በኦሞ አካባቢ አራት የስኳር ፕሮጀክቶች አሉ። ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1፣2፣3 እና 5 በመባል ይታወቃሉ። ከነዚህም ውስጥ 2 እና 3 ማምረት ጀምረዋል። በሂደት የፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የሚያስችሉ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው። ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 በስሩ ዘጠኝ ፓኬጆችን ያካተተ ሲሆን የመስኖና የእርሻ ስራዎች ተሰርተዋል። የፋብሪካው ግንባታ ግን በሚፈለገው ደረጃ አልተከናወነም።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጥር ወር አንድ ቡድን ወደ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1፣3 እና 5 ስኳር ፋብሪካዎች የመስክ ምልከታ አድርጎ ተመልሷል። በመስክ ምልከታ ሪፖርት ዙሪያ ቋሚ ኮሚቴው ከስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ በፓርላማ ውይይት አድርጓል። በሶስቱም ፋብሪካዎች ላይ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎችና እጥረቶች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በርካታ እጥረቶች እንዳሉበት በሪፖርቱ ከተመለከቱት ፋብሪካዎች ውስጥ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ተጠቃሽ ነው። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ፋብሪካ ከዚህ ቀደም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተይዞ የነበረ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ ግንባታውን በማጓተቱ የግንባታ ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ከሜቴክ ጋር የነበረው ውል እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ግን ፕሮጀክቱን ከሚገነባ አዲስ ኮንትራክተር ጋር የግንባታ ውል አልተፈረመም። በዚህም ምክንያት የፋብሪካው ግንባታ በዕቅዱ እየተጓዘ አለመሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ አመልክቷል።
ከወራት በፊት ከሜቴክ ጋር ርክክብ መፈጸሙንና አዲስ ኮንታራክተር መለየቱን ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል መፈራረም ብቻ እንደቀረ ስኳር ኮርፖሬሽኑ ለቋሚ ኮሚቴው አሳውቆ እንደነበር የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አካላት፤ እስካሁን ድረስ ለአዲስ ኮንትራክተር ሳይተላለፍ መቆየቱ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
እንደ ቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ ስኳር ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካውን ለአዲስ ኮንትራክተር አስተላልፎ በ2011 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅዱ ላይ አስቀምጧል። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ፕሮጀክቱ በዕቅዱ መሰረት እየተሰራ አይደለም። በዚህ አካሄድ ፕሮጀክቱ በተያዘው እቅድ መሰረት ሊጠናቀቅ አይችልም። ይህም ሀገሪቷ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ያደርጋል። በተለይም የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ጫና አሳድሯል፤ እያሳደረም ይገኛል።
በፋብሪካው መጓተት ሳቢያ የአካባቢው አርብቶ አደር ማሳ ላይ የተመረተው ሸንኮራ አገዳ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ የአካባቢው አርብቶ አደር በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣም ምክንያት እየሆነ እንደሆነ አስረድተዋል። ስኳር ኮርፖሬሽን ራሱ ያመረተው ሸንኮራ አገዳ እንዳይበላሽ ቁጥር ሶስትና ሁለት ላይ ወስዶ ሲጠቀም አርብቶ አደሮች ያመረቱትን አገዳ ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆኑ አርብቶ አደሮችን ማስቆጣቱን ጠቁመዋል።
እንደ ጥናቱ ግኝት የፋብሪካው መጓተት በአርብቶ አደሮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን የዞኑ እና የወረዳው አመራሮች በኮርፖሬሽኑ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል። ከዚህ ቀደም የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከአካባቢው አመራሮች ጋር የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ አለመደረጉ አመራሮች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል። በዚህም ምክንያት ፋብሪካው ላይ የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙ ነው ሲል ሪፖርቱ ይገልፃል።
የስኳር ኮርፖሬሽን ተወካይ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዋዮ ሮባ እንደሚናገሩት፤ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ በሜቴክ ሲገነባ ነበር። ሜቴክ ባሳየው ደካማ አፈጻጻም ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ውሉ እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ በሜቴክና በስኳር ኮርፖሬሽን መካከል ርክክብ የማድረግ ሂደት ወራትን ፈጅቷል። ርክክቡ ከመፈጸሙ በፊት በፕሮጀክቱ ስር በሚገኙ በሁሉም ፓኬጆች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። ያለቀውንና ያላለቀውን ስራ መለየት አስፈላጊ በመሆኑ ስራው ተከናውኗል ብለዋል።
ከሜቴክ ጋር ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ በፊት ፋብሪካው ውስጥ ያልተካተቱ አዳዲስ ስራዎች ጭምር ተሰርተዋል ያሉት አቶ ዋዮ፤ የዲዛይን ችግር ያለባቸው ፓኬጆች ላይ የማስተካከያ ስራዎች ተሰርተዋል። ምክንያቱም መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ሳይስተካከሉ ለአዲስ ኮንትራክተር በአፋጣኝ ተላልፏል ለማለት ብቻ ተላልፎ ሌላ ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ ስላለበት ነው። እነዚህ ስራዎች ከግማሽ ዓመት በላይ መፍጀታቸውንም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዋዮ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ ቴክኒካልና ፋይናንሺያል ግምገማ ተጠናቋል። ለአዲስ ኮንትራክተር ለማስተላለፍ የድርድር ኮሚቴም ተቋቁሟል ድርድር እየተካሄደም ነው። ድርድሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል ይታሰራል ተብሏል። ድርድሩ ተጠናቆ ከአዲስ ተቋራጭ ጋር ውል ከታሰረ በኋላ እንደ በፊቱ አይጓተትም። ከስድስት እስከ ሰባት ወር ባሉ ጊዜያት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ኮርፖሬሽኑ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፕሮጀክት ላይ የለማውን ሸንኮራ አገዳ ቁጥር ሶስት ላይ ወስዶ መጠቀሙን የገለጹት አቶ ዋዮ ቁጥር 1 አቅራቢያ ያሉ አርብቶ አደሮች ያለሙት ሸንኮራ አገዳ ግን ስላረጀ ቁጥር 3 ላይ ሄዶ አገልግሎት ሊሰጥ የማይችል በመሆኑ እንዲወገድ መደረጉን ገልጸዋል። አገዳው ጥቅም ላይ ባይውልም እንኳ ለአርብቶ አደሮቹ ካሳ በመክፈል እንዲወገድ ተደርጓል። ፋብሪካው በአጭር ጊዜው ውስጥ ስለሚጠናቀቅ ከአሁን በኋላ አርብቶ አደሮች ያለሙት አገዳ እንደማይባክን ቃል ገብተዋል።
እንደ አቶ ዋዮ ማብራሪያ፤ ብድር ሳይዘጋጅ፣ የሀገር ውስጥ አቅም ሳይፈጠር፣ ፋብሪካዎችን ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት ሳይዘረጋ 10 ስኳር ፕሮጀክቶች መጀመራቸው አሁን ለሚታየው ችግሮች መንስኤዎች ናቸው። ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙት ችግሮች እንዳይደገሙ ኮርፖሬሽኑ፣ ተቆጣጣሪ አካላትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በመቀናጀት ያልተጠናቀቁት ፋብሪካዎች እንዲጠናቀቁና በማምረት ላይ ያሉት በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማስቻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለምለም ሀድጉ እንደተናገሩት፤ ህዝቡ ለስኳር ያለው ፍላጎት በከተማም በገጠርም እየጨመረ መጥቷል። በመገንባት ላይ ያሉ ስኳር ፋብሪካዎች ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ፍላጎት አንጻር እጅግ ተጓተዋል። የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ሀገሪቱ ስኳር ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያጣች ነው።
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድን ጨምሮ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ቢጠናቀቁ የሀገሪቱ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይችላል። ውጭ ሀገር በመላክ ምንዛሬ ማስገኘት ባይቻል እንኳ በሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት በማሟላት ስኳር ከውጭ ለማስገባት እየወጠ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚቻል አመልክተዋል።
መድሃኒትን የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ ነገሮችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት መዋል ያለበት የውጭ ምንዛሪ ስኳር ለማስገባት ማዋል መቆም አለበት ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ‹‹ሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ስኳር እንዴት ከውጭ ይገባል የሚል ቁጭት በውስጣችን ሊያድር ይገባል›› ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች በአፋጣኝ በማጠናቀቅ የሪፎርሙ ውጤት በስኳር ፕሮጀክቶች ላይ በተጨባጭ መታየት መጀመር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። እንደ ወይዘሮ ለምለም ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ የስኳር ፋብሪካዎች መቼ ግንባታቸው ተጠናቆ መቼ ማምረት እንደሚጀምሩ አሁንም በእርግጠኝነት አይታወቅም። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይጠናቀቃል ተብሎ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸው ሳይጠናቀቁ ቆይተዋል። ከተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ሶስቴና አራቴ የተራዘሙ አሉ። ይህ ከአሁን በኋላ መቀጠል የለበትም ብለዋል።
ስህተት አንዴ ወይም ሁለቴ እንጂ በተደጋጋሚ እንዲፈጠር መፈቀድ የለበትም። ፕሮጀክቶቹ ባለመጠናቀቃቸው በድህነት አረንቋ ውስጥ ያለች ሀገርና ህዝብ እያጡ ያሉትን ጥቅም ቆም ብለን ካለማየት የመነጨ ነው። ይህ አካሄድ ከአሁን በኋላ መቀጠል የሌለበት በመሆኑ መስተካከል አለበት። ቋሚ ኮሚቴውም ለኮርፖሬሽኑ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ የቋሚ ኮሚቴውን አቋም ተናግረዋል።
የስኳር ፋብሪካዎች ሁለመናቸው በአካባቢው ካለ ማህበረሰብ ጋር የተቆራኘ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ለምለም፤ ማህበረሰቡ ፋብሪካዎቹን የኔ ናቸው ብሎ እንዲያስብ መሰራት አለበት ብለዋል። ለፋብሪካዎቹ ዋስትና የሚሆነው ከመንግስት ጥበቃ በላይ የአካባቢው ማህበረሰብ ጥበቃ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 አካባቢ ካሉ አርብቶ አደሮች ‹‹መንግስት ዋሽቶናል›› በሚል በስኳር ኮርፖሬሽኑ ላይ ቂም መቋጠራቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑንም አብራርተዋል። ኮርፖሬሽኑ ለአርብቶ አደሮቹ ቃል ገብቶ ተግባራዊ ያላደረጋቸውን ነገሮች በአፋጣኝ ማስተካከል አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል። ከኮርፖሬሽኑ አቅም በላይ የሆነ ነገር ካለም ለአርብቶ አደሮቹ በግልጽ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የኦሞ ቁጥር 1 የስኳር ፕሮጀክት ካሉበት የቆዩ ችግሮች ተላቆ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ጥቅም እንዲያበረክት የሚመለከታቸው አካላት የሚያደርጉት ርብርብ ወሳኝ ነው። በመሆኑም የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮችም ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን ጭምር በማከናወን የፕሮጀክቱን ትንሳኤ ሊያረጋግጡ ይገባል።
ለተጨማሪ ሊንኩን ይጫኑ
መላኩ ኤሮሴ