የጠብ ድግስ በመጥመቅ የሚታወቀው ሽብርተኛው ትህነግ በኢትዮጵያውያን ላይ የሉአላዊ ስጋት ከደቀነ ከሁለት ዓመት በላይ ሊሆነው ነው። ከታሪካዊ የአገራችን ጠላቶች ጋር በመመሳጠርና ቡድናዊ ፍላጎቱን በማስላት ብቻ በኢትዮጵያውያን ላይ ክህደት እየፈፀመ ይገኛል። ይህንን ተፈጥሯዊ የጭካኔ፣ የግፍ፣ የስግብግብነት ግብሩን ለማሳካት ሳር ቅጠሉን እየነጨ፤ ዳገት ቁልቁለቱን እየቧጠጠ ይገኛል።
እየሱስ ክርስቶስን ሦስት ጊዜ እንደከዳው ጴጥሮስ የትግራይ ሕዝብን አግቶ ኢትዮጵያውያንን እናቶች ያጎረሱትን እጅ ነክሶ ባለፉት ሁለት ዓመት ብቻ ተደጋጋሚ ወረራዎቹን አድርጓል። ለውጭ ጠላቶች ጫና አገራችን እንድትጋለጥ፤ የአገር ዳር ድንበር እንዲሳሳ ከማድረግ ባለፈ፤ ኢትዮጵያን የመበታተን ቅዠቱን እውን እንዲሆን እንቅልፍ አጥቶ እየሠራ ይገኛል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን የሰላም አየር እንዲተነፍሱ፣ ሰቅዞ የያዛቸውን ድህነት በጠንካራ ክንዳቸው ታግለው እንዲያሸንፉ ካለው ፍላጎትና ኃላፊነት ጭምር የሽብርተኛውን ቡድን ተደጋጋሚ ትንኮሳ፣ ጭፍጨፋ እንዲሁም ከፍተኛ ወረራ ወደጎን በመተው ለሰላም እጁን በመዘርጋት የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረጉም በላይ በሆደ ሰፊነት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ድጋፍ ከሌለው አገር አፍራሽ ቡድን ጋር «ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደራደር» የሚል ጥሪ አቅርቦ ረጅም እርቀት ተጉዟል።
አሸባሪው ትህነግ ግን ከውልደቱ ጀምሮ የትግል አጋሮቹን በበረሃና በየጢሻው በግፍ እየረሸነ የመጣ አረመኔ ቡድን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ «ተቀምቻለሁ» ብሎ ያሰበውን መንበርና የዝርፊያ ሰንሰለት ዳግም በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ለማስፈን ወረራን፣ የግፍ ጭፍጨፋንና ጠብ አጫሪ መንገድን መርጦ «በአንድ ራስ ሦስት ምላስን» የሚል አውሬያዊ ሕግ እየተከተለ ይገኛል።
ቡድኑ እንደ እስስት የሚቀያየር የሽብር ቡድን ነው። ይህን ለመረዳት የሰሞኑን ድርጊቶቹን ብቻ መቃኘት በቂ ነው። ላለፉት ወራት በኢትዮጵያ መንግሥት ይሁንታ የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የትግራይ ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና አዛውንትን በአስገዳጅ ሁኔታ ጦርነት ውስጥ ለመማገድ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
የአዞ እንባውንም በማፍሰስ እርዳታ እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጥያቄዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያደረገ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝቦች ላይ ጫና ለመፍጠር ከላይ እታች ሲል ሰንብቷል። በክልሉ ለሰብአዊ ተግባር ይቀርብ የነበረውን እርዳታና ነዳጅ በመዝረፍ እና በግፍ ከንፁሃን አፍ በመንጠቅ ለእኩይ አላማው ማስፈጸሚያ ለጀመረው ጦርነት እያዋለው ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በተዋጊዎቹ ምሽጎች እየተገኙ ያሉት የእርዳታ አቅርቦቶቹን ማየት በቂ ነው።
ቡድኑ በአንድ በኩል በአገር ውስጥና በዓለምአቀፍ ደረጃ ባሰማራቸው ተከፋይ ሎቢስቶችና ፕሮፓጋንዲስቶች በኩል የቅጥፈት የበሬ ወለደ ወሬዎችን በስፋት በማሰራጨት የዓለምአቀፉን ኅብረተሰብ እያደናገረ በሌላ በኩል ከክልሉ በሚዋሰኑ ሕዝቦች ላይ ወረራ በማካሄድ ዝርፊያ እና የጅምላ ጭፍጨፋ ያካሂዳል።
የቡድኑ ወታደራዊ ሆነ ፖለቲካዊ አመራሮች በበኩላቸው የመንግሥትን ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት እንደ ሽንፈት እየወሰዱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መፎከርና ማቅራራት ዋነኛ መገለጫውም ከሆነ ውሎ አድሯል። «ጦርነቱ አብቅቷል፣ እጅ ስጡ፤ ይሄን ሺ ሰራዊት ገደልን፤ማረክን » በሚሉ የቅዥት ቃሎች እራሳቸውን ሲያጽናኑም መስማት ተለምዷል።
መንግሥት ትዕግስቱ አልቆ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ «ያዙኝ ልቀቁኝ» የሚለው ፉከራቸው ብዙም ሳይቆይ «ተገደልን፣ ተጨፈጨፍን፣ የትግራይ ሕዝብ ከበባ ውስጥ ነው፣ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ይግባ፣ የገላጋይ ያለ» የሚል ለቅሶና ዲስኩር በቅጥረኞቻቸው በኩል ያሰማሉ።
«ትህነግ ሦስት ምላስ ነው ያለው» አልን እንጂ የዚህ ሽብር ቡድን ምላስ እጅግ ብዙ ነው። ከሰሞኑ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲናዘዝ የነበረውን በርካታ የተምታታ ጉዳይ ካስተዋልን እንኳን ብዙ አስቂኝ ነገሮችን እናገኛለን። አንዴ ጀግና አንዴ ደግሞ ቅልስልስ ይሆናል።
የሰሞኑን የቡድኑ መሪ «የአድኑኝ» ጥሪን ስናይ ለውጭ ኃይሎች ፈረስ ሆኖ እንደሚጋለብ በአደባባይ የሚያጋልጥና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ድጋፍ ካላገኘ አንድ እርምጃ እንደማይጓዝ በተጨባጭ ያመላከተ ነው። ይህ ሙከራው አልሳካ ሲልና እንደለመደው ጊዜ ለመግዣ «በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ» የሚል ዲስኩር አሰምቷል።
የትህነግ ተለዋዋጭ ባህሪ እና እስስታዊነት በዚህ የሚያበቃ አይደለም። «ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ» ብሎ ይፋ መግለጫ ባወጣ ማግስት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተዘናጋ ሲመስለው በሱዳን ድንበር በሁመራ አካባቢና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጦርነት በመክፈት አንድ ጊዜ በጦርነት፣ ሌላ ጊዜ በለቅሶ እንዲሁም በገላግሉኝ ተለዋዋጭ ባህሪው ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክና አገራችንን የማፈራረስ ህልሙን ለማሳካት እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
ግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚሆን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትህነግን ያውቀዋል። ከዚያም አልፎ ለ27 ዓመታት በጭቆና መንበሩና አገዛዝ ሥርዓቱ አሳልፏል። ቡድኑ አላማውን ለማሳካት «በሬ ወለደ» ብሎ እንደሚያሳምን ጠንቅቀን እናውቃለን። ግቡን የሚያሳካለት ከሆነ የትኛውንም ድንጋይ እንደሚፈነቅል፣ አንዴ አንበሳ አንድ ጊዜ ደግሞ ውሻ እንደሚሆን ሃቅ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን መረዳት ይኖርበታል። ማንኛውም ግጭት በድርድርና ጦርነት ቢፈታ መልካም ነው። ከአሸባሪው ትህነግ ባህሪ አንፃር ግን ይህ እንደማይሆን ማወቅ ብዙ የሚቸግር አይደለም። ያለፉትን ነገሮች እረስተን ወደ ፊት እንሂድ ብንል እንኳን የሰሞኑን የትህነግን ተለዋዋጭ ባህሪና እርስ በእርስ የሚጣረስ መዘላበድ እንዴት መዘንጋት እንችላለን።
የቡድኑን የባንዳነት አገር የማፍረስ ተልዕኮ ለማክሰም እና ዘላቂ አገራዊ ሰላም ለማስፈን መንግሥትም ሆነ ጀግናው ሰራዊታችን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ሆነው ሊቆሙ ይገባል። በቡድኑ የከፋ ጭቆና ስር የሚገኘው ኢትዮጵያዊው የትግራይ ሕዝብም ከዚህ አረመኔ ቡድን ነፃ መውጣት እንዳለበት ልናምን ይገባል። በቡድኑ «እደራደራለሁ» የሚል ማዘናጊያ ዲስኩር አምኖ ሕዝቡን ለዳግም ወረራ፣ ጭፍጨፋና ውድመት የሚጋብዝ መንግሥት እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል።
መንግሥት ከቡድኑ ደጋፊና ጋላቢ ኃይሎች ሊደርስበት የሚችለውን ጫና የሚቋቋምበት ስልት ደግሞ ደጋግሞ መንደፍ ይገባዋል። የመጀመሪያው ትህነግ በኢትዮጵያ ውስጥ የበቀለ እባጭ እንጂ ሕጋዊ መሠረት ያለው ቡድን አለመሆኑን ደጋግሞ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ዓለምአቀፍ ተቋማትም ሆነ የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማያከብር መልኩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ማስገንዘብም ሆነ ማሳሰብ የዕለት ተዕለት ሥራው መሆን አለበት።
ይህ ተግባር የአሸባሪው ትህነግ የቀብር ሥነሥርዓት እስካልተፈፀመ ድረስ መቆም የለበትም። ለዚህ የሚሆን በሳል የዲፕሎማሲ ሥራ ከተሠራ፣ ወጣቱ መከላከያን ተቀላቅሎ ወረራውን መመከት ከተቻለ፣ የሴራ ፖለቲካ የሚጎነጉኑና የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተን ተግባር ውስጥ ያሉ የውጭም ሆነ የውስጥ ቡድኖች የረዘመ እጅ ከቆረጥን መላው ኢትዮጵያውያን የሰላም አየር የሚተነፍሱበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። የሽብር ቡድኑ ትህነግ «በአንድ ራስ ሦስት ምላስ» አካሄድ ማብቂያም እንደዚሁ። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም