አዲስ አበባ፡- « በአገራዊ የለውጡ ሂደት ውስጥ በሶማሌ ክልል ላይ አዲስ የሰላም አየር መንፈሱ ለሶማሌ ክልል እና ለሀገራችን ትልቅ የለውጥ ስኬት ነው» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መግለፃቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ሶዴፓ/ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ለሶዴፓ ጉባዔተኞች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች እና ለክልሉ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳመለከቱት በክልሉ በተፈጠረው ሰላም የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አባላት እና አመራሮች እንዲሁም በእስር ቤቶች ሲማቅቁ የነበሩ ወገኖች የጉባዔው ታዳሚ መሆናቸው ልዩ ትርጉም ያለው የለውጥ ውጤት ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ መጀመሪያ የተንቀሳቀሱት ወደ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል መሆኑን አስታውሰው በወቅቱ ወደ ክልሉ የመጡት በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት እንዲቻል ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ለመወያየት የነበረ መሆኑን ተናግረዋል:: ችግሮቹንም መፍታት በመቻላቸው ምስጋና አቅርበዋል::
የሶማሌ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሟላ ሁኔታ በምሁራን እንዲመራ መደረጉ መል ካም ጅምር መሆኑን እና ፓርቲውም የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ሶዴፓ/ በማለት መቀየሩ የሶማሌ ህዝብ ያለምንም ተቀፅላ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያረጋገጠ መሆ ኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል::
የክልሉ አመራር እና ህዝብ ቀጣዩ ሥራ መስኖን ማስፋፋት፣ የሥራ አጥነትን ችግር ለመፍታት ጠንክሮ መስራት፣ ኮንትሮባንድን፣ የፖለቲካ እና የገንዘብ ሌቦችን መታገል መሆኑን አመላክተዋል:: ክልሉ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት ድጋፍ የማይለየው መሆኑን አረጋግጠዋል::
የዛሬ ዓመት የክልሉ ሽማግሌዎች በሶማሊ ላንድ አስተዳደርና በሶማሊያ መንግሥት መካከል መግባባት እንዲኖር የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ባቀረቡላቸው መሠረት፣ ባለፉት ወራት ከሁለቱም መሪዎች ጋር ተገና ኝተው በመደመር ፍልስፍና አብረው ለመስራት ማስማማታቸውን አስታውሰዋል። የሁለቱም ወገኖች መስማማትም ለቀጠናው ውህደት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር