አደይን የማያውቃት ማን ይኖር ይሆን? አደይ ወቅትን ጠብቃ አዲስ አመትን ልታበስረን በወርሃ መስከረም ብቅ ብላ የምታደምቀን አበባ ነች፤ አደይ አበባ። አደይ ወቅትን ጠብቃ መጥታ ወቅትን ጠብቃ ትሄዳለች፤ እንደ ህይወት። የእያንዳንዳችን ህይወትም በሆነ ወቅት የተገኘ የሆነ ጊዜ ደግሞ ምድርን የሚለቅ ነው። መነሻውም ሆነ መድረሻዋ በወቅት የሚገለጽ። አደይ በወቅት ውስጥ ትርጉም ያላት፤ በወቅት ውስጥ የምትኖር። በወቅቷ መጥታት የወቅቷን መልእክት አስተላልፋ የምትሄድ፤ የወቅት መልእክትኛ። የዘንድሮዋ አደይ ግጥም ገጥማ ግጥሟንም በዜማ አዋዝታበአደባባይ ላይ ወጥታ እየዘመረች ነው። ዝማሬውን የሰሙ ዝማሬ ይሆን እንጉርጉሮ እየተምታታባቸው ቢሆንም። በአደባባይ የተገኘ ሰው አደይን ለመስማት ግር ብሎ ወጥቶ የተገኘ ነው። በመገረም ለመመልከት፤ በመገረም ዝማሬን ለመስማት የሆነ ግር ማለት። የዝማሬዋ አዝማች እንዲህ ይላል፤
ዘመን ሄደ ዘመን መጣ፤
ሰው ተዘርቶ አፈር ወጣ፤
ሰው ከአፈር መሆኑ ቀርቶ፤
አፈር ተመዘነ ከሰው ቀሎ፤
ዝማሬ ወይንስ እንጉርጉሮ ብያኔው ለእያንዳንዱ አድማጭ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ በአደባባይ የሚሰማው ግን በቃ ይኸው ነበር። የአደይ ዜማ በአንድነት የሰበሰባቸው የወቅቱን መልእክት ለመስማት የተሰበሰቡት ወደ መጡበት ሲመለሱ ግን በሃዘን ውስጥ ሆነው ነበር።
ሚዲያ ላይ ስለ ወቅቱ የአደይ ዝማሬ አስተያየታቸውን የሚሰጡም ብዙ ነበሩ። “ጥበብ አቅሟ የሚታወቀው እንዲህ ባለ ወቅት ነው” በማለት የሥነ-ጽኁፍ አስተማሪው የአደይ ዝማሬን ተከትሎ በአንዱ ሚዲያ ቀርበው እየተነተኑ ነው። የአፈር አጥኚ ባለሙያ ደግሞ “አደይ በአፈር ውስጥ ስላለው እውነት በዜማዋ እንዴት እንደገለጠች የሚያስገርም ነው። አፈር ለሰው ልጅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስረዳ ዝማሬ ነው። አፈርና የሰው ልጅ ፈጽሞውኑ ሊነጣጠሉ እንደማይችሉ አደይ እያስተማረችን” ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ። የፖለቲካ አጥኚ ግለሰብ ደግሞ በሌላ ሚዲያ ላይ ቀርበው “የአደይ ዜማ ስለ ወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ብዙ የሚለው አለ። በጦርነት ሰው እረግፎ አፈር እየሆነ፤ ከአፈር የመጣው ሰው ወደ አፈር እንዲህ እየተመለሰ፤ መንገዳችን ማስተዋል የጠፋው ሲመስል ነው አደይ ለዜማ መውጣቷ” አሉ። የሃይማኖት አስተማሪው እንዲሁ በአንድ ሃይማኖታዊ ሚዲያ ላይ ቀርበው ስለ ዘመን አቆጣጠር እና በዘመናት ውስጥ የሰው ልጅ አፈር እየገፋ እንዴት ህይወትን ቅርጽ እንደሰጡ፤ይህም የሰው ልብ በላቡ ወንዝ እንጀራን እንዲበላ ከተጣለበት ኃጢአትን ተከትሎ ስለመጣው ትእዛዝ እንደሆነ እየተረኩ ነው። ነጋዴው በበኩሉ የሚዛን ጉዳይ አሁንም ቦታ ሊሰጠው የተገባ እንደሆነ ነጋዴው ከጊዜያዊ ጥቅሙ ባሻገር ስለ ህዝብ ማሰብ እንዳለበት የሚገባ መሆኑን አደይ በዜማዋ መልእክት እያስተላለፈች እንደሆነ ተረድቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የአደይ ዝማሬ አይሉት እንጉርጉሮ ብዙ መነጋጋሪያ ሆኖ ቀጠለ። አደይ በተገኘችባቸው አደባባዮች ግን የወቅቱን መልእክቷን እያሰማች ጉዞዋን ቀጥላለች። አደይ የዘንድሮው ወቅቱ የሰጣትን ጊዜ ስትጨርስ ትሰወርና ቀጥሎ ባለው አዲስ ዓመት ደግሞ ትመጣለች። የሰው ልጅ ግን ከትላንት ታሪኩ ሳይማር ትላንትን ዳግም እየደገመ ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር እየተሸጋገረ በሰላም መኖር እየቻለ በጸብ ውስጥ ዘመኑን ይጨርሳል።
አደይ የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚያደርገውን ድርጊት በሙሉ ስትታዘብ ትቆይና የኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫን መነሻ አድርጋ መልእክት ይዛ ትመጣለች። መልእክቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ የመጣ መልእክት ነው። የሰው ልጅ የምድር ላይ ክፋት ከቀን ወደ ቀን እንዴት እየጨመረ መሆኑን ተረድታ አመቱን ሙሉ ስትቆዝም ቆይታ በአጭር ጊዜ መገለጧ እውነቷን ተናግራ መልሳ የምትደበቅበት የወቅት ድምጽ የመሆን ልማድ።
የአደይን ጥበባዊ ምልከታ ተመልክተው አካሄዳቸውን ስንቶቹ ማስተካከል እንደቻሉ አደይ እርግጠኛ አይደለችም። ጥበብ ግን ሁሌም ትናገራለች። አስተዋይ ሰው ጥበብን ገንዘቡ ያደርጋል። በጥበብ ውስጥ የትላንት ውድቀት የዛሬን ቤት መስሪያ ትልቅ ግብዓት መኖሩን አስተዋይ ብቻ ይረዳል። አመቱን ወደ ኋላ በጥበብ መነጽር ውስጥ መመልከት የቻለ የአደይን ጥሪ በተረዳ ነበር። አደይ ልትል የፈለገቸውን ለራስ በሚመች መንገድ ተርጉሞ መነሳት ይቻላል። እውነታውን ፊትለፊት እንጋፈጥ ከተባለ ግን ወደ ኃላም ሆነ ወደጎን ሳይባል በእውነት መቆም ይቻላል። ጥበብ የምትነግረን እውነት ከአፈሩ በላይ የከበረው የሰው ልጅ አጠገባችን ያለ መሆኑን ነው።
አጠገባችን ያለው የሰው ልጅ እንደ አደይ ወቅትን ጠብቆ ብቅ ብሎ የሚጠፋ መልሶ የሚመጣም አይደለም፤ ሁሌም አብሮን ያለ እንጂ። ዛሬ ታክሲ ላይ ይሆን የዳቦ ሰልፍ ላይ፤ ስብሰባ ላይ ይሁን የምንኖርበት ጊቢ ውስጥ፤ በግራም ይሁን በቀኝ በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ተሰልፈዋል። አደይ የሰው ልጆች በአጠቃላይ እየኖሩት ያለውን ኑሮ ተመልክታ ያዜመችው ዜማ ውስጥ እኛ ከአጠገባችን ካለው ሰው ጋር ያለን መስተጋብርም አካል ነው።
ከአደይ የወቅቱ መልእክት ውስጥ ሁለት ነጥቦችን አውጥተን 2015ን አብረን እንቀበል። አፈር እና ሰው።
አፈር
“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለው የፈጣሪ ቃል ደጋግሞ ሲነገር ሰምተናል፤ እውነቱም እንዲያ ሆኖ የትላንት ትውልድ አፈር ሆኖ እነሆ አፈር ከሰፈራችን አለ። ከመነሻው አፈር የሆነው አፈር እና ከአፈር የሆነው የሰው ልጅ ወደ አፈር እየተመለሰ የሆነው አፈር ተደባልቀው እነሆ አሉ። አፈሩም ለግብርናም ሆነ ለአምራቹ ዘርፍ ግብዓት ሆኖ የሰውን ልጅ እያገለገለ ነው። አፈሩ ታርሶ ምርትም እየሆነ ነው።
