10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሂዷል ። በ9 የተለያዩ ዘርፎችም በህዝብ ጥቆማ ከተሰጠባቸው ከ700 በላይ በጎዎች መካከል 27 እጩዎች ቀርበው ተሸልመዋል ። ከዘጠኙ ዘርፎች መካከል አንደኛው የቅርስና ባህል ዘርፍ ሲሆን የመጨረሻዎቹ እጩዎችም አቶ አቡ ገብሬ ፤ ሐጂ መሀመድ አወል ሀምዛ እና መምህር ዜና ማርቆስ እንዳለው ሆነዋል ። በዛሬው እትማችን ባለዋሽንቱን በጎ ሰው አቡ ገብሬን የሕይወት ታሪክ በመርሀ ግብሩ ላይ ከቀረበው ግለ ታሪኩ በመውሰድ እንቃኛለን ።
አቡ ገብሬ ኬቶ በ1966 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ሽሮሜዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ ። እድሜው ለትምህርት ሲበቃ በ1975 ዓም አምሃ ደስታ ትምህርት ቤት በመግባት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተከታተለ ሲሆን የ8ኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት አልፏል ። አቡ ገብሬ በ1983 ዓ.ም የ9ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት የሙዚቃ ዝንባሌ ስለነበረው ዝንባሌውን ከትምህርት ጎን ለጎን ያስኬድ ነበር ። በወቅቱም ከአማተር ቴአትር ክበባት ጋር በመሆን ሙዚቃ መሳሪያ በመጫወትና በማዜም ያሳልፍ ነበር ።
በ1986 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወሰደበት ዓመትም በህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ለመቀጠር በቃ ። አቡ ይሄን አጋጣሚ ለቀጣይ ሕይወቱ መስፈንጠሪያና ለዛሬው ማንነቱ መሰረት የጣለበት አጋጣሚም ሆነ ። በህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ተቀጥሮ የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች የማግኘት እድል ስለነበረው የጊታር፣ የዋሽንት፣ የክራር ችሎታውን ለማዳበር ችሏል። ይሁን እንጂ የዋሽንት ዝንባሌው እያየለ በመምጣቱ በዚሁ ዘርፍ ብዙ ስራዎችን ለመስራት በቅቷል ።
አቡ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ሙዚቃን በመጫወት የግልም የቡድንም ልምድ አካብቷል። በስራ ውስጥ በሚገኝና በሚፈጠር ውይይትና መተጋገዝ ራሱንም ሆነ የቡድን ጓደኞቹን በእውቀትና ልምድ ደግፏል ። በተለያዩ ታዋቂ ሆቴሎች ለ18 ዓመታት ከመደበኛ ስራው በኋላ የባህል ምሽቶችን በመዘዋወር ተጫውቷል ።
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገራችን ባህላዊ ዘፈኖች ላይ በመሳተፍ ትልቅ እውቅናን ያተረፈ ሲሆን ኤፍሬም ታምሩ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በጋራ ያዜሙት ‹‹ኑኑ››፣ ታደለ ሮባ የተጫወተው ‹‹ኢትዮጵያ››፣ የዳዊት ጽጌ አልበም ‹‹የኔ ዜማ››፣ የጃኖ ባንዷ ሀሌሉያ ተክለጻዲቅ የተጫወተችው ‹‹ሸግዬ››፣ የኛ የሙዚቃ ቡድን የተጫወቱት ‹‹አቤት››፣ የሚካኤል በላይነህ ‹‹ስቄ ሸኝሻለሁ››፣ የራሄድ ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያ››፣ የወንዴ ማክ ‹‹በውይይት›› እና ሌሎችም ላይ ተሳትፏል ። ከአስቴር አወቀ፣ ጸደንያ ገብረማርቆስ፣ አበባ ደሳለኝ እና ሌሎች ታዋቂ ድምጻውያንም ጋር እንዲሁ አብሮ ሰርቷል ።
አቡ ለሙዚቃው ኢንደስትሪ ካበረከታቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ በርካታ ወጣቶች ክራር ተጫዋች እንዲሆኑ ሙያውን ማጋራቱ ነው ። ዛሬ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ስመጥር ወጣት የክራር ተጫዋቾች የአቡ ሙያዊ እገዛ የተቸራቸው ናቸው ። በተለይም የኢትዮጵያ የባህል መሳሪያ በሆነው ዋሽንት ዙሪያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ጥናት ሲያካሂዱ ለምርምር የራሱን አበርክቶ ሰጥቷል ። ሁለት የውጭ አገር የሙዚቃ ምሁራንም ዋሽንትን ለማጥናት በመጡበት ወቅት የሙያ ተሞክሮውን አካፍሏል ።
አቡ ገብሬ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በተለያዩ የውጭ አገራት በተዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ በመሳተፍ ስራውን አቅርቧል ። ጀርመን፣ ሰዊዘርላንድ፣ እስራኤል፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ ወዘተ በተደጋጋሚ ተዘዋውሮ የሰራባቸውና የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ያስተዋወቀባቸው አገራት ናቸው ።
ከአስር ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአቡ ዋሽንት ያልገባበት ቦታ የለም ማለት ማጋነን አይሆንም ። ከ100 በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖናና እና ትውፊት የተሰሩ መዝሙሮች ላይም ተሳትፏል ። በሲኒማው ኢንደስትሪም የአቡ አበርክቶ ከፍተኛ ነው ። ጤዛ፣ አልቦ፣ አትሌቱ እና ዓባይ ወይስ ቬጋስ በዋሽንት ከተሳተፈባቸው ስራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው ። አቡ ሰርከስ ኢትዮጵያ መስራች አባልም ነበር ። ዋሽንቱን ይዞ ሰርከስ ኢትዮጵያን ካቋቋሙት ሰዎች መሀከል አንዱ ሆኖ ተሳትፏል ። በባላገሩ አይዶል ላይ የመክፈቻ ፕሮግራሙን እንዲሁም ከአንድ እስከ ሶስተኛ ዙር ያለውን ውድድር አጅቧል ። አቡ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ፍቅር ቴአትር እየሰራ የሚገኝ ሙዚቀኛ ነው ።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም