
አዲስ አበባ፡- መንግሥት የጀመረውን ህግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ አስታወቀ።
የፕሬስ ሴክሬታሪዋ ቢልለኔ ስዩም ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት መንግሥት የጀመረውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮች እንዲቆሙ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነና ይሄንንም እንደሚቀጥልበትም በመግለፅ ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በሰላማዊ መንገድ ብቻ ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚኖርበት ተናግረዋል። የመንግሥት ዋነኛ ስራ የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ በመሆኑ የሚወሰዱት እርምጃዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
«በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ ነው» ያሉት ሴክሬታሪዋ፤ ከለውጡ በፊት ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ተደርሶ እንደነበር በማስታወስ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ሚኒስትር ከማቋቋም ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ከሙስና ጋር በተያያዘ የተጀመረውም የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራ የአንድ ብሔር ላይ የሚያተኩር እንዳልሆነና በጸረ ሙስናና በዓቃቢ ህግ የተጀመሩት ስራዎች የሚቀጥሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከተጀመረው ሪፎርም ጋር ተያይዞ እየመጡ ያሉት ለውጦች ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ገልጸው ለችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄ መጠቀም፣ ሰላም ለማስጠበቅና የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር የተሰሩት ስራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሴክሬታሪዋ ጨምረው እንደተናገሩት ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አለው። በመድረኩ በሀገር ውስጥ ያሉና ከውጪ የገቡ ገና ያልተመዘገቡ፣ በትጥቅ ትግል የነበሩ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን በመግለጽ ይህም አብሮ ለመስራት ከለውጡ ጋር አብሮ ለመራመድና የተሻለ የፖለቲካ ምህዳርና ባህል ለመፍጠር እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