᎐ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባለች

በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን በትናንትናው ዕለት ሽልማት ተበረከተለት። አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ስፖርት ኮሚሽን፣ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር በውድድሩ ተሳታፊ ለሆኑትና ሜዳሊያ ላመጡት እንደየ ደረጃቸው ሽልማት አበር ክቷል።
በሻምፒዮናው ወርቅ ላመጡ አትሌቶች 30ሺህ ብር፣የብር ሜዳሊያ ላመጡ 20 ሺህ ብር፣ የነሀስ ሜዳሊያ ላመጡት 10ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡት ስድስት ሺህ ብር ሲያበረክት ለተሳትፎ ሶስት ሺህ ብር የብሄራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አበርክቷል። በውድድሩ ከተገኘው ድል ጀርባ ሚናቸው ከፍተኛ የነበሩ፤ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎችና የህክምና ሙያተኞች የገንዘብ ሽልማቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ650 ሺህ ብር ለሽልማት ማዋሉ ተገልጿል።
በአራራት ሆቴል በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት የተገኙት የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት አሰፋ፤በመጣው ውጤት በእጅጉ ኮርተናል።የተገኘው ድልም በቀጣይ ለሚደረጉት አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለይም
ሞሮኮ ላይ ለሚካሄደውና ኳታር ላይ ለሚጠብቀን የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም ለቶኮዮ ማራቶን በእጅጉ መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የተጀመረውን መነቃቃት ለማስቀጠል በቅርብ ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል በማለት ቃል የገቡት ዶክተር ሂሩት፤ ያለፈውን የአረንጓዴ ጎርፍ ታሪክ ዳግም መመለስ እንዲቻል የቡድን ሥራን በማጠናከርና በመደመር መንፈስ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በክብር በዓለም ፊት እንድትቆምና ሰንደቃችን እንዲውለበለብ ማስቻላችሁ ትልቅ አክብሮት የሚቸረው ተግባር ነው።በቀጣይም የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የሀገርን ስም ማስጠራት ይገባል በማለት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፤ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ እንደገለፁት፤ውድድሩ እጅግ በጣም ፈታኝ ቢሆንም ውጤት ማምጣት ተችሏል። በመጣው ውጤት ሳንዘናጋ ለሌላ ድል ዝግጅት የምናደርግ ይሆናል።በዚህም ከ15 ቀን በኋላ አቡጃ ላይ የወጣቶች የአፍሪካ ሻምፒዮና ይጀመራል። በተመሳሳይም ከፊት ለፊት የሚጠብቁን ሌሎች ውድድሮችን ያለእረፍትና መታከት የምንቀጥል ይሆናል በማለት ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም፤ በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ የአዘጋጅነቱን ዕድል እንድታገኝ ምክክር መደረጉን ልፀዋል። የ2023 የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ እንዲሰጥም ጥያቄ መቅረቡንና በቅርቡም አቡጃ ላይ በሚደረገው ስብሰባ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውሰው ኢትዮጵያ የታላላቅ አትሌቶች መገኛ እንደ መሆኗ ጥያቄው ተቀባይነትን እንደሚያገኝና ተስፋ እንዳለው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ አምስት የወርቅ፣ ሶስት የብርና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ አሥራ አንድ ሜዳሊዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አገራት አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በሻምፒዮናው 28 አትሌቶችን ጨምሮ በድምሩ 46 የልዑካን ቡድን አባላት ዛሬ እኩለ ሌሊት አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን ነገ ጠዋት በአራራት ሆቴል እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ታውቋል።ውድድሩ በአዋቂ ወንዶ ችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር፣በወጣት ሴት ስድስት ኪሎ ሜትርና በስምንት ኪሎ ሜትር ድብልቅ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በሁሉም ርቀቶች ላይ ተካፍላለች።
በውድድሩ አምስቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች በወጣት ወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር በአትሌት ሚልኬሳ መንገሻ፣ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በስምንት ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብልና ቀሪዎቹ የወርቅ ሜዳሊያዎች ደግሞ በአዋቂ ሴትና በሁለቱም ጾታ ወጣት ቡድን የተገኙናቸው።ሶስቱ የብር ሜዳሊያዎች በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር በአትሌት ደራዲዳ፣በወጣት ሴቶች በስድስት ኪሎ ሜትር በአትሌት አለሚቱ ታሪኩና በወጣት ወንዶች ደግሞ በአትሌት ታደሰ ወርቁ የተገኘው ውጤቶች ናቸው።በአዋቂ ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ በወጣት ሴቶች ፅጌ ገብረሰላማና በአዋቂ ወንዶች የቡድን ውጤት ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ67 አገራት የተውጣጡ 582 አትሌቶች ተሳትፈዋል።የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረና ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር መሳተፍ የጀመረችው ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ጥሩው ውጤትም ከምታስመዘግብባቸው የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የሚጠቀስ ነው።ከ1989 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በተካሄዱት የዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ውጤት በ1999 ዓ.ም በኬንያ በተደረገ ውድድር ላይ 3ኛ ደረጃን ካጠናቀቀችበት በቀር ባለፉት 18 ውድድሮች የአንደኛ ወይም የሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች መሆኑ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በ ዳንኤል ዘነበ