
በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር ዙል ሂጃህም ይሰኛል። በዚህ ወር ዘጠነኛ ቀን በመላው ዓለም ያለው ሕዝበ ሙስሊም ተሰባስቦ ወደ መካ ይተማል። ይህ ዘጠነኛ ቀን አደም እና ሐዋ የአላህን የተከለከለ ትዕዛዝ በመተላለፋቸው ከአደም ጀነት ተባረው ወደ ምድር የተሰደዱበት ነው። ቀኑ 5ሺህ 500 ዘመንም ተራርቀው ከቆዩ በኋላ የተገናኙበት (የተዋወቁበት) ስለመሆኑ የእስልምና ሐይማኖት እምነት ተከታይ አባቶች ይናገራሉ። አባቶቹ ይሄ አደም እና ሐዋ የተዋወቁበት ሥፍራ አረፋ ስለመባሉም ያነሳሉ።
ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ ማለት «የመተዋወቅ ተራራ » ማለት ነው ይላሉ። በዓሉ የሀጂን ሶላት ተከትሎ ወሩ በገባ 10ኛ ቀን የሚከበረውን የአረፋ በዓልን ተከትሎ ያሉትን ሦስት ተከታታይ ቀናቶች እርስ በርስ በመረዳዳትና እና በመከባበር በተለይ ሀብታሙ የእምነቱ ተከታይ ካለው አንድ ሦስተኛውን ለሌላቸው በማካፈል ማኅበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክርበት እንደሆነም የሚነገርበት ነው። ኃላፊነቱን ጭምር በመወጣት የሚከበር ስለመሆኑ የሐይማኖቱ አስተምህሮ ይደነግጋል።
ዛሬ ይሄ በዓል በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር ዙል ሂጃህ 10ኛ ቀን ላይ እንገኛለን። ቀኑ የእስልምና አምስተኛው መሰረት የሆነው የሃጂ ሥርዓት የሚከወንበትም ነው። ይሄን የሀጂ ሥነስርዓት ክዋኔ ተከትሎም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ የኢድ አል አድሃ ወይም የአረፋ በዓል ሥርዓተ ይካሄድበታል። ለመሆኑ ይህ በዓል በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ምን አይነት ትርጉም አለው?
ለዛሬም የዚህኑ በዓል የሕዝበ ሙስሊሙን ማኅበራዊ መስተጋብር የበለጠ የሚያጠናክር ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ ሂደት አስመልክተን ከዑስታዝ መሐመድ አባተ ጋር ቆይታ አድርገናል። ዑስታዝ መሀመድ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና እስላማዊ ተቋማት ፈቃጅ ናቸው።
ዑስታዝ መሐመድ እንዳጫወቱን ታድያ ወሩ የእስልምና አምስተኛው መሰረት የሆነው የሃጂ ሥርዓት የሚከወንበት ነው። በዚህ ወር ሙስሊሙ ማኅበረሰብ (በተለይም ተዘወትሮ የሃጂ ተጓዥ የሚሰኘው) ጾታ፤ ሥልጣን፤ ዕድሜ፤ሀብት እና ሌሎች ደረጃዎች ሳይወስኑት ከያለበት የዓለም ጫፍ ተጠራርቶ የምድር እንብርት በሚላት በመካ ከተማ ይሰባሰባል። የሃጂ ሥነሥርዓቱንም በዚሁ ቅዱስ ተራራ ይከውናል።
ቦታው አረፋ ተብሎ የተከለለ ሰፊ ቦታ ሲሆን ነብዩ መሐመድ አረፋ ከየት እስከ የት እንደሆነ ተናግረው፤ ድንበሩን አሳይተው ነው ያለፉት። በመሆኑም ሕዝበ ሙስሊሙ ለአንዲት ሰከንድ፤ ደቂቃ፤ ሰዓት ይሄ ድንበር ባለበት ቦታ ላይ መገኘት ለእምነቱ ተከታዮች ከፈጣሪ ዘንድ ያቀርብና ያስቀድሳል የሚል ትልቅ ትርጉም አለው። የመስዋዕትነት፤ የፀፀት፤ የምህረት፤ ማሳያ ተደርጎም ይታመናል። ለአንድ ሰከንድ፤ ደቂቃ፤ ሰዓትም ቢሆን የግድ መገኘት እንዳለበት የነብዩ መሐመድ የእስልምና አስተምህሮ ያዛል። ይሄ ተራራ ታዲያ ከመካ በስተምስራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ከሥር ሆኖ ሽቅብ ሲመለከቱት አብዝቶ መንፈሳዊ ደስታ ያጎናጽፋል። ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችንም በዚሁ ተራራ መፈፀም እንዳለበት የሐይማኖቱ አስተምህሮ ይደነግጋል።
ከሚያከናውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱ ደግሞ በተራራው የሚካሄደው የሶላት ስግደት ሥሥርዓት ነው። ተራራው በአጠቃላይም የተራራው ዙርያ ገባ ድንበር በነብዩ መሐመድ ተወስኗል። እዚህ ተራራ ላይ መውጣትም አለመውጣትም የተከለከለም፤ ያልተከለከለም አይደለም። ከአምልኮቱ ጋርም አይያያዝም። ነገር ግን መውጣት እፈልጋለሁ የሚል ሙስሊም ቢኖር ከአራት ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታይ በሚታደምበት የተጨናነቀ ሁኔታ ለመውጣት አለመቻሉ ነው። ነብዩ መሐመድ ራሳቸው የአረፋን ቀን ተራራው ላይ በመውጣት ሳይሆን ከስር ሆነው ነው በማስተማር ማሳለፋቸው የነገሩን። በመሆኑም ሕዝበ ሙስሊሙ በሥፍራው ማልዶ ይገኛል። ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስም ሶላት እየሰገደ፤ ቅዱስ ቁራንን እያነበበ፤ ፈጣሪውን እያመሰገነ እና የምህረት እጁን እንዲዘረጋለት ሲማፀን ይቆያል።
ዑስታዝ መሐመድ እንደሚሉት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በተለይ በመካ የሚከወነው አምልኮ ፈፃሚ የሃጂ ተጓዦች በዛው በመካ አካባቢ በሚገኘው አያሌ ሙስሊሞችን ማስተናገድ በሚችል ሙዝዳሊፋህ አቅንቶ ቀሪ የሐይማኖት ሥርዓቱን ያከናውናል።
ወደ መካ መጓዝ ያልቻለ የእምነቱ ተከታይ ደግሞ በዕለቱ በያለበት አካባቢ ሆኖ በርካታ ሰው መያዝ በሚችል ሰፊ ሜዳ ላይ የሶላት ስግደት ያከናውናሉ። ይሄ ስግደት አዲስ አበባ ላይ በስታዲዮም ነው የሚከናወነው። ስግደቱ ከመካው በተመሳሳይ ሰዓት ማልዶ የሚከወን ሲሆን የእምነቱ አስተምህሮ የሚያዘው አለባበስ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንዶችም ሴቶችም ይሳተፉበታል። የሰላቱ አፈፃፀም ሂደቶች፤ የእርድ አቀራረብ፤ ከሌላው የተለየ ሳይሆን ተመሳሳይ ነው። ሆኖም ለበዓሉ ድምቀት እናቶች ብዙ በሚደክሙበት ሁኔታ ወንዶች ዝም ብለው የሚያዩበት እገዛ በሚያደርጉበት ሁኔታ መስተካከል አለበት። በአጠቃላይ በዓሉ ድምቀት እንዲኖረው፤ ሁሉ የተሟላ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር የሚኖራቸው አስተዋጾ በጣም ከፍ ያለ መሆኑን ዑስታዝ መሐመድ ይናገራሉ።
የምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ ዑስታዝ መሐመድ የኢድ አል አድሃ ወይም የአረፋ በዓል የሚከወነው ይሄን የሀጂ ሥነሥርዓት ሂደት ተከትሎ ስለመሆኑ ያወሳሉ። የአረፋ በዓል መሰረታዊ ክዋኔ ከሀጂ ሥነሥርዓት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ። “አረፋ ከሀጂ ከሚከወን ሥነሥርዓትም አንዱ ክፍል ነው ”ሲሉም ይናገራሉ። እንደሳቸው ታድያ ይሄ በዓል በ10ኛው በዙል ሂጃህ ወር ላይ የሚከናወን ነው። መስዋዕት እንዲቀርብ የሚያዝ ሲሆን በዕለቱ ሁለት ተግባራት ይከናወናሉ። እነዚህም ሐይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ኩነቶች ናቸው።
ሐይማኖታዊ ኩነቱ በመግቢያችን እንዳጫወቱን የበዓሉ ዕለት በማለዳ ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ ሰላት የሚሰገድበት መሆኑንን ያስታውሳሉ። እንደ ዑስታዝ መሐመድ ገለፃ ታድያ ይሄ የሰላት ስግደት ተጠናቅቆ ሕዝበ ሙስሊሙ ወደየቤቱ በሚመለስበት ጊዜ ሌላ ሐይማኖታዊ ተግባር የተላበሰ ማኅበራዊ ክዋኔ ያካሂዳል።
ሥራ አስፈፃሚው ዑስታዝ መሐመድ እንደሚሉት የመጀመሪያው የእርድ ሥነሥርዓት ማከናወን ነው ። ኢዳል አደሃ (አረፋ) የራሱ የሆነ ሐይማኖታዊ ታሪክ አለው። ሂደቱ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ዝግጅት ከደረጉበት ሂደት ጋር በብርቱ ይሰናሰላል። ሆኖም ለመስዋዕት ካዘጋጁ በኋላ አላህ ታዛዥነታቸውን (ተገዥነታቸውን) አስተውሎ ሙክት በግ ያቀረበላቸው መሆኑን እና ሊሰውለት በአዘጋጁት ልጃቸው እስማኤል ምትክም ይሄንኑ ሙክት በግ ማረዳቸውን የሚያስታውስ ነው። በዚህም የአረፋ በዓል የመስዋዕት በዓል ተብሎም እንደሚከበር ዑስታዝ መሐመድ ይናገራሉ።
እንደሳቸው ታድያ ሕዝበ ሙስሊሙ በዚህ የሐይማኖት አስተምህሮ መሰረት በሬም ሆነ በግ ቢያርድ የሚያካፍልበት እራሱን የቻለ የሕዝበ ሙስሊሙን ማኅበራዊ እና እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕላዊ መስተጋብር የበለጠ የሚያጠናክርበት ሥነ ሥርዓት አለ። ለምሳሌ፦ የሚያርደው በግ ቢሆን ያረደውን በግ ለሦስት እንዲከፍለው ነብዩ መሐመድ አስተምህሮ ሰጥተዋል። ለሦስት ከተከፈለው በግ አንደኛውን ክፍል ለቤተሰቦቹ ሊያደርገው ይችላል። ሁለተኛውን ክፍል ደግሞ ይሄን እርድ ማረድ ለማይችሉ ለጎረቤቶቹ አካላት ያቀርባል። ቀሪውን ሦስተኛ ክፍል ለሌላው ቀጣይ የበዓል ቀናቶች ሊያስቀምጥ ይችላል። በዚህ ዓይነት መልኩ የእርድ ሥነሥርዓቱ እንዲከወን ነብዩ መሐመድ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። እርድ ማረድ አቅሙ ያለው ሙስሊም ሁሉ የእርድ ሥነ-ሥርዓቱን እርድ ማረድ ላልቻሉ ለሌሎቹ የእምነቱ ተከታይ ደሀ ወገኖች በዚህ ዓይነት መልኩ በማካፈል ነው የሚከውነው።
የአረፋ በዓል «አድሃ » የተባለው ከብት እርድ መስዋዕት የሚቀርብበት መሆኑን ያነሳሉ። መነሻ ምክንያቱም ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ መስዋዕት ፍፁም ከመዘጋጀታቸው እና አላህ ይሄንኑ ለእሱ ያላቸውን ጽኑ ፍቅርና ታዛዥነት ተመልክቶ ቢላዋውን ልጃቸው እስማኤል አንገት ላይ ሲያሳርፉ የሚሰውት ሙክት በግ አቅርቦላቸው በምትኩ በጉን ከማረዳቸው ጋር ይያያዛል። በዓሉ ብዙ አንደምታዎችን የያዙ ሰዋዊም፤ ማኅበራዊም ተጨባጭ ኩነቶች አሉት። ለምሳሌ፦ ሀብታምና ደሃ የሚተያዩበት ጊዜ ነው። ሀብታሙ ደሀውን አብዝቶ ይጎበኘዋል። እነዚህም የመተያየት ሁኔታ በሌሎች ወራቶች ማዳበር እንዳለባቸው ዑስታዝ መሐመድ ይመክራሉ።
ነብዩ መሐመድ ስለዚሁ ደንግገው የሄዱበት እስላማዊ ሕግ ስለመኖሩ ያነሳሉ። ካካበተው ሀብት በበዓሉ የሚያከናውነውን እርድ ጨምሮ አንድ ሦስተኛውን ለደሆች፤ ለሰደቃ፤ለዘካ ማውጣት እንዳለበት አዝዘዋል ባይ ናቸው። “ከበዓሉ በፊት የሚያደርጉትን አምልኮ ሙሉ ተቀባይ የሚያደርገው ይሄው ማኅበራዊ መስተጋብር ያለውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ መወጣት ነው”ይላሉ።
ዑስታዝ መሐመድ በምሳሌ አስደግፈው እንደሚናገሩት ሀብታሞች በየትኛውም የኢዳቸው ፍፃሜ (በሁለቱም ኢዶች) ከረመዳን ጾም ፍች በኋላም ሆነ ከሀጂ ሥነሥርዓት በኋላ እንዲሁም የአረፋ በዓል ላይ ሊፈጽሙት የሚገባ ሐይማኖታዊ አስተምህሮ ያለው ግዴታዊ ትዕዛዝ አለ። ትዕዛዙ የዕለት ጉርሳቸውን ከመሸፈን ጀምሮ ብዙ ሀብት በማፍራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱትን የእምነቱን ተከታዮች ሁሉ ይመለከታል። ሀብታም የሆኑ ሙስሊሞች በአካባቢያቸው ያሉ እና የበዓሉን ቀን ማሳለፍ የማይችሉ ሙስሊሞችን ማየት ግዳቸው ነው። በነዚህ በዓላት ጊዜ እነዚህን ደሆች ማየትና መጎብኘት ለሀብታሙ ሙስሊም የሕብረተሰብ ክፍል ከበዓሉ በፊት ያደረገውን አምልኮ ሙሉ ተቀባይ የሚያደርገው ከመሆኑ ባሻገር በደሀውና በሀብታሙ ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን የሀብት ክፍተት በመሙላት ከፍተኛ ማኅበራዊ መስተጋብር ይፈጥራል።
ደሃው ሀብታሙን እንዲወደው ወይም ለሀብታሙ ፍቅር እንዲኖረው፤ ከፈጣሪው በታችም እንዲያመሰግነውና ለደህንነቱም ዱአ እንዲያደርግለት ያደርጋል። የእርስ በርስ መረዳዳት እና መተሳሰብንም ያዳብራል። እርስ በርስም ይከባበራል። እንዳይናናቅ፤ ምቀኝነት እንዳይኖር ሌሎች ለማኅበራዊ ግንኙነት፤ ለሠላም እና በአንድነት አብሮ ለመኖር ብሎም ለሀገር እድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን እንደሚያስወግድም ያስረዳሉ። በዛን ሰዓት ሁሉም ሕዝበ ሙስሊም የሚያወጣው እና ለችግረኞች የሚሰጠው እንዲኖር ነብዩ መሐመድ ደንግገው የሄዱትም ይሄንኑ የማኅበራዊ ግንኙነትን የበለጠ የሚያጎለብት እሴት ታሳቢ አድርገው መሆኑን ዑስታዝ መሐመድ ይናገራሉ።
በተለይ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ የነብዩ መሐመድን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ እርድ ማቅረብ የማይችሉ ጎረቤቶችን መጎብኘት ትልቅ አስተዋጾ አለው። በሐይማኖቱ አስተምህሮ በግዴታነት የተቀመጠ በመሆኑም መፈፀም አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባሉ። ይሄ ሐይማኖታዊ አስተምህሮ የሚያስቀምጠው፤ የማኅበረሰቡን የእርስ በርስ ማኅበራዊ መስተጋብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት አብዝቶ መገንዘብ እንደሚገባው ያብራራሉ።
ይሄም በራሱ አካባቢን፤ ማኅበረሰብን፤ ሀገርን ሊጠብቅ የሚችል ትልቅ የማኅበረሰብ እሴት ስለመሆኑ ሐይማኖታዊ አስተምህሮው መጠቆሙንም ያነሳሉ። ሐይማኖታዊ አስተምህሮው የእርስ በርስ ትስስርን ሊፈጥር የሚችልበትን ሁኔ ታ ያስተምራል።
ኡስታዝ መሐመድ እንደሚናገሩት፤ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በእምነቱ እርስ በርሱ የሚተባበርበትና የሚለይበት ቢኖርም በባሕል፤ በቋንቋ፤ በአመጋገብ፤ በአለባበስ ሥርዓት ከሌሎች ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የሚጋራው እጅግ በጣም ደስ የሚሉ መስተጋብሮች አሉት።
እርዱን የሚመለከታቸውን በመጎብኘት ተደስተው እንዲያሳልፉ ማድረግ እንዳለ ሆኖ እስልምና የማንኛውም ማኅበረሰብ የአመጋገብ እና የአለባበስ ሥነሥርዓቱ በቀጥታ ከሸሪያው ጋር አስካልተጋጨ ድረስ ያስኬዳል። በበዓሉ ዕለት ኢትዮጵያ የብዙ ባሕል ባለቤት እንደመሆኗ መጠን በከተማ እንዲሁም በሰሜኑ ክፍል ቀይ እና አልጫ ወጥ ተሰርቶ፤ እንጀራና ዳቦው ተጋግሮ፤ ክትፎው በየዓይነቱ የሚቀርብበት ሁኔታ አለ።
በበዓሉ ዕለት ጎረቤት ከጎረቤቱ፤ዘመድ ከዘመዱ ጋር ይጠያየቃል። በጋራ ይበላል፤ ይጠጣል። አላህን የማመስገን ፤ ከፍ የማድረግ ሂደቱም ከዚሁ ጎን ለጎን አብሮ ይተገበራል። የአረፋ በዓል ቀናቶች አብሮ የመብላት፤የመጠጣት እና አላህን ከፍ የማድረግና የማስታወስ ቀናቶች ናቸው።
“ኢ ስንመለከት አንድ ቀን ይውላል፤ ቀጥሎ ያለው ቀን የሚፈልግ የሚጾምበት ነው። ያቺ ቀን ካለፈች በኋላ ያለው የበዓሉ ቀን አልፏል ማለት ነው” ይላሉም ዑስታዝ መሐመድ። እንደእሳቸው የኢዳል አደሃ ወይም የአረፋ በዓል ግን አራት ቀን ነው የሚከበረው። የመጀመሪያው ቀን የአረፋ በዓል የሚባለው 10ኛው ቀን ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ የየራሳቸው ስያሜ ያላቸው ሦስት ተከታታይ ቀናቶች አሉ። እነዚህ ቀናቶች በገጠር በከተማ ያለው የአኗኗር እና የአመጋገብ ሥነሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ምንም ዓይነት የአኗኗር ደረጃ ሳይገድበን በጋራ የምንጠጣበት፤ የምንበላበት፤ ዘመድን የምንጎበኝበት፤ በአጠቃላይም የእርስ በርስ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን የምናጠናክርበት ነው። ዘንድሮም በዓሉን በዚሁ መልኩ አክብሮ ማለፍ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። መልካም የአረፋ በዓል ለመላው የእምነቱ ቤተሰቦች !
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም