የአፈር ሳይንስና ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ባለሙያና የሀወሳ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው ። የዛሬ የስኬት አምድ እንግዳችን። ለስኬት አምድ ስናስባቸው የዩኒቨርስቲ መምህርነት ወይም አካዳሚክ ህይወታቸው አይደለም የሰባን። በሀዋሳ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ በሚያካሂዱት የከተማ ግብርና ተጠቃሽ መሆን መቻላቸው ነው። የከተማዋን የአረንጓዴ ልማትንም ያማክራሉ፤ ዶክተር ጋሻው ምትኬ።
በቅርቡ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በ2015 በጀት አመት በሚያከናውናቸው እቅዶች ላይ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ለመስራት እንዲያስችለው ካዘጋጀው መድረክ ጎን ለጎን የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክቶችን አስጎብኝቶ ነበር። ከፒያሳ ወደ ሴንትራል ሆቴል እና አሞራ ገደል የሚወስደውን ውብ መንገድ ይዘናል። አሞራ ገደል ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ዋናውን መንገድ ወደ ቀኝ ትተን ወደ ግራ ታጠፍን። መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ደርሰን፤ ዶክተር ጋሻው ከውጭ ተቀብለውን ወደ ግቢያቸው ይዘውን ዘለቁ። ዶክተር ጋሻው ምትኬን ያገኘናቸውም፣ የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ የእኚህን ሰው የከተማ ግብርና ስራ እንድንጎበኝ ባመቻቹት መሰረት ነው።
ግቢው በእጅጉ ይማርካል፤ የጓሮ አትክልቶቹ፣ የፍራፍሬ ተክሎቹ፣ ቡናው፣ አበቦቹ፣ ሳሩ ግቢውን በእጅጉ አስውበታውታል። መሬቱን ብቻ አይደለም ያለሙት፤ በሽቅብ ግብርናም/ ቨርቲካል ፋርሚንግ/ አጥሩንም፣ ግድግዳውንም አትክልት በአትክልት አድርገውታል። ሳሩ ተከርክሞ ሲታይ ከመጥበቡ በስተቀር ስታዲየም ይመስላል። ችግኝ የሚያፈሉበት ስፍራም አላቸው።
ዶክተር ጋሻው፣ የተወለዱት በጅግጅጋ ከተማ ነው። የወታደር ልጅ ነኝ ይላሉ። አሁን ወደ ጡረታው እያልኩ ነኝ የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ ረጅም፣ ገዘፍም ያሉ ናቸው። በእዚህ እድሜያቸውና ቁመናቸው ያን ልማት ጎንበስ ቀና እያሉ ይሰሩታል ተብሎ አይታሰብም። እሳቸው ግን የግቢያቸውን አትክልቶች ብቻ ሳይሆን ከግቢያቸው ውጪም ተሻግረው ይሰራሉ።
የከተማ ግብርናውን ከጀመሩ ሁለት አመታት ተቆጥረዋል፤ ዶክተር ጋሻው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥም በዩኒቨርሲቲው ግብርና ኮሌጅ ግቢም በአረንጓዴ ስፍራ ልማት ሰርተዋል፤ ሀዋሳ አሁን ለያዛችው ገጽታ ታስክ ፎረስ በመምራትና በፈቃደኝነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። አሁን ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመጡም የነዚያ አካባቢዎች ተሞክሮ ማስፋታቸውን ይገልጻሉ።
በየቀኑ ማለዳ 11፡30 ተነሰተው የአካባቢውን አረንጓዴ ስፍራ በሙሉ በረጅም ቱቦ ውሃ ያጠጣሉ። በዚህም እናቶች ይመርቋዋል፤ ወደ ግቢያቸው ተመልሰውም ተመሳሳይ ስራ ይሰራሉ። የውጪውን ቢያንስ በሳምንት ሁለት ሶስት ቀን ፣ የግቢያቸውን ግን በየቀኑ ውሃ ያጠጣሉ። በእሳቸው አቅም ያልሆነውን ደግሞ ሌሎች ያግዟቸዋል።
እሳቸው እንደተናገሩት፤ የከተማ ግብርናውን የሚያካሂዱት ከ600 እስከ 700 በሚሆን ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው። በዚህ የአትክልት ስፍራ ሶስት አይነት ስራዎች /ኮምቢኔሽን/ ይታያሉ። መሀል ላይ የፍራፍሬ ተክሎች፣ /አቦካዶ፣ ፓፓዬ፣ ማንጎና ሮማን እና ቡና/ አላቸው። እንደምታዩት ደግሞ አበቦች አሉ የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ የአትክልትና የመሳሰሉትን ችግኞች ያፈላሉ፤ ችግኞቹም የአትክልት ምርቶቹም ከእሳቸው ፍጆታ በላይ ናቸው። ‹‹ቆስጣ በጣም ጥሩ ተከል ነው። አራት አምስት ጊዜ ምርት ይሰጣል ሲሉ ገልጸው፣ እሳቸው ለገበያ እያመረቱ አይደለም፤ ከፍጆታ ውጪ ያለውን ምርት ገጠር አካባቢ እንደሚደረገው ለማህበረሰቡ ይሰጣሉ።
ለአትክልት መትከያ እቃ ፍለጋ ሲሉ አንዳንዴ እቃዎችን በቆራሌ መልክ እንደሚሰበስቡም ነው የሚናገሩት። ለአትክልት መትከያ የሰበሰቧቸውን የዘይት እቃና የመሳሰሉትን ቁሳቁስን አሳዩን። ጣሳው ተበስቶ አፈር ተሞልቶ ጊዚውን ጠብቆ ችግኙ ይተከላል፤ የሚፈላም ከሆነ ዘሩ ይዘራል።
ለከተማ ግብርናው ላንድስኬፕ ሌላው ኮምፓነንት ነው የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ የአትክልት የአበባ የሳር አይነቶችን ይሰበስባሉ፤ ሳሩ እንደመጣ አይተከልም፤ እየተበተነ ነው በመስመር የሚተከለው፤ ፍግ ያደርግበታል፤ ውሃ በአግባቡ እንዲጣጣ እየተደረገም ነው ውብ ሊሆን የቻለው። በእዚህ ላይ ችግኞች ያዘጋጃሉ።
ዶክተር ጋሻው፣ የተሻሻለ የፓፓያ ዝርያ ከደቡብ ክልል የአትክልት ባለሙያዎች ወስደው ለመትከልም አቅደዋል፤ በጣም በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሬዲሜድ የሚባል ዝርያ ነው፤ አይታችሁት ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወላይታ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የጎበኙት የፓፓያ ዝርያ ነው፤ በጣም ጣፋጭ አጭርና በትንሹ 60 እና 70 ፓፓያ የሚይዝ ነው ። እሱን በብዛት መትከል እፈልጋለሁ ሲሉ ገለጹልን።
የአርሶ አደር ልጅ አይደሉም፤ የወታደር ልጅ ናቸው፤ ታዲያ ትምህርታቸው ወይስ ያደጉበት አካባቢ ነው ወደ ከተማ ግብርና አንዲያዘነብሉ ያደረጋቸው? ከተባለም፤ ሁሉንም አይደሉም። እርግጥ ነው ዶክተር ጋሻው ፕሮፌሽናሊ ለግብርና የተጠጉ ናቸው። በከተማ ግብርናው ላይ ይህን ያህል እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው ግን ይህ ምክንያትም አይደለም። ባደጉበት አካባቢ ስለባቄላ፣ጤፍና ሌሎች የሰብል አይነቶች አያውቁም፤ ከጅግጅጋ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ነው የእነዚህን ሰብሎች ልማት የተመለከቱት ፤ ቢሾፍቱ። ‹‹የሆነ ነገር ተተክሎ ሲያድግ የማየት ፓሽን አለኝ፤ ከልጅነቴ አንስቶ ውስጤ ያለ ነገር ስለሆነ እንጂ ከትምህርትም ከአስተዳደግም ጋር የተያያዘ አይደለም ሲሉ ያብራራሉ።
በከተማ ግብርናው ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል። በዚህም በእጅጉ ተደስተዋል፤ ተከታይ ማፍራታቸውን በስራው ስኬታማ ለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ አርገውም ይወስዱታል። የአካባቢው ነዋሪዎች እሳቸውን ተከትለው የጓሮ አትክልት ማልማት ጀምረው ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው። እሳቸውም እነሱን ያሰልጥናሉ፤ ይከታተላሉ/ ኮች ያደርጋሉ/።
በአቅራቢያችን አንዲት አካል ጉዳተኛ በእኔ ኮቺንግ አትክልት ማምረት ጀምራ በአሁኑ ወቅት ከራሷም አልፋ ለሰዎች እየሰጠች ነው ሲሉ የሚጠቅሱት ዶክተር ጋሻው፣ ውሃ ልማት በሚባለው በሚኖሩበት አካባቢ የሴቶች እና የወጣቶች አደረጃጀቶች በክፍለ ከተማው ያለውን ሰፊ ክፍት ቦታ ተደራጅተው በማልማት አትክልት በብዛት እያመረቱ ናቸው። የእናቶች የልማት ቦታና ምርቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ፓስት እየተደረጉ መሆናቸውን ዶክተር ጋሻው ይገልጻሉ። በተለይ ቆስጣ ደስ የሚል ነገር አለው፤ ምርቱን ይዞ ቤት ሲኬድ በጣም ያረካል፤ ይህም በዚህ በተወደደ ኑሮ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል ይላሉ።
እሳቸው መናኸሪያ አካባቢ ካለ ምግብ ቤት ጋር በፈጠሩት ትስስር አምራቾቹ አንድ ጊዜ ከእምስት ሺ ብር በላይ ሌላ ጊዜ ከስድስት ሺ በላይ ብር አግኝተዋል። በተለይ ሰላጣ በደንብ ሽጠዋል፤ ባለሆቴሏ በተለይ ሴቶችን ማበረታት የምትፈልግ በመሆኗ በቀጣይም ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
ልጆች ላይ ሰርተዋል፤ ሆነ ብለው ሰብስበው ግን አይደለም፤ እኔን ሲያገኙ ዶክተር ስለሚሉኝና ውሃ እንዲያጠጡ እድሉን ስለምሰጧቸው ይደሰታሉ፤ የቀለም ጣሳ በሚገባ በስተው አዘጋጅተው ይሰጧቸዋል፤ እነሱም የተከሉትን አምጥተው ያሳዩዋቸዋል። ይሄ ለእሳቸው ትልቅ እርካታ ሰጥቷቸዋል። በእዚህ ሁሉ በጣም ተሳክቶልኛል።
በሰዎች በእናቶች አእምሮ አድርያለሁ፤ በዚህ በኩል ብዙ ሰዎች ወደ መዳህኒአለም ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ፤ የእነሱን የየቀኑ ምረቃ ደግሞ ልዩ ነው ፤ መልካም ምኞታቸውን ሁሌም እንደገለጹልኝ ናቸው። እኔን እንደ ማመሳከሪያ /ሪፈረንስ/ ይመለከቱኛል ይላሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ፣ የፌዴራል መንግስት ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች የአትክልት ስፍራቸውን በተደጋጋሚ መጎብኘታቸውን ይናገራሉ ። በከተማና መሰረተ ልማት ሃላፊዎች በፓርላማ አባላት ጭምር ስራቸው ተጎብኝቷል። ሰዎች ስራቸውን ሊጎበኙ ወደ ግቢያቸው ሲመጡ ደስተኛ ሆነው ያስተናግዳሉ።
ምቹ ሁኔታ ባገኝ በቀጣይም ስራውን ባሰፋ እወዳለሁ የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ በዚህ ስራ በምኖርበት ቀበሌ፤ ክፍለ ከተማና ከተማዋ ላይ ያስገኘነው ጥሩ ውጤት አለ ሲሉ ገልጸው፣ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጉብኝት የሚመጡ ሁሉ ይህን ለማስፋት ምን ሀሳብ አለዎት የሚል ጥያቄ እንዳቀረቡላቸውም ይናገራሉ። ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ ለማስፋት ደስተኛ መሆናቸውን እንደነገሯቸው ይጠቅሳሉ።
የቤተሰብና የስራ ባልደረቦቻቸው ድጋፍ አላቸው። ባለቤታቸው በክልሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በተፈጥሮ ሀብት ላይ ይሰራሉ። የግብርና ግንዛቤው ስላላቸው በዲዛይንና በመሳሰሉት ለዶክተር ጋሻው ድጋፍ ያደርጉላቸዋል። ከእሳቸው ሙያ ውጪ በሆኑት ደግሞ በዲዛይን የሚያግዝ የስራ ባልደረባ አላቸው፤ ከተባይና ከበሽታ ጋር ያሉትን ችግሮች በመፍታት በኩል የማያወቋቸውን የተባይ መከላከያ ባለሙያዎችን ያማክራሉ።
ሀዋሳ ከመጣሁ በሁለት አመት ውስጥ ለከተማዋ የበኩሌን ብዙ አስተዋጽኦ በፍላጎቴ አድርጌያለሁ የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ በእዚህም ሰርተፍኬቶች እና የተለያዩ ሽልማቶች አግኝተዋል፤ የሚኖሩበት ከፍለ ከተማ በከተማ ግብርናው አንደኛ ወጥቶ ሰሞኑን መኪና ተሸልሟል። ለእሳቸው ደግሞ የምስክር ወረቅትና የአራት ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ። ከሳምንት በፊትም በክፍለ ከተማ ደረጃ ዋንጫና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል። ሁሉም የበለጠ እንድሰራ የሚያበረታቱ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ ይላሉ።
እኔ የፓለቲካ ሰው አይደለሁም የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ የከተማ ግብርናው ዋና አቀንቃኝ ግን ነኝ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። ለእዚህ ተሰልፈው እስከ መጨረሻው ለመስራት ዝግጁም ናቸው።
የከተማ ግብርና ስራውን የሚያካሂዱት በፓለቲካ ግፊት እንዳልሆነም ይገልጻሉ። በኛ ደረጃ የተማሩ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ጭምር እንዲህ አይነቱን ነገር ከፓለቲካ ጋር ያይዙታል፤ የግርግር የፓሮፓጋንዳ ስራ አርገው ይመለከቱታል ሲሉ ዶክተር ጋሻው ጠቅሰው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ግብርና ስራም የሚያሾፉ አንዳንድ የፌስ ቡክ ቀበኞች እንዳሉም ይጠቅሳሉ።
ይሄ በምንም አይነት መልኩ የፓለቲካ ስራ አይደለም፤ አሁን በየቦታው ሰዎች በክፍት ቦታዎች፣ በተለያዩ ቁሳቁስ አትክልት እያመረቱ ናቸው። እነዚህን ምርቶች ፍለጋ ወደ ገበያ አይሄዱም፤ ንጹህ ምርት ያገኛሉ፤ ልማቱ ለምግብ ዋስትና ፋይዳ አለው፤ ግብርናው በእርግጠኝነት የሰዎችን ሕይወት ይቀይራል፤ ገቢን ይጨምራል፤ እናቶች አየተጠቀሙ ናቸው ሲሉ ስለከተማ ግብርናው ፋይዳና ስለደረሰበት ደረጃ ያብራራሉ።
እኛ ባለሙያዎችና አመራሮች የምንሰራውን ማህበረሰቡ ይወስዳል ። ህዝቡ ጥሩ ነገር ካሳየነው ለሀገር ይሰለፋል የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ ህዝቡ ለመከላከያ ሲባል እንዴት ሆኖ እንደተነሳ ታይቷል። በመሀል ውዥንብር የሚፈጥሩ ቢኖሩም ለሀገሩ ሉአላዊነት የሚሰራም አለ። የተነሳው ለልማት ከሆነ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። ብዙ አስቸጋሪ ነገር አለ ፤ በምንችለው ግን ያንን ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ አለብን ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ማህበረሰቡ ለምሁራን የሚሰጠው ትልቅ ቦታ አለ። በእኔ በኩል እድሜዬና ዶክተርነት አለ፤ ይሄ አሁን ብዙ አስፈላጊ ባይሆንም አሁን በከተማ ግብርናው እየሰራሁ ያለሁት ስራ በማህበረሰቡ ዘንድ ያድራል፤ ሰዎች በእዚህ ነገር በጣም ይሳባሉ፤ እኔ ሰዎች አፍርቻለሁ፤ ምርቱን መስጠቱ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ነገር እንደ ልማድ /ሆቢ/ እንዲይዙት አምርቶ መብላት፤ ንጹህ ነገር ማግኘትና ኑሮን መደጎም አንደሚቻል ማሳየት የቻልኩ ይመስለኛል ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር ጋሻው ኢትዮጵያዊነት ላይም ጠንካራ አመለካከት አላቸው። ‹‹ለአባቴ እግዚአብሄር ይሰጠውና ኢትዮጵያዊነት ውስጤ አለ። ›› ሲሉ ይናገራሉ። በእዚህ በጣም ይኮራሉ፤ በወታደር ልጅ ዲስፕሊን ነው ያደጉት ይላሉ። አባታቸው በኦጋዴን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ ተሰልፈው አገልግለዋል፤ አሁን በጡረታ ላይ ናቸው። የእሱን እድሜ በእኔ መገመት ይቻላል የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ ቤታቸው ውስጥ ከፍተኛ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳለም ነው የሚናገሩት፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልኩኝ ለኢትዮጵያ እኔስ ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ ብዬ መስራት አለብኝ? ሲሉ ራሳቸውን ይጠይቃሉ ።
ብቻውን ዶክተር ነኝ ብትል ብዙም ዋጋ የለውም፤ ለራሰህ ፐብሊሽ ልታደርግ ትችላለህ፡ ከዚያ ያለፈ ለማህበረሰቡ ምን አደረግሁ ማለት ያስፈልጋል፤ ይህን ሁሉ አትክልትና የአረንጓዴ ስፍራ ውሃ ስታጠጣ ሰዎች ላይ የማሳደረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም የሚሉት ዶክተር ጋሻው፣ ይህም ለእኔ ስኬት ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
ራሴን ከፍከፍ ማድረግ አልፈልግም፤ ይሄ የወረደ ስራ አይደለም፤ በሰራሁት ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ መግባቴ በጣም ያስደስተኛል ሲሉ ገልጸው፣ ሁሉም ይህን ማድረግ እንደሚችል መክረዋል፤ በከንቱ ጣት መቀሰር እንደማይጠቅም፣ የጠፋ ነገር ካለ ጠጋ ብሎ መምከር እንደሚገባና ሀገር በፌስ ቡክ ዘመቻ እንደማይገነባም ያስገነዝባሉ።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም