ሰላም በሦስት ፊደል ብቻ ይገለጽ እንጂ ሁሉም ነገር ነው። የተለያዩ የአማርኛ ቃላት መፍቻ መዝገቦች ሰላምን ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ እንዲሁም የእርስ በእርስ ስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር መቻልና የዕረፍት ስሜት ሲሉ ትርጉም ይሰጡታል። በአጠቃላይ ሰላም ከሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱና ዋነኛው ነው።
ሆኖም ይህ መሰረታዊ ፍላጎት በተለያዩ አላላት ሲደፈርስ ይታያል። ከሰላም ይልቅ ከጦርነት በሚያተርፉ አካላት አማካኝነት ግጭት፤ ሁከትና ብጥብጥ በአለማችን ላይ ነግሶ ይታያል። የእኛዋም ኢትዮጵያ የዚሁ ሰለባ ከሆነች ሰነባበተች። በጥባጭ ካለ መች ደህና ይጠጣል እንደሚባል ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ሕወሓትና በግብረ አበሮቹ ምክንያት ሰላማቸውን ካጡ ሰነባብተዋል።
ለዚህ አባባል ደግሞ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ በአገራችን ላይ በሕወሓት ቡድን የተከፈተው ጦርነት በራሱ አንዱና ትልቁ መገለጫ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሰላምን በመሻት እየተወጉም ጭምር ለሰላም በርካታ መንገድ ተጉዘዋል። ከታዋቂ ሰዎች ጀምሮ እስከ ኃይማኖት አባቶች ጭምር የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ከጦርነት በሃሪው እንዲወጣና ሰላም እንዲያሰፍን በብዙ ቢለፋም ቡድኑ ጦርነት አምላኪ በመሆኑ የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ መክነው ቀርተዋል።
እንደ መንግስት በአገር ደረጃ የሰላም ሚኒስቴርን ከማቋቋዋም ጀምሮ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ጽኑ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይሄንን ጽኑ የመንግስት አቋም አዲስ አበባ በተካሄደው በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ”በአገራችን ሰላም ለማስፈን የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም” ሲሉ የተናገሩትን ማስታወሱም ማሳያ ይሆናል። በሌሎች አገራዊ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ውይይቱን የሚያካሂድ ኮሚቴም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ በብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙን ሲናገሩ ማድመጣችንም ቢሆን የመንግስትን ሰላም ፈላጊነት ያመላክታል።
በመንግስት የሚመራውና ሰላምን በባለቤትነት ይዞ እንደ አገር የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴርም በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን ጨምሮ በሕ›ወ.ሓ.ት የተከፈተውን ጦርነት ጭምር በሰላም ለመፍታት ዘወትር ጥረት እያደረገ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነትም ውስጥ ሆኖ የሰላም አማራጮችን የሚያስቀድም መንግስት ነው።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም መንግስት የዛሬዋን ዕለት ጭምር ለሰላም በማዋል ጷጉሜን ሦስት የሰላም ቀን ብሎ እስከመሰየም ደርሷል። ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ዕለት ለሰላም ይተጋሉ፤ በዛሬዋ ቀን ደግሞ ድምጻቸውን በአንድነት ያሰማሉ። ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ዜጓቿ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት አገር እንድትኖራቸው ይጸልያሉ። በርካታ ወጣቶች ሴቶች በግልና በጋራ ጦርነትን፤ ሁከትንና ብጥብጥን አንሻም በማለት በጋራ ይቆማሉ፤ በአሸባሪ ቡድኑ አማካኝነት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጦርነት ድርጊቶችን ያወግዛሉ።
ብዙዎችም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም ያሰማሉ። ሴቶች ደግሞ ለዚህ ግንባር ቀደም ሚናውን ወስደዋል። ከነዚህ አንዷ በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተመዘገበችው አገር በቀል ድርጅት ትምራን ናት። ትምራን ሴቶች በፖለቲካዊ እና አመራርነት ዘርፎች በጉልህ የሚሳተፉባት ኢትዮጵያን ለማየት እየሰራች የምትገኝ ማህበር ናት።
ወይዘሮ እየሩስዓለም ሰለሞን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ናቸው።
ትምራን ከተመሰረተች ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በሰላም ዙርያ ስትሰራ መቆየቷንም አውስተዋል። እኛ ሴቶች ሰላምን ነው የምንሻው። ጦርነትን አጥብቀን እንቃወመዋለን። ኢትዮጵያ ልጆቻችን በሰላም እንዲያድጉ፤ እንዲማሩ፤ እኛም በሰላም ሰርተን የምንኖርባት እንድትሆን እንፈልጋለን ይላሉ። በየዓመቱ የሰላም ቀን ተብሎ የተሰየመውንና ዛሬ እየተከበረ ያለውን ጷጉሜን ሦስትን በዚሁ መልኩ አክብሮ ለመዋልና ለማሰብ የሚያስችልና ከሴቶች አደባባይ ተነስቶ እስከ መስቀል አደባባይ የሚዘልቅ ታላቅ የእግር ጉዞ መዘጋጀቱንም ይናገራሉ።
ትምራን ጦርነትንና ሁከትን የሚቀሰቅሱ ማናቸውም ኃይሎች ሆኑ ሕ.ወ.ሓ.ት ወደ ሰላም ፊታቸውን እንዲመልሱ ሳታሰልስ ትሰራለች ያሉት ሥራ አስኪያጇ ከመንግስትና ከየትኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምትሰራ መሆኗንም አውስተዋል። ሕ.ወ.ሓ.ትም ሆነ የትኛውም ቡድን ለሰላም እንዲቆምና ለሰላም መቆም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ብለዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ መንግስት ሳያሰልስ ሲሰራ መቆየቱንና እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ እየሩስ አለም ከዚህ ጦርነት ማንም እንደማያተርፍና ከሁለቱም ጎን የሚያለማ ወጣት እየረገፈና የአገሪቱም ሀብት እየወደመ መሆኑን ተረድቶ ወደ ሰላም መፍትሄ መምጣት አስፈላጊ እንደሆነም አስ ምረውበታል።
ስራ አስኪያጇ እንደሚሉት አሁን ላይ ‘’ሴቷ ሰላምን ትምራ’’ በሚል መሪ ቃል ሰላምን በአገራችን የማስፈን ምኞትን ያነገበ የሴቶች የእግር ጉዞን ከኢትዮጵያ ሴት ማህበራት ቅንጅት ጋር በጋራ በመተባበር ያዘጋጀችው ሰላምን ለማስፈን ነው፡፡ ሰላም ማጣት ከማንም በላይ ዋጋ ከሚያስከፍላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶችና ህፃናት ዋነኞቹ ናቸው ። ምንም እንኳን ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት እና ለሁሉም እኩል አስፈላጊ ቢሆንም፤ ሰላም በማጣት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለጥቃት ተጋላጭ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረው ጦርነት ዋነኛ ማሳያ ነው።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ እና የጉዳዩን ወቅታዊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሴቶች እራሳቸው ሰላምን እንዲሰብኩ፣ እንዲገነቡ እና የሰላም መሪዎች እንዲሆኑ እንዲሁም በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ዳግም እያንሰራራ ያለው የግጭት እና የጦርነት ሃሳብ ከምንጩ እንዲደርቅ በመመኘት “ሴቷ ሰላምን ትምራ” የሚል መፈክር በማንገብ ጳግሜ 03/2014 ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ከሴቶች አደባባይ በመነሳት መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገ የሰላም የእግር ጉዞ ከ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (NEWA) ጋር በመተባበር ማካሄድም አስፈልጓል፡፡
በእግር ጉዞው በርካታ ሴቶች፣ የሴት አደረጃጀቶች፣ የሴት መብት ተሟጋቾች እና ማህበራዊ አንቂዎች ይሳተፉበታል። እንዲሁም መርሀ ግብሩ ለዘለቄታዊ ሰላም ሴቶች ያሉዋቸውን ሀሳቦች ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ፤ በሌሎች አካባቢዎች የተነሱ ሀሳቦች የተሻለ የማስፈፀሚያ ዘዴ በማመላከት እና የዓመቱ የሰላም እንቅስቃሴ በሴቶች ጉልህ ተሳትፎ እንዲመራ አቅጣጫ በመስጠት ይጠናቀቃል ብለዋል። በጉዞው ላይ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የሰላም ሚኒስትር የሴቶች ተሳትፎ እንዲረጋገጥ መልዕክት ያስተላልፋሉ።
በአጠቃላይ የሰላም ቀንን በመጠቀም ሕወሓትና መሰሎቹ የአገራችንን ሰላም ከማወክ እንዲቆጠቡ እና ከጦርነት ውድመት እንጂ ሌላ ትርፍ እንደማይገኝ መልዕክት ይተላልፍበታል። የጦርነት ቅድሚያ ተጎጂ የሆኑት ሴቶችም በአገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አቋም የሚወስዱበት ይሆናል ሲሉ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014