ጅግጅጋ፡- በሐምሌ 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በተለያዩ ከተሞች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና የንብረት ውድመት ለደረሰባቸው አካላትን ለመደገፍ 100 ሚሊዮን ብር መድቦ ለተጎጂዎች ለማከፋፈል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አደም ፋራህ ኢብራሂም በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ችግሮቹ ከተከሰቱበት ከ8 እና 9 ወራት ወዲህ የክ ልሉ መንግሥትና መሪው ድርጅት የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ) በተደራጀ ሁኔታ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመሆኑም በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካላት እንዲደገፉም በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የክልሉ አቅም በሚፈቅደው መሰረት የተመደበው የ100 ሚሊዮን ብር በትክክልና በፍትሃዊነት ለተጎጂዎች እንዲደርስ ኮሚቴ መቋቋሙን የገለፁት አቶ አደም ኮሚቴውም ከተጎጂዎች ጋር በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል። የሶማሌ ክልል መንግሥት የመስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ሮብሌ በበኩላቸው እንዳመለከቱት የጥፋት ኃይሎቹ በወቅቱ በክልሉ የመንግሥት ስልጣን ላይ በነበሩ ሰዎች መሪነት ተቀነባብሮ የተፈፀመ ነው።
በዚህም ከህይወት መጥፋት በተጨማሪ ብዙ ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ ብዙ ቤቶችና ሱቆችም ተቃጥለዋል ብለዋል። ‹‹በጠራራ ፀሐይ ዜጎች ሰርተው ያገኙትን ንብረት ተዘርፈዋል፤ ወድሞባቸዋል፤ ቤተክርስቲ ያኖችም ተቃጥለዋል። የሃይማኖት አባቶች ተገድለዋል። የከፋ ዝርፊያ ተካሂዷል፤ ብዙ ሴቶች ተደፍረዋል በአጠቃላይ በጣም አሰቃቂ ወንጀል ተፈፅሟል።›› ሲሉ የጥፋቱን ደረጃ አስረድተዋል።
ተጎጂዎችን የመርዳት ኃላፊነት አለብን የሚሉት አቶ መሀመድ ዩሱፍ ጅግጅጋ ከተማ ብቻ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ወድሟል። ‹‹ይህንን በሙሉ እንደ ካሳ መክፈል አንችልም። እንደ ክልል በካቢኔው የተወሰነ ማቋቋሚያ እንዲሰጣቸውና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠ ናቋል፤ድጋፉም እየተሰጠ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በወንድወሰን መኮንን