በአንድ አገር የልማት ጉዞ ውስጥ የማይተካ ሚና ካላቸው የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሾች መካከል የገንዘብ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው። ከገንዘብ ተቋማት መካከል ደግሞ ባንኮች በግንባር ቀደምትነት ይመደባሉ። ባንኮች ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ለስራ እድል ፈጠራ የሚሆን ገንዘብ በቁጠባ አሰባስቦ በማቅረብ የአገራትን የልማት ጉዞ በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገትን እውን ለማድረግ የያዘቻቸውን እቅዶች ለማሳካት እንዲያስችሏት በመንግሥትም ይሁን በግል ዘርፎች ለምታከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ያስፈልጋታል። የዚህ የፋይናንስ ምንጭ ከሆኑ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች መካከል ባንኮች ዋነኞቹ ናቸው። ይሁን እንጂ የልማት ፕሮጀክቶችም ይሁኑ የግሉ ዘርፍ የሚፈልጉት ፋይናንስና የአገሪቱ ባንኮች አቅም የሚመጣጠን እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ደግሞ ለችግሩ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ በብዙ ወገኖች እንደ አንድ መፍትሄ የሚቀርበው የውጭ ባንኮችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት አሰራር በአማራጭነት እንዲነሳ ሲያደርግ ቆይቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው የሚጠቀሱ ትልልቅ የውጭ ባንኮች ወደ አገሪቱ ገብተው የብድር፣ የእርዳታ እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ተግባራት ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉበት አሰራር ሳይተገበር ቆይቷል። ከሳምንት በፊት ይፋ የሆነው የመንግሥት ውሳኔ ግን ለብዙ ዓመታት ዝግ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንደሚሆን አሳውቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱ የባንክ ዘርፍ አገልግሎቶችን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፤ የፋይናንስ ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ ውጤታማትና ቀልጣፋነት በመጨመር በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲሳለጥ፤ የሥራ እድል ፈጠራውም እንዲጎለብት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነትንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል በተባለው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውይይት አድርጎ ግብዓቶችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
መንግሥት የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንደሚሆን አስቀድሞም በተደጋጋሚ ሲጠቁም ቆይቷል፤ የሀገር ውስጥ ባንኮችም ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ መክሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ ስለፋይናንስ ዘርፉ አፈፃፀም ገለፃ አድርገው ‹‹ … የመንግሥትና አብዛኞቹ የግል ባንኮች አዳዲስ ህንፃዎቻቸውን ሰርተው ጨርሰዋል። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራም እየጀመሩ ይገኛል፤ ለውጥም አለ። ነገር ግን ባለፈውም እንዳነሳሁት አሁንም ደግሜ ማንሳት የምፈልገው ላለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች ሌላ ባንክ መጥቶ ሳይሻማቸው ብቻቸውን የሚሰሩበት እድል አግኝተዋል። በብዙ ምክንያቶች ይህንን ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ማቆየት አይቻልም።›› ሲሉ አስገንዝበዋል። ‹‹ ተጨማሪ ሀብትና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ስለሚያስፈልገን ባንኮች እናመጣለን። ለምሳሌ፣ በጎረቤታችን ጅቡቲ፣ አንድ ሰው ዶላር ባንክ ውስጥ ለማስቀመጥ ለባንኩ መክፈል አለበት። ባንክ ዝም ብሎ ዶላር አይቀበልም። የግል ባንኮች በስፋት ባሉበት አገር የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት በንፅፅር ከእኛ ይሻላል። እኛ የውጭ ባንክ ሳናስገባ ዘግተን የቆየንበት ሁኔታ እስካሁን ላለው የጠቀመ ቢሆንም ከአሁን በኋላ ግን ባንኮች ራሳቸውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በዘመናዊ አሰራር አዘጋጅተው ከፍ ላለ ውድድር መዘጋጀት ይኖርብናል›› ሲሉ ገልጸዋል።
‹‹ይህን እንደአንድ ማሳያ ለማመላከት፣ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ የሞባይል ባንኪንግ ጀምረን ነበር። በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ 14 ሚሊየን ደንበኛ አፍርቷል፤ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈፅሞበታል። ይህ አብዛኛው ባንኮች ጋር የሚገኝ ቁጥር አይደለም። በስምንት ወራት ውስጥ ለዓመታት የሠሩ ባንኮችን አቅም መፍጠር የቻለው ቴክኖሎጂና ተደራሽነት እየሰፋ በሚሄድበት ሰዓት የባንኮች ሥራ ሊበለጥ እንደሚችል ያመላክታል›› ብለዋል።
‹‹እናም ባንኮች ዝግጅት አድርገው አሁን ያለውን እድገት ጠብቀው አገራዊ ባንኮች ይበልጥ በፉክክር ውስጥ አዳጊ መሆን እንዲችሉ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል። መንግሥት ከዚህ አንፃር የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ነው። ቅድመ ሁኔታዎች ካለቁና ባንኮች ከተዘጋጁ ወደዚያ ሁኔታ ስለምንገባ የግል ባንኮችና የመንግሥት ባንኮች ከወዲሁ በተቀናጀና በተባበረ መንገድ ራሳቸውን ለውድድር ማዘጋጀት እንዳለባቸው ማሳሰብ ያስፈልጋል›› በማለት አብራርተው ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ ሀገር በቀል ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚኖረው ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ሲያሳስቡ መቆየታቸውም ይታወሳል። ዶክተር ይናገር ከባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ‹‹ያልተደራጁ 20 እና 30 ባንኮች ከሚኖሩን ይልቅ ሁለት እና ሶስት ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ባንኮች ቢኖሩን እንመርጣለን›› ብለው ነበር። የውጭ ባንኮችም ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መሥራት የሚያስችል የሕግ ማርቀቅ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተናገረው ነበር።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት የተሻለ የኢንቨስትመንት ካፒታል ለማቅረብ እድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ። ይህም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፈንድ በማስገኘት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ የባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ መሰማራት የሀገር ውስጥ ባንኮች በአቅም ውስንነት ምክንያት የተሻለ የኢንቨስትመንት ካፒታል ለመፍጠር ለሚቸገሩበት አሰራር እልባት ይሰጠዋል። መንግሥት የሀገር ውስጥ ባንኮችን ተወዳዳሪነት ለመጠበቅ ብሎ ገደብ ካላስቀመጠባቸው በስተቀር የውጭ ባንኮች የተሻለ ገንዘብ የማምጣት አቅም አላቸው። በተጨማሪም ባንኮቹ የየራሳቸው የአሰራር ስርዓት ቢኖራቸውም ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔም (Lower Interest Rate) አላቸው። በአጠቃላይ ባንኮቹ በሀብትም ሆነ በወለድ ምጣኔ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ይህም ተጨማሪና የተሻለ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ በማስገኘት የባንኮቹ ሚና ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት አወንታዊ ሚና እንዲኖረው ያደርጋል።
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭቶች ባሉበት፣ የውጭ ጫናዎች በበረቱበትና ምጣኔ ሀብቱ ባልተረጋጋበት በዚህ ወቅት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ተገቢ አይደለም የሚሉ ወገኖችም አሉ። ዶክተር ሞላ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። ‹‹በመንግሥት በኩል የተላለፈው ውሳኔ ከአገሪቱ አለመረጋጋት ጋር የሚገናኝ አይደለም። መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ ነው ያደረገው። ውሳኔው ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅም በማስገኘት የተጎዳው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሻሻልና እድገት እንዲያስመዘግብ ያግዛል›› ይላሉ።
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ ግርማ በበኩላቸው፤ የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆን የሚፈቅደው ረቂቅ ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንዲጨምር በማድረግ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በሌላ በኩልም ለኢንቨስትመንት ማደግ ከሚኖረው አወንታዊ ሚና በተጨማሪ በጥንቃቄ ካልተመራ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ረዳት ፕሮፌሰሩ ጠቁመው፣ ለእዚህም የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ይገልፃሉ።
‹‹የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ሲሰማሩ ለአብዛኛው ሕዝብ የፋይናንስ አማራጮችን ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ፣ የባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባት በአገር ውስጥ ባንኮች የሚታየውን የብድር አቅርቦትና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ በማቃለል የፋይናንስ አማራጮችን ለማቅረብ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ።
‹‹የሐገር ውስጥ ባንኮች የኤሊቶች (Elites) መክበሪያ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል። ባንኮቹ በአብዛኛው ሃብታሙን የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። የፋይናንስ ተደራሽነት እውን የሆነው በጣም ጥቂት ለሆኑ አካላት ብቻ ነው። አብዛኛው ሕዝብ ከፋይናንስ ተደራሽነት የራቀ ነው።›› ሲሉ አመልክተው፣ የባንኩ ዘርፍ እስካሁን ድረስም ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ሆኖ የቆየው የሀገር ውስጥ ባንኮችን ለመጠበቅ ታስቦ እንደሆነ ቢገለፅም ይህ ፉክክርን የመሸሽ ልማድ ግን ሊቀየር ይገባል›› ይላሉ። ‹‹ፉክክርን መፍራት አያስፈልግም። የባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አማራጭ የብድር አቅርቦቶችን ማግኘት የሚያስችሉ አሰራሮች ስለሚኖረው ውሳኔው ለድሃው ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍልም መልካም ዜና ነው›› ብለዋል።
የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ እርምጃ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ እንደሆነ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያም የባንክ ዘርፏን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ስታደርግ በከፍተኛ ጥንቃቄ በታጀበ አሰራር ሊሆን እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
ዶክተር ሞላ መንግሥት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ ትግበራው ጥንቃቄን የሚፈልግ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የአገር ውስጥ ባንኮችን ካቀጨጩ በኋላ ጥለው የሚሄዱ ከሆነ ምጣኔ ሀብቱ ምስቅልቅል ውስጥ መግባቱ አይቀርም። መንግሥት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረጉን ሥራ በቅድመ ሁኔታና በሕጋዊ ማዕቀፎች በተደገፈ አሰራር እንዲተገበር ማድረግ አለበት›› ሲሉ ያስገነዝባሉ። ባንኮቹ ለማን ብድር ማቅረብ እንዳለባቸው፣ አሠራራቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው … የሚሉትን ጉዳዮች በጥልቀት በማጤንና ከባንኮቹ ጋር በመስማማት ወደ ሥራ መገባት ይኖርበታል ብለዋል።
ባንኮቹ ሥራቸውን መስራት ያለባቸው በአገሪቱ ሕግና ደንብ መሰረት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ፖሊሲው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሚጠቅም መልኩ መተግበር እንዳለበት ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ግልጽ መመሪያና የአሠራር ስርዓት ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ባንኮቹ ብድር ለማን እና እንዴት መስጠት እንዳለባቸው የሚያመለክቱ መመሪያዎች ሊያዘጋጁና ክትትሎችም ሊደረጉ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ አካታችነት (Financial Inclusiveness) እንዲኖር ማድረግም ተገቢ ነው። የተሻለ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅም ላላቸው እንዲሁም ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራት የሚፈልጉ ካሉ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ይመክራሉ።
የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትሮች ክፍት ሲደረግ አሳሳቢ ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል የአገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪነትና ህልውና አንዱ ነው። የውጭ ባንኮች ካላቸው የገንዘብና የቴክኖሎጂ አቅም አንፃር የአገር ውስጥ ባንኮች በገበያው ላይ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ይቸገራሉ የሚለው ጉዳይ የብዙ ወገኖች ስጋት ነው። በዚህ ረገድ ዶክተር ሞላ ‹‹የውጭ ባንኮች በሀብት፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የዳበሩ በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር ልምድ የሌላቸውን የሀገር ውስጥ ባንኮችን ጫና ውስጥ ይከቷቸዋል። ባንኮቹ አሁን ባላቸው ቁመና ከውጭ ባንኮች ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። መንግሥት የአገር ውስጥ ባንኮች አንድ ላይ ተጣምረው በመስራት ጠንካራ እንዲሆኑ ደጋግሞ መክሯል። ስለሆነም የሀገር ውስጥ ባንኮች ተጣምረው ከመስራት በተጨማሪ ከውጭ ባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራት ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎችም ማሰብ ይኖርባቸዋል›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ ደግሞ ‹‹ባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በሌሎች አገራት ውስጥ ያላቸውን የአሠራር ስርዓት ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ይመጣሉ ማለት አይደለም። ለባንኮቹ የሚፈቀዱና የማይፈቀዱ አሰራሮች ተለይተው ሊቀመጡ ይገባል። መንግሥት፣ ባንኮቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን መመሪያዎች በማዘጋጀት የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት›› በማለት የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ እርምጃ ትግበራው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ አገራት ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ባንኩ የሚያዘጋጀው የአሠራር ስርዓት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር በሂደቱ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋት ሊቀንስ የሚችል የሕግ ማዕቀፍን ያካተተ እንደሆነ በብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው መናገራቸው ይታወሳል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2015 ዓ.ም