አዲስ አበባ፡- ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ኢትዮጵያ ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ወጪ ከ5 እስከ 10 በመቶ ለማዳን እየሠራ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የባዮፊዩል ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ገሠሠ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ነዳጅ ከውጭ ሀገር ለማስገባት በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። የተለያዩ የታዳሽ ኃይል አለኝታዎችን በመጠቀም ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ምንዛሪ ለማዳን እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። የባዮፊዩል አጠቃቀም አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ሚካኤል፤ በአዋጁ ረቂቅ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትም እየተደረገ ነው።
ከዚህ ቀደም የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዳይሆን አድርጎ መቆየቱን በመግለጹ አዋጁ ሀገሪቱ የዘርፉን እምቅ ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል። እንደ አቶ ሚካኤል ማብራሪያ፤ ለኃይል ማመንጫነት የተለያዩ ምንጮችን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። ከስኳር ፋብሪካዎች የሚወጣውን ኢታኖል በመጠቀም ቤንዚን የማምረት ዘዴ ሲሆን ይህም ባዮ ኢታኖል በመባል ይታወቃል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደኖች በመመንጠራቸው እህል በማያበቅሉ የተጎዱ መሬቶች ላይ ለኃይል ማመንጫነት የሚሆን ዘይት የሚያመነጩ ተክሎችን በማልማት ተክሎቹ የሚያፈሩት ናፍጣ መሰል ቅባትን ከነዳጅ ጋር ቀላቅሎ በመጠቀም ኃይል ማመንጨት ይቻላል። ይህም ባዮ ዲዚል በመባል እንደሚታወቅ ይገልፃሉ። በረቂቅ ደረጃ ያለው የባዮፊል አዋጅ በተለይም በተመነጠሩና ለሰብል ልማት በማይውል መሬት ላይ ለነዳጅነት የሚውል ዘይት የሚያመነጩ ተክሎችን የማምረት ፍላጎት ያላቸው አካላትን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።
እነዚህ ተክሎች የሚለሙት የመንገድ ተደራሽነት በሌለባቸው አካባቢዎች በመሆኑ በዘርፉ ለሚሰማሩት የተለየ ማበረታቻ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል። የባዮፊዩል ረቂቅ አዋጁ ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከመተካት ባሻገር ሰፊ የስራ እድልና የገቢ ምንጭ እንደሚፈጥር በመግለጽ የባዮፊዮል ምርትና ቴክኖሎጂን ለማሳደግ የረቂቅ አዋጁ ላይ ግብዓት እንደሚሰበሰብበት ተናግረዋል።
ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ሀገሪቱ ነዳጅ ከውጭ ሀገር ለማስገባት የምታወጣውን ወጪ ለማዳን ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ስትራቴጂ ተቀርጾ ሲሠራ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የሚፈለገውን ስኬት ማምጣት አልተቻለም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በመላኩ ኤሮሴ