የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 700 ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ያካተተ ነው። ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የመምህራንን መብትና ጥቅሞችን በማስከበር፤ ግዴታዎችን በማሳወቅ ዙሪያ እንደሚሰራ ይታወቃል። ማህበሩ እስካሁን ምን አይነት ስራዎችን ሲሰራ ቆየ ? ምንስ ችግሮች አጋጠሙት ? የመምህራን የተለያዩ ጥያቄዎች በምን መልኩ እንዲስተናገድ እያደረገ ነው? በሚሉና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ለዶክተር ዮሐንስ በንቲ ጥያቄዎችን አቅርበን ምላሻቸውን እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምን ምን ስራዎችን እየሠራ ነው? ከሚለው እንጀምርና ሌሎች ጥያቄዎችን እናስከትላለን።
ዶክተር ዮሐንስ፡- እሺ! መምህራን ማሕበሩ ቀድሞ ይሠራ እንደነበረው ዓላማዎችን ለማስፈፀም የሚመነዘር ስልታዊ ዕቅድ እያወጣ በዓመታዊ ዕቅድ እየተመራ ዓመታዊ ምክር ቤት እያካሔደና በየአራት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ እየተሰበሰበ ቀጥሏል። ከመምህራን ጥቅማጥቅም፣ ከትምህርት ጥራትና ከሌሎችም አገራዊ አጀንዳዎች ጋር ተያይዞ አጀንዳ ቀርፆ እየሠራ ይገኛል። ሃላፊነቱንም በትጋት በመወጣት ላይ ነው።
አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ በማድረግ አፍሪካን በመወከል የዓለም የመምህራን ቦርድ አባል በመሆናችን አጠቃላይ ከመምህራን ጋር ተያይዞ ድምፅ በሚያስፈልግበት ቦታ በሙሉ በመሳተፍ አስተዋፅ እያደረግን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- መምህርነት የሞያዎች ሁሉ መሠረት ነው። በዓለም ቀርቶ በአገር ውስጥ ያለው የመምህራን ቁጥር ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር ማህበሩ ምን ያህል ጠንካራ ነው ይላሉ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ጥንካሬ እንደእይታ ነው። በእኛ በኩል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አምስት ዓላማዎች አሉት። እንደአጣዳፊነታቸው መጠን ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲተገበሩ እየሠራን ነው። ለምሳሌ ከትምህርት ልጀምርና ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል። ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ጥናትና ምርምር ማካሔድ ነው። የተካሔዱ ጥናቶችን ደግሞ መድረክ ፈጥሮ ውይይት እንዲካሔድባቸው ያደርጋል።
እንደወቅቱ ሁኔታ ጥናት ሊደረግባቸው የሚገቡ ወይም መምህራኖች አጥንተው በእጃቸው ካለ ለመለየት የትኩረት ነጥቦችን ለይተን ለማወዳደር ለምሁራን የጥሪ ወረቀት እናሰራጫለን። ወረቀት መበተን ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃንም በማስተዋወቅ ጥሪ በማድረግ ሰባት ወረቀቶች መርጠን በየዓመቱ ሰኔ የትምህርት ጥራት ኮንፈረስ እናካሒዳለን። ኮንፈረሱ ላይ መምህራን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካሎች ተገኝተው ክርክር ተደርጎ ግብዓት ይወሰዳል።
በኮቪድ ምክንያት ከተቋረጠው ውጪ ለስምንት ዓመታት ሲካሄድ ነበር። በተጨማሪ በቃለጉባኤ ታትሞ ለሚመለከታቸው አካላት ለፖሊሲ አውጪዎችና ለትምህርት ሚኒስቴር ይላካል። እንዲሁም የዓለም የመምህራን ቀንን ምክንያት በማድረግ ጥቅምት 5 ላይ የሁለት ቀን ኮንፈረንስ እናዘጋጃለን። በዚህ ኮንፈረስ ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ቁልፍ ነጥቦች ተለይተው እዚህ ላይ ጥናት ማድረግ የምትፈልጉ ብለን ተመሳሳይ ጥሪ እናደርጋለን። እዛ ላይም 15 ጥናታዊ የምርምር ፅሁፎች ይቀርባሉ።
የተሻለ የመምህራን ማህበር እንቅስቃሴ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የዓለም የመምህራን ቀንን ምክንያት በማድረግ ኮንፈረሱን የሚያዘጋጁ ሲሆን፤ ከክልል ማህበሮቻችን ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኮሌጆች፣ ከቴክኒክና ሞያ ተቋማት አቅም በፈቀደ መጠን ኮታ እየተሰጠ እንዲሳተፉ ይደረጋል። በተመሳሳይ መልኩ የውይይቱ ሰነድ አጠር ባለ መልኩ ተዘጋጅቶና ታትሞ ለፖሊሲ አውጪዎች ይላካል።
ሌላው አቅም በፈቀደ መጠን ምልከታ (ሱፐርቪዥን) ላይ እንሰራለን። የዓለም አቀፍ የመምህራን ቦርድ ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ትምህርትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በተለይ ትምህርት ቤቶች ላይ ችግሮች ሲያጋጥሙ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ድምፃችንን እናሰማለን። ለምሳሌ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ትምህርት በተቋረጠ ጊዜ እንዴት አድርገን ይህን እናካክሳለን በሚሉት ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው ውይይት ሲደርግ ነበር። እነዛን ተሞክሮ እያመጣን ለአገር በሚመች መልኩ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ። ከማዕከል ጀምሮ የክልል ማህበራት ተመሣሣይ ሥራዎችን ይሠራሉ። የዓለም የመምህራን ቀን ላይም አንድ ምርጥ መምህር በመምረጥ የዕውቅና ሰርተፍኬት እና አነስተኛ የገንዘብ ሽልማት እንሰጣለን።
በጥቅማ ጥቅሞች ላይም በተመሳሳይ መልኩ እንሰራለን። የተለያዩ ማበረታቻዎች ላይ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና ለመምህራን በሚሰጡ የትምህርት ዕድሎች ላይም የኮሚቴ አባል ነን። ከአገራዊ ልማት ጋርም የአባይ ግድብ ላይም እንሰራለን፤ ሠርተናል። የተለያየ ጉዳት ሲደርስ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም ምላሽ እንሰጣለን። ሌላው ከሠላም ጋር ተያይዞ ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ ተጨባጭ ሥራዎችን ሠርተናል።
አዲስ ዘመን፡- የመምህራን ጥቅማጥቅም ጉዳይ ሲነሳ ማህበሩ ትኩረቱ አዲስ አበባ ላይ እንደውም የሚሠራው ከዩኒቨርሲቲ በታች ያሉት ላይ ብቻ ነው የሚል ቅሬታ ከመምህራን ይደመጣል። በተለይ በክልል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ከቤት ጋር ተያይዞ ትልቅ ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ። በእርግጥ ማህበሩ የዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም በክልል ያሉ መምህራንን በሚመለከት እኩል እይታ አለው?
ዶክተር ዮሐንስ፡- የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አገር አቀፍ ነው። አገር ውስጥ ያሉ መምህራን በሙሉ የተደራጁበት እና እነርሱን በሚመለከት በተመሳሳይ ሁኔታ ክትትል እናደርጋለን። ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ነባር የመምህራን ጥያቄ አለ። ይህ ጥያቄ ከ50 ዓመት በላይ የፈጀ ነው። እኛ ዕድለኞች ሆነን በእኛ የአመራርነት ዘመን ተፈቅዷል። በ1985 ዓ.ም ቤት ወይም ቤት መሥሪያ ቦታ ለመምህራኖች እንዲቀርብ ጥያቄ ቀርቧል። ነገር ግን ከሌሎች ዜጎች በተለየ መልኩ መምህራን ለማየት እንቸገራለን የሚል ምላሽ ተሰጥቶ ነበር። በኋላ በ2001 ዓ.ም በግልፅ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ ተጠይቆ ትምህርት ሚኒስቴር እና የመምህራን ማህበሩ ሁኔታውን ያዘጋጁ ሲባል፤ እስከ 2008 ዓ.ም ክርክር ተደርጎ ይሁንታ ካገኘ በኋላ ተፈቅዷል። ለመስማማት ወደ ሰባት ዓመት ፈጅቶብናል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በ2008 ዓ.ም ክልሎችም እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ እያፀደቁ ተግባራዊ እንዲደረግ ተብሏል። እስከ 2013 ዓ.ም ባለን ሪፖርት በአገር አቀፍ ደረጃ 110 ሺህ መምህራን ቤት ወይም የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አግኝተዋል። ከዛ ወዲህ የተጠናቀረ ሪፖርት አልሰበሰብንም፤ ብንሰበስብ በእርግጠኝነት ከዚህ በላይ ይሆናል።
አዲስ አበባ ላይ የተገኘው ቤት የመስሪያ ቦታ አይደለም፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ነው። ለዛውም ተጓቷል። 2009 ዓ.ም ላይ አምስት ሺህ አካባቢ ለሚሆኑ መምህራን የኮንደሚኒየም ቤት አቅርቦት ተፈቅዶ ነበር። በክልሎች ደግሞ አንዳንዶቹ ቤት መስሪያ ቦታ ሲሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤትም የሠጡ አሉ። እንደውም ከአዲስ አበባ ይልቅ የክልሎቹ የተሻለ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች በማህበር ተደራጅተው ቤት የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መወሰኑን መረጃ አለኝ። አዲስ አበባ ላይ ተጠቃሚ ከሚሆኑት የመንግስት ሠራተኞች መካከል መምህራን ይገኙበታል። ስለዚህ ትኩረታችን አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ላይ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ትኩረት የሚፈልጉ ክልሎች እንዳሉ እናውቃለን፤ በእነርሱ ላይም ጠበቅ አድርገን እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- ከአካባቢ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ድረስ ትኩረታችሁ በእኩል ደረጃ አይደለም እየተባላችሁ ትታማላችሁ። ለምሳሌ ብዙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤት ወይም የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አላገኙም። እንደውም በአንዳንድ ክልሎች ለዩኒቨርሲቲ መምህራን መሬት እንዳይሠጥ የሚል ደብዳቤ እስከመበተን የደረሱ አሉ ይባላል፤ይህንን እንዴት ታዩታላችሁ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ትክክል ነው፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የቤት ጉዳይ የሚታየው በተለየ ሁኔታ ነው። የ2008 ዓ.ም የቤት ፓኬጅ ሲፀድቅ ለአጠቃላይ ትምህርት ብቻ የታሰበ ነበር። ነገር ግን ቴክኒክና ሞያም በትግል እንዲገባ ተደርጓል። በወቅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተነጋገርነው ዩኒቨርሲቲዎች በቂ አቅም አላቸው፤ ለጊዜው ግቢያቸው ውስጥ ቤት በመገንባት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፤ እንዲሁም አነሱም በዛም የቤት አበል ያላቸው በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆን የለባቸውም ተብሎ ነበር። እንደውም የቴክኒክና ሞያ ተቋማትም መውጣት አለባቸው ብለው ነበር። ነገር ግን በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በየአንዳንዱ ወረዳ አንዳንድ የቴክኒክና ሞያ ተቋማት ይኖራሉ ተብሎ በመታሰቡ ስርጭቱ ከበዛ ከአጠቃላይ ትምህርት ቤት ብዙም ስለማይለዩ ቢያንስ እነዚህ መግባት አለባቸው ብለን ተከራክረን የእነርሱ መግባት ችሏል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የቤት ፓኬጁ አይፀድቅም የሚል ስጋት ስለነበረበት የዩኒቨርሲቲ መምህራኖቹን ጉዳይ በሒደት እናስከትላለን ብለን ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ መምህራንን የሚያካትት ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም በሥራ ላይ ሆነው ብቻ ሳይሆን ጡረታ ወጥተውም የሚኖሩበት ዘላቂ ሃብት እንዲኖራቸው ጠይቀናል። ለጊዜው በዛ መልክ ቢቀጥልም፤ በየምክር ቤቱ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ እኛም ግፊት ስናደርግ ኖረናል።
በተለይ በ2013 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተደራጅተው አንድ ላይ ያመጧቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የመኖሪያ ቤት ነው። ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አንዳንዶቹ እየተመለሱ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ገና ብዙ ሥራን የሚጠይቁ ናቸው። አሁን ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ቤት መፈቀድ አለበት የሚል ግፊት እያደረግን ነው። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው። መፍትሔ ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከዛ ፓኬጅ አንፃር ከሆነ በእርግጥ አይካተቱም ነበር። ከዛ ውጪ ግን ጭራሽ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የአካባቢው ተወላጅ ሆነም አልሆነ እንደማንኛውም ሰው ቤት ወይም መኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም እያገለገለ ያለው ያንኑ ሕዝብ ነው።
የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከማስተማር እና ምርምር ከማድረግ በተጨማሪ የማህብረሰብ አገልግሎት ሥራንም የሚያከናውኑ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ማንኛውም ዜጋ የሚያገኘውን መብት እና ጥቅም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማግኘት አለባቸው። በእርግጥ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ተለይቶ መሬትና ቤት እንዳይሰጥ የሚል ደብዳቤ የሰጠ አካል ካለ ደብዳቤውን አግኝተን ተጠያቂ መሆን ያለበትን ተጠያቂ ብናደርግ ደስ ይለኛል። በፓኬጅ የሁሉም ዩኒቨርሲቲ መምህራን መኖሪያ ቤት ሊኖራቸው ይገባል። ምክንያቱም ለዩኒቨርሲቲ መምህራን መኖሪያ ቤት ማደሪያ ብቻ ሳይሆን መስሪያም ጭምር ነው።
መምህር እንደሌላ የመንግስት ሠራተኛ ከስራ ሰዓት ውጪ በእረፍት ቀንም ጭምር በቤታቸው ሳይቀር የምርምር ሥራን ይሠራሉ። ሁሌም ያነባሉ፤ ይዘጋጃሉ። ለዚህ ቤት ያላቸው እና የተረጋጉ መሆናቸው ለመማር ማስተማሩም ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር በዚህ ጉዳይ ላይ መምህራን ማህበሩ አጥብቆ የሚሠራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በየዩኒቨርሲቲው እና በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች የመምህራን እና የሠራተኞች ማህበራት አሉ? ማህበራትን መመሥረት ላይ ክልከላ የለም?
ዶክተር ዮሐንስ፡- አዎ! መምህራን ማህበር አለ። ማን ይከለክላል? ሰሞኑን ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ላይ የነበረውን መምህራን ማህበር አጠናክረን መጥተናል። አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበርም አለ። ከእርሱ ማህበር ጋር አንድ ላይ በመሆን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርን እንዲደግፉ የተላለፈ ደብዳቤ አለ። እርሱን መሠረት አድርገን እንዲደራጁ እንደግፋለን።
አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች በንቃት ያለመሳተፍ ሁኔታ አለ። ነገር ግን በ45ቱም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ተደራጅቷል ማለት አይቻልም። የሚከለከልበት ምክንያት የለም። ነገር ግን የሠራተኛ ማህበር እና የሞያ ማህበር አደረጃጀት ይለያያል። በግልፅ የመምህራን ማህበርን የሚከለክል የለም፤ ነገር ግን ቢሮክራሲ ሊኖር ይችላል። የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርም አገር አቀፍ ሆኖ ለመመስረት 17 ዓመት ፈጅቶበታል። በ1940 ዓ.ም ተመስርቶ አገር አቀፍ እውቅና ያገኘው በ1957 ዓ.ም ነው። ፈቃድ የተሰጠው ደግሞ ቆይቶ ነው። ወደፊት የመምህራን ማህበሩ ወደ ሠራተኛ ማህበር ያድጋል ብለን አስበናል።
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርሲቲ መምህራኖች በዓይነትም ሆነ በገንዘብ የተለያዩ ጥያቄዎች ማቅረባቸው ይገለፃል። አንዳንዶቹ የተጋነኑ እና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያካተቱ አይደሉም ይባላል። የቀረቡት ጥያቄዎች ምን ምን ናቸው ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- እናንተ ቀድማችሁ የሰማችሁት ጥያቄ ምንድን ነው?
አዲስ ዘመን፡- ከዶላር እስከ ሽቶ ጥያቄ አቅርበዋል ይባላል። ይህ ስም ማጥፋት ነው። ወይስ እውነት ነው?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። አሁን ጥያቄውን ብዘረዝር እጅግ ብዙ ናቸው። በ2013 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበራት መጋቢት አካባቢ ወደ 14 የሚሆኑ ጥያቄዎች በዝርዝር አቅርበዋል። ይህን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 30 አቅርበን ነበር። ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት እና ከሥራ ምዘና ጋር ተያይዞ የተቀመጠው አይመጥነንም በማለታቸው ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲሁም ከጥያቄዎቹ መካከል ተደጋጋሚ ግብር ይነሳል የሚል ሃሳብ የተካተተበት በመሆኑ ለገቢዎች ሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው ሁሉ ጥያቄዎቹን አቅርበናል። እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይገባቸዋል በማለት ደብዳቤ ፅፈን ልከናል። ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገቡ በሒደት ደግሞ የሚመለሱ አሉ።
ሁሉንም በአንድ ጊዜ መመለስ አይቻልም። ከ70 ዓመት ታሪካችን እንደተረዳነው ጥያቄዎች የሚመለሱት በሒደት ነው። የመኖሪያ ቤት ለመምህራን የሚል ጥያቄ መቅረብ የጀመረው በ1961 ዓ.ም ነው። በ1985 በግልፅ ቀርቦ ቅድሚያ ለመስጠት እንቸገራለን ተብሎ ነበር። እንደገና በ2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበራት ምስረታ 60ኛ ዓመት ሲከበር ጥያቄው ከቀረበ በኋላ መፍትሔ ቢያገኝ ይሻላል ተብሎ ከሰባት ዓመት መደራደር በኋላ በ2008 ዓ.ም ምላሽ ተገኘ።
የመምህራን ማህበራት ጥያቄውን በማቅረቡ ምክንያት እና ፀድቆ ወደ ክልሎች በመላኩ፤ ክልሎች ደግሞ ይህንን ተገን አድርገው ለሌሎችም የመንግስት ሠራተኞችም የሠጡ አሉ። ይህ ሲታይ ጥያቄው ከቀረበ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መመለሱ አይቀርም። ጥያቄው ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ ምላሽ ማግኘቱ አይቀርም። ለምሳሌ አንዱ የቀረበው የመኖሪያ ቤት ነው። የቤት መስሪያ ቦታ ተከልክለናል የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ይሔ ምላሽ ማግኘት አለበት። ሥራችን በደንብ አልተለካም የሚል ጥያቄ ቀርቧል፤ ትክክል ነው። ይህ የእኛም እምነት ነው። መስተካከል አለበት። የዝውውር ጥያቄ ቀርቧል። ውሎ ያደረ እንደማበረታቻ የሚታይ የዝውውር ጥያቄ አለ። ድሮም በደርግ ጊዜም በንጉሱ ጊዜም ይሠራበት ነበር። አዲስ ምሩቅ ሩቅ ቦታ ሔዶ ያገለግላል። ነባሮቹ ደግሞ የተሻለ መሰረታዊ አገልግሎት ወደሚገኙበት ቦታ የሚቀየሩበት ሁኔታ ነበር። አሁን ግን ይህ የሚደረገው በትውውቅ ብቻ ሆኗል። ግልፅ መመሪያ የለውም። ከጥያቄዎቹ መካከል ይህ አንዱ ነው።
ግልፅ መመሪያ መኖር እንዳለበት የመምህራን ማህበሩ ያምንበታል። የሥራ ክብደት ምዘናው ላይ አንድ ደረጃ ምላሽ ተሰጥቷል። ነገር ግን የረዳት ምሩቃን እና የፕሮፌሰሮች አልተነካም። ይህቺ አንድ ደረጃ የተሻሻለችው ለጥያቄያችን መልስ በቂ አይደለችም ብለዋል። ይህ በእኛ በኩልም መታየት አለበት ብለን እየተከታተልን ነው። የቤት አበል ላይም ሥራ እየተሠራ ነው፤ ገና አልተጠናቀቀም።
ሌላው የክፍያ ተመን ጉዳይ ማለትም ለመጀመሪያ እና ለሁለተኛ ድግሪ ማሟያ ፅሁፍ የማማከር ሥራ ሲሠሩ፣ ምርምር ሲደረግ የሚከፈለው ክፍያ ከዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ይለያያል። መመሪያው ተመሳሳይ ቢሆንም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲ አልገባንም ብሎ ቢሮክራሲ ያበዛል። ምክንያቱም በተለያየ ጊዜ የተለያየ መመሪያ በመውጣቱ ነው። ስለዚህ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ሆኖ እንዲተገበር የተበታተነው ሰብሰብ ተደርጎ አንድ መመሪያ ተዘጋጅቷል። መጠኑ ላይ ቅሬታ ቢኖርም ተመሳሳይ ክፍያ እንዲኖር ተመቻችቷል።
በተረፈ ግን ላፕቶፕ፣ ደሞዝ በዶላር ይከፈለን የሚል እና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበዋል። ጥያቄዎቹ ለምን ቀረቡ ማለት አይቻልም። ከ2013 በኋላ በዚህ ዓመት መጋቢት ላይ ባለፈው የጠየቅነው ምላሽ ዘግይቷል ብለው ተጨማሪ ጥያቄ አክለው እንደገና ጥያቄዎችን በ2014 አቅርበዋል። እኛ ደግሞ በድጋሚ ጥያቄዎቹን ከሸኚ ደብዳቤ ጋር አያይዘን ማን ምን መሥራት እንዳለበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲመለስ ጠይቀናል።
አዲስ ዘመን፡- በዶላር ይከፈለን ማለታቸውን ተከትሎ ብዙዎች እንዴት የአገሪቷን አቅም እያወቁ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ያቀርባሉ የሚል ሃሳብ ሲሰነዝሩ ይሰማል፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔ የምናገረው ለወከልኳቸው ለመምህራንም ሆነ ለመንግስት የመጨረሻ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ማንኛውንም ጥያቄ ለምን ቀረበ ከማለት ይልቅ ጥያቄው ምን ታስቦ እንደተጠየቀ መረዳት ያስፈልጋል። ኬኒያ ለመምህራኖቿ የምትከፍለው በሺሊንግ ነው በዶላር፤ ናይጄሪያ፣ ዑጋንዳ እና ሌሎች አገሮችስ የሚከፍሉት በምንድን ነው? ብሎ ማጥናት ይገባል። በዶላር ይከፈለን ተብሎ መጠየቅ ለምን ያስገርማል? ይሔ እኮ ተዓምር አይደለም። ሰው አገር እየጠየቀ ባለበት ጊዜ በዶላር ደሞዝ ጠየቀ ብሎ አጀንዳ አድርጎ ጊዜ መፍጀት ተገቢ አይደለም። ይልቁኑ ቁጭ ብሎ ይህ ጥያቄ የሚመለስበት ሁኔታ ላይ መነጋገር ይሻላል።
ሌላው የመንግስት ሠራተኛ ሶፍት ሲያገኝ መምህር ሶፍት እንኳን አያገኝም። ይህ ጥያቄ ለምን ቀረበ? የሚሉ አሉ ሌላው ካገኘ መምህር ለምን አያገኝም? በየቢሮ ጥሩ ሽታ እንዲኖር የሚረጭ ኤር ፍሬሽነር አለ። መምህር ቢጠይቅ ምን ነውር አለው? ከተቻለ ለእያንዳንዱ መምህር ካልተቻለ ደግሞ ፅዳት ሰራተኛ ክፍሎቹን ካፀዳች በኋላ እንድትረጭ በማድረግ ምላሽ መስጠት ይቻላል። ነገር ግን በተቃራኒው ለምን ይሔ ጥያቄ ቀረበ ብሎ ማጋነን አይገባም።
በእርግጥ መምህሩ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለባት ያውቃሉ። ነገር ግን በፊት የነበረው ደሞዛቸው አሁን ምንዛሪ በመጨመሩ ቀንሷል። የዶላር ምንዛሪ 30 ብር ሆኖና 52 ብር ሆኖ ልዩነቱ ግልፅ ነው። ዶላር ሲጠየቅ እንዴት እንፍታው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኛ በኩል ግን የቀረበውን ጥያቄ አገራዊ ሁኔታን በማሰብ ጉዳዩን በተረጋጋ መልኩ የያዝነው ቢሆንም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለጥያቄው ትኩረት መደረግ እንዳለበት መጋቢት 2014 ዓ.ም ላይ በድጋሚ ጥያቄዎቹን ለሚመለከታቸው ሁሉ ልከናል።
እኛ የእዚህችን አገር አቅም እናውቃለን። ከአገር የተነጠልን አይደለንም። አቅም የለም ብሎ ሁሉም ላይ ድፍን ያለ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ በቅርብ መመለስ የሚችለውን መመለስ ይገባል። ለምሳሌ 1500 ብር የቤት አበል ተከፍሎ ከእርሱም ግብር ይቆረጣል። ሌሎች ግን ከፍ ያለ የቤት አበል ያገኛሉ። ለእነዛ መክፈል የተቻለውን ለመምህራን ሲሆን ለምን መክፈል አይቻልም ይባላል። ጥያቄው የፍትሃዊነት ነው። አገር ድሃ ከሆነች ለሁሉም ነው። መምህራን ለማን ምን እንደሚከፈለው ከነፔሮሉ ያገኙታል። ስለዚህ ጥሩ የሚሆነው ጥያቄውን በምን መልኩ እንመልሰው የሚለው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእውነቱ ለመምህራን የሚከፈለው ደሞዝ የሚገባቸውን ያህል አይደለም ብለዋል። ይህ መታወቁ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ጥያቄው እንዴት ይፈታ የሚለውም መታየት አለበት። የሥራ ምዘና (ጂኤጂ) ማሻሻል ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። በመሰረቱ የሥራ ምዘና (ጂኤጂ) የትምህርት ሥርዓቱን መለካት የሚችል አለመሆኑን ቀድመን ገልፀናል። አሁን ሊመልሱ የሚችሉትን መመለስ፤ በረዥም ጊዜ መመለስ ያለባቸውን ወደፊት መመለስ ይገባል። ይሔ ከአሁኑ ሐምሌ ጀምሮ ይቀጥላል የተባለው የሥራ ምዘና ደረጃ የበለጠ መሻሻል አለበት። የቤት ኪራይ አበልም ለሌላው የሚከፈለው ለመምህሩ መከፈል አለበት። የኮሌጅ መምህራንም ተመሳሳይ ጥያቄ አላቸው።
ጫና መፍጠር ተገቢ ነው። ለጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል። መምህራን በእጃችን ያለው ትውልድ በመሆኑ ማስተዋል ያለብን ጉዳይ አለ። መምህር ጥያቄው እንዲመለስለት ብዙ መንገዶች አሉ። ለዛም እኛ ጭምር መግለጫ እየሰጠን ነው። አንዳንዶቹ የመመሪያ ጥያቄዎች አሉ፤ እነርሱን መመለስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ለተማሪ ቀለብ ገዝቶ ለመምህር ደሞዝ ከፍሎ እና አሻሽሎ አይችልም። ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው የሚል ምላሽ ከመንግስት ተሰጥቶ ነበር። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዮሐንስ፡– መምህራኖች ይህንን መቼ ጠሉት? ይህንን የአገሪቱ የመፈፀም ችግር እንጂ መምህራኖች ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲችሉ ይፈልጋሉ። ይህ በዓለም ደረጃ አለ። ነገር ግን ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እስኪችሉ የመምህራን ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የለበትም ከተባለ ችግር ነው። ምክንያቱም የሚጎዳው ትምህርት ነው። በዋናነት መታወቅ ያለበት የመምህራን ጥያቄ መልስ ለግለሰቦች ሳይሆን ለትውልድ ሲባል የሚፈፀም ነው።
መምህራን ተረጋግተው እንዲሰሩ፤ በትርፍ ሰዓታቸው ፎቶ ኮፒ ቤት እንዳይከፍቱ መሆን አለበት። አሁን ያለው ሁኔታ ይሄ ነው። መምህሩ መብላት እና መኖር አለበት። አሁን ረዳት ምሩቅ ደሞዙ 6100 ብር ነው። እነዚህ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ የቀሩ ልጆች ‹‹እኛ ደክመን ጥሩ ውጤት አምጥተን ዩኒቨርሲቲ ስንቀር፤ ተንጠልጥሎ የተመረቀው ግን ሌላ ተቋም ገብቶ ከኛ የተሻለ ይኖራል›› ይላሉ። ይሔ እውነት ነው። ይህንን ማየት ይገባል። በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቀው መምህር ይደጋገፋል፤ አብሮ የሚቆም ነው። ስለዚህ የዚህኛው መምህር ችግር ሲፈታ ሌላው ይበረታታል። የመምህር ደሞዝ፣ ቤት ኪራይ፣ ቀለብ፣ የቤተሰብ ድጋፍ እና ሌሎች ወጪዎች ሊሸፍን ይችላል፤ አይችልም የሚለውን ባለስልጣናት ማየት አለባቸው። ከተደማመጡ መምህር ይረዳል።
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መውጫ ፈተናን በሚመለከት ያሎት አስተያየት ምንድነው ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- እዚህ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይደመጣሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የአመራር፣ የመምህር፣ የሃኪም፣ የዳኝነት፣ የአገር መምራት፣ የውትድርና የጋዜጠኛ ወይም የየትኛውም ሞያ የብቃት ጉድለት የሚገናኘው ከትምህርት ጋር ነው። እነዚህ ሰዎች የትምህርቱ ውጤት ናቸው። ኢትዮጵያ ለምን ድሃ ሆነች ከተባለ ችግሩ ከትምህርት ጋር ይያያዛል። የትምህርት አቅርቦት አንድ ነገር ቢሆንም ዋናው ጥራትም ነው። ጥራት ወይም ብቃት ከተባለ ይሔኛው አንደኛው መንገድ ነው። ሕግ እና ሕክምና ላይ ቀድሞም ተጀምሯል። ስለዚህ እዚህ ላይ እኛ ድጋፍ አለን። የመውጫ ፈተና ሲሰጥ በጥንቃቄ ሞያውን መሠረት አድርጎ፤ የሚፈለገውን ዕውቀት በአግባቡ እንዲለካ ይደረግ የሚል እንጂ ሁሉም ይደግፈዋል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ረጅም ጊዜዎት እንደሆነ ይታወቃል። ይሄን የቆይታ ጊዜ የማህበሩ ህገ ደንብ ይፈቅዳል?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። የምርጫ ዘመን በየአራት ዓመቱ ነው። ብቃት ያለው ሰው ድጋፍ ካለው በየጊዜው መመረጥ ይችላል። የእኛ በጎ ነገር ይሄ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር በአማካኝ አንድ ሚኒስቴር የሚቆየው ለሁለት ዓመት ነው። በዚህ ጊዜ ብዙ አይሠራም። አንድ የስትራቴጂክ ዕቅድ ዘመን ሳይጠናቀቅ የሚሰናበት ሰው ብዙ ውጤታማ ሥራ መሥራት አይችልም። ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ነኝ። ብዙዎች ግን በመከራ ምናልባት ቢቆዩ ሰባት ዓመት ነው። ስለዚህ ባለበት እርገጥ ነው።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በ75 ዓመት ታሪኩ የዓለም አቀፍ የመምህራን ቦርድ አባል የሆነው አሁን ነው። አፍሪካን የምወክለው እኔ ነኝ። ቅድም ያነሳሁት የመምህራን ደረጃ በ1987 ስድስት ነበር። በ2004 ከስድስት ወደ ሰባት ከፍ አስደርገናል። ብቻዬን ሳልሆን ከቡድኔ ጋር አብረን ሰርተን፤ በ2008 ደግሞ ፕሳ ዘጠኝ አድርሰነዋል። የመኖሪያ ቤት ጉዳይም ያለፈውን ጥያቄ ቆፍረን በ2001 ዓ.ም ጥያቄውን አቅርበናል።
በተጨማሪ ይሔ ማህበር ሃብቱ መቀየር አለበት፤ ለመምህራን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለን ተነስተናል። መምህር መፅሃፍ ፅፎ ለህትመት ልመና እንዳይሄድ ባለ32 ፎቅ ሕንፃ እንገነባለን ብለን 2013 ላይ የመሠረት ድንጋይ ጥለናል። ስለዚህ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ማተሚያ ተቋም እንዲኖር እየታሰበ ነው።
የማህበር ፕሬዚዳንት መሆን ለግለሰቡ ከላይም ከታችም ጭቅጭቅ ነው። ነገር ግን አባላቱ ራሳቸው ፈልገው ከዚህ በላይ ሰው አያገልግል ብለው መወሰን ይችላሉ። ነገር ግን ሌሎች ደግሞ እዚህ ቦታ ላይ ማገልገል ራሱ መከራ ነው፤ ቆይቶ ማገልገሉ ልምዱ ይጠቅመናል ብለን እስከአሁን ቆይተናል። ባለፈው 2014 ዓ.ም ጥቅምት ላይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል። ተመርጫለሁ። ደሞዜም የአስተማሪ ደሞዝ ነው። ለመምህራን እና ለሌሎችም ድምፅ መሆኔ ያስደስተኛል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2/2014