የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮቹ እንደ ወትሮው ሁሉ ድጋፋቸውን ሊያደርጉላቸው በአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ እማማ ግምጃ ቤት ተገኝተዋል። የዕድሜ ጫና መነሳት ስላላስቻላቸው አልጋቸው ላይ ቁጭ እንዳሉ ነው የተቀበሏቸው። ዕድሜ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በላያቸው ላይ ሲፈራረቅ የኖረው ድህነት እንዳደከማቸውና አቅም እንዳሳጣቸው ያስታውቃሉ። በድምጻቸው ለይተው እከሌ ነህ፤ እከሊት ነሽ ይበሏቸው እንጂ ዓይናቸው ማየት ተስኖታል። ሰውነታቸው አልታዘዝልሽ በማለቱ እንቅስቃሴ የናፈቀው እግራቸውም ድልድል ብሎ አብጧል።
እማማ ግምጃ ሮባ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚደግፋቸው አቅመ ደካሞች አንዷ ናቸው። የዛሬ አራት ዓመት የለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጠየቀው መሰረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አማካይነት በደሃ ደሃ ተመልምለው አውድ ዓመትን ምክንያት በማድረግ እንዲደግፋቸው ከተሰጡት አምስት አቅመ ደካማ እናቶች አንዷ ሲሆኑ፤ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞችም ቃላቸውን አክብረው ድጋፍ እያደረጉ ነው።
እማማ ግምጃ በዚህ ባሉበት ሁኔታ የአውድ ዓመት ዋዜማ በመጎብኘታቸው ደስታ የፈነቀለውን ሳቃቸውን መሸሸግ አልቻሉም። በየወሩ የተወሰኑት የድርጅቱ አመራሮች እያዋጡ በሚሰጧቸው 1ሺህ 800 ብር ላይ አውድ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ ሌሎች ጥቂት ሠራተኞች አዋጥተው ያከሉበትን የበዓል መዋያ አራት ሺህ ብር የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ከተማ ሲሰጧቸው ደስታቸውን መቆጣጠር ተሳናቸው። እጃቸውን እንቅ አድርገው ይዘው ደጋግመው እየሳሙ የማያቋርጥና የተለመደ ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱት።
የአቶ ፍቃዱን እጅ ሳይለቁ ዶሮና እንቁላል ጨምሮ ለበዓል የሚያስፈልገውን ገዝቶ እንዲመጣም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከወደ ጓዳ ልጃቸውን ተጣሩ። ልጃቸው መንግስቱ በፍጥነት ከጓዳ ብቅ ‹‹ብሎ ምን ልታዘዝ ›› አላቸው። ፈጣሪ በላከላቸው ገንዘብ
ለአውድ ዓመት የሚያስፈልጋቸውን ገዝቶ ለመምጣት ስላበቃው በቀለጠ እልልታ እያመሰገኑት ገንዘቡን ሰጥተው ላኩት።
ሰርቶ እሳቸውን ማስተዳደር ባለመቻሉ ባደረበት ጭንቀት የአእምሮ ህመምተኛ የነበረ ልጃቸው አሁን ላይ በተደረገለት ህክምና ከበሽታው ማገገም ቢችልም ዛሬም ቢሆን ሰርቶ ለእናቱና ለእሱ መሆን የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም። እሳቸውም ህመማቸው እየተባባሰና ከዕድሜ ጫና ጋር እየደቆሳቸው ስለመጣ ለልጃቸው እንዲቆዩለት የሚያስችል ሕክምና የሚያገኙበትን እንዲያመቻቹላቸውም በምስጋናና በምርቃት በማጀብ አሳሰቡ።
የእማማ ግምጃ ምርቃት በዚህ ብቻ አላበቃም። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮች ከለውጡ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት በአውድ ዓመትና ሰርክ በጋራም በተናጠልም ሲያደርጉላቸው የነበረውን ድጋፍ እያስታወሱ መረቁ።
እማማ ግምጃ ከዚህ ቀደም “የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለያየ መልኩ ትኩረት አግኝቼ እንድታወስ በማድረጉ በ2014 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ፈርሶ የነበረው ቤቴ በተለየና ባማረ መልኩ ተገንብቶልኛል።ከሶፋ፣ ቴሌቪዥንና ምጣድ ጀምሮም አስፈላጊውን የቤት ዕቃ አሟልቶልኛል። ነገር ግን የቀድሞ ቤቴ ምንም ያህል ቢፈርስና በእንጨትና በአሮጌ ቆርቆሮ ተደጋግፎ ቆሞ የነበረ ቢሆንም እኔን የመሰሉ አቅመ ደካሞች ወለሉ ላይ ተኝተው አድረው ማልደው እንዲወጡ አከራይቼ 700 ብር አገኝና ዳቦም ሆነ እንጀራ በመግዛት ቀለቤን እሸፍን ነበር። ቤቴ ከተሰራ በኋላ ግን ይሄን ባለማድረጌ ተርቤያለሁ። አንተ ለፋሲካ እንዳደረክልኝ ሁሉ አልፎ አልፎ እየመጣህ ብትደጉመኝም አንዳንድ ኃላፊዎችም ቢደግፉኝም ዘላቂ አይደለም። የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ባለማቻሌ ተቸግሬያለሁ” ብለው ነበር። ከዚህ መልዕክት በኋላ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ በግላቸው ከነቤተሰቦቻቸው መጥተው ጾማቸውን ያስፈቷቸው መሆኑንና በዓሉን አብረዋቸው ማሳለፋቸውንም አብራሩ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌትነት የትንሳኤ በዓልን ከእማማ ግምጃ ጋር ባሳለፉበት ወቅት የእማማ ግምጃ ምርቃት ይድረሳችሁ በሚል የምርቃቱን አጭር አንጀት የሚበላ የቪዲዮ መልዕክት ለሠራተኛው አጋርተው ነበር።
ብዙ ሠራተኞች በግልም በጋራም ወደ እማማ ግምጃ ቤት እየሄዱ የየራሳቸውን ድጋፍ አድርገዋል። በየጊዜው ሳይቋረጥ እየተሰጣቸው ያለው 1ሺህ 800 ብርም አመራሩ የወሰነው በዚህ መልኩ ነበር።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ፍቃዱ ከተማ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋዊያን፣ለአካል ጉዳተኞች፣ ለተማሪዎችና በተለያየ ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች፣ ለመከላከያ ሠራዊት በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣባቸው ካሉ ተግባራት አንዱ ሲሆን፤ ተግባሩ በተለይ እንደ እማማ ግምጃ ላሉ አረጋዊያን ስለሳቸው የሚያስብ አይዞሽ ባይ መኖሩን ተገንዝበው ተስፋ እንዲኖራቸው ያስችላል። ጤናና ዕድሜንም ሊጨምር ይችላል። ኅብረተሰቡም በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች፣ በግንባታ እቃዎችና በሌሎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት በማረጋጋትም ሆነ የመረዳዳት እሴትን በማጠናከር ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
በኢትዮጵያውያን መካከል ያለ ቤተሰባዊ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና ትውውቅ በማሳደግ አንድነትና ማህበራዊ ሕይወት ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል። የላላውን የአገርን ሉዓላዊነት ማገርም የሚያጠብቅና ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ጽሑፋችንን ከማሳረጋችን በፊት ስለሳቸው ትንሽ ስለ እማማ ሮባ እንንገራችሁ። ግምጃ ሮባ ዕድሜያቸውን በውል አያውቁትም። ሆኖም ፊደል ያልቆጠረው ብልህ አእምሯቸው የመጀመሪያው የጣሊያን ጦርነት የተጀመረ ዕለት ሰላሌ መወለዳቸውን ከወላጆቻቸው የሰሙበትን ደህና አድርጎ መዝግቧል።
ከትውልድ ቀያቸው ከመጡ በኋላ በአዲስ አበባ ለበርካታ አመታት ኖረዋል።በልማት ምክንያት ከነበሩበት ተነሱና አሁን ያሉበት አራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን ጀርባ አካባቢ ተለዋጭ ቤት ተሰቷቸው እየኖሩ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2015 ዓ.ም