብረን ከዚህ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንትጋ እላለሁ። ለመንግሥት የማስተላልፈው መልዕክት ዲሞክራሲን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ያህል የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ትንሽ ክፍተት የሚታይ በመሆኑ እዚህ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ቢወስድ የሚል ነው።
ማሙሽ እያሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ለእኛ ለወጣቶች ለአገራችንም ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ሰርተውልናል። እኛም የእርሳቸውን አርዓያ ተከትለን ለራሳችንና ለአገራችን ጥሩ ነገር እንድንሰራ አነቃቅተውናል።
የሥራ ዕድልም እየተፈጠረልን ነው። ነገር ግን ዶክተር ዐብይና ከላይ ያለው አመራር ለወጣቶች ጥሩ ጥሩ ነገር እንዲሰራ ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑም ከታች ሥራውን የሚፈጽሙት አካላት ግን በትክክል እየተገበሩ አይደሉም። በጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ላይ አድልኦ ይታያል።