የዘንድሮ የጳጉሜ ቀናት መካከል አንዱ የሆነው ጳጉሜ ሁለት የአምራችነት ቀን ተብሎ ተሰይሞ ስለ አምራችነት መልእክቶች ሲተላለፉ ሰምተናል። የእርዳታ ጥገኛ የሆነች ሀገር ውስጥ ስንኖር የአምራችነት ቀን ተደጋግሞ የሚነሳ ቀን ሊሆን እንደሚገባው እያሰብንም ቀኑን አሳልፈነዋል። አምራችነት ከአፈር ጋር የተሳሰረ ሆነና አፈራችንን በመጠበቅ ውጤታማ አምራቾች ለመሆን በአፍር ጥበቃው ብዙ ለመስራትም እንደክማለን። አፈርን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካልም ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲሰራም ይታያል። ባእድ ነገሮች ወደ ሀገር ገብተው አፈራችን እንዳይበከል ለማድረግ የሚሰራው ስራም እንዲሁ የሚጠቀስ ነው። አፈር ውስጥ የተቀመጡት ማእድናት በወቅቱ ወጥተው ለሀገራችን ጥቅም የሚሰጡ እንዲሆኑ እንዲሁ የሚሰራው ስራም ከዜና ገጾች ላይ ይነበባል። ዛፍ የመትከል ልማድም እያደገ እንዲመጣ የሚሰራው ስራ ከአፈር ጥበቃ ጋር ያለው ግንኙነት ቀጥተኛ ነውና ሊነሳ ይችላል። ስለ አፈር የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሉት ዝርዝር ነገርን ለባለሙያዎች ሰጥተን ስለ አፈር ከትላንት ዛሬ እየተሻገረ የመጣው የፍትሕ አሰጣጥ መንገዳችንን ግን እንመልከት። ስለ አንድ ስንዝር መሬት የሚከፈለው ዋጋ፤ ስለ እፍኝ አፈር የሚፈሰው ደም። አንድ ዝንዝር መሬትን አሳልፎ ላለመስጠት ህይወትን በመገበር ጭምር የሚደረገው ኢትዮጵያዊ ባህላችን ስለ ሀገራችን ቁራሽ መንገድ ያለንን ቀናኢነት በሰፊው የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያን አፈር በጠላትነት የረገጡ ወራሪዎች ከባድ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደረገ የታሪክ ገጻችን ጥቂት አይደለም። የሌሎችን ያለመፈለግ የራስንም አሳልፎ ላለመስጠት የተደረጉት ተጋድሎዎች በኢትዮጵያ አፈር ዙሪያ ሃሳብን ማዋጫ ጉዳይ ሊሆንም ይችላል። ከሌሎች ጋር ስለ አፈራችን የገባነው ፍልሚያ እንዳለ ሆኖ እርስበእርሳችን ያደረግነውም የታሪካችን አንድ አካል ሆኖ ግን ድምር ውጤታችን ኪሳራ ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል። የአፈር ወረት ከማህበራዊ ወረታችን በላይ ሆኖ በግትርነት ያጠፋነው ጥፋት።
ጥበብ ስራዋን ስትሰራ በታሪካችን ውስጥ እድገት ያለውን ቦታ ታሳየናለች። ትላንት እና ዛሬን በማነጻጸር እድገታችንን እንድንፈትሽ የሚያደርግ። ግለሰባዊም ሆነ ማህበረሰባዊ እድገት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች የትላንት ጉዞ በዛሬው ላይ ያለውን ተጽእኖ በስፋት ያነሳሉ። ኢትዮጵያውን ስለ ማንኛውም ጉዳይ ከእዚህ ቀደም የሄዱበት መንገድ ለዛሬውም የመምጣቱ እድል ሰፊ ነው። በትላንት ችግር አፈታት ውስጥ ፍጹም ሰላማዊ የሆኑ መንገዶች እንዳሉ ሁሉ ጦርኝነትም የሚይዘው ስፍራ ብዙ ነው።
በአፈራችን ላይ የፈሰሰው ደም፤ ከአፈር ጋር ተደባልቆ አፈር የሆነው ኢትዮጵያዊ የጦር ሜዳ ውሎ የታሪካችንን ገጾች የተቆጣጠረ ነው። የሰላም መንገድ የተናቀና መናኛ መንገድ ሆኖ ነገሮችን በብረት ለመፍታት የመሄድ መንገድ አፈርን አብዝቶ ይሆናል እንጂ ሰውን ሊያባዛው አልቻለም። የበዛው አፈርስ እንደ ብዛቱ ፍሬን መስጠት ስለመቻሉ ከእውነት ጋር ሆኖ የሚጠይቅ ሰው የማያሻማ መልስ ያገኛል። ከደም የተነሳ ምድር ፍሬዋን እንደምትከለክል የቃየልና አቤል ታሪክ አስተማሪ ሆኖ እናገኘዋለን። ቃየን በቅናት ተነሳስቶ የሄደበት መንገድ ለጊዜው አቤልን በማጥፋት አሸናፊ የሆነ ቢመስልም አቤል ወደ አፈርነት በመቀየሩ ምድር ፍሬዋን እንዳትሰጥ ተከለከለች። በምድርም ላይ ተንከራታችና ተቅበዝባዥ መሆን ቀጠለ። የሰው ደም አፈሩ ምርታማ እንዳይሆን የሚያደርግ ነዋሪውም ተቅበዝባዥ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም በኋላ የተጠኑ ጥናቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ወይንም የስደት ኑሮ ከግማሽ በላይ የጨመረ መሆኑን ያሳያል። ስደት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሆነ ቢነገርለትም ከፍተኛ የሰው ደም መፍሰስ ባስከተሉ የለውጥ ወቅቶች የነበሩ ስደቶች ከፍተኛ ደረጃውን ይዘው በእያንዳንዱ ቤት ጓዳ ውስጥ ስደትን የተከተለ የሃዘን መዝገብ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል።
ዛሬ በኢትዮጵያ አፈር ላይ የምንኖር ፈጽሞውኑ ከትላንት መንገድ በመመለስ ልዩነቶቻችንን በሰላም የመፍታትን ልምምድ ማድረግ እንዳለብን የግድ ይላል። ስለ ሰላም የሚኬደው የትኛውም እርቀት አሸናፊ የሚያደርገው ሁሉንም ነው። የዘንድሮዋ አደይ እንጉርጉሮ በሚቀጥለው ወደ ሙሉ ደስታ ይቀየር ዘንድ የኢትዮጵያ ልጆች አብረን አፈሩ ላይ ቁጭ እንበል። አብረንም በፍቅር በመተማመን እንቀመጥ። አንዳችን በአንዳችን ቁስል ላይ እንጨት ከመስደድ ተጨማሪ ቁስል ውስጥ ላለመግባት ሰላማችንን ለመፍጠር እንሰማራ። ስለ ሰላም ጎዳና መሰየሙ ደስ ያሰኛል፤ ለእውነተኛ ሰላም ቁጭ ብሎ አብሮ መጨነቅ መቻል ደግሞ የበለጠ ደስ ያሰኛል። ከአፈሩ በላይ የሆነ ስላለ፤ ሰው።
ሰው
ሰው ማለት በቃ ሰው ነው፤ በውስንነት የሚኖር የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ ፍጥረት። ሰው ከተገኘበት ከምድር አልፎ ወደ ሌሎች ዓለም በመሄድ ሌሎች ፍጥረቶችን ለማጥናት አመታትን የሰጠ ሃብቱንም እያፈሰሰ ያለ በእውቀት እረክቶ የማይቀመጥ እጅግ አስደናቂ ፍጥረት። በሰው አካላዊ ውቅር ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች አካላትን የበለጠ ለማወቅ ጥናት በተደረገ ቁጥር የሚደረስበት መደምደሚያ ሰውን አጥንቶ መጨረስ የማይቻል መሆኑን አመላካች ነው። ሰው እንኳን በሰው፤ በፈጣሪውም የጸጸት ምክንያት እንደሆነ የተጻፈለት ነው፤ የቆንጆዎች መጽሐፍ ደራሲ “አስቀድሞ ነው እንጂ መጥኖ መደቆስ” ብሎ የተሳለቀበት የመጽሐፉ ክፍል። ፈጣሪ በስራው የማይሳሳት ቢሆንም ከፍጥረቱ ሁሉ ግን በሰው የተቸገረ መሆኑን የሃይማኖት አስተማሪዎች ደጋግመው የሚያነሱት ነው፤ ሁላችን ደግሞ በኑሯችን የምንረዳው።
ሰውን መርምሮ አለማወቅ አንድ ጉዳይ ሆኖ እያለ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሰው የሚኖረው አተያይ ግን ሊኖር ግድ ነው። ሰውን በሙሉ ክፋት ወይንም ሰውን በፍጹምነት የማየት የሁለት ጥግ አስተሳሰብ ትክክለኛ አይደለም። ሰው ሁሉ ክፉ፤ ሰው ሁሉ ደግ አይደለም። ከሰው ውስጥ በመልካምነት የምንገልጻቸው ሰዎች አሉ፤ ከሰው ውስጥ በክፋት የምንገልጻቸውም እንዲሁ።
በአደይ ዝማሬ ውስጥ ሰው አደይ ሚዛኑ የቀለለ እንደሆነ እና ከሰውነት ይልቅ ግዑዝን መከተል የቀደመ መሆኑን ትናገራለች። የዓለማችን የሃይል አሰላለፍ እንካ በእንካ ሆኖ እውነትና መርህ ሳይሆን ይዞ መገኘት የትክክለኛነት ማሳያ እየሆነ እንዳለ እናያለን። ሰዎችን በሰውነታቸው የመመልከትና አጠገባችን ያለ ማናቸውም ሰው ከሰውነቱ የሚመነጨው ታላቅነቱን የመረዳት ስራ መሰራት አለበት።
ሰዎች ከአጠገባቸው ሰው የሆነ ሰው ባጡ ቁጥር ወደ መገለልና ራሳቸውን ወደ መጉዳት ይገባሉ። ያለፉት ሃያ አመታት ውስጥ የታየው እውነት በየአመቱ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ከ30% በላይ የጨመረ መሆኑን ነው። ሰዎች ትኩረትን የሚፈልጉ ፍጥረቶች ናቸው። ፍጥረትም በሙሉ ስለ እነርሱ የሆነላቸው ልዩ ፍጥረቶች።
ሰዎች ትኩረት እንድንሰጣቸው የሚያደርገን የመጀመሪያው ምክንያት ሰው መሆናቸው ነው፤ ቀጥሎ አሁንም ሰው መሆናቸው ነው፤ ሲሰልስም ሰው መሆናቸው ነው። ከመልካምነታቸው ይሁን ከክፋታቸው ባሻገር እንዲሁ ሰው በመሆናቸው ልዩ ፍጥረት ናቸው፤ ልዩ ትኩረት፤ ልዩ ቦታ፤ ልዩ እይታ የሚገባቸው። የሰዎችን መብት ከማክበር አልፈው ስለ እንስሳት መብት ለመሞገት የሚደራጁ፤ ሚሊዮኖችን የሚበጅቱ፤ ቢሮ የሚከራዩ፤ ሙሉ ጊዜ ሰራተኛን የሚቀጥሩ ወዘተ ስንመለከት ከፍጥረታት ሁሉ የገዘፈው ፍጥረት እንዴት የከበረው ነገር እንዲገባው እናስተውላለን። ከፍጥረታት ሁሉ የተሻለውን ሊያገኝ የሚገባው ፍጥረት። ከሰዎች ጋር ስለሚኖር ግንኙነት ልንኖራቸው ስለሚገቡ መርሆች የተለያዩ ጸሃፍት የየራሳቸውን ብዙ ብለዋል። እማሆይ ትሬዛ ቀላል ህይወትን እያንዳንዱ ሰው ቢኖር ሌላው ሰው ህይወትን በቀላሉ መኖር የሚችልበትን እድል እንደሚያገኝ መናገራቸው ይጠቀስላቸዋል። ከእርስ በእርስ ህይወት ውስጥ በስፋት ተቀባይነትን ያገኘው አስተሳሰብ አንድ ሰው ለእራሱ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ለሌሎች እንዲያደርግ የሚያስተምረው የክርስቶስ ትምህርት ነው።
ውድ ወገኖቼ፤
የአደይ ዝማሬን አድምጠን ሚዛናችንን በማስተካከል ለሁላችንም መልካሙን የምንመኝበት ደግሞም የምናደርግበት ዘመን ከፊታችን እንዲሆን እሻለሁ። መልካሙን!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም