ጠዋት ማታ በጭንቀት ስትብሰለሰል የከረመችው ወይዘሮ አሁንም ማሰብ መተከዟ አልቀረም። ካረፈችበት መጠለያ እንደመሰሎቿ ተኝታ መነሳትን ለምዳለች። ይህ ብቻ ግን እፎይታ ሰጥቷት አያውቅም። ሁሌም ከዛሬ ባሻገር የሚመጣው ነገ ሕልም መስሎ ይታያታል።
በየቀኑ ልቧ ስለነገ መልካምነት ሳይነግራት አይውልም። ያም ሆኖ ውስጠቷ እረፍት የለውም። በነገ ውስጥ ያለው ዕድል ዕውን ሆኖ እስክታየው ለራሷ ፊት አትሰጥም። ሁሌም በመሆን አለመሆን ውስጥ እንደሆነች ቀኑ መሽቶ ይነጋል ። ወጣቷ ወይዘሮ እንዲህ እየተጨነቀች አራት ልጇቿንና ባለቤቷን ደጋግማ ታስባለች።
ባለቤቷ ለፍቶ አዳሪ ባተሌ ነው። ልጆቿ ደግሞ ለዓይን የሚያሳሱ እንቦቃቅላዎች። እሷ ለነዚህ ዓለሞቿ የዓመታትን ዋጋ ከፍላለች። ሁሌም ሰላም አድረው መነሳታቸው የተለየ ትርጉም ይሰጣታል። የእነሱ ቤት ዕንቅልፍ ደግሞ እንደሌሎቹ አይደለም። ስጋት እንደሞላው፣ ፍርሃት እንደሸበበው ሌሊቱ በጭንቅ ይነጋል።
እስከዛሬ የት እንደነበረች ፈጽሞ አትዘነጋም። ከባድ ክረምቶችና የጭንቅ ሌሊቶች እንደዋዛ አልፈዋል። አስራ አምስት ዓመታትን በትዳር ስትኖር ሕይወቷ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በመኖሪያ ቤት ችግር ብዙ ተፈትናለች፣ ልጆች በማሳደግ፣ ስድስት ቤተሰብን በወጉ ይዞ መምራት ቀላል አልነበረም። ጥቂት የማይባሉ ፈተናዎችን፣ ሸካራማ የሕይወት መንገዶችን በጽናት መሻገር ግድ ነበር።
ወይዘሮ ዳግማዊት ተስፋዬ ያለፈችውን ጠመዝማዛ መንገድ እያስታወሰች ከዛሬ ባሻገር ስለሚመጣው አዲስ ነገ ታስባለች። አዎ! ነገ ከትናንትናው የበለጠ መልካም እንደሆነ ልቧ ሹክ ይላታል። ነገ ብሩህ ተስፋ ይዞ ብቅ እንደሚል ውስጠቷ ይነግራታል። ያም ሆኖ ቀኑ ደርሶ በአይኗ እስክታየው ራሷን አታምንም። ጥርጣሬና ስጋት እየተመላለሱ ይፈትኗታል።
ዳግማዊት እስከዛሬ የቤት እመቤት ነበረች። ባለቤቷ ሰርቶ በሚያመጣው ገቢ እሷንና ቤተሰቦቿን የምታስተዳድር ወይዘሮ። አሁን ደግሞ ውላ የምትገባበት የስራ ዕድል በእጇ ሆኗል። ይህ ዕድል ነገ ከምትናፍቀው ቀን ጋር የተቸራት ስጦታ መሆኑን ታውቀዋለች። ያም ሆኖ ውስጧ በጥርጣሬ እንደተሞላ ቀኑ መሽቶ ይነጋል።
ዳግማዊት ይህን ማሰቧ ያለምክንያት እንዳልሆነ ለራሷ ትነግራዋለች። ማግኘት እንዳለ ሁሉ ከእጅ የገባ ዕድልን መነጠቅ እንደሚኖር ከሕይወት ተምራለች። አሁን የምትጠብቀው ተስፋ ፈልጓት እንጂ ፈልጋ አላገኘችውም። እንዲህ መሆኑ ስጋቷን እየጨመረ ዕንቅልፍ ይነሳት ከያዘ ቀናት ተቆጥረዋል። እሷንና ቤተሰቦቿን ሰብስቦ ከያዘው ጊዜያዊ መጠለያ ወጥታ እስክትመለስ ጆሮዎቿ ክፉ ዜና እንዳያሰሟት ፈጣሪዋን ትማጸናለች።
ከዓመታት በፊት …
ጥንዶቹ ትዳር መስርተው ጎጆን ለማቅናት መነሻ ምክንያታቸው ጽኑ ፍቅር ነበር። ፍቅር ያጸናው ጥምረት ከቁም ነገር ደርሶ አብሮነቱ ሲሰምር በአንድ ጣራ ይኖሩ ዘንድ ግድ ሆነ። ትዳር እንደቃሉ ማነስ ቀላል አይደለም። ሶስት ጉልቻ ጠንቶ ቁምነገር ሲታሰብ ልጆች መወለዳቸው፣ ቤተሰብ መበራከቱ አይቀሬ ይሆናል።
ይህን ተከትሎ የሚመጣ የኑሮ ለውጥም ማንነትን ሊፈትን፣ ከባድ ሀላፊነትን ሊያሸክም የግድ ነው። በወይዘሮዋና በባለቤቷ ሕይወት የሆነውም እንዲሁ ነው። አዲሱ ጎጆ በልጆች በረከት አማረ። ቤታቸው በህጻናት ለቅሶና ሳቅ ደመቀ። ይህ ብቻ ግን ኑሯቸውን ሞልቶ እፎይታን አልሰጠም። በዓመታት ልዩነት የተወለዱ አራት ልጆች ምቹ መኖሪያ፣ የተሻለ ማረፊያ ያስፈልጋቸዋል።
በወቅቱ ወላጆች ይህን አላጡትም። ልጆቻቸው የተሻለው ሁሉ ይገባቸዋል። ያም ሆኖ ካሰቡት የሚያደርስ በቂ ገቢ የለም። ባለቤቷ በጋራዥ ጥቂት መኪኖችን ይጠግናል። ወይዘሮዋ የአባዋራዋን እጅ የምትጠብቅ የቤት እመቤት ነች። ልጆች የመንከባከብ ፣ቤት ጓዳዋን የመምራት ጫናው ለእሷ ተጥሏል። ጥንዶቹ ስለመኖሪያ ቤት ይበጃል ያሉትን ወሰኑ። ኑሮ ሕይወታቸው በአንዳቸው ቤተሰብ ግቢ እንዲሆን ተስማሙ።
ትዳርና ፈተናው
እንደታሰበው ሆኖ ሕይወት በቤተሰብ ግቢ ‹‹ ሀ…›› ብሎ ጀመረ። ባልና ሚስት ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ማድቤቱን ቤት አድርገው መኖርን ቀጠሉ። በኪራይ ቤት ልጆች ከስቃይ መዳናቸው መልካም ሆነ። ውሎ አድሮ ዓመታት ከነችግራቸው እንደዋዛ ነጎዱ።
ልጆች ሲጨመሩ፣ ኑሮ ሲወደድ፣ ነገሮች በነበሩበት አልዘለቁም። ዓመል ተለወጠ፤ የቀድሞ ፍቅር ቀዘቀዘ። እግር ከእግር እንደሚጋጭ ሁሉ ሀሳብ ከሀሳብ ተቃረነ። ዛሬ እንደትናንቱ አልሆነም። ለሚመጣው ነገ አብሮነት ሻክሮ ፍቅር ተፈተነ።
በቤተሰብ ግቢ የተጀመረው ሕይወት ከዚህ እውነታ አልራቀም። እንዲህ መሆኑ የ‹‹እኔ›› ይሉት ቤት ለሌላቸው ጥንዶች ከማንም በላይ ሆድ ያስብሳል። ሌት ተቀን በሀሳብ ያስተክዛል። ስለልጆች ዕጣ ፈንታ፣ ስለነገው የሕይወት መንገድ ከልብ ያስጨንቃል።
አንዳንዴ ሕይወት ሁኔታዎችን እንዳላየ፣ እንዳልሰማ፣ ማለፍን ታስተምራለች። አንዳንዴ ደግሞ ለሰላም ሲባል ሁሉን ትቶ ፣ በራስ ላይ መፍረድን ታሳያለች። የነዳግማዊት የመጨረሻ ውሳኔም በአንደኛው ላይ ሆነ። ለሰላም ሲባል ሁሉን መተው።
አሻጋሪው ቶማስ …
የዳግማዊት ባለቤት የጋራዥ ባለሙያ ነው። እጆቹ አሮጌን ይጠግናሉ። መኪኖች ፈተው ይገጥማሉ። ይህን የሚያውቁ አንዳንዶች ፈልገው ያገኙታል። ሙያውን የሚሹም ካለበት ይደርሳሉ። ከምንም በላይ ግን ስለእሱ የሚጨነቅ አንድ ሰው ስለስራው አጥብቆ ያስባል። ቋሚ ቦታ ያለማግኘቱ ያሳስበዋል። የባልንጀራው የቤት ችግር ያስጨንቀዋል፣
አንድ ቀን ቅን አሳቢው ቶማስ ሁሉን አመቻችቶ ባልንጀራውን አስገረመ። እሱ ከሚኖርበት የቀበሌ ቤት ግርጌ ጠጋ ብሎ እንዲሰራ ቦታ ጠቆመው። የጨለማ ብርሃን በሆነው ሰው ምሪት ደጁ የደረሰው ባለሙያ ከቀናት በኋላ ሙሉ ስራውን ጀመረ። ውሎው በቋሚነት ያለእንግልት መሆኑ ውጤታማ አደረገው። እሱን ተከትለው ባለቤቱ ዳግማዊትና አራት ልጆቹ ስፍራውን ተቀላቀሉ። አመጣጣቸው ሊጠይቁት አልያም ሊጎበኙት፣ አልነበረም። እንደ ሙሴ የሚያሻግራቸው ቶማስ ለመኖሪያቸው መፍትሄ በማምጣቱ እንጂ።
በወቅቱ የተገኘው መኖሪያ የኪራይ አልያም የቀበሌ ቤት አልነበረም። የቤተሰቡ ብቸኛ አማራጭ በስፍራው የላስቲክ ቤት ወጥሮ መስራት ብቻ ነው። ዳግማዊትና ባለቤቷ አራት ልጆቻቸውን ይዘው በአዲሱ የላስቲክ ጎጆ ኑሮን ጀመሩ። አካባቢው ከስራ ቦታ ባለፈ ሌሎች ሰዎች ጭምር ላስቲክ ከሸራ ወጥረው ይኖሩበታል።
ኑሮ በላስቲክ ቤት…
በእነዚህ ቤቶች ያሉ በርካታ ቤተሰቦች፣ ችግር ከመከራ ይገፋሉ፣ ደስታና ሳቅን ይጋራሉ። ስጋት ፍርሃትን ይቀባበላሉ። በቤቶቹ ያሉ ነፍሶች በአብዛኛው በቂ ዕንቅልፍ ይሉትን አያውቁም። ሁሌም ከሰውና ከተፈጥሮ አደጋዎች ራሳቸውን ለመታደግ በተጠንቅቅ ቆመው ያድራሉ። ዳግማዊትና ቤተሰቦቿ ይህ አይነቱን የላስቲክ ቤት ሕይወት በየቀኑ ይኖሩታል። ቤታቸው ያረፈበት ቦታ ቀድሞ የጣሊያኖች እንደነበር ይነገርለታል። ይህ በሰፈረ ልደታ ወረዳ ዘጠኝ ክልል የሚገኝ ስፍራ ለዓመታት ታጥሮ የቆየና የማንንም እይታ ያልሳበ ነው። አሁን ግን ነባሮቹን አሮጌ ቤቶች ባጀቡ ጥቂት የላስቲክ ጎጆዎች ደምቆ ይውላል። እንዲያም ሆኖ ለኑሮ ፍጹም አመቺ አይደለም።
የክረምቱ ዶፍና ጎርፍ፣ የሌሊቱ ብርድና ቆፈን፣ የንፋስ ፀሀዩ ግለት ሁሉ በቤቶቹ ላሉ ነፍሶች የየዕለት ሰቀቀን ነው። ምናልባት ድንገቴ እሳት ቢነሳ ይሉት ስጋትም የሁሉም ነዋሪ የጋራ ፍርሃት እንደሆነ ዘልቋል።
ዳግማዊት ለአራት የደረሱ ተማሪ ልጆቿ በዕድሜያቸው የሚያስፈልገውን ታውቃለች፡፤ በየቀኑ ከእኩዮቻቸው ጋር የሚኖር ፉክክር አይጠፋትም። እሷ እንደ እናት ያሰበችውን፣ ካሰቡት ብትሞላ ትወዳለች። ይህ እንዳይሆን ብዙ ብዙ ጎዶሎዎች ይቀድሟታል። የቤት ፍላጎት፣ የኑሮ ጫና፣ የትምህርት ወጪና ሌላም።
በላስቲኳ ጎጆ ቤተሰቡ በአንድ ተኝቶ፣ በእኩል ይነሳል። እንግዳ፣ ዘመድ ወዳጅ የሚያርፍበት ሌላ ክፍል አይታሰብም። ምግብ ለማብሰል፣ አቅርቦ ለመጉረስ፣ ታሞ ለመተኛት መልከ ብዙ የምትሆነው ጠባቧ የላስቲክ ቤት ነች። ‹‹ኑሮ ካሉት›› እንዲሉ ሆኖ ቤተሰቡ አያልፉ ይመስሉ ችግሮች እንደዋዛ ተሻግሯል።
ሁሌም በወይዘሮዋ ቤተሰብ፣ በጠባቧ ጎጆ ፍቅር ነግሶ ያድራል። አባወራው ለሚስቱ፣ ልጆች – ለእህት ወንድሞቻቸው መተሳሰብን አስተምረዋል። እስከዛሬ በዚህች ቤት ሳቅና ደስታ ሲመረት ቆይቷል። እንዲህ በመሆኑ አስፈሪ የጨለማ ጊዚያት፣ ነጎድጓዳማ የክረምት ወራት፣ ቀዝቃዛዎቹ የውድቅት ሌሊቶች ድል ተነስተዋል።
በመንደሩ እነሱን መሰል ጥቂት ቤቶች ተመሳሳይ ችግርን ይጋራሉ። በነዋሪዎች ዘንድ የጉርብትናው ትርጉም ከሌሎች ዓለም ይለያል። ሁሉም ስሜታቸው አንድ ነው፣ ክፉ ቀናትን፣ የደስታ ጊዚያትን፣ በእኩል ተሻግረዋል። ጨለማውን፣ ያውቁታል። የችግርን ጥግ እስከጫፍ ተጉዘውታል። ሀዘንና ደስታ፣ ይሏቸው እውነቶች ለእነሱ ትርጉማቸው ልዩ ነው። አንዳንዴ እንደሰው ይጋጫሉ፣ ይኳረፋሉ። ጠብ ቅያሜቸው ግን ስር አይሰድም። ተመልሰው እንደቀድሞው ሊሆኑ ሕይወት ግድ ይላቸዋል። ባሉበት፣ ኑሯቸውን ባዋቀሩበት ጎስቋላ መንደር ነገ ማለት ለእነሱ በ‹‹ይሆናል›› የሚናፍቁት ተስፋ ነው።
የድንገት እንግዳ…
ከዕለታት በአንዱ ቀን በነዳግማዊት የላስቲክ መንደር የደረሱ እንግዶች በድንገት አካባቢውን ተዟዙረው ይጎበኙ ያዙ። ከዚህ በፊት እነሱን መሰል ፀጉረ ልውጦች በስፍራው ታይተው አያውቁም። ነዋሪው የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ ሌሎችን ባየ ጊዜ ስሜቱ ተከፈለ፣ ውስጡ በጉራማይሌ ሀሳብ ታመሰ፤ አንዳንዱ አሻግሮ በጎውን ተመኘ፣ ሌላው ደግሞ የሚባለውን ሊያደምጥ ራሱን አዘጋጀ።
አዲስ አበባ በርካታ ነዋሪዎቿ በቤት እጦት ይፈተናሉ። አብዛኞቹ ከከተማ ርቀው ጎጆ ይቀልሳሉ። የበርካቶቹ መኖሪያ በህገወጥነት ተፈርጆ ጎጇቸው ይፈርሳል፣ ኑሯቸው ይበተናል። እነዳግማዊትን የመሰሉት ደግሞ በመሀል ከተማ ኑሮን ለማሸነፍ በላስቲክ ቤት ሕይወትን ይገፋሉ። አሁን እንግዶቹ ያዩትን አይተው ከስፍራው ሄደዋል። ከጉብኝቱ በኋላም አካባቢው እንዲፈርስ መወሰኑ ተሰምቷል። ይሄኔ ነዋሪዎቹ በድንጋጤ ይይዙትን አጡ። ቤቶቹ ማለት ለእነሱ መኖሪያዎች ብቻ አይደሉም፣ የዕለት ገቢያቸውን የሚያፈሩበት እንጀራቸው ጭምር እንጂ።
አጋጣሚ ሆነና በመንደሩ ነዋሪ ዘንድ መልካም ተስፋ ፈነጠቀ። የጉብኝቱ ውጤት ቤትን በማፍረስ ብቻ አልተወሰነም። አካባቢው በዘመናዊ ቤቶች እንዲተኩ ተወስኗል። ለጎስቋላ ቤቶቹ ነዋሪዎች በድንገት ይህን እውነት መስማት በቀላሉ የሚታመን አልሆነም። አስደንጋጩ የምስራች ዕንባና ሳቅ በወረሰው ስሜት ሲቀባበል ከረመ።
አይቀሬው ጭንቀት
አሁን ዳግማዊት እነዛ ፈታኝ የመከራ ጊዚያት እንደክረምቱ ዝናብ ሊያልፉ እንደሆነ አውቃለች። ከሰማይ እንደወረደ መና የመጣላትን ድንቅ ስጦታ ግን አምና መቀበል ተስኗታል። አሁንም ፈልጋው ሳይሆን ፈልጓት በመጣው አስገራሚ ዕድል እየተገረመች ነው። እንዲህ መሆኑ በብዙዎች ሕይወት አልተለመደም። እሷም ፍርሀትና ጥርጣሬ እየፈተኗት ነው። ቤቶቹ ተገንብተው እስኪጠናቀቁ ነዋሪዎቹ በተዘጋጀላቸው መጠለያ እንዲቆዩ ሆኗል።
ዳግማዊት ግን ጭንቀቷ በርትቷል። የቤተሰቧ ህልውና የቆመው በባለቤቷ ገቢ መሆኑን ታውቃለች። አሁን ቤቱ አስኪገነባ፣ የእሱ ስራ ሊቆም ነው። ስድስት ቤተሰብ ምን ይበላል? ኑሮና ሕይወትስ እንዴት ይቀጥላል? እነዚህ ጥያቄዎች ለወይዘሮዋ በእጅጉ አስጨናቂ ናቸው።
ጊዜያዊው መጠለያው ይሰጣል የተባለውን ቤት የሚተካ ባይመስላት ወይዘሮዋ ጠዋት ማታ ጭንቀቷ አይሏል። እስካሁን እንደምታውቀው ቤትን ያህል ወሳኝ ጉዳይ በቀላሉ አይገኝም። ብዙዎች ስለቤት ሲሉ ዓመታትን ተግተዋል። ሁሉም ግን የሀሳባቸው አይሞላም። እሷና መሰሎቿ ደግሞ በድንገት ቤት ‹‹ይሰራላችሁ›› ተብለዋል። ዳግማዊት ሁሉን እያየች የሚሆነውን አላመነችም። ነገ ደርሶ የተባለው ዕውን እስኪሆን በጥርጣሬ ዋተተች።
የመጠለያው ኑሮ ቀጥሏል። የአዲስ ቤቶቹ ግንባታም እንዲሁ። ዳግማዊት ግን እንደሌሎች በስፍራው ዝር አላለችም። ‹‹ካልታዘልኩ አላምንም›› እንዳለችው ሙሽራ የተባለው ተስፋ ከእሷ ደርሶ እስክታየው በዝምታ ከረመች።
ደማቋ ቀን…
እነሆ! የጭንቅ ቀናት ታለፉ። የሀሳብ ጊዚያት ተረሱ። ክረምት አልፎ መስከረም እንዲመጣ ጨለማው ጠፍቶ ብርሃን ፈነጠቀ። አሁን ስጋት ተወግዷል። ‹‹የት እደርስ›› ይሉት ሀሳብ፣ ታሪኩን ቀይሯል። የላስቲክ መንደሮቹ አጸድ በዘመናዊ ቤቶች አምሮ አካባቢው ተውቧል። ‹‹ይገባናል›› ሳይሉ ‹‹ይገባችኋል›› የተባሉት ነዋሪዎች ደስታቸው ወደር አጥቷል። ይህ ቀን ደርሶ፣ የተባለው ዕውን እስኪሆን የብዙዎች ጭንቀት ነበር። አሁን ግን ያለፈው ‹‹ነበር›› ሊባል ዕድል ከዕድለኞች ፊት ቀርባለች።
ለነዋሪዎች ቤቱን ተከትሎ መልካም አጋጣሚዎች ደርሰዋል። በአካባቢው የአዋቂዎች የምገባ ማዕከል ተገንብቷል፣ ለበርካታ ሙያዎች የሚሆኑ ሱቆች ተሰርተዋል። ዳግማዊትን ጨምሮ በምገባ ማዕከሉ የስራ ዕድል ያገኙ ጥቂቶች አይደሉም። አሁን በጌጃ ሰፈርና አካባቢው የቀድሞ ታሪኮች የሉም። በአዲሱ ቤት የእፎይታ ዕንቅልፍ ጀምሯል፣ ሁሉም ለመልካም ሕይወት፣ ለጠንካራ ስራ ዝግጁ ሆኗል። ቤቶቹ ሲመረቁ ከብርት ከንቲባ አዳነች አበቤ በስፍራው ተገኝተው ለነዋሪዎች ስጦታ አበርክተዋል።
ቤት -ለእምቦሳ
ዛሬ በአዲሱ የወይዘሮ ዳግማዊት መኖሪያ ቤት በእንግድነት ተገኝቻለሁ። መልከ መልካሟ ወይዘሮ በተለየ ፈገግታና አክብሮት ተቀብላ እያስተገደችኝ ነው። ከሰፊው የሳሎን ዕልፍኝ አረፍ ብዬ ቤቱን መቃኘት ጀመርኩ። ሁለት መኝታ ቤቶች፣ የማብሰያ ክፍልና ዘመናዊ መታጠቢያ ከመጸዳጃ ቤት ተሟልቶለታል። ከአዲሱ ቤት ጋር የስራ ዕድልን ያገኘችው ዳግማዊት ከውሎዋ መልስ የሆነውን ሁሉ እያወጋችኝ ጨዋታችን ቀጥሏል።
አሁን መላው ቤተሰብ ከስጋት ርቋል። ልጆች እንደእኩዮቻቸው በወጉ ይማራሉ። ዳግማዊት ዕንባዋ ታብሷል። ሕይወቷ ተቀይሯል፣ የሆነላትን ሁሉ ስታስብ ሁኔታዎች ከቃላት በላይ ሆነው መናገር ይሳናታል። ከምንም በላይ ባገኘቸው የስራ ዕድል አቅመ ደካሞችን መመገብ መቻሏ ደግሞ ለሕይወቷ ምላሽ ነው።
አመስግና አትረካም፣ የእሷና የመሰሎቿ ታሪክ ለሌሎች ወገኖች ጭምር ታላቅ ተስፋ እንደሚሆን ታምናለች። አዲሱን ዓመት በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ቤት ሆና ስትቀበለው ደስታዋ ወደር የለውም። እኛም ደማቅ ፈገግታዋን ተጋርተን፣ አዲስ ተስፋዋን ተመኝተን ቤቷን ‹‹ቤት ለእምቦሳ›› ብለናል።
‹‹መልካም አዲስ ዓመት››
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም