አረንጓዴ ቀለም ያለውና ከማሽላ ምርት ወይንም ፍሬ ጋር የሚመሳሰል ነው። ለብዙዎችም የተለመደ እንዳልሆነ እገምታለሁ። የምግብ ንጥረ ነገሩ ከፍተኛና ጠቃሚ እንዲሁም በዋጋም ከጤፍ በልጦ በኩንታል እስከ ዘጠኝ ሺ ብር የሚያወጣ መሆኑ የበለጠ ትኩረቴን ሳበው።
ማሾ የሚል መጠሪያ ያለውና ከቅባት እህል ውስጥ እንደሚመደብ የነገሩኝ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበር ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ፈቃደ ናቸው፣ ሰብሉ በአማራ ክልል ይፋት ሸዋ ሮቢት አካባቢ እንደሚመረትና አረንጓዴ ወርቅ የሸዋ ማሾ የሚባል ስያሜ እንደተሰጠውም እኚሁ ሃላፊ አጫውተውኛል።
እሳቸው ሰብሉ በሀገር ውስጥ ለምግብነት ከሚውል ይልቅ ለውጭ ገበያ ቀርቦ የውጭ ምንዛሬ ቢያስገኝ ከአምራቹ ባለፈ ለሀገር የኢኮኖሚያዊ እድገት ፋይዳው ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አላቸው። የአካባቢው አምራችም ይህንኑ እንደሚመርጥ ነው የተናገሩት። ምርቱ አነስተኛ በመሆኑ ለገበያ የማቅረቡን ምርጫ አስቀደሙ እንጂ፣ በብዛት ተመርቶ ሕዝቡ ለምግብ ፍጆታ ቢጠቀመው ሰብሉ የያዘው ንጥረ ነገር ከፍተኛ መሆኑ በዘርፉ አካላት እንደሚገለጽም ይናገራሉ።
ስለ ማሾ ሰብል ምርትና የአመራረት ዘዴ ከማሕበራዊ ድረገጽ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያስረዳው እንደ ህንድ፣ ቻይና ፓኪስታን፣ ታይላንድ፣ ፊሊፒንስ ባሉ ሀገራት ሰብሉ ይመረታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ፣ እስያ፣ኢትዮጵያና በሌሎችም ሀገሮች መመረት ጀምሯል።
በኢትዮጵያ አዲስ የሆነው ማሾ በአርሶ አደሩ በስፋት ባለመታወቁ ልማቱም ሰፊ አይደለም። ሰብሉ ድርቅን የሚቋቋም በመሆኑ በተለይ ዝናብ አጠር በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ቢመረት ያዋጣል። ምርቱ ከሐምሌ መጀመሪያ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ነው የሚከናወነው። የማሾ ሰብልን የማወቅ እድሉን ያገኘሁት የሰሜን ሸዋ የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበር ዩኒየን ‹‹የጋራ ጥረት ለሀገር እድገት›› እንዲሁም ‹‹አምራችነት ለሁለተናዊ እድገት›› በሚል መሪ ቃል ጳጉሜን 2 ቀን 2014 ዓ.ም በተሰየመው የአምራቾች ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ዝግጅት ላይ የአካባቢያቸው የምርት ውጤቶችን ለገበያ ለማስተዋወቅ ይዞ በቀረበበት ወቅት ነው። በዝናብ አጠር አካባቢ ተፈላጊ፣ በምግብነቱም ተመራጭና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትም ባለው የኢኮኖሚ ፋይዳ ስለማሾ ሰብል ብናወሳም፣ ኢትዮጵያ መልካምድሯ ፣የአየርፀባዩዋ፣ ሰፊ መሬቷና የውሃ ሀብቷ ለተለያየ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ በመሆኑ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከማሳካትም ባለፈ የአግሮ ኢንዱስትሪውን (የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ) ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ምርት ማምረት የሚያስችል ዕድል አላት።
በዚህ የአምራቾች ቀን መድረክ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባሳለፈችው አራት የሪፎርም ዓመታት የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የሎጅስቲክ ትራንስፖርት ሥርዓትን ለማሳለጥ፣ በሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦትን በመጨመር፣ በውጭ ምንዛሬ በግዥ ወደ ሀገር የሚገቡ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና ወደ ውጭ ለመላክም በብዛትና በጥራት ለመጨመር ሲሰራ ቆይቷል። ለእዚህም በበጋ የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቡና ልማት የተመዘገቡት ውጤቶች ማሳያ ናቸው።
በጳጉሜን ሁለት በተሰየመው የአምራቾች ቀን አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁና ለገበያ እንዲያውሉ የማድረጉ ዓላማም በአምራቾችና በመንግሥት የጋራ ጥረት እየተመዘገቡ ባሉ ለውጦች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ለ2015 በጀት ዓመት ለበለጠ ውጤት ለመዘጋጀት መሆኑን ጠቁመዋል።
‹‹መስኖ ለምግብ ሉዓላዊነት›› በሚል መሪ ቃል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርም እየሰራ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢኒጅነር አይሻ መሐመድ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል። ሀገር እንደ ሀገር መቆም የምትችለው ሉዓላዊነቷ ሲጠበቅ ነው። ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በትግል ወይንም ወታደር በማቆም ብቻ ሳይሆን በምግብ እህል ራስን ለመቻል ሲሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዓለም ላይ ያለውን ጫና መወጣት የሚቻለውም አምራች እና በምግብ ሉዓላዊ መሆን ሲቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ወደፊት ጦርነቱ በመሣሪያ ብቻ እንደማይሆን ከወዲሁ አመላካች ነገሮች ይታያሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል በተፈጠረ ጦርነት ምክንያት ለዓለም የስንዴ ምርት አቅራቢ የሆነችው ዩክሬይን የገጠማትን ፈተናም ጠቅሰዋል። ሀገሪቱ በገጠማት ጦርነት ምክንያት ስንዴ በግዥ ከሀገሪቱ የሚገዙ ሀገሮች ምን ያህል እንደተጎዱም ተናግረዋል። ስንዴን በግዥ የሚጠቀሙ ሀገራት በራሳቸው አምርተው መጠቀም ካልቻሉ ወደፊት የሚሆነው የዓለም ጦርነት የምግብ እንደሚሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ስጋቶችን ለመቀነስ ልማትን ማፋጠን ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለልማቱ ሥራ ወሳኝ ከሆነው አንዱ መስኖ መሆኑንም ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ እንደ ሀገር በመስኖ ማልማት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በሚፈለገው ልክ መጠቀም ግን አልተቻለም። ግብርናው በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው።
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሶሶ የሆነውንና ሰፊ የሰው ኃይል በመያዝም ድርሻ ያለውን የግብርና ሥራ በመስኖ መደገፍ ግዴታ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። መስኖ ለልማት እንዲውል በብዛት የመስኖ መሠረተ ልማት እንዲከናወን መንግሥት ጥረት አድርጓል።
በ2013-2014 የምርት ዘመን የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን የመስኖ አገልግሎት ጥቅም ላይ መዋል አስተዋጽኦ አድርጓል። ለእዚህም የቆላና የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ይጠቀሳል። የግብርና ሥራ በመስኖ እንዳይደገፍ ማድረግ በግብርና ምርታማነት ላይም ሆነ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል።
በስንዴ ልማት ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብም የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት እንደ ሀገር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ በላቀ መልኩ ለመወጣት ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሆን የእርሻ ማሣ በመስኖ እንዲለማ ለማስቻል ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተልእኮውን እንደሚወጣም ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለአምራችነት የሚውለውን ሰፊ የእርሻ መሬትና የውሃ ሀብት የማገናኘት ሥራ የሚሰራ ድልድይ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህንንም በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት ነው ኃላፊነት የተሰጠው ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሌላው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተልእኮ የአርብቶ አደር ወይንም የቆላማ አካባቢ ልማት ሲሆን፣ አርብቶ አደርነት አንዱ የኑሮ ዘይቤ ነው። ይህም በተለያዩ የሀገሪቱ ፖሊሲዎች ተቀባይነት ያገኘ ነው። ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ በራሱ ግብ እንዳልሆነ ግምት ውስጥ በማስገባትም በፖሊሲ ተቀባይነት እንዲኖረው የተደረገውን የሚያስፈጽም አስፈጻሚ ተቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ሰፊ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የያዙ በመሆናቸው በአካባቢው የሚገኙትን ሀብቶች አካባቢንም ሀገርንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እንደፖሊሲ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየመራ ይገኛል። በዚህ ረገድም ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ጎሎልቻ ‹‹ወደ 115 ሚሊዮን ሕዝብ አለን። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶ የሚሆነው አምራች ነው። ካመረትን ደግሞ ሸጠንና ለውጠን ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን እንችላለን። ይሁንና በተፈጥሮ ፀጋ የታደልን ብንሆንም፣ አምራች ኃይል ቢኖረንም ምርታማ አይደለንም፤ ገና ወደምርታማነት ለመግባት ጥረት እያደረግን ነው›› ይላሉ።
እንደ ሀገር ሉዓላዊ ሆኖ መኖር የሚቻለው ማምረት ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰው፣ በግብርናው ዘርፍ እርሻውን፣ በኢንዱስትሪውም የግብርና ግብዓቶችን ማቀነባበር እንዲቻል ፣ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለማምረትና እቅዱንም ለማሳካት መንግሥት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ይገልጻሉ።
ግብርናውን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ትላልቅ የማቀነባበሪያና የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና አስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማቶችን በመገንባት መንግሥት ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል ሲሉም ይገልጻሉ።
አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል ከፍተኛ ስኬት ለማስመዝገብ በቅንጅት መንቀሳቀስ እጅግ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የኢንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት፣ ዘላቂ የሆነ ተወዳዳሪነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ለሀገራዊ መዋቅራዊ ሽግግር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ንቅናቄ በመፍጠር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል። ጥረቶቹን በማጠናከር ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም በተናበበ መልኩ የየራሳቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስድስት አስፈጻሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት መንቀሳቀሳቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም በገጠማት የተለያየ ፈተና ውስጥ ሆና በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ የሚባል ስኬት ማስመዝገቧን የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ፤ እንደ ሀገር በተጀመረው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። አምራች ዘርፉንም በማጠናከር መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ላይ ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ግብርና፣ ማዕድንና አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚጠቀሱ አስታውሰዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ፤ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ከወጪ ንግድ ስብጥር አኳያ ግብርና በ2012ዓም ከደረሰበት 77 በመቶ በ2022 ዓ.ም ወደ 36 ነጥብ 4 በመቶ፣ አምራች ኢንዱስትሪ በ2012 ዓ.ም ከደረሰበት 13 ነጥብ 3 በመቶ፣ በ2022 ዓ.ም ወደ 48 ነጥብ 4 በመቶ ፣ የማዕድን ዘርፍ ደግሞ በ2012 ዓ.ም ከደረሰበት 6 ነጥብ 9 በመቶ፣ በ2022 ዓ.ም ወደ 11 በመቶ እንዲያድግ መንግሥት አቅዷል።
ይህን ለማሳካት ሰፊ ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም መንግሥት ደጋፊ የሆኑ አስፈጸሚ የሚኒስቴር ተቋማትን እንደ አዲስ በማወቀርና የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተሳለጠ አምራች ዘርፍ መገንባትና የተጠናከረ ኢኮኖሚ መፍጠር መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪን የኋልዮሽና የፊትዮሽ ትስስር በማረጋገጥ የግብርናና የማዕድን ኢንዱስትሪዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ፍላጎት በማከለ መልኩ እንዲያመርቱ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዘርፎቹን ትስስር የሚያረጋግጡት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ምርቶችን በጥራትና በወቅቱ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርሱ የትራንስፖርትና የመንገድ መሠረተ ልማት አቅርቦቶችን የማረጋገጥ ኃላፊነቶችን መወጣት ይኖርባቸዋል ፤ እየተወጡም ይገኛሉ ብለዋል።
ወሳኝ የሆነውን አምራችነት ለማረጋገጥ ግን የሁሉንም የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። የተቋማት ቅንጅትና አብሮነት አስፈላጊነትን ለማስመስከር የሚያስችለውን እንቅስቃሴና የኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ በምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ለማሳየት በአምራችነት ቀን ላይ በቁጥር 50 የሚሆኑ ምርቶች በአንድ ቦታ ለማየት መቻሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፣ መስሪያ ቤታቸው ለምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ወደ ማምረቻ፣ የተመረተውን ወደ ተጠቃሚው በወቅቱና በጊዜው በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች በማድረስ በቅንጅት ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን ይጠቅሳሉ። ለአብነትም በወጭ ንግድ (ኤክስፖርት) በግብርናው ዘርፍ ከነበሩት ስኬቶች መካከል ምርቶችን በኮንቴነር በማሸግ እንዲጓጓዝ በማድረግ ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ተጠቃሚው ዘንድ እንዲደረስ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተለይም የቡና ምርት 98 በመቶ በኮንቴነር አሽጎ የማጓጓዝ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፣ የመርከብ፣ የባቡርና የጭነት ትራንስፖርትን በማቀናጀት፣ የማዳበሪያ ግብዓትም በወቅቱ እንዲደረስ፣ ነጻ የንግድ ቀጠና በማቋቋም አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፉን ተደራሽ በመሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥረት ማድረጉን ይገልጻሉ። አገልግሎቱን በጥራጥሬና ሌሎች ምርቶች ላይም በማስፋት ምርቶችን በጥራትና በወቅቱ ተጠቃሚው ዘንድ የማድረስ አቅም በመፍጠር የበለጠ ለመሥራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል።
የጳጉሜን ሁለቱ ‹‹የአምራችነት›› መርሃግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚን ተደራሽ እስከ ማድረግ የሚዘልቅ ቅንጅታዊ ተልዕኮን ለማስፈጸም መሰረት የተጣለበት ሊባል የሚችል ነው። መርሀ ግብሩ በተለያየ የግብርና ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የአርሶ አደሮች አደረጃጀቶች የሆኑ ዩኒየኖች፣ በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች፣ በእንስሳት፣ አትክልትና ልማት ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰሩ ባለሀብቶች፣ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ምርታቸውን ለሚያቀርቡ በግብርና ሜካናይዝሽንና ኬሚካል ማምረት ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች የገበያ ትስስር ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም