የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ሰላማዊ አማራጭን እየተከተለ ባለበት ወቅት፣ በመላው ህዝባችን የሰላም ጉዳይ ብዙ ተስፋ በተጣለበት ወቅት ያለጦርነት የማይኖረው አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቷል፡፡ ሀገሪቱም ወደ ጦርነቱ ተገዳ ገብታለች፡፡ ሆኖም ጦርነቱን እየመከተች፣ ለሰላማዊ አማራጩ ተስፋ ሳትቆርጥ አሁንም እጇን ለሰላም ዘርግታለች፡፡
በርግጥ ቡድኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጦርነቱን ሊጀምረው እንደሚችል ምልክቶች አስቀደሞ ታይተዋል፡፡ የተኩስ አቁም ተጣሰ፣ የሰላም ንግግሩ ቅድመ ሁኔታዎች አልተፈጸሙም፣ ወዘተ. ሲል መቆየቱ ፤ ይህን ተከትሎም የሰላም ንግግሩ ቴክኒካሊ ፈርሷል ማለቱ “የዘፈን ዳር ዳሩ “እንዲሉ ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ቡድኑ ባጋጠሙት አስገዳጅ ውስጣሳዊና ውጪያዊ ችግሮች ጦርነቱን ለመጀመር ተገዷል። በዚህም ከትናንት ስህተቶች መማር ሳይችል ቀርቶ የትግራይ ወጣቶችን ለዳግም እልቂት እየዳረገ ይገኛል።
ጦርነት የባህል ጨዋታዬ ነው የሚለው ይህ ቡድን፤ የጀመረውን ጦርነት ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት አስቦ ከጦርነት ከመቆጠብ ይልቅ፤ ጦርነት ከፍቶ ጦርነቱን መንግስት ነው የጀመረው በሚል አደንቋሪ ጩኸቱ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት እየሞከረ ይገኝል። ቡድኑ ጦርነት ከፍቶ ተከፈተብኝ ሲል ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ሰሜን እዝ ላይ ራሱ ክህደትና ጥቃት ፈጽሞ፣ ጦርነቱን የጀመረው መንግስት ነው ለማለት ድፍረት የነበረው ነው፤ አሁንም የሆነው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡
መንግስት ስለ ሰላም ጦሩን ከትግራይ ክልል ባወጣ ማግስት በተያዘበት የጦርነት አባዜ ምክንያት “ ከአማራ ክልል ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ “ ብሎ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራውን በማካሄድ ወደመሀል ሀገር ዘልቆ በህዝባዊ እንቢተኝነት ያጣውን ስልጣን መልሶ ለማግኘት ሞክሯል፡፡
በዚህ ሶስተኛው የጦርነት ድግሱም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው፡፡ ለጦርነቱ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው መግለጫዎች ሲያስታውቅ ቆይቷዋል፤ በሀገሪቱ የሰላም አማራጭ እየተቀነቀነ ባለበት ሁኔታ አሸባሪው በአማራና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ትንኮሳችንም ያደርስ ነበር።
በአፍሪካ ህብረት በኩል ለሚደረገው የሰላም ንግግር ራሱን ዝግጁ ከማድረግ ይልቅ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲደረድርም ቆይቷል፤ ነገሮች እሱ በሚፈልገው መልኩ ሳይሄዱ መቅረታቸውን ሲገነዘብ ደግሞ የሰላም ንግግሩ ጉዳይ ቴክኒካሊ ፈርሷል ወደ ማለት ተሸጋግሮ ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ዳርዳርታ ምን ለማድረግ እንደሆነ የማይገነዘበው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ከዚህም በላይ ታጣቂዎቹ በሚገባ የሰለጠኑ መሆኑንም በየአደባባዩ ሲያውጅ ነበር ፡፡ ልክ እንዳለፈው ጦርነት ሁሉ ከትህነግ ታጣቂዎች ፊት የሚገባ ቁጥር ስፍር የሌለው ህጻናት፣ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወዘተ. የተካተቱበት ጀሌዎችን እንደ ሰብአዊ ጋሻ አድርጎ ሲመለምል ነበር፡፡
ለትግራይ ህዝብ የገባ የእርዳታ አቅርቦቶችን ከህዝብ ጉሮሮ በመንጠቅ ለተዋጊ ሀይሉ ራሽን እንዲሆን በየመጋዘኑ አከማችቶ የጦርነት መጀመሪያ ጊዜውን ሲጠባበቅ የነበረ ሲሆን፤ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከአለም የምግብ ድርጅት መጋዘን ላይ የፈጸመው የነዳጅ ዘረፋም የዚሁ የጦርነት ዝግጅቱ አንድ ምእራፍ ነበር።
ቡድኑ በአንድ በኩል በትግራይ ህዝብ የሚነሱ ልጆቻችን የታሉ ጥያቄን መመለስ አለመቻሉ፤ በሌላ በኩል ለቡድኑ እኩይ ተግባር የፋይናንስና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በቡድኑ ያላቸውን እምነት እያጡ መሄዳቸው የፈጠሩት ጫና ጦርነቱን እንዲጀምር አስገድደውታል።
ጦርነቱን መጀመሩ እየጋለቡት ለሚገኙት ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንዳልሞተ ፤ በህይወት መኖሩን ለማሳወቅ እንደ አንድ አማራጭ የወሰደው ነው ፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም ከቁዘማቸው ወጥተው በአዲስ የአይዞህ ባይነት መንፈስ እንዲነሳሱና መኖሩን አምነው ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ጭምር ነው ።
ይህ በትግራይ ህዝብ መከራና በትግራይ ወጣቶች ደም የሚቆመር የፖለቲካ ቁማር የአሸባሪውን ሕወሓት እድሜ ከማርዘም ያለፈ ፋዳ የሚኖረው ባለመሆኑ የትግራይ ህዝብ እውነታውን በስክነት ሊመለከተው ይገባል።
“ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” እንደሚባለውም የትግራይ ህዝብን ጨምሮ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ያለጦርነት መኖር የማይችለው ይህ ቡድን መንግስት ጦርነት ከፈተብኝ ለሚለው የማደናገሪያ ጩሀት ጆሮውን ሊሰጥ አይገባም።
ቀድሞውንም ቢሆን ስለሰላም ሲያዜምና ለሰላም ብዙ እድሎችን ሲሰጥ የቆየው ፤ ከዛም ባለፈ የቡድኑን ትንኮሳዎች ስለሰላም በልበ ሰፊነት ሲያልፍ የነበረው ፤ከሁሉም በላይ ሰላም እንደ ሀገር ለጀመርነው ልማት ስሌት ወሳኝ አቅም ነው ብሎ የሚያምነው መንግስት ወደ ጦርነት ለመግባት ምን ምክንያት ይኖረዋል ?
የአለም ምግብ ፕሮግራምን እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የሚገቡ ከባድ መኪኖችን ለወታደራዊ አገልግሎት እስከማዋል የደረሰ ዘረፋ የፈጸመ ቡድን ነው፡፡ ይህን ድርጊት አምና ፈጽሞታል፤ ዘንድሮም ጭነት ይዘው ከገቡ ከባድ መኪኖች ብዙ ያልተመለሱ አሉ፤ ለምን አልተመለሱም ለሚለው ደግሞ ባለፈው አመት ያልተመለሱበትን ምክንያት መጥቀስ የሚያስኬድ ይሆናል፡፡
ከመርደቁዮስ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2015 ዓ.ም