መምህርት አሚና መሐመድ ዮሱፍ ሀገራቸውን በብርቱ ይወዳሉ። ዜጎችን ማገልገል ያረካቸዋል። የትኛውም የሰው ልጅ እንዲራብ፤ እንዲታረዝና እንዲጠማ አይሹም። በየትኛውም ሁኔታ ሲበደል፤ ሲገፋና ሲቸገር ማይት አይሆንላቸውም። ዛሬም በጡረታ ጊዜያቸው ማልደው ከቤታቸው በመውጣት ማታ ላይ የሚመለሱት እንባ አብሰው ረክተው ደስ ብሏቸው ነው። በዚህ መልኩ ሁለት ሶስት ሰው ነጻ ሳያደርጉ ወደ ቤታቸው ገብተው አያውቁም። በተለይ በባህልና በኢኮኖሚም ሆነ ሕብረተሰቡ ለሴቶች ባለው የተዛባ አመለካከት እየተጎዱ የመጡ ሴቶችንና የሀገርን ችግር ቢችሉ ከኪሳቸው ባይችሉ ሕብረተሰቡን በማስተባበር መቅረፍ የተለመደ ተግባራቸው ነው። ሕወሓት ከአንድም ሁለቴ በከፈተው ጦርነት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲሁም ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት በግላቸው በገንዘብና በጉልበታቸው እንዲሁም ሕብረተሰቡን በማስተባበር ድጋፍ በማድረጉ ረገድ ቀዳሚ ናቸው። ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበው ሰጥተዋል። በሶ፤ ቋንጣ፤ ድርቆሽ ፤ማኮሮኒ፤ ፓስታና የተለያዩ አልባሳት በእሳቸው አስተባባሪነት ከተደረገው ድጋፍ ይጠቀሳሉ። አሁንም ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ ባደረገው ወረራ በዚሁ መልኩ ያሰባሰቡትን ዱቄት፤ ሩዝ፤ ፓስታ፤ ማኮሮኒና የተለያዩ አልባሳት ሰብሳቢ በሆኑበት በድሬዳዋ ሴቶች ማህበር ቢሮ ውስጥ በማኖር ለመከላከያ ሠራዊቱና በጦርነቱ አካባቢ ላሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማድረስ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ይሄንኑ ድጋፍ ችግሩ እስከሚፈታ አጠናክሮ ለማስቀጠልም በትጋት ደፋ ቀና እያሉ ነው።
በድሬዳዋ ምድር እኝህን በጎ ሴት የማያውቅ የማሕበረሰብ ክፍል የለም። ማሕበረሰቡ በሁለት ጉዳዮች አብዝቶ ያውቃቸዋል። አንደኛው ለ36 ዓመታት ባገለገሉበት በመምህርነታቸው ሲሆን ሁለተኛው በበጎነታቸው ነው። በዚሁ በበጎነታቸው ከልጆቻቸው አልፎ በድፍን ድሬዳዋ ነዋሪዎች ማዘር ትሬዛ የሚል ቅጽል ስምም ተሰጥቷቸዋል። አሁን ላይ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ኃላፊነት ላይ ያሉ ተማሪዎችን ያፈሩበትን 36ቱን ዓመታት የመምህርነት ሙያቸውን ያሳለፉትም የቀለም ትምህርቱን ከማስተማር ባሻገር በነዚህ ዙሪያ አያሌ በጎ ተግባራቶችን በማከናወንም ነው። ከድሬዳዋ ከተማ ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር በሚርቅ የገጠር ክፍል የሚኖሩ በርካታ ልጃገረዶችን የኢኮኖሚ ችግር በግላቸውና በጋራ ድጋፍ በመቅረፍ ወደ ድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲመጡ ያደረጉበት የድሬዳዋ የገጠር ሴት ተማሪዎች መኖርያ አንዱ ማሳያ ነው።
በድሬዳዋ ከተማም ሆነ በአጠቃላይ በሀገራችን የመጀመሪያው በሆነው በዚህ የሴቶች ሆስቴል 38 የገጠር ገበሬ ማህበራት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን የሁለተኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋዳሽ አድርገዋል። ዛሬም በጡረታ ከተገለሉ በኋላ የመሰረቱትን ሆስቴል በዳይሬክተርነት እያገለገሉ የሚገኙት መምህርት አሚና ዛሬ ብዙዎቹ በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን በተለያየ መንገድ መጥቀም የሚችሉ እንደሆኑላቸው ይናገራሉ። ሁሉም በሥራ የመሰማራታቸው ምስጢር ድሬዳዋ ላይ ከሆስቴል የወጡ ተማሪዎች በተገኘው ሥራ ላይ እንዲመደቡ ካቢኔው መወሰኑንም ያወሳሉ። በክራንችና በዊልቸር የሚሄዱትን ጨምሮ በርካታ አካል ጉዳተኛ ሴቶች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ያነሳሉ። የተወሰኑትም ከዲግሪ በላይ በትምህርት ለመግፋት ወደ ውጭ ወጥተዋል። ባህላችን ዲግሪያችን ነው። በኋላ ላይ ዲግሪው የሚያመጣውን ባል እንጠብቃለን የሚል የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተዋል። በለውጡም ለ 38ቱ ገጠር ቀበሌ ማሕበረሰብ አርአያ መሆን ችለዋል። ዘንድሮም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ካሉ በርካታ ሴት ተማሪዎች መካከል በተፈጥሮ ሁለት እጅ የሌላትና የማትናገር ተማሪዎች በሆስቴሉ እንደሚገኙ ይገልፃሉ።
ሆስቴሉ ባይኖር አካል ጉዳተኞችን በሴትነት ከሚደርስ ተደራቢ ችግር ጋር እዚህ ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻል እንዳልነበረ የሚያወሱት መምህርቷ የዛሬ 14 ዓመት ሆስቴሉ ወደ ስራ ሲገባ የነበሩትን ተደራራቢ ፈታኝ ችግሮችም ሆስቴሉን ለመመስረት ካነሳቸው ምክንያት ጋር እያዋዙ አጫውተውናል።
እንዳወጉን ለመመስረት ያነሳሳቸው ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዘጠኝ የከተማና 38 የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማሕበር አላት። 38ቱ ቀበሌዎች ከድሬዳዋ ከተማ በትንሹ ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ከ14 ዓመት በፊት ታዲያ ከነዚህ ቀበሌዎች መጥቶ ድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መጥቶ የሚማር ሴት ተማሪ አልነበረም። ምክንያቱ ፈርጀ ብዙ ቢሆንም ገዢው የአካባቢው ማሕበረሰብ ሴት ተምራ የት ትደርሳለች የሚል ለሴት ልጆች የነበረው የተዛባ አመለካከት ነበር። ከዚህ ተነስቶ ትምህርት ቤት የሚልከው ወንድ ልጆቹን ነበር።
አሚና ከመምህርነት ወደ ትምህርት ቢሮ ተዛውረው አቅም ግንባታ ላይ መምጣታቸው ምክንያቱን እንዲመረምሩ አገዛቸው ። በአራት ከላስተር የተደራጀውን 38 የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ነዋሪ ማሕበረሰብን አወያዩ ። የኢኮኖሚ ችግር ስላለብን ሴት ልጆቻችንን ወደ ድሬዳዋ አምጥተን ማስተማር አንችልም። ማስተማር የምንችለው እስከ አራተኛ ክፍል ነው። ግፋ ቢልም ስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ነው የሚል ምላሽ ሰጧቸው። ከዚህ በኋላ ሴት ልጆቻቸውን መዳር እንደሚፈልጉም እቅጩን ነገሯቸው። ምክንያታቸው የሴቷ ማግባት የሚያስቀርላቸው የኢኮኖሚ ጫና እንዳለውም አስረዷቸው።
ሌላው ወደ ትምህርት ቤት የማይመጡበት ዋናው ችግር ሩቅ መሆኑና ቤት ተከራይቶ ማስተማር ያለመቻሉ ነበር፡፡ ድሬዳዋ ላይ በቅርበት የምትማሩበት ብታገኙስ ብለው ጠየቋቸው። ሁሉም በአንድ ቃል ልጆቻቸውን ልከው እንደሚስተምሩ ገለጹላቸው። ማረፊያ ያጡ አንዳንድ ሴት ልጆችን በግላቸው ማረፍያ እየሆኑ ያግዙ የነበሩት አሚና ጊዜ አላጠፉም ። ከውይይቱ መልስ በፍጥነት በቁጭት ሆስቴሉን የመገንባት ፕሮጀክት ቀርፀው ለመንግሥት አቀረቡ። ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሳይገጥመው ፕሮጀክታቸው ፀደቀና በ1999 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቀቀ።
ሆኖም ወቅቱ በበርካታ ፈተናዎች የታጠረ ነበር። ኮንትራክተሩ ቁልፉን ሲያስረክባቸውና ከስምንተኛ ክፍል ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያለፉ 47 ሴት ተማሪዎች መግቢያ ካርዳቸውን ይዘው ወደሳቸው መጥተው ነበር። በተጨማሪም ድሬዳዋ በከባድ ጎርፍ አደጋ የተጎዳችበት ፤በወቅቱ የነበሩ የካቢኔ አባላት ተቀይረው በአዲስ የተተኩበት ነበር። እንዲሁም ሌሎች በርካታ ችግሮች የነበሩበት ሆነ ፤ እርሳቸውም ለጊዜው በግላቸው ለ47ቱ ተማሪዎች በእለቱ ማረፍያና ምግብ እየሰጡ ለዘላቂ መፍትሄ ልጃገረዶቹን እያስከተሉ መጮህ ጀመሩ። ‹‹ልመናና ማሕበረሰብ ማስተባበር ይዋጣልኛል›› የሚሉት በጎዋ ሴት ኦሮሚኛ፤ አማርኛና አደሪኛን ጨምሮ አረብኛ፤ እንግሊዝኛ ጨምሮ ከስድስት በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች በደንብ መናገር፤ ማንበብና መፃፍ በመቻላቸው ከተለያዩ ባለሀብቶች 600 የውሃ ቱቦዎች ድጋፍ አገኙ። በዚህ ሆስቴሉን ካፀዱ በኋላ ደግሞ መብራት አልነበረውምና እንዴት ከጭለማ ወጥተው ጨለማ ውስጥ በማደር ተምረው ውጤታማ ይሆናሉ በማለት ደግሞ ወደ መብራት ኃይል ሄደው ጮሁ። አቅማቸው ኩራዝ ከመግዛት የማያልፍና በኩራዝ ማጥናት ከተማ ውስጥ የማይታሰብ እንደሆነና መንግሥት ውሃ መብራት ያስገባል ብለው ወተወቱ። በዚህም ተሳክቶላቸው የመብራት ብርሃን አገኙ ። በሌላ በኩል ደግሞ ልጃገረዶቹን ወደ ማረፍያው አስገብቶ ለማኖር ከአንሶላና ፍራሽ ጀምሮ ምግብና መጠጥ እንዲሁም በርካታ ነገሮች ያስፈልጉ ነበርና የመምህርቷ እግር አሁንም ለልመና ከመሮጥ አልቦዘነም። ወደ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አመሩ ከብዙ ውይይት በኋላ ልመና የሚሆንላቸው አሚና ኃላፊውን አሳምነው ማመልከቻ ጽፈው እንዲያስገቡ ተፈቀደላቸው። አስገብተውም አንሶላና ብርድ ልብስ፤ ፍራሽን ጨምሮ ሳህንና ሹካ ማኒኪያዎችና ብረት ድስት ተሰጣቸው። ይሄኔ በመኖርያ ቤታቸው፤ በሆቴሎችና በተለያዩ ቦታ ያሳረፏቸውን ልጃገረዶች ወደ ሆስቴሉ በማምጣት ማሳረፍ ቻሉ።
በጎዋ ሴት ልጃገረዶቹ በሆስቴሉ አርፈው ትምህርታቸውን መማር ከጀመሩ በኋላ በዩኒሴፍ የድሬዳዋ ፎካል ፐርሰን የነበሩትን ናይጀሪያዊት ሴት ሆስቴላቸውን እንዲጎበኙ አደረጉ ። በጉብኝቱም ሀስቴሉ ያለበትን ችግር ብሎም ለሴት ተማሪዎቹ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ በትምህርታቸው ስኬታማ እንደሚያደርጋቸው ነገሯቸው። በዚህም ተወካዩ ከ 350 ሺ ብር በላይ እርዳታ አገኙ ። ልጃገረዶቹን እንደ ፍርኖ ዱቄት ፤ማኮሮኒ፤ ፓስታና ሌሎች ተመጣጣኝ ምግቦች እንዲመገቡ ማድረግ ተቻለ።
በዚሁ መልኩ ዩኒሴፍ ለ10 ዓመታት ያህል ሆስቴሉን ሲደግፍ ቆየ። በርካታ ውጤታማ ተማሪዎችም መውጣት ቻሉ። ከ10 ዓመት በኋላ ዩኒሴፍ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም በማለት እዚህ ድረስ ካደረስናችሁ ራሳችሁን ቻሉ ሲል ደግሞ የክልሉ መንግሥት በጀት እንዲመድብለት አስደረጉ። ሆኖም በዓለማችን በተለይም ከተለያዩ ወቅታዊ ቀውሶች ጋር ተያይዞ በእጅጉ ካሻቀበው የምግብ ዋጋ ሊመጣጠን አልቻለም ። በተለይ በ2013 እና በ2014 ልጃገረዶቹ በእጅጉ የተራቡበት ነበር። ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አቅንተው ፓስታ፤ ሩዝ፤ማኮሮኒና ዱቄት ለምነው በማምጣት በጀቱን ደጉመው ማለፍ ቻሉ። አንሶላና ብርድ ልብስ አላቂ እንደመሆናቸው በየጊዜው ለማሟላት የማያንኳኩት በር ብዙ ነው። አጋጣሚዎችን በመጠቀምም የሚወዳደራቸው የለም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበር ጥምረት ሥልጠና ለመስጠት በመጣበት ጊዜ አባላቱን ወደ ሆስቴሉ በማምጣት ልጃገረዶቹ ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ በማሳየት እያንዳንዳቸው አዝነውና አልቅሰው ከአበላቸው ላይ አዋጥተው እንዳገዟቸውም ይናገራሉ ።
በጎዋ ሴት መምህርት አሚና እንዲህ እያሉ ነው ዛሬ ላይ ሆስቴሉን ያደረሱትና በርካታ ልጃገረዶች በትምህርትና በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻሉት።
አሁን ላይ ሆስቴሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ ቢገኝም ኮምፒውተሮቻቸው አሮጌ በመሆናቸው በአዲስ ቢተኩና የኮምፒውተር ክፍሉ ቢጠናከር የሚል ሃሳብ አላቸው። ማጠናከሪያ (ቲቶር) ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ በሆስቴሉ ውስጥ ቢመቻች ከሴቶች ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ጀምሮ በተለያዩ ነገሮች ቢደገፉ እንዲሁም ተመጣጣኝ ምግብ ላይም ከኑሮ ውድነት አንፃር የመግዛት አቅሙ በመዳከሙ የክልሉ መንግሥት የሚመድበውን በጀት መደገፍ ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው።
በጎዋ ሴት ተምሮ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲይዝ ያደረጉትን የሆስቴሉን ጥበቃ ጨምሮ በርካታ ዜጎችን ከኪሳቸው እያወጡ ያስተማሩ፤ ሴት ተማሪዎች በሃይማኖትና በሥነምግባር እንዲታነፁ ደግሞ ከቤተሰብ የመጡና ብዙ የጠለቀ እውቀት ስለሌላቸው ተታለው ለአደጋ እንዳይጋለጡ ሰፊ ጊዜ ወስደው የሚያስተምሩ፤ ማሕበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ናቸው። በተለይ ከሼሪያ ፍርድ ቤት ጋር እና ከተለያዩ የሕግ አካላት ጋር በመሆን ባሎቻቸው ከቤት ያባረሯቸውን ሴቶች ወደ ቤት ይመልሳሉ። በጉልበትና በዕውቀት ማነስ ወይም በተዛባ ፍርድ የተቀሙትን ንብረት የሚያስመልሱ ናቸው። እኛም በቅርቡ ከስኬታማ ሴቶች አንዷ በመሆናቸው የታጩትንና ለብዙ የሙስሊም ሴቶች ጠበቃ በመሆን በባሎቻቸው የተቀማ ንብረት የሚያስመልሱ ከቤታቸው የተባረሩ ሴቶች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርጉ ጠበቃ፤ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪና በጎ አድራጊ መምህርት ላይ ያተኮረ ጽሑፋችንን ደመደምን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም