አዲስ አበባ፡- የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አዲሱን የዲጅታል መታወቂያ በሙከራ ደረጃ መስጠት መጀመሩን አስታወቀ። ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ለመጀመር የኔትወርክ ችግር ፈተና እንደሆነበት ኤጀንሲው አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አዲሱ ዲጅታል የነዋሪዎች መታወቂያ በሙከራ ደረጃ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል። ክፍለ ከተማው ለኤጀንሲው ያለው የቦታ ቅርበት መታወቂያውን በሙከራ ደረጃ ለመስጠት ተመራጭ እንዳደረገው ያስረዱት ዳይሬክተሯ በክፍለ ከተማው አስር ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በዘጠኙ ወረዳዎች ዲጅታል መታወቂያው መሰጠት ተጀምሯል ብለዋል።
እስከ አሁን ድረስ ከአራት ሺ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው ሦስት ሺ ለሚሆኑት መታወቂያው መሰጠቱን አስታውቀዋል። በቀጣይም ለሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዲጅታል መታወቂያውን ለማደል በኤጀንሲው በኩል ያለው ዝግጅት ከሞላ ጎደል የተጠናቀቀ ቢሆንም «የኔትወርክ ችግር ግን ለሥራው ትልቅ ፈተና ሆኖብናል» ብለዋል ዳይሬክተሯ። ዲጅታል መታወቂያው አንዴ ከተጀመረ ወደኋላ ወይም ወደ ቀድሞው አሰራር መመለስ አይቻልም። ለዚህ ደግሞ መታወቂያውን ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ለመስጠት እንዲቻል ኔትወርኩ አስተማማኝ መሆን አለበት።
‹‹መታወቂያውን በቶሎ ሰርተን ጨርሰን ለህብረተሰቡ መስጠት እንችል ዘንድ እንደ አይሲቲ ኤጀንሲና ኢትዮ ቴሌኮም የመሳሰሉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው። መብራት በጠፋ ቁጥር ሥራ ለመስራት እየተቸገርን ነው›› ብለዋል ዳይሬክተሯ። «በተለይም ኢትዮ ቴሌኮም ቅድሚያ ሰጥቶ ልዩ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል» ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ቴክኖሎጂው አዲስ ከመሆኑ አኳያ በኤጀንሲው በኩልም ከክህሎት ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ ችግሩ በስልጠና የሚፈታ በመሆኑ ያን ያህል አሳሳቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። ስለሆነም ዋነኛው ችግር የኔትወርክና ከሲስተም ዝርጋታ ጋር የተገናኘው በመሆኑ በአይሲቲ ኤጀንሲና በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ያለው ሥራ ከተጠናቀቀ በኤጀንሲው በኩል ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ዲጅታል መታወቂያውን መስጠት የሚጀምሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በይበል ካሳ