የካ አባዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለአራት እና ባለስድስት ወለል ፎቅ የጋራ መኖሪያ ቤት በስፋት ተገንብቶ ሰዎች መኖር ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። በአንድ ሕንፃ ላይ አነስተኛው አርባ ከፍተኛው ስልሳ አካባቢ የሚደርሱ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸው ሲሆኑ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ በእጅጉ መላመድ ጀምሯል። የኢትዮጵያውያን እሴት የሆነው የሴት፣ የወንድ እና የእራት እድር ከማቋቋም በተጨማሪ እቁብ በማሰባሰብ ወላጆች እርስ በእርስ መደጋገፍ እና መመካከር ጀምረዋል።
ወጣቶች በአካባቢው ባሉ ሜዳዎች እና ጎዳናዎች ላይ ስፖርት መስራት፣ ሩጫ መወዳደር እና በቡድን እግር ኳስ መጫወት እንደልማድ መቆጠር ከጀመረ ሰነባብተዋል። በተለይ አመሻሽ ከ11 ሰዓት በኋላ የየካ አባዶ ሜዳዎች በማንኛውም ቀን በሰው የተሞሉ ናቸው። ገሚሱ እግር ኳስ ሲጫወት ገሚሱ ቮሊቦል ይጫወታል። የተቀረው ተመልካች ሆኖ ቆሞ እያፏጨ ያጨበጭባል። በዛ መሃል ደግሞ አንዳንዴ ፀብ ይነሳል።
የወጣቶቹ ፀብ እጅግ አስፈሪ ነው። እስከ ሕይወት መጠፋፋትም ይዘልቃል። ሜዳ ላይ በድጋፍ ወይም በሌላ ምክንያት የተነሳ ፀብ ውሎ አድሮ እየከረረ ይቀጥላል። ቡድን ሰርተው አንዱ ሌላውን እያስፈራራ አንዱ ሌላውን እየመታ እና እየጎዳ ወላጆች ጭንቀት ውስጥ መግባት ጀምረዋል። ወጣቶቹ ስለቀጣይ ሕይወታቸው የሚያስቡ አይመስሉም። ስለት ይዘው እስከ መወጋጋት ይደርሳሉ። ምክንያታችሁን ግልፁ ሲባሉ ደግሞ ውሃ የሚያነሳ መልስ አይሰጡም።
የአንደኛው ቡድን ወጣት የሌላኛውን ቡድን ወጣት ካገኘ አሳዶ ይመታል፤ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ያስከትላል። ብቻ ወጣቶቹ እርስ በእርስ እየተጋጩ መግቢያ መውጫ አጡ። በግጭቱ ውስጥ በዋነኛነት ቀንደኛ ሆነው ከሚሳተፉት መካከል ሃይመን ጄላን አንዱ ነው። ሃይመን ድርድር አያውቅም፤ የተቃራኒ ቡድን አባላትን ካገኘ ከመደባደብ ወደ ኋላ አይልም። በተለይ እርሱ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ በተቃራኒ ጎራ ከተሰለፉ ቡድኖች አንዱን ወጣት ካገኙ መግቢያ እስኪያጣ አሳደው ይጎዳሉ።
ወንድምየው
ፍቃዱ ወንድሙ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው የካ አባዶ ኮንደሚኒየም አካባቢ አገር ሰላም ብሎ ከገደራ አካባቢ በእግሩ ቀስ እያለ ወደ መስቀለኛ ሲራመድ፤ ከሩቅ እርሱን እና የእርሱን ጓደኞች አሳድደው በመያዝ የሚደበድቡ ወጣቶች ማለትም እነ ሃይመንን ተመለከተ። እነርሱ ሳያዩት በተለምዶ ‘ጂ ሰቨን’ ተብለው ከሚጠሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች ጀርባ መሮጥ ጀመረ። ሲሮጥ የተመለከቱት እነ ሃይመን አሳደዱት፤ እግሬ አውጪኝ ብሎ የ’ጂ ሰቨን’ ሕንፃዎችን ጨርሶ ዋናውን አስፓልት ከተሻገረ በኋላ ሮጦ ደህንነቱ ወደ ሚጠበቅበት ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወደ ቤቱ አቅራቢያ ደረሰ። ከሚኖርበት ቤት ሕንፃ ጀርባ ዞሮ አጎንብሶ ተነፈሰ።
ከጓሮ ቁጭ ያለውን ቃልአብን ሲያይ፤ ቁና ቁና እየተነፈሰ እነ ሃይመን አግኝተውት እንደነበረ እና ከሩቅ አይቷቸው ሲሮጥ እንዳሳደዱት እንዲሁም ሮጦ እንዳመለጠ ነገረው። ይህ መሳደድ እና ማሳደድ ለወጣቶቹ ከፍተኛ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ነገሩ ይበልጥ እየተጋጋለ ቢቀጥልም፤ ገላጋይ ጠፍቶ ወጣቱ ወጥቶ ለመግባት ተቸግሯል። ቃልአብ እና ፍቃዱ ከሚኖሩበት ሕንፃ ጀርባ ባለ የአትክልት ቦታ ላይ ቁጭ ብለው እየተነጋገሩ ቆዩ። ስለሁኔታው ፍቃዱ እያስረዳ ቃልአብ ደግሞ እያዳመጠ፤ ሌላኛው ጓደኛቸው ልክ እንደፍቃዱ እያለከለከ ደረሰ፡፡
ጓደኝየው ፍቃዱን ሲያይ ‹‹ወንድምህን እነ ሃይመን ይዘውታል፡፡›› አለው፤ ፍቃዱ ሮጦ ያመለጣቸው ወጣቶች፤ ወንድሙን እንደያዙ ሲሰማ፤ ፍቃዱ ዘሎ ቤት ገብቶ የሽንኩርት ቢላዋ ይዞ ሊጋፈጣቸው ወጣ። ከቤቱ ወጥቶ ጓደኛውን ወንድሙን የት አካባቢ እንደያዙት ጠየቀ። መስቀለኛ አካባቢ ላይ መሆናቸውን ሲነግረው፤ ወደ ግራ ሄዶ በአስፓልቱ ቁልቁል እየተንደረደረ መሮጥ ጀመረ። ጓደኞቹ እየሮጡ ተከተሉት።
እርሱ ከእነ ቤተሰቦቹ የሚኖረው ባለ አራት ፎቅ ሕንፃዎች ባሉበት አካባቢ ነው። ከ’ጂ ሰቨን’ ልጆች ጋር ፍፁም መጣጣም አልቻሉም። አሁን ደግሞ ወንድሙን እያጠቁበት መሆኑ አንሰፈሰፈው፤ በመጨረሻም ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ወጣቶቹ ከባድ ስህተት ፈፀሙ። ስህተት ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ሕይወታቸውን የሚያበላሽ ወንጀል ውስጥ ገቡ። ቀድሞ እንደቀልድ የታየው ጠብ መዘዙ የወጣቶቹን ሕይወት እስከ ወዲያኛው የሚበጠብጥ ሆነ።
ደብዳቢው ቡድን
ሃይመን የሚንቀሳቀሰው ታጅቦ ነው። በዘመኑ የጋንጊስተር ቡድን ለመመስረት ያሰበ ይመስላል። በአጀብ ሲንቀሳቀስ እየጠራ የፈለገውን ይሰድባል፤ የፈለገውን በጥፊ አልያም በእርግጫ ካልሆነም ማንበርከክን እንደመብቱ ቆጥሮታል። ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ወጣቶች እርሱን የማይደግፉ ከሆነ ወዮላቸው፤ ጠብቆ ብቻውን ሳይሆን ሌሎችንም አደራጅቶ ያጠቃቸዋል።
አንድ ወጣት ካየ ተያይዞ ማሯሯጥን እንደጀግንነት የሚቆጥረው ተግባር ነው። መስቀለኛ ጋር ሆኖ ከሩቅ ኬላው ጋር ያዩትን ፍቃዱ አሯሩጠው ሊይዙት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። በገዛ መንደራቸው ተሹለክልኮ አመለጣቸው። እርሱ እንዳመለጣቸው እርግጠኛ ሆነው በአስፓልቱ ቁልቁል ወደ መስቀለኛ ሲራመዱ ያመለጣቸው የፍቃዱ ወንድሙ ወንድም የሆነውን ሙሉቀን ወንድሙን አገኙት። እርሱ እንደፍቃዱ ቀድሞ አላያቸውም። ሮጦ ማምለጥ አልቻለም።
ሃይመን ጄላን ሙሉቀንን ሲያይ በደስታ እና በድል አድራጊነት ፈገግ አለ። ወንድምህ ቢያመልጠንም አንተን አገኘንህ ብሎ በመጠጋት ሆዱን በቦክስ መታው፤ ይህንን ከሩቅ ሲመለከት የነበረው የወንድማማቾቹ ጓደኛ እየሮጠ ወደ እነ ፍቃዱ ቤት አቀና። ሕንፃው አካባቢ ፍቃዱን ቢመለከትም ማግኘት አልቻለም። ከጀርባ ሲያይ ቃልአብ እና ፍቃዱ ተቀምጠዋል። ሙሉቀንን እንደያዙት ሲነግራቸው፤ ፍቃዱ ተነስቶ ቆመ።
የሞት ፅዋ
ከላይ ቁልቁል እየተንደረደረ እነ ሃይመን አቅራቢያ የደረሰው ፍቃዱ ወንድሙ ሙሉቀን ወድቆ ሲያይ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ። አንድ ማህፀን የተጋራው የውድ ወንድሙ ደም ሲፈስ ሲያይ የሚሆነውን አጣ። ሙሉቀን መሬት ላይ ወድቆ ደሙ እየፈሰሰ የነበረው ሃይመን ጄላን ጀርባው ላይ በስለት ስለወጋው ነበር። ይህንን የተመለከቱት የሃይመን ጄላን አጃቢዎች የደሙን መፍሰስ ተከትሎ ሃይለኛ ድንጋጤ ውስጥ ገቡ።
የሙሉቀን ወንድም ፍቃዱ መምጣቱን ቢያዩም ደፍረው ለመጠጋት አልሞከሩም። ፍቃዱ የያዘውን የሽንኩርት ቢላዋ መዘዝ አድርጎ የእናቱን ልጅ ወንድሙን በስለት የወጋበትን ሃይመንን ለመውጋት ተጠጋ። ማንም ሊያስጥለው አልሞከረም። ፍቃዱ የልብ ልብ ተሰማው፤ ወንድሙን ሲያይ የሙሉቀን ደም እየፈሰሰ ነው። ፍቃዱ ቢላዋውን ወደ ሃይመን አንገት ሰነዘረ። አልሳተውም የሃይመንን አንገት ቆረጠው።
ሃይመን ከሙሉቀን ጎን ወደቀ። ደሙ ከሙሉ ቀን በላይ መፍሰስ ጀመረ። የሃይመን ወዳጆች ብዙ በመሆናቸው አውራቸው ሲወጋ ግርግር ፈጠሩ። ነገር ግን አውራቸውን ማዳን አልቻሉም። በሌላ በኩል በአብዛኛው ሲጠቃ የነበረው የእነ ፍቃዱ ቡድን አባላት በፍጥነት ባጃጅ አምጥተው ሙሉቀንን ይዘው በአካባቢው ወዳለ ጤና ጣቢያ አፈተለኩ።
ሙሉቀን ምንም እንኳ ደሙ እየፈሰሰ ቢቆይም በሕክምና ባለሙያዎች እርዳታ ሕይወቱ ተረፈ። የሃይመን ቡድን አባላት አውራቸውን ሕክምና ቦታ አላደረሱትም። እዛው አስፓልት ላይ እንደተጋደመ ሕይወቱ አለፈ። ጩኸት በረከተ፤ እናቶች ተጠራርተው ነጠላቸውን እያዘቀዘቁ ወደ መስቀለኛ ሮጡ።
ፖሊስ ተጠራ፤ የፖሊስ የምርመራ ቡድን አስክሬኑን ለምርመራ ከላከ በኋላ ማጣራት ጀመረ። ፍቃዱ ወንድሙን ጨምሮ የቡድን ፀብ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩትን በሙሉ ሃይመንን ገድላችኋል በሚል ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር አዋለ። በመጨረሻ ጥርጣሬው ወደ ፍቃዱ በማድላቱ ሌሎቹ ተለቀው ከዛ ጊዜ ጀምሮ ፍቃዱ ወንድሙ እስር ቤት ሆኖ ሲከራከር ቆየ።
የክሱ ዝርዝር
የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ ማስረጃዎችን አሰባሰበ። በብርቱ ጥረት ድርጊቱን ማን እንደፈፀመ አረጋገጠ። በመጨረሻም ለአቃቤ ሕግ እነ ፍቃዱ ወንድሙ በሚል ክስ እንዲመሰረት ይደረግ ሲል፤ መረጃውን እና ማስረጃውን ለአቃቤ ሕግ አቀረበ። ዐቃቤ ሕጉም ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከ30 አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው የካ አባዶ ኮንደሚኒየም መስቀለኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪው ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን፤ የቡድን ፀብ አንስቷል። በተነሳው የቡድን ፀብ ሟች ሃይመን ጄላን የተባለውን ወጣት አንገቱ ላይ በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል ሲል ክስ መሠረተ።
ክርክሩ በአቃቤ ሕግ እና በእነ ፍቃዱ ወንድሙ መካከል ሲካሄድ፤ አቃቤ ሕግ የሰው ምስክር እና ከሰው እና ከሆስፒታሉ ማረጋገጫ የሰነድ ማስረጃ አቀረበ። የሟች አስክሬን የምርመራ ውጤትና የወንጀሉን አፈፃፀም እንዲሁም ሟች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያሳይ ገላጭ ፎቶዎች በማስረጃነት ሰጠ።
ከማስረጃዎቹ መካከል የሟች ማንነት ጉዳቱ የደረሰበትን የሟች የሰውነት ክፍል፣ የወንጀሉ ሥፍራ እና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቢላዋ ለማሳየት የተነሱ ፎቶ ግራፎች ለፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይህንን ሁሉ ማስረጃ ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ የቅጣት ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል ሲል ጠየቀ።
– ውሳኔ
ተከሳሽ ፍቃዱ ወንድሙ ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ፤ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 1ኛ ምድብ ወንጀል ችሎት በጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃው ከሕግ ጋር አገናዝቦ የወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል ብሎ ባመነበት በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም