በለምለሙ የገጠር ቀበሌ ነው ተወልዳ ያደገችው። ይህ ቀረሽ የማትባል ቆንጆ የሆነችው ወጣት ለቤቱ ሶስተኛና ብቸኛ ሴት ልጅ ናት። ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ልጅ ያገኙት እናቷ የረሀቤ መድሃኒት ሲሉ የራብ ብለው ስም አውጡላት። የራብ ብርሃኔ እንደ አካባቢው ልጆች ከብት ስታግድ ወላጆቿን ስትደግፍ አደገች። ይች ልጅ ስምን መልአክ ያወጣዋል ይሉት ነገር ሆኖ እውነትም እንደ ስሟ ለእናት ለአባቷ ደጋፊ ሁነኛ ልጃቸው ሆነች። ሴት ልጅ ተርበውና ተጠምተው አምላካቸውን ሲማጸኑ ያገኟት የአይናቸው ብቻ ሳትሆን የድካማቸው ማረፊያ አገልጋያቸው ሆና ነው የተፈጠረችው።
በአጋጣሚ እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ በተወለደችበት አካባቢ በቅርበት አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይከፈታል። ትምህርት ቤቱ የወላጆቿ ቤት አቅራቢያ በመሆኑና በፈረቃ ትምህርት ግማሽ ቀን ብቻ ስለምትማር “ቶሎ መለስ ብላ ትረዳናለች” በማለት ወላጆቿ ያለምንም ማንገራገር ትምህርት ቤት እንድትገባ ይፈቅዱላታል።
የራብ በልጅነቷ ንቅት ያለች ቀልጣፋ ልጅ ስለነበረች ትምህርቱን ለመያዝ ብዙም አልተቸገረችም ነበር። አስተማሪዎቿ የሚናገሩትን አዳምጣ ወዲያው የምትረዳ የቀለም ቀንድ የሆነች ጎበዝ ልጅ ወጣት። ከትምህርት ቤት መልስም ወላጆቿን አስከፍታ ከትምህርት እንዳያስቀራት በማሰብ ቀደም ትሰራው ከነበረው በላይ ጨምራ በመስራት ታስደስታቸው ጀመር።
አመት አመትን እየወለደ የራብም ከልጅነት ወደ ኮረዳነት እድሜ ተሸጋገረች። ከዛም ባለፈ አካባቢያቸው የሚገኘው ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምር ስለነበረ ትምህርቷ እዚህ ላይ ሊቋጭ ይሆን በሚል ስጋት ተወጠረች። የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ከወሰደች በኋላ በጣም ከምትወደው ትምህርቷ የመቅረቷ ነገር ያሳሰባት ይች ልጅ ለማንም ሳትተነፍስ በውስጧ መብሰልሰል ጀመረች።
የልጃቸውን መጨነቅ ያስተዋሉት አባቷ ምን እንደሆነች ሲጠይቋት ትምህርቷን የመቀጠል ፍላጎት እንዳላትና ትምህርት ቤቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ መሆኑ እንዳሳሰባት ታስረዳቸዋለች። አባቷም “እስኪ ቅድሚያ ውጤቱ ይምጣና እንማከራለን” በማለት ያልፉታል። ለአፋቸው ይሄንን ይበሉ እንጂ ጎበዟ ልጃቸው ዝቅተኛ ውጤት እንደማታመጣ ልባቸው ያውቀዋል።
ለእሷ ይሄንን ካሉ በኋላ በአቅራቢያቸው ያለ የገጠር ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስለመኖሩና በምን መልኩ መማር እንደምትችል ሲያስቡና ሲያስተካከሉ ቆዩ። የራብም በለስ ቀንቷት በከፍተኛ ውጤት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። ቤት ተከራይተውላት ስንቅ ቋጥረው የላኳት ብቸኛ ሴት ልጃቸው ተምራ እንደምታኮራቸው ያመኑት አባቷ ምንም የማጀቱ አድማቂ ብትሆን እንኳን ከምትወደው ትምህርቷ ሊነጥሏት አልፈለጉም ነበር።
የአባቷና የእናቷ ተስፋ የሆነችው ወጣት ውጤታማ በመሆን በፋርማሲስትነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያዘች። ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት በራቀቻቸው ወቅት የነበረውን ናፍቆት የተረዳችው ወጣት ቤተሰቦቿ ከሚኖሩባት የገጠር ቀበሌ አጎራባች በሆነችው በሁለት እጁ ነሴ ወረዳ ቀራንዮ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ በአንድ ግለሰብ መድኃኒት ቤት ተቀጥራ ትሰራ ጀመር።
ስራ በማይኖራት ቀን በአገኘቻት ብር የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ ቁጥርጥር አድርጋ በመሄድ እናት አባቷን ጠያቂ ወንድሞቻን ደጋፊ አስተማሪ የሆነች ጠንካራ ወጣት ሆነች። በቤተሰቧ ተወዳጅ የሆነችው ይች ወጣት የቤተሰቧ ፍቅር በልጦባት ትዳር ፍቅረኛ ስለሚባል ነገር ጨርሶም አስባ አታውቅም ነበር።
በልስላሴ ድፍት ከሚለው ሃር ከመሰለው ዘንፋላ ፀጉሯ አንስቶ ጥርት ያለው ውብ ጠይም የቆዳ ቀለሟ፤ የተኳሉ የሚመስሉት አይኖቿ፤ እንደ ፀበል ኩስኩስት ቀጥ ብሎ የወረደው ውብ አፍንጫዋ፤ ሞላ ያሉት ከንፈሮቿ በአጠቃላይ አብ ሳላት የተባለላት አይነት ውብ ሴት ናት።
ይች ውብ የጤና ባለሙያ ብቻዋን ገባ ወጣ ማለቷን በአይነቁረኛ የሚከታተሉ ጎረምሶች በረከቱ። አይናቸውን ከመጣል በሻገር ደፈር ብለው የፍቅር ጥያቄ ያቀረቡላትም አልታጡም። የራብ ግን ልቧ የገባ ሰው ትጣ ወይም የወላጆቿ ፍቅር ሁለመናዋን ተቆጣጥሮት ባይታወቅም ስሜቷ ማንንም በፍቅር አይን ለመመልከት አላስቻላትም ነበር።
የእንቢታ መልሷን የሰጠቻቸው ሰዎች በሙሉ መልሱን በፀጋ ተቀብለው ቢመለሱም ከአፍቃሪዎቿ መካከል አንዱ የፍቅር ጥያቄውን ያለመቀበሏን በንቀት ቆጥሮት በልቡ ቂምን አዝሎ መውጫ መግቢያዋን ይቆጣጠራት ገባ። ሁልጊዜ መከታተሉ ምቾት ያልሰጣት ወጣት ይረሳኝ ይሆናል በማለት የአመት ፈቃዷን ወስዳ ቤተሰቦቿ ጋር ሰነባብታ ተመለሰች።
ይሁንና ጭራሽ ከአይኑ መጥፋቷ ያሳበደው አፈቀርኩ ባይ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ወደ ስራ ገበታዋ የምትመለስበትን ቀን ይጠባበቅ ጀመር። መድረሱ አይቀርም የእረፍቷ ቀኗ አብቅቶ ወደ ስራ ገበታዋ ተመለሰች። ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሆዷን ባር ባር እያለው የተለየቻቸው ቤተሰቦቿን ተመልሳ የማታያቸው ያህል እንባ እየተናነቃት ነበር ከተወለደችበት ቤት የወጣችው።
ወደ ስራ ገበታዋ በተመለሰች በሶስተኛው ቀን ከየት መጣ ሳትለው አፈቀርኩሽ የሚላት ሰው እጇን ለቀም አድርጎ ያዘ። አይኑን አጉረጥርጦ ለምን ሳትነግረው እንደሄደች በጩኸት ጠየቃት። ‹‹የሚሄድበትን ሁሉ ላንተ የማሳወቅ ግዴታ የለብኝም›› አለች ፈርጠም ብላ። “አንቺ የእኔ ካልሆንሽ የማንም መሆን አትችይም እሰራልሻለሁ” በማለት ጥርሱን ነክሶ የቅናት ክብሪቱን በራሱ ላይ ለኩሶ በውስጡ እያንቦገቦገ ተለያት።
ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም እንደተለመደው በጠዋት ከቤቷ ወጥታ ቤተክርስቲያን ተሳልማ ወደ ስራዋ ሄደች። ያለወትሮዋ ቅፍፍ በሚል እንቅልፍ እንቅልፍ በሚል ስሜት ውስጥ ነበር የዋለችው። ድብርቷን ያስለቅቅላት ይመስል ደጋግማ ቡና ስትጠጣ የነበረችው ወጣት ምንም ቀለል ያለ ስሜት አልሰማት ሲል ቤት ሄጄ ልረፍ በማለት ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ከሥራ ወጣች።
ያች የውበት መለኪያ የሆነች ውብ የገጠር ወጣት ከስራ ስትመለስ የፍቅር ጥያቄዬን መቀበል አለብሽ ያላት ሰው መንገድ ላይ ጠብቆ አሲድ በፊቷና በራሷ ላይ ደፈባት። ቃጠሎውን መቋቋም የከበዳት ያች ወጣት እየጮሄች ብትጠርገውም ሰውነትዋ ከመበጣጠስ ያለፈ ቃጠሎው ሊታገስላት አልቻለም።
ሰውነቷ ላይ በተደፋው አሲድ በፊቷ፣ በግማሽ እራሷና በአንድ ጡቷ ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት ያደረሰባት ሲሆን ተሰምቷት የማያውቅ አይነት ሰቃይ ውስጥ እንደከተታት ትናገራለች። ወጣቷ ስትጮህ በአካባቢው በርካታ ሰዎች ቢሰበሰቡም እላይዋ ላይ ውሃ ከመድፋት የዘለለ እርዳታ ስላላደረጉላት ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን ችሏል።
ጉዳቱን ያደረሰው ግለሰብ ወዲያውኑ ከአካባቢው
ለመሰወር ሙከራ ቢያደርግም በህብረተሰቡ ርብርብ ሊያዝ መቻሉን ያስታወቀው ፖሊስ ግለሰቡ የፍቅር ጥያቄዬን አልተቀበልሽኝም በሚል የተናቅኩ ስሜት ተነሳስቶ እንዲህ አይነት የከፋ ጉዳት እንዳደረሰባት በማስረጃ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ ነሴ ወረዳ ፖሊስ የተፈፀመው የአካል ማጉደል ወንጀል ላይ የዓይን ምስክሮችን፤ የህክምና ማስረጃን በማካተት የሰነድ ማስረጃ ለወረዳው አቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ መስርቶ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።
ፍቅር ናፋቂው ወንጀለኛ
ደብረታቦር አካባቢ በምትገኝ የገጠር ቀበሌ ነበር የተወለደው። ወላጅ እናቱ በልጅነቷ በመዷራና ሰውነቷ ሳይጠና በማርገዟ የተነሳ እሱን እንደወለደች ነበር ሕይወቷ ያለፈው። ወላጅ አባቱ ብዙም ሳይቆይ በማግባቱ እንጀራ እናቱ ታሳድገው ጀመር። አባቱ የመጀመሪያ ሚስቱን በጣም ያፈቅራት ስለነበር ልጁ የገደላት ያህል አምርሮ ይጠላው ነበር። ሲወጣ ሲገባ “አንተ ገፊ” በማለት ነበር የሚጠራው።
በእናት ፍቅር እንክብካቤ ሳያገኝ በጥላቻ በተሞሉ ሰዎች መካከል ያደገው ይህ ልጅ ከፍ ብሎ እግር እንዳወጣ ነበር ወደ ምስራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ ነሴ ወረዳ የመጣው። በዛም ያገኘውን እየሰራ በትርፍ ጊዜው እየተማረ እራሱን ሲያሳድግ ኖረ።
ቤታቸው ተከራይቶ ይኖርባቸው የነበሩ ልጅ ያልነበራቸው ሴትም ልክ እንደ ልጃቸው እያዩት እሱም ያጣውን የቤተሰብ ፍቅር ያለስስት የሰጡትን ሴት እየደገፈ በቤተሰብነት ይኖሩ ጀመር።
አንድ ቀን ያየውን ማመን እስከሚያቀተው ድረስ ምትሃት የሆነ ውበት ከፊት ለፊቱ ሲመጣ ይመለከታል። በጣም የምታምር ቆንጆ ወጣት በተረጋጋ እርምጃ ከፊቱ መጥታ አጠገቡ ደርሳ እስክታልፍ ደረስ አፉን ከፍቶ እየተመለከታት ነበር።
እንዲህ ፍቅር ዳሶት የማያወቀውን ከራሱ ሌላ ምንም የኔ የሚለው የሌለውን ሰው ልብ ወከክ ያደረገችውን ልጅ ሲፈራ ሲቸር ቆይቶ የፍቅር ጥያቄውን አቀረበላት። እሷም እንደማይሆን ግልፅ በሆነ አማርኛ ነግራው ወደ ቤቷ ሄደች።
ያን ቀን ነው እንግዲህ ልቡ ውስጥ ተሸሽጎ የኖረው ፍቅር የማጣት የመጠላት ስሜት ቀንድ አውጥቶ የእጅና የእግር ጥፍሩን አሹሎ ከወደ ልቡ ስር የወጣው። ያለመፈለግ ስሜቱ አድጎና ጎልብቶ የማይፈልጉትን የማይወዱትን ሊያጠፋ ተነሳ። ይህ ክፉ ስሜት ውቧ የራብ ላይ እጁን እንዲያነሳ አደረገው። ያችን ታይታ የማትጠገብ ወጣት ግማሽ ፊቷንና ግማሽ አካሏን በአሰቃቂ ሁኔታ አሳጣት። በዚህ ስራውም ፍትህ ሊጠይቀው ከህግ ፊት መቆም ግድ ሆነ።
ውሳኔ
ዓቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤት ማስረጃና መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል። “ግለሰቡ ወንጀሉን ሆን ብሎና አቅዶ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የፈፀመው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 84 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት በወንጀል ማክበጃነት ይዟል” ብለዋል።
ተከሳሹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፣ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የለብኝም በሚል ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ከፈፀመው ወንጀል አንጻር ያቀረበውን የፍርድ ማቅለያ ሳይቀበለው ቀርቷል።
የወረዳው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ሌላውንም ህብረተሰብ ያስተምራል፤ ጥፋተኛውንም እንዲጸጸት ያደርጋል በሚል በፈጸመው ወንጀል ግለሰቡን በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል። ወንጀለኛ በጥፋቱ የተወሰነበትን ቅጣት መቀጣቱ ግድ ነውና አከራረሙን ማረሚያ ቤት አደረገ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም