– ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በአ.አ.ዩ. ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ
የተወለዱት በቀድሞ ከምባታ አውራጃ በያያማ አካባቢ፣ ዘግሾ መንደር በ1943 ዓ.ም ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ከምባታ እንዲሁም በወላይታ ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ እና በአምቦ ጉደር የተማሩ ሲሆን፣ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋም ብቁ መሆናቸው ሲረጋገጥ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅንተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለመማር በቅተዋል – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ።
በዓባይ ግድ ጉዳይ ላቅ ያለ አስተዋጽዖ በማበርከት የሚታወቁት እንግዳችን ሁለት የማስተርስ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉዳይና በፖለቲካል ሳይንስ መስክ አሜሪካ ከሚገኘው ኦሐዩ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። የዶክትሬት ትምህርታቸውን በሲውዘርላድ ከሚገኘው ከታዋቂው ዙሪክ ዩኒቨርሲቲ በናይል ውሃ ጉዳይ በፖለቲካል ሳይንስ መስክ አጠናቀው የፊሎሶል ዶክተርነት ተቀብለዋል። ከትምህርታቸው ባሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መስክ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የፖለቲካል ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።
ዶክርተር ያዕቆብ፣ የፖለቲካ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር፣ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል። የአፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የውሃና ማሕበረሰብ ምርምር አባልና የኢትዮጵያ አስተባባሪ ናቸው። እንዲሁም የሰሜንና የደቡብ አህጉራዊ ምርምር የምስራቅ አፍሪካ ዘርፍ አማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነውም አገልግለዋል። የዋቸሞና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአመራር ቦርድ አባል እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ቦርድና የኢትዮጵያ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን አባል ናቸው።
ዶክተር ያዕቆብ ብዙ ናቸው ማለት ይቻላል፤ በኢትዮጵያ የጠፉ ወንዞችና የውሃ ሀብቶችን የመመለስ እንቅስቃሴ አስተባባሪም ናቸው። በብዙ ደርዘን የሚቆጠሩ ሙያ ነክ የምርምርና የስርጸት ጽሑፎችን አበርክተዋል። እንዲሁም በርካታ የሙያ ማጠናከሪያና ማስፋፊያ መጻሕፍትን ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ያበረከቱ ሲሆን፣ ‹‹ናይልና ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ደግሞ መጽሐፍ ማሳተም ችለዋል። በአፍሪካ፣ በኢስያ፣ በአውሮጳና በአሜሪካ ተዘዋውረው ትምህርታዊ ሌክቸር ሰጥተዋል። በድንበር ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ወንዞች የድርድር ጉዳይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪም ናቸው
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፓነል አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሕዳሴ ግድቡ ብሔራዊ የድርድር ቡድን አባል ናቸው። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ናቸው። የሰሯቸው ስራዎችና ያለባቸው ኃላፊነቶች ከብዙ በጥቂቱ ይህን የሚመስል ሲሆን፣ ለሰሯቸው ስራዎችና ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ከተበረከቱላቸው ሽልማቶች ጥቂቶቹ ደግም በጀርመን አገር የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ፒቴር ቤከር የ1999 የሰላም ምርምር ተሸላሚ፣ የ2012 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ፣ የ2013 ዓ.ም የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዱራሜ ካምፓስ ልዩ ተሸላሚ ናቸው። ሌላው አንድ ሽልማት ጀርመን ሜልበርግ ውስጥ ፊሊፕስ ዩኒቨርሲቲ የሚባል እርሳቸውና የጓደኛቸው በውሃ ላይ ባቀረቡት ጥናት ገንዘብም ያካተተ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰርተፍኬቶች፣ የምስጋና ደብዳቤዎች እና የምስክር ወረቀቶች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪም ተሰጥቷቸዋል። ከዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳችን›› ከዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር ያዕቆብ የእርስዎና የዓባይ ውሃ ቁርኝታችሁ ጥብቅ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህ ጉዳይ ለምን ያህል ጊዜ ጥናትና ምርምር አደረጉ?
ዶክተር ያዕቆብ፡-በናይል ወንዝ ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመርኩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል በ1972 ዓ.ም የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ ነው። ወቅቱ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ጦርነት ተጠናቆ ኢትዮጵያ ድል ያደረገችበት ጊዜ ቢሆንም የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ በወቅቱም ቢሆን ትኩሳት ያለበት ነበር።
በወቅቱ በርካታ አገሮች ከሶማሊያ ጎን ሆነው ኢትዮጵያን በመቃወም የሚታወቁ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ብዙ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ ስለነበር በተለይም ግብጽና ሱዳን በተለየ ሁኔታ ደግሞ ግብጽ ጫናዋ የበረታ ነበር። ግብጽና ሶማሊያ የአረብ ሊግ አባል በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማንኛውም ነገር በግብጽ በኩል ተደጋፊ በመሆኑም ጭምር ነው። ስለዚህም ይህ ጉዳይ በጂኦፖለቲካው ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ያመጣው ተጽዕኖ ከኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ጋር የተገናኘ መሆን አለመሆኑን በመጠየቅ ነበር የተነሳሁት። በተጨማሪም የግብጽና የሶማሊያ መቀራረብ በመሰረቱ ከውሃ ሀብታችን ጋር ባለን ሽኩቻ የተወሳሰበ መሆን አለመሆኑን ጠይቄም ነው የተነሳሁት። የመመረቂያ ጽሑፌንም የጻፍኩት በዚሁ ጉዳይ ላይ ነው። በናይል ፖለቲካ ላይ ትኩረት አድርጌ ስሰራ የቆየሁት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። ጉዳዩ በጥቅሉ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ያለው የሃይድሮ ፖለቲካ ጉዳይ፣ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የሃይድሮ ፖለቲካ ዋናው እምብርት የኢትዮጵያና የግብጽ ሽኩቻና የጥቅም ግጭት ላይ ያጠነጠነ ነው ማለት ይቻላል።
ሌሎች አገሮች ቀስ እያሉ እዛ ላይ መጥተዋል። ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኖርኩት ስለምስራቅ አፍሪካ ሃድሮ ፖለቲካ፣ ስለምስራቅ አፍሪካና ስለመካከለኛው ምስራቅ ሃይድሮ ፖለቲካ ምን አይነት እንደሆነ ስከታተል ነው። በክፍለ ትምህርቴ በኩል ኮርስ አዘጋጅቼ ሥርዓቱን ተከትዬ በዩኒቨርሲቲ አጸድቄ ተማሪዎቻንን ሳስተምር ቆይቻለሁ። ማስተማር ብቻ ሳይሆን በርካታ የማስተርስ ተማሪዎች ከኢትዮጵያም ከሌሎች አገሮችም እዚህ ማስተርስ የሚገቡ ተማሪዎች ሃይድሮ ፖለቲካ በተለይም ናይልን በተመለከተ ኮርስ ወስደዋል፤ ከኬንያም፣ ከዩጋንዳም እንዲሁም ከሲውዘርላንድ፣ ከፈረንሳይ፣ ከዴንማርክ፣ ከቻይና እንዲሁም ከእስራኤል መጥተው የተማሩ አሉ።
ከዚህ ከማስተምረው ኮርስ ጋር አንድ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳንና ከግብጽ ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ጋር በአንድ ላይ ለአንድ ሳምንት ያህል የፈጀ ሴሚናር አዘጋጅቼ አስተማሪዎቻውንም ጭምር እንዲከታተሉ አድርጌያለሁ። ይህ የዓባይ ግድብ ከመጀመሩ በፊት የሆነ ነው።
ሃሳቡ ምንድን ነው ያልሽኝ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆኑ የውሃ ተቀባዮች ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንንና ግብጽን በሚመለከት የጋራ ፍላጎትና ጥቅም ያለበት ገዳይ ስለሆነ ወጣት ተማሪዎች ደግሞ የነገ መሪዎች ስለሆኑ ይህንን ቢያውቁና እርስ በእርሳቸው ቢነጋገሩ መልካም ነው በሚል ነው ሴሚናሩ የተደረገው።
እንዲህ ሲባል ግን እኔ በናይል ጉዳይ ጀማሪ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉም ሆኑ ሌሎችም ከ1940ዎቹ ጀምሮ ያሰቡበትና የሰሩበት ብዙ ሰዎች አሉ። የእኔን ትንሽ ልዩ
የሚያደርገው በዚህ ጉዳይ ባለፉት 42 ዓመታት ያህል ዓመታት በተከታታይ በየደረጃው እያደገ እንዲሄድ ከምርምር፣ ከማስተማርና ከማስፋት በኋላም ፖሊሲ በመደገፍ እንዲሁም ወደ ድርድርና አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ አንዳች ክፍተት ሳይፈጠር እንዲሰራ መልካም ጥረት ማድረጌ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያሉ ነው ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያያዥነት ያለው ጥናት ማድረግ የጀመሩት፤ ከገቡበት በኋላ እንዴት አገኙት?
ዶክተር ያዕቆብ፡- በጣም ተደስቻለሁ። ሳስተምርም፣ ስመራመርም ሆነ በድርድሩ ውስጥም እንዲሁም በዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ላይ በአዘጋጅነትም ሆነ በተሳታፊነት ስንቀሳቀስ የምሰራው በጥልቅ የፍቅር ስሜት ነው። የዚህ መነሻ ምክንያት ደግሞ ይህ ትልቅ ብሔራዊ ሀብት ስለሆነ እና ይህን ሀብት ማንቀሳቀስ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ትልቁ በር ከፋች ስለሆነ ነው። በተጨማሪም በውሃ ሀብታችን የመስኖም ሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና ሌሎቹን የልማት አጀንዳዎች በኤሌክትሪክ ኃይል በማካሄድ ከድህነት እንደምትወጣ ስለማምንም ነው። በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካው መድረክም ጎልታ እንድትታይ ስለሚያደርጋትም ነው።
ኢትዮጵያ የዓባይ ብቻ ሳይሆን በርካታ ወንዞች አሏት። እነዚህ ወንዞች ከኢትዮጵያ ሆድ ውስጥ የሚወጡ ንጥር የአካሏ ክፋይ ናቸው። እነዚህ ወንዞች ደግሞ ወደ 93 በመቶ ከአገር ውስጥ ወጥተው ወደጎረቤት አገር የሚሄዱ ናቸው። አባይን ብቻ ሳይሆን ዋቤ ሸበሌን፣ አኮቦን፣ ባሮን፣ ተከዜን፣ ኦሞን፣ ግቤን፣ ገናሌን እና ሌሎቹንም ማልማት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በእነዚህ ወንዞች ልማት ጉዳይ ተማሪዎቻችንን ከስር ማሰልጠን የነገ መሪዎቻችንን እንደማሰልጠን ይቆጠራል። ዲፕሎማቶችንና ኤክስፐርቶችን ማሰልጠን ማለት ክርክራቸው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እንደማድረግ ይቆጠራል።
አጠቃላይ የምሰራቸው ስራዎች፣ በመጣጥፍ መልክ የሚቀርቡ ጽሑፎችም ሆኑ በኮንፍረንሶች ላይ የማቀርባቸው ሁሉ በዚሁ መስመር የሚሄዱ ናቸው። ለዚህም ነው እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርንም ሆነ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ለረጅም ጊዜ በውሃ ድርድርና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፖሊሲ የማማክረው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹን ጨምሮ ሌሎቻችን በአባይ ግድብ ላይ ያደረግናቸው ድርድሮች እውቀትና ብልሃት የተሞላበት አካሄድ ስለተከተሉ ውጤታማ መሆን ተችሏል እንጂ አፈሙዝ አሊያም ሻሙላ በመማዘዝ የተገኘ ስኬት የለም።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ የእርስዎ ተማሪዎች የነበሩ ዶክተር ያዕቆብ የአደባባይ ምሁር ናቸው ይላሉ፤ በዚህ ሃሳብ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔ በዚህ አይነት አባባል ራሴን አስቀምጬ አላውቅም። ነገር ግን ምንጊዜም የምስራውን ለተማሪዎቼም ሆነ ለኢትዮጵያውያን አካፍላለሁ። ሌላው ደግሞ ይህ ጉዳይ ሃሳብ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሃሳቡን እስከ ጫፍ ድረስ የመግፋትና የመመካከር አንዳንዴም ያ ሃሳብ እንዲጸናም ጭምር ስለሆነ ይህን የምሰራው በልበ ሙሉነት ነው። ስለዚህ በእርግጥ ከሱዳንና ከግብጽ አቻዎቼ ጋር አብረን እንጽፋለን፤ አብረን እናሳትማለን። የእነርሱም የእኛም ፍላጎት ሌላ መሆኑን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ክርክራችን አንድ ላይ ስለሚሄድ ሶስተኛው አንባቢ በአንድ ላይ ያነበዋል። ፈራጁ ሶስተኛ ወገን ሊሆን ይችላል በሚል ከእነርሱ ጋር በልበሙሉነት ስንሰራ ቆይተናል። ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሰዎች በዚህ አይነት መዝነውት ከሆነ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎ ስም ከግድብ ድርድር ጋር በተያያዘ ለብዙዎች ቅርብ ነው፤ ግድቡ ደግሞ ሊጠናቀቅ የቀረው ከሃያ በመቶ በታች ሆኗል፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያሰጋ ነገር አለ?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህም አድርገን ማሰብ አለብን፤ ሁልጊዜ የደረስንበትን ጉዳይ መጠየቅ አለብን። ከዚህ አንጻር ጥያቄው ጠቃሚ ነው። ከዚህ በኋላ የሚኖረው ተግዳሮት
ከመጣንበት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቀደም ሲል እኛ ሳንፈቅድላችሁ ግድቡን ልትሰሩት አትችሉም የሚል ነበር። ነገር ግን ግድቡ እናተን የማይጎዳ እኛን የሚጠቅም ግድብ ነው ስንላቸው ቆይተናል። ይሁንና ግድቡ ጥራት አይኖረውም፤ መሬቱም ልል ነው፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ጸባይም ይኖረዋል እያሉ ሲያስወሩ ነበር። ነገር ግን የእኛ ምሁራን እነርሱ ያሏቸው ስጋቶች እንደሌሉ ሲያስረዷቸው ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ግድቡን ለመስራት ልምድ የላችሁም ለሚሉት ደግሞ በግብጽ የተሰራው የአስዋን ግድብ የተሰራው በሶቪት ሕብረት ሰዎች ነው። በተመሳሳይ ሱዳን ውስጥም የተሰሩ ግድቦች በሌላ የሰው ኃይል የተሰሩ ናቸው። በኢትዮጵያ የተሰሩ ግን ኢትዮጵያ የሌሎችን ድጋፍ ጠይቃለች እንጂ ኢትዮጵያውያን በሚገባ ተሳትፈው የሰሯቸው ናቸው። ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ ግድብ ሲሰራ የዓባይ ግድብ የመጀመሪያው ሳይሆን ብዙ ግድብ ተሰርቷል። አንዱም የመፍረስ አደጋ አላጋጠመውም በሚል በየአጋጣሚው እናስረዳቸዋለን።
ቀጥሎ የነበረው የገንዘብ ተግዳሮት ነበር፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ተሳትፈውበት እዚህ አድርሰውታል። ሌላው ደግሞ ግድቡን ለመሙላት ግብጽ አልፈቀደችም፤ ጦሯን ልትመዝ ትችላለች ሲባል ነበር። የመጀመሪያው ነገር ግብጽ ጦር ልትመዝ አትችልም፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት። በዲፕሎማሲውም በኩል ግብጾች ያመጡት ጫና አሜሪካዎችን፣ ምዕራባውያኑንና አረቦችን ደጋፊ አድርገው መነሳታቸው ነው፤ ይሁንና የግድቡ አሰራርም ሆነ ዲዛይኑ ግልጽ ስለሆነ እና የሚመለከታቸውም አካላት ስላዩት ግድቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ግድቦች ምንም ልዩነት የሌለው ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም በዲፕሎማሲው በኩል ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሰነድ በግልጽ ስለታየ በዚሁ ተቋጭቷል። ይህ ማለት በግድቡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ ተግዳሮት የተሞላበት ነበር ማለት ይቻላል።
ይሁንና ይህ ሁሉ ታልፎ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል፤ ሁለተኛው ተርባይንም ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ስለሆነም ከዚህ በኋላ የቴክኒክ ተግዳሮት የሚያጋጥም አይመስለኝም፤ ከፍተኛ የመንግሥትም ትኩረት ያለበት ነው። ሱዳንም ግብጽም ውሃ አንሷቸው አያውቅም። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የሚኖርባት ተግዳሮት ይህን ግድብ ከመጨረስ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ተጨማሪ ሌሎች የውሃ ሀብቶችን እንዴት አድርገን እናልማ እና እንዴት ከድህነት እንውጣ የሚለው ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብን ለማጠናቀቅ ጫፍ ላይ ተደርሷል፤ በዚህ ውስጥ በጥናቱም፣ በማማከሩም ሆነ በድርድሩ የእርስዎ ሚና ከፍ ያለ ነውና በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎ የተደሰቱበት አሊያም ያዘኑበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፤ እኔ የግድቡ የመጀመሪያውን፣ ሁለተኛውንና ሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሊቶች በተከታታይ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁ በእጅጉ የተደሰትኩበት ጊዜ ነው። በምንም አይነት ሁኔታ ይህን ግድብ በጨለምተኝነት አይቼ አላውቅም። በተለይ ደግሞ የኃይል ማመንጫ በተኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተጭነው ኃይል እንዲያመነጭ ባደረጉበት ሰዓት ውስጤን የፈነቀለ ደስታ ተሰምቶኛል። በቦታው ሆኜም በአይኔ ያየሁት በመሆኑም ኩራት ተሰምቶኛል።
ያዘንኩበት ነገር ቢኖር ግድቡ ከአሁን በፊት ማለቅ ሲገባው ግድቡ ላይ ኃላፊነት፣ ገንዘብና ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ከቦርድ ሊቀመንበርነት እስከታች ድረስ የነበሩ ግድቡን እየሰራን ነው፣ የውሃ ሙሊቱን በዚህ ዓመት እንጀምራለን እያሉ እያታለሉ መቆየታቸው ነው፤ በተለይ የግድቡን ስራ ከስር እየገዘገዙ በመጨረሻም ግድቡ ሊወድቅ አፋፍ ላይ በደረሰበት ጊዜ በጣም ትልቅ ኀዘን ተሰምቶኝ ነበር። እንደዛ ሆኖ ቢቀር ኖሮ በጣም እንዳዘንኩ እቀር ነበር። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ክፉ ነገር ተሸንፏል፤ ክፉ የሰሩ ሰዎችም በተለያየ መንገድ ታርመዋል። ግድቡ ረጅም ጊዜ ቢወስድም የተቀመጠለትን ኢላማ ስለመታም የአሁን ደረጃው ላይ ደርሷል። በመሆኑ ኀዘኔም ተስተካክሏል።
አዲስ ዘመን፡- በአሜሪካ፣ በምዕራባውያኑም ሆነ በአረብ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ሲደረግ ከነበረው ጫና መካከል ልብዎን ያሳዘነ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- በእርግጥ ከፈረንጆቹ ጥሩ ነገር ጠብቄ አላውቅም፤ እነሱ የሚያስቡት ኢትዮጵያን በሌላ በምን አይነት ጥቅም እንለውጣት በሚል ነው እንጂ ታላቅነቷንና የሥልጣኔ ምንጭ የሆነች አገር መሆኗን አይደለም። ግብጽን መደገፋቸው ደግሞ ምንም አያስደንቀኝም። ምክንያቱም የግድቡን ዲፕሎማሲ የሚያሸንፈው በኢትዮጵያ በኩል ቁርጠኝነት ተይዞ ግድቡን ትከክለኛ እውቀት ላይ በመመስረት ሰርቶ መጨረስና ስራ ላይ ማዋል ነው።
ቀደም ሲልም ማን ወዳጅ ማን ጠላት የሚለው ጉዳይ በዓድዋም ሆነ በማይጨው ጊዜ የነበረ ነው። ስለዚህም ከፉ ቀን ሲያጋጥመን የሚያጋጥሙን ወዳጆች አሉ። ይህ ግን በእኛ ጥንካሬና በምናሳየው ትጋት እና ቁመና የተለካ እንጂ በመልካችንና በቁመታችን ስለወደዱን አይደለም።
አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያኑ ምኞታቸው ኢትዮጵያን አንካሳ ማድረግ ነበር። በተለይ የግብጽ ፍላጎት እንዲናኝና ራሳችንን የሚጎዳን ጉዳይ በገዛ ፈቃዳችን እንድንፈርም አድርገው አዘጋጅተው ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችና የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ድጋፍ ታክሎበት ጫና ያለበት ዲፕሎማሲ ከሽፎ ዛሬ ላይ ተደርሷል። በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መኩራት ያለብን ይመስለኛል። ምክንያቱም ይህ የተሰራው በአርበኝነትና በትጋት እንጂ በቅጥረኛ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ ግድቡን ከጀመረች ጀምሮ የተለያዩ ጫናዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ ተደጋጋሚ ጦርነት ደግሞ ከሕወሓት በኩል ሲነሳ ተስተውሏል፤ ለዚህም እርስ በእርስ መባላት ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?መፍትሔውስ?
ዶክተር ያዕቆብ፡-ይህ ጥያቄ በራሱ ብዙ የሚያነጋግርና ሰፊ የሆነ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ብዙዎች በተለያየ መንገድ ሃሳብ ይሰጡበታል። ስለዚህ በመጀመሪያ ማየት ያለብን ኢትዮጵያን ነው። ኢትዮጵያ በቅርብ የተፈጠረች አገር አይደለችም። ለረጅም ዘመን ስትገነባ የመጣች አገር ናት። ሕዝቧም በፍጹም የተዛመደና የተጋመደ ነው። በውስጥ የአንድነትና የሕብርነት መንፈስ የተላበሰ ሕዝብ ነው። አደጋ በአገርህ ላይ ደረሰ ሲባል ደግሞ መሪውን እንኳን ማን እንደሆነ በቅጡ የማያውቅ ሁሉ በነቂስ ወጥቶ የሚሰለፍ ነው።
ገዢ አገሮች ሌሎች አገሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በማስመሪያ እያሰመሩ ሲቀራጩ ኢትዮጵያ ግን አልተነካችም። ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከማን በልጣ ነው በሚል ብዙ ጦርነት ተካሂዶባታል። ነገር ግን አሸናፊ ነበረች። ያሸነፈችው ደግሞ ንጉሡና አዛዦቹ ብቻ ስለተዋጉ አይደለም። መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለተጋደለም ጭምር ነው። ገሚሱ ጦረኛ፣ ግማሹ ደጀን፣ ሌላውም ደጎም በጾም ጸሎቱም ጭምር ስለተባበረ ነው ኢትዮጵያን ከገዢዎች ማስመለጥ የተቻለው። ጣሊያን በአምስት ዓመት ውስጥ አገሪቱን በቅጡ እንኳ ሳያዳርስ ተባርሮ መውጣት የተገደደው በነበረው ትብብር ነው። የኢትዮጵያውያን ልብ ጠላት የማሸነፍና አገርን የማዳን መንፈስ የተሞላ ነው። ስለዚህም ነው የዓድዋ ድል በዓለም ላይ አንጸባራቂ ድል መሆን የቻለው። አሁንም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ገድላችን ተጽፎ አላለቀም ። በዚህ ጦርነት የተጋደሉ ጀግኖች ሁሉም ታውቀዋል ብዬ አላስብም። ይህ አይነት ልበ ሙሉነት በሶማሊያም ሆነ በባድመ ጦርነት የአንድነት መንፈስ በእጅጉ የታየበት ነው።
እንዲህ አይነት አገር በየቦታው በብሔረሰብ ስም ቢጠራ፣ የተለያየ አይነት ቋንቋ ቢናገር በዚህ ነው መተዳደር ያለበት በሚል ሲኬድበት ቆይቷል። ኢትዮጵያ በቢላዋ ተቆርጣ የጎሳ አገር ተድርጋና የጎሳ ሕግ ወጥቶ፣ የጎሳ አደረጃጀት ተፈጥሮ፣ የጎሳ አለቃ ተበጅቶ፣ የጎሳ ሚሊሻ ተዋቅሮ በአጠቃላይ በጎሳ ሰው ተከልሎና በሕገ መንግሥት ተቀርጾ ይህን ነገር ለማስተዳደር የተደረገበት ሙከራ አንደኛ አገር የሚያጠፋ፣ የሚያዳክም ነው። በአንድነቱ ከሚኮራበት እሴቱ የሚነጥልና ከሕብረቱ የሚያስተጓጉል ብሎም ሃሳቡ በግድ የተጫነበት በመሆኑ ይህ አደረጃጀት ውሎ አድሮ ዛሬ ላለንበት ግጭት ዳርጎናልና ይህ በጣም አሳዛኝ ነው።
ኢሕአዴግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እኛ እስከምናውቀው ድረስ የጎሳ ግጭት አንድም ጊዜ በርዶ አያውቅም። ወይ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ደቡብ፣ ሶማሌ ወይ ደግሞ ሌላው ቦታ ሲከሰት የቆየ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሰነዶች አሉ። አሁን ያለንበት ጦርነት ቁስሉ አመርቅዞ ካንሰር ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ነው። አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወረራ የሚባለው እና አልፎ ተርፎ የአገርን ሉዓላዊነት ሌት ተቀን የሚጠብቅ የአገር መከላከያ ሁሉ የተወጋበት ምክንያት በጎሳ አደረጃጀት ነው። የጎሳ አደረጃጀቱም ቢሆን ለአንተ ለጎሳ መሪው ትቼልሃለሁ የሚባል ሳይሆን በጎሳ ተደራጅና እኔ ከላይ ሆኜ እመራሃለሁ በሚል የተደረገ ነው። በጎሳ መሰረት የሕግ ረቂቅ ተበጅቶና ጸድቆ አገር ሰላሟ ይጠበቃል ማለት አያስደፍርም።
መፍቻው እዚህም እዚያም የሚሰማውን ግጭት አሊያም የሚነሳውን ጦርነት ማስተካከል ሳይሆን መሰረታዊ የሆነ የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ መንፈስን ማምጣት ነው። ኢትዮጵያዊ የትም ቦታ ቢሆን ኢትዮጵያዊ መሆኑን ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ አገር መሆኗን የሁሉም ሰው ትልቅነት መገለጫ ስለሆነ ኢትዮጵያን ወደቀድሞ አንድነቷ ማምጣትና መልሶ በዚህ መንፈስ መገንባት ተገቢ ይመስለኛል። የኢትዮጵያን ሕብርነት ማምጣት መፍትሔው ነው እላለሁ። ይህ የሕግ የበላይነትም ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ የኤ፣ቢ፣ሲ ወይ የዲ አገር ብቻ ሳትሆን የሕብረተሰብ አገር ናት። ይህ እንዳይሆን ሸብበው የያዙ በጎሳ የተመሰረተ ሕግጋቶችና አሰራሮች መሻር አለባቸው። ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ መለወጥ መቻል አለባቸው። ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያን የማፍረስ ባህሪ ያለው ነው። ስለዚህም ለዘመናት የተጋመዱ ኢትዮጵያውያን መፍረስ የለባቸውም። ሰው ከሰላሙ፣ ከከፍታው፣ ከክብሩ መውረድ ለምን ያስፈልገዋል። በተለይ በሕገ መንግሥት ኮሚሽን በነበረው ትልቅ ውይይት እኔም የተሳተፍኩበት ሲሆን፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1986 ዓ.ም ታህሳስ 21 እና 22 ባወጣው እትሙ የእኔ ሃሳብ ከአንዴም ሁለቴ ተካቷል። ያኔም ቢሆን ሕገ መንግሥት ተቀባይነት ያልነበረው ሲሆን፣ እስከዛሬ ድረስ ዘልቋል። ስለዚህም ይህ ሕገ መንግሥት የግጭት እርሾ ሆኖ ቆየ እንጂ የሰላምና የሕብረት ምክንያት መሆን አልቻለም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ አልነበረም። ለወደፊቱም ቢሆን ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቴ ነው ብላ የምትይዘው ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን የሚወክል ሕገ መንግሥት እንጂ እነ እገሌንና እገሊትን የሚወክል ብቻ መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት ሕገ መንግሥቱ በመከፋፈሉ ረገድ ሚናው የጎላ ቢሆንም ታላቁ የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያውያን አንድ ከማድረግ አኳያ ምን ያህል ርቀት ሄዷል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ከረጅሙ በአጭሩ ይህንን ግድብ ኦጋዴን ያለው ሰው ወይም በደቡብ ኢትዮጵያ ጫፍ ላይ ያለው ዳሰነች አሊያም ኛጋቶም ያለው ሰው ወይም ደግሞ ጋምቤላ ኢታንግና አቦቦ ያለው ሰው እንዲሁም ወደምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውና መሃል አገር የሚኖረው ሰው ሁሉ ደግፎታል። የደገፈበት ምክንያት ደግሞ ግድቡ የሚያመጣለትን የኤሌክትሪክ ኃይል ወይም ደግሞ ሌላ ነገር አስቦ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ውሃ ላይ ግድብ ገድቦ ለኢትዮጵያ ጥቅም ለማዋል ሲፈልግ ይህን አታደርግም የሚል ጠላት ስላለ ይህንን መመከት አለብን ከሚል የተነሳ ነው።
ቀደም ሲል የነበረው ቅኝ ግዛት እንዲሁም የውጭ ወረራና ተጽዕኖ እንደተመከተ ሁሉ ይህንንም መመከት አለብን በሚል ስሜት ይመስለኛል በአንድነት የመደገፋቸው ምስጢር። እንደ እኔ በውስጡ የኢትዮጵያዊ አርበኝነት ያለበት ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው። በእርግጥ ልማቱ ሲመጣ አልጠቀምም ብሎ አያስብም ማለት ሳይሆን ትልቁ ነገር ግን አርበኝነቱ ነው። የአባይ ግድቡ ቀድሞ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን አንድነት የመለሰ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ እቅድዎ ምንድን ነው? አያይዘውም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት እድሉን ልስጥዎት?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ትልቅ ተሞክሮ ስላካበተች በቴክኒኩም፣ በዲፕሎማሲውም ሆነ በጂኦፖለቲካው ተጽዕኖ በመቋቋም ትልቅ ተሞክሮ አሳይታለች፤ ይህም ኢትዮጵያውያኑን ያኮራና ውጤቱም ያማረ ሆኗል። ጎረቤቶቻችንም እየተቀየሙን አስቸገሩን እንጂ ለእነርሱም በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ይህ ተሞክሮ ውጤት ያገኘ በመሆኑ በቀጣይም እሱ ላይ አስፍቼ እስራለሁ የሚል እቅድ አለኝ። ግድብ የልማት ስራ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ወንዞች አሉና የመላ ኢትዮጵያውያ ስለሆኑ ወንዞቻችንን መንከባከብ አለብን፤ አረንጓዴ አሻራም ቀጣይነት ያለው እንዲሆን እሻለሁ። ልምዱም በአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ ያለ ቢሆንም ጉድለት በማሳየቱ በዚህ ደረጃ አልታየም ነበር። የአሁኑ ግን በእጽዋት ምርጫም ሆነ በእንክብካቤ ደረጃ ከፍ ብሎ የታየ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ከተፈጥሮ ጋር ያለን ቁርኝት ከፍ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደካንሰር አንድነታችንን እየቦረቦረ ያለው ጎሰኝነት ስለሆነ ይህም ቀድሞ ሲገዙ በነበሩ ሰዎች የተተከለ ብዙዎቹን የሚጎዳ ጥቂቶችን ደግሞ ለጊዜው የሚጠቅም የሚመሰል ነው። ነገር ግን ለዘለቄታው የማይጠቅም በመሆኑ በአጠቃላይ ይህ እንደ ስህተት ተቆጥሮ ከታረመ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው ያላቸው ቁርኝትና የአገር አርበኝነት እንዲሁም የልማትና የህብር ጥምረት እንደገና እንዲገነባ ይረዳል። ኢትዮጵያውያኑም እንዲህ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም