«ከ19 ዓመታት በፊት የ15 ዓመት ልጅ፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቫይረሱ በደሜ መኖሩን አስባለሁ። ያኔ በሴት ጓደኛዬ አማካኝነት በሰፈራችን ልጅ ተደፈርኩ።በዚያን ጊዜ የክፍለ ሀገር ልጅ ሆኖ እንዲህ ዓይነት ነገር መፈጸም አይታሰብም» ትላለች የዚህ ታሪክ ባለቤት ሠናይት ደረጀ (ስም ተቀይሯል)።
አንድ ቀን በጫካ ወደተከበበችው ትምህርት ቤቷ እየሄደች ሳለ አንድ ወጣት ልጅ ሠናይትን ያዛት። የሚያስጥላት ሰው አልነበረም። ሰውነቷም ስላልጠነከረ ታግላም ራሷን ማዳን አልቻለችም። ጫካ ውስጥ አስገድዶ ደፈራት። ሁኔታዎች አልፈው የ17 ዓመት ልጅ ሳለችም አገባች፤ ወለደችም። ግን የባለቤቷ ሞት ብቸኛ አደረጋት። አብራት ትሠራ የነበረች ልጅ «እርሷ እኮ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ናት ባሏ ሞቷል» ብላ ታወራባት ነበር። ስትሰማ ተናደደች። ተመርምራም ውጤቱን አወቀች። «ውጤቱን ሳውቅ አልደነገጥኩም» ትላለች።
ልጄን አስመረመርኳት ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩ አሳመመኝ። ልጄ አልፎ አልፎ «እኔን እኮ ማትረፍ ትችይ ነበር» ስትለኝ ውስጤ ይወቅሰኛል፤ ዕረፍት አጣለሁ፡፡ በዚህ ዘመን ሕፃናቶችን ማትረፍ ሲቻል በቫይረሱ ሲሰቃዩ ማየት ህመሜን ይቀሰቅሰዋል። እየነገርኳቸውም ግንኙነት ለማድረግ የሚፈልጉ ወንዶች ያስገርሙኛል። ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩ ልጆች ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው። መጠጥ፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕጽ ስለሚጠቀሙ ቀጥለው የሚያደርጉትን አያውቁም። በመሆኑም ለእነርሱ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ስትል ትመክራለች ሠናይት።
ኤድስ ሄልዝ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ተፈራ እንደሚሉት፤ ያለፉት 20 ዓመታት የመከላከል ሥራ በአግባቡ ተሠርቷል። ሆኖም በሽታው የማህበረሰብ ችግር አይደለም የሚል ግንዛቤ በመፈጠሩ የመረጃ ስርጭትና በመቆጣጠር ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የመከላከል ሥራው ካልተጠናከረ የተገኙትን ውጤቶች እናጣለን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2030 ኤች አይ ቪ /ኤድስን የማህበረሰብ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ለማሳካት ፈተና ይሆናል፤ በሽታውም ህይወት እየቀጠፈ ይቀጥላል የሚል ስጋት አላቸው።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ፀረ ኤች አይ ቪ ዘመቻ ላይ በወጣቱ ደረጃ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ያሰጋል። በአሁኑ ወቅት ያሉት በርካታ ወጣቶች ኤችአይቪ/ኤድስ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በሚገባ አልተገነዘቡትም። በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ የነበረውን ሰቀቀን በሚገባ አያውቁም፤ የሰዎችን ህልፈተ ሕይወትም አላዩም፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ በስፋት መሠራት ይኖርበታል፡፡ የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና ዋጋ እንደሌለው የመቁጠር፣ ዘግይቶ የመጀመርና ማቋረጥ የሚስተዋሉ ችግሮች በመሆናቸው መስተካከል ይኖርበታል።
ከተማ ውስጥ፣ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶችና የእነርሱ ደንበኞች፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሠሩ ወጣቶች፣ ረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ እፅ የሚጠቀሙ ሰዎች፣ ባለቤቶቻቸውን በሞት ያጡ ሰዎች፣ ከእናት ወደ ልጅ በመተላለፍ ለበሽታው ተጋላጮች መሆናቸውን ያመለከቱና እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የመከላከል ሥራው ትኩረት ሊያደርግ ይገባል የሚለው የዶክተር ተስፋዬ ምክር ነው።
በኤድስ ሄልዝ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት የመከላከል ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ እንደሚሉት፤ በወቅቱ አሳሳቢ ስለነበር ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ ይደረግ ስለነበር ውጤት ተገኝቷል። ሆኖም ውጤቱ ለመዘናጋቱ እንደ ምክንያት ይታሰባል። አመራሮችም ሚናቸውን ቀንሰዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥታትንና አገራትን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ይስተዋላሉ። ይህንን ተከትሎ የበጀት ሽሚያ ተፈጥሯል። በመሆኑም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል የሚመደበው ገንዘብ በመቀነሱ ሥራው ተዳክሟል።
እንደ አቶ ሄኖክ ሃሳብ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ለውጦች ታይተዋል፤ ስርጭቱም ቀንሷል፡፡ ግን አሁንም ቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ የሆነባቸው ክልሎች አሉ፡፡ የቫይረሱ ስርጭት በከተማ 2ነጥብ9 በመቶ ሲሆን፤ በገጠር ደግሞ 0ነጥብ4 በመቶ ነው፡፡ አሁን ያለው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እንዳያንሰራራ ከፍተኛ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡
ኤች አይ ቪ/ኤድስ ባለመጥፋቱ፤ ማህበረሰቡ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል። ቀድሞ የነበረው የመከላከሉ ሥራ የተዳከመ ስለነበር ወጣቶችና ልጆች መረጃዎችን በአግባቡ ያልተዳረሰ ሲሆን፤ የእውቀት ደረጃቸውን ከ30 በመቶ ያልዘለለ ነው። በቀጣይም በትኩረት ካልተሠራበት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን በበኩላቸው፤ እ.ኤ.አ በ2030 ኤድስን በመግታትና የማህበረሰብ ችግር እንዳይሆን ተጋላጭነትን ትኩረት ያደረገ ምርመራና የምክር አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ወገኖችም ድጋፍና ክብካቤ ማድረግና የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት እንዲያገኙ መሠራት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡
መድኃኒቱን የጀመሩትም እንዳያቋርጡ፣ ያቋረጡትንም ፈልጎ ማግኘት የሚያስችል ስልት መዘርጋት እንዳለበት በመጠቆም፤ የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ ያረጋግጣሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2011
በዘላለም ግዛው