በአሁን ወቅት እያንዳንዳችን በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ሰፊውን ጊዜ እየተሻማብን ያለው ማህበራዊ ሚዲያ ነው። ስለ ማህበራዊ ሚዲያ ዊኪፒዲያ ያስቀመጠውን አጠር ያለ ትርጉም ስንመለከት፤-
“ማህበራዊ ሚዲያ ማለት፤ ሰዎች በኢንተርኔት የሚገናኙበት ወይም የሚነጋገ ሩበት የድረገጽ ዘርፍ ነው። “ሚዲያ” ማለት ማህደረ-መረጃ ወይም መረጃ ማሰራጫ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ዝነኛና ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ድረገጾች እንደ L5a፣ uÊp፣ ¢•5s ግራም ወዘተ… ይጠቀሳሉ። ከዚህ በላይም በየቋንቋው ብዙ ሌሎች ድረገጾች ማግኘት ይቻላል።” በማለት አስቀምጦታል።
እንደ ኢንስታግራም፣ ትዊተርና ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ምንም እንኳን ፈጣን መረጃዎችን በፍጥነት የሚያቀብሉን ቢሆንም፤ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ደግሞ እንደአንድ አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ ወይም የእህል ውሃን ያህል ቦታ ከሰጠናቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
ስለሆነም፤ በህይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ይሁንና፤ እነዚህን ሚዲያዎች በአዎንታዊ ወይም ለመልካም ነገሮች ስንጠቀምባቸው በእኛ በተጠቃሚዎቹ ህይወትም ሆነ በሌሎች ላይ እሴት ይጨምራሉ። በተቃራኒው ደግሞ፤ በአሉታዊና አፍራሽ በሆነ መንገድ ስንጠቀምባቸው ቅድሚያ በኛ በተጠቃሚዎቹ፤ በመቀጠል በዙሪያችን ባሉ ሰዎች፤ ከፍ ሲልም በማህበረሰብና በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው።
እንግዲህ ዘመኑ የመረጃ ነውና “መረጃ አይናቅም አይደነቅም” እንደሚባለው አብዛኛው ሰው ከተለያዩ ቦታዎች በተለይም በእጅ ስልኩ መረጃ በቀላሉ እንደሚያገኝ ይታወቃል። በተለይም ወጣቱ በሚይዛቸው ዘመናዊ ስልኮች አማካኝነት በኢንተርኔት ከሀገር ውስጥ እስከውጭ ሀገራት ድረስ በመገናኘት የተለያዩ ጠቃሚም ሆኑ ጎጂ መረጃዎችን በመለዋወጥ ውድ ጊዜውን ሲጠቀምም/ሲያባክንም ይስተዋላል።
አንዳንድ ጊዜማ፤ አጠገባችን ስላለው ሰው እንኳን ግድ የማይሰጠንና አጠገባችን የተቀመጠው ሰው ይሁን አውሬ የማናስተውል፤ ሲያናግሩን አዳምጠን መልስ የማንሰጥ፤ ምናልባት ትንሽ ይሉኝታ ቢጤ ሲጎበኘን ብቻ ሳናዳምጥ እ…እ…እ አዎ… አዎ የምንል ብዙ ሰዎች እንዳለን በየዕለቱ የምናየው እውነታ ነው።
በእርግጥ ዘመኑ የቴክኖ ሎጂ ነውና በአሁን ወቅት፤ ሁሉም ዜጋ በማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ጋዜጠኛ መሆን ችሏል። ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት፤ ገና የዴሞክራሲ ጭላንጭል በሚታይበትና የፖለቲካ ትኩሳት በበረታበት በዚህ ዘመን ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እንዳመዘነ መታዘብ ይቻላል። ለዚህም ወቅትና አጋጣሚን እየጠበቁ የሚሰራጩ በርካታ መረጃዎች ብሔርተኝነትን፣ ፅንፈኝነትንና የሐይማኖት አክራሪነትን መሰረት ያደረጉና ህብረተሰቡን እርስ በእርስ የሚያጋጩ መሆናቸው በራሱ ዋነኛ ማሳያ ነው።
ከላይ እንደቀረበው ሁሉም ዜጋ በማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኛ መሆን የሚችልበት አጋጣሚ የተፈጠረለት በመሆኑ በርካታ መረጃዎች ያለገደብ ይንሸራሸራሉ። በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት የሚንሸራሸሩት መረጃዎችም ለህብረተሰቡ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ ቢሆኑም ፍሬውን ከገለባ መለየት ካልተቻለና በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በሚያስከትለው ጉዳትም የመጀመሪያ ተጠቂዎች እኛው ነን።
ከዚህም በላይ ማህበራዊ ሚዲያ በእያንዳንዳችን ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ በፈቀድንለትና በሰጠነው ቦታ ልክ፤ አንዳንዴም ከአቅም በላይ ሆኖ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ አሉታዊ ተፅዕኖውን እያሳረፈብን ይገኛል።
ዶክተር ወልደአብ ተሾመ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር፤ ማህበራዊ ሚዲያ በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖና በተለይም ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ጭልጥ ብሎ በመጥፋቱ ምክንያት ማህበራዊ ግንኙነቱ ላልቶ ከማህበረሰቡ ማግኘት የሚገባውን ነገር ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራሉ።
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ ማህበራዊ ሚዲያ በዋናነት የሚያስከተለው ችግር የሰዎችን ማህበራዊ ግንኙነት፣ የእርስ በእርስ ተግባቦትና ጠንካራ የሆነ ትስስር ከማላላቱም በላይ እያጠፋው እንደሚገኝ ገልፀዋል። ለምሳሌ፤ በአሁን ወቅት እያንዳንዱ ወጣት የራሱ የሆነ የእጅ ስልክ አለው። በዚሁ ስልክ አማካይነትም ብዙ ጉዳዮችን ይከታተላል። አጠቃላይ ትኩረቱን ሁሉ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማድረግ ሙሉ ጊዜውን ይሰጣል።
አንድ ሰው ደግሞ ሙሉ ጊዜውን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ካዋለ ከቤተሰቡ፣ ከህብረተሰቡ፣ ከትምህርት ቤቱና ከተለያዩ ሰዎች ማግኘት የሚገባውን በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች ማግኘት አይችልም። ምክንያቱም፤ ትምህርት ቤትም ቢሄድ ከተለያዩ ሰዎች ጋርም በአካል ተገናኝቶ ሀሳብ ለሀሳብ በመለዋወጥና በማህበራዊ ግንኙነቱ ውስጥ የሚያገኘው ጥቅም በእጅጉ የላቀ ነው።
ብዙ ጊዜ እንደታዘብኩት፤ ከወጣቱም በላይ ትላልቅ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ በተያዩ ቦታዎች በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ሲገናኙ እርስ በእርስ ከመወያየትና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ፤ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ብቻ በማተኮር እዚያ ላይ የሚያገኙትን መረጃ ሲያነቡና ሲያዳምጡ አጋጥሞኛል። ይህ ደግሞ ወደፊት ለሚኖረን ማህበራዊ ግንኙነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል።
በአብዛኛው ከማህበራዊ ሚዲያ የምናገኛቸው መረጃዎች ጠቃሚም ጎጂም መሆናቸው ይታወቃል የሚሉት ዶክተር ወልደአብ፤ ነገር ግን መረጃዎቹን አይቶ ብዙ ማመዛዘን የማይችል ሰው በተለይም ወጣቱ መረጃውን መሰረት በማድረግ የተሳሳተ አመለካከት ሊያራምድ ይችላል። በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው፤ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ጽሁፎች ስሜት ኮርኳሪና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከትቱ በመሆናቸው ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሲመሩት ቆይተዋል።
ከዚህም ሌላ፤ አንዳንዴ በፌስቡክ ተዋውቀው ትዳር የሚመሰርቱ አሉ። ትዳር መመስረቱ መልካም ነገር ቢሆንም፤ ሳይተዋወቁና ሳይግባቡ ትዳር መስርተው ሌላ ችግር ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። በአጠቃላይ ማህበራዊ ሚዲያ የራሱ የሆነ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ እንዳለው ሁሉ፤ ከማህበራዊ ሚዲያ የሚገኘውን መረጃ በሙሉ ከመጠቀም ይልቅ በጥልቀት ማጤንና ማመዛዘን የተጠቃሚው ግዴታ መሆኑን በመናገር ዶክተር ወልደአብ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
እርግጥ ነው፤ አሁን አሁን ለእያንዳንዱ ጉዳይ ቀዳሚ የመረጃ ምንጫችን አድርገን የምንጠቀመው ማህበራዊ ሚዲያ በብርቱ እያገለገለን ይገኛል። ለምንማረው ትምህርት ተጨማሪ መረጃም የምናገኘው በቀላሉ በእጅ ስልካችን ኢንተርኔት በመጠቀም ነው። ከዚህም በላይ በዚሁ በማህበራዊ ሚዲያ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ማህበራዊ ግንኙነት የምንከውንበት ግንባር ቀደም መሳሪያችን ይህው የእጅ ስልካችን ነው።
ታዲያ፤ በዚሁ በስልካችን አማካኝነት ለቅሶ እንደርሳለን፤ ያዘነ እናፅናናለን፤ የታመመ እንጠይቃለን፤ የወለደ እንመርቃለን፤ ለሰርግና ለልደት መልካም ምኞት እንላላካለን፤ ለበዓል እንኳን አደረሰህ/አደረሰሽና አደረሳችሁ እንባባላለን፤ ነገር ግን፤ ብዙዎች እንደሚስማሙት ማህበራዊ የሆነውን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ትስስር፤ እንዲሁም በክፉም ይሁን በደግ ጊዜ አጠገብ መሆንን እየሸረሸረውና አካላዊ ቀረቤታን እያጠፋው፤ በአንጻሩ ግለኝነትን እያጠነከረው መጥቷል።
በስራ ቦታም ይሁን በመዝናኛ፤ እንዲሁም በመኖሪያ ቤታችን ሳይቀር እያንዳንዳችን የራሳችንን ደሴት ፈጥረን ግለኝነትን አጥብቀናል። ማህበራዊ ሚዲያን መሸሸጊያና መደበቂያ በማድረግ ጓደኛ፤ ቤተሰብ፤ ትምህርትና መዝናኛ አድርገነዋል። ይህ ደግሞ ግለኝነቱን ይበልጥ እያገዘፈው በመምጣቱ በዙሪያችን ስላሉ ሰዎች ግድ እያጣን ከነሱ የሚገኙትን ቁምነገሮችም ሳናገኝ ቀርተናል። አጠቃላይ ጉዟችን ማህበራዊ ሚዲያ በቀደደልን ቦይ መፍሰስ ሆኗል።
በተለይም አሁን አሁን ጊዜው የፈቀደላቸው አክቲቪስቶች፤ ፖለቲከኞች፤ ብሔርተኞችና ኃይማኖተኞች በሚያደርጉት አንዳንድ ያልተገባ እንቅስቃሴ ማመዛዘን የማይችለውን ወጣት ይዘውት ሲጠፉ ይስተዋላል። በተለይም ራሳቸውን ደብቀው የተለያዩ ስሜት ኮርኳሪና አነሳሽ የሆኑ መልዕክቶችን በመልቀቅ ህብረተሰቡን፤ በተለይም ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ በርካታ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች አሉ።
ታዲያ እነዚህ ግለሰቦች እነዚህንና መሰል ድርጊቶችን በመልቀቅ ህብረተሰቡን ከማሸበርና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከመምራት እንዲቆጠቡ መንግስት አስፈላጊውን ርምጃ ሊወስድ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ክፍል ከማህበራዊ ሚዲያ የሚያገኘውን ማንኛውም መረጃ እውነት ነው ብሎ ከመቀበል ይልቅ ፍሬውን ከገለባ ለመለየት የማመዛዘንና የማጣራት ግዴታውን ቢወጣ መልካም ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በፍሬህይወት አወቀ