እነሆ ! የዝናቡ ፣ የክረምቱ ወቅት ሊያልፍ አሁን ጊዜው ቀርቧል። ከወንዝ ጅረቱ፣ ከጭቃው ብርዱ፣ ከነጎድጓድ መብረቁ ጀርባም አዲስ ቀን ሊብት መስከረም ሊጠባ ግድ ነው። ይህ እውነት ዕውን ይሆን ዘንድ የተፈጥሮ ህግጋት ያስገድዳሉ። በተፈጥሮ ህግ እውነታዎች አይዛቡም፣ መሰረቶች አይናጉም። የነበረው በሂደቱ ይቀጥላል፣ የሚሄደው በሚመጣው ይተካል።
የጽሁፌን መነሻ በተፈጥሮ ህግ ላይ መመሰሌ ያለምክንያት አይደለም። ተፈጥሮን ከባህሪውና ከህጉ ጋር ለማዛመድ የመሻቴ እውነት አሁንም በምክንያት ነው። በእኔ እሳቤ ልክ እንደተፈጥሮ ሁሉ ጉዳዮቻንን ሳናዛባ ከያዝን ዒላማችን ግቡን አይስትም። ከመነሻ እስከ መድረሻ የሚኖረው መስመር ሳይንጋደድ፣ሳይጣመም ከታሰበው ይደርሳል።
ከጥንት እስከዛሬ ስንመሰክረው የኖርነው ኢትዮያዊነት መሰረቱ የጠበቀ ፣ ውሉ የተገመደ ህብር ነው። ይህን ሀቅ ደግሞ በየዘመናቱ ሊያጠቁን የቀረቡን ጠላቶቻችን ጭምር ሲመሰክሩት ኖረዋል። እኛም ይህ የዜግነት ጥምር ድር በየምክንያቱ ሲገለጥ አይተናል።
ሀገር በርሀብና ድርቅ ከስጋት በወደቀች ጊዜ ማንነታችን በተግባር ተረጋግጧል። በተፈጥሮ አደጋና መሰል ችግሮች በጽኑ ስትፈተንም አንድነታችን ከእኛው ጋር ነበር። ኮቪድን በመሰሉ ክፉ ወረርሽኞች በተጠቃን ጊዜም ወገን የወገኑን እጆች ጨብጦ ክፉውን ዘመን ተሻግሯል።
ይህ ብቻ አይደለም ። አብሮን በኖረው የመተጋገዝ፣ መረዳዳት ባህላችን የብዘዎችን ዕንባ ማበስ ልማዳችን ነው። አውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ በርካቶቻችን ያጣ ፣ የነጣ ጎረቤታችን ላይ ጀርባ አዙረን በር ዘግተን አንበላም። ያለንን ካለው ተካፍለን ፣ በጎደለው ሞልተን ኑሮን መምሰላችን ብርቃችን አይደለም። ይህ የኢትዮጵያዊነት ልዩ መገለጫ ከቃል በላይ መለያችን እንደሆነ ዘመናትን ዋጅቷል።
ወደቀደመው ሃሳቤ ልመለስ። ወደማይዛባው የተፈጥሮ ህግና ግዴታዎቹ። አዎ ! አሁን የክረምቱ ዝናብ ለበጋው ፀሀይ ተራውን ሊያስረክብ ጊዜው ደርሷል። እንዲህ በሆነ ጊዜ የሞሉ ወንዞች ሊጎድሉ፣በውሀ የራሱ መስኮች በአቧራ ሊሸፈኑ ግድ ይላል። የክረምቱ ብርድ በሙቀት ሲተካ፣ ፀሀይ ሀሩሩ ቦታውን ይይዛል ለምን? ካሉ የውል አይስቴው ተፈጥሮ ግዴታ በመሆኑ ። ይህ አይነቱን እውነት ወደ ራሳችን ወስደን እንኑረው ካልን የኢትጵያዊነትን የተጋመደ ህብር በዚህ ምሳሌ ማጣመር እንችላለን።
አዎ ! ኢትዮጵያዊነት በዘመናት መፈራረቅ ስሪቱን በማይስተው ተፈጥሯዊ ፀጋ ይመሰላል። ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ክብሩና ስያሜው በቀላሉ የማይላላ ጥብቅ ሰንሰለት ነው። አንዱ በአንዱ ማንነት ተሳስሮ ባሳለፈው ታሪክም በርካታ ቁምነገሮች ተቀምረው ጥቂት የማይ ባሉ ክፉ ቀናት አልፈዋል።
‹‹እሾህን በእሾህ›› እንዲሉ አንድነታችንን ሊበትኑ የወረሩን ባዕዳን ሽንፈትን የቀመሱት በዚሁ የአንድነታችን ግማድ ነው። ይህ የማንነታችን መለያ ክብራችንን አስመልሶ ስማችንን በከፍታ አድምቋል። ይህ ጠንካ ራው ክንዳችን ድንበራችንን በማይፈርስ ግንብ አጥሮ ጥንካሬችንን አውጇል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት በጀመረ ችው ሕልውናን የማስከበር ዘመቻ በርካታ ችግሮችን ተሻግራለች። ሰላምን ‹‹ዕምቢኝ›› ሲል ጦርነትን ምርጫ ባደረገው ወራሪ ሀይልም ዕልፍ ልጆቿ ለሞት ፣ በቀላሉ የማይተኩ ሀብቶቿ ለውድመት ተዳርገዋል። ይህ ብቻ አይደለም አስከፊው ጦርነት ያስከተለው ክፉ ጠባሳ በሺዎች የሚቖጠሩ ወገኖቻችንን ለመፈናቀል ዳርጎ ከድህነት አዘቅት ጥሏል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከተደረገ በኋለ እንደ ክፉ አውሬ አድብቶ የከረመው የወያኔ ቡድን ዛሬም የጥፋት እሳቱን ማቀጣጠል ጀምሯል። ለሰላም የተዘረጉ እጆችን ገፍቶ ለሶስተኛ ጊዜ በፈጸመው ጠብ አጫሪነትም ንጹሀንን በማስጨፍጨፍ ፣ ትውልድን ማስጨረሱን ይዟል።
ሽብርተኛው የወያኔ ቡድን ‹‹እሞትልሀለሁ›› የሚለውን የትግራይ ህዝብ አስቀድሞ መግደል የጀመረው በጦርነቱ ብቻ አይደለም። የሰላም እጦቱን ተከትሎ በተከሰተው ችግር በእርዳታ የሚገባ እህልን ሳይቀር ከአፉ በማስጣል ለርሀብ ጥማት ዳርጎታል። ዛሬ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ለጦርነት ማግደው ይልሱት ይቀምሱትን ናፍቀዋል።
አሁን በትግራይ ምድር ከጦርነት ያለፈ ሌላ ህይወት አይታስበም። ትምህርት፣ ጤና፣መብራትና ባንክ ይሏቸው መሰረታዊ ጉዳዮች የቅንጦት ያህል ተዘንግተዋል። ህዝቡ ለሚሆንበት ግፍና በደል ሁሉ ስለምን ? ሲል መጠየቅ መብት የለውም።
ሃሳብ ጥያቄውን ልሞክረው ቢል ምላሹን አሳምሮ ያውቀዋል። ራሱንና መላ ቤተሰቡን ለጦርነት ከመገበር ውጭ ምርጫ አልተሰጠውም። በግል ፍላጎትና በውጭ ሀይሎች ተላላኪነት ሀገር ለማፍረስ የተነሳው ቡድን ዛሬም ከነዕብሪቱ ቀጥሏል።
በትግራይ ምድር ያሉ ህጻናትና አረጋውያን ፣ሴቶችና ወጣቶች፣ ሌሎች ወገኖቻቸውን ጦር ይዘው እንዲወጉ ግዳጅ ተጥሎባቸዋል። በጥላቻ ፖለቲካ የተሞላው ቡድንም አገርን በማተራመስ ስትራቴጂው ዛሬም ድረሰ በንጹሀን ደም መታጠቡን ይዟል።
ጦርነት መቅሰፍት ነው። ