አዲስ አበባ፡- ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በየዓመቱ የሚካሄደው የቻይና የንግድ ሳምንት በሚቀጥለው ወር ከሚያዚያ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የዘንድሮው የንግድ ሳምንት ከዚህ ቀደሞቹ የተሻለ ለውጥ የሚታይበትና የሁለቱን አገራት የንግድ ማህበረሰቦች የንግድ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል። የቻይና የንግድ ትርኢትና አውደ ርዕይ ዋና አዘጋጅ የሆነውና መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ኤም.አይ.ኢ ግሩፕ ሊቀ መንበርና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ዋንግ እንደገለጹት፣ የንግድ ሳምንቱ የኢትዮጵያንና የቀጠናውን የንግድ ማህበረሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም ካላቸው የቻይና አምራቾችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር በቀጥታ ያስተሳስራል።
የአቻ ለአቻ የንግድ ግንኙነቱንም የበለጠ ያጠናክረዋል። የኤም.አይ.ኢ ግሩፕ ዓለም አቀፍ ኩነቶች ዳይሬክተር ሚስተር ዛሁር አህመድ በበኩላቸው «ኢትዮጵያ ወሳኝ ኢኮኖሚያዊና ክፍለ አህጉራዊ ለውጦችን እያስመዘገበች በምትገኝበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ የዘንድሮውን የቻይና የንግድ ሳምንት ለየት ያደርገዋል» ብለዋል። ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በተሻለ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ማህበረሰቦችን ያሳትፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ከንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡና የምክክር ጉባኤዎችም እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።
ዝግጅቶቹ የዘን ድሮውን የቻይና የንግድ ሳምንት ለየት እንደሚ ያደርገው አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የቻይና ንግድ ሳምንት ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በበኩላቸው፤ የቻይናና የኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።የቻይና የንግድ ሳምንት በኢትዮጵያ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ የአገራቱ የንግድ ትብብር ከመጠናከሩ በተጨማሪ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ትላልቅ የቻይና ኩባንዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ከአንድ መቶሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የንግድ ሳምንትም ኢትዮጵያ በንግድ ትርኢትና የቢዝነስ ሁነቶች ዘርፍ ልታገኝ የሚገባትን ድርሻ ከፍ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና አለው።ለአገር ውስጥ ባለ ሀብቶችና በአጠቃላይ ለንግዱ ማኅበረሰብ ቴክኖሎጂን በማሸጋገርም አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በሚቀጥለው ወር ከሚያዚያ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በሚሊኒየም አዳራሽ ለሦስት ቀናት የሚቆየው የዘንድሮው የቻይና የንግድ ሳምንት በኢትዮጵያ የንግድ ትርዒትና አውደ ርዕይ በአምራችና በቴክኖሎጂ አቅርቦት ዘርፍ የተሰማሩ ከአንድ መቶ በላይ ዓለም አቀፍ የቻይና ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቀላል ኢንዱስትሪዎችና ጨርቃጨርቅ፣ የግንባታ ዕቃዎችና ማሽኖች፣ የምግብና መጠጥ ማቀናበሪያ ቴክኖሎጂዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችና የእንጨት ውጤቶች፣ የኃይልና የብርሃን አማራጭ ምርቶች፣ የውበትና የጤና መጠበቂያ ምርቶች፣ የሞተር ተሽከርካሪ ክፍሎችና መለዋወጫዎች፣ ባዮ ኬሚካልና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች የዘንድሮው የቻይና የንግድ ሳምንት ትኩረት ያደረገባቸው ዘርፎች ናቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በይበል ካሳ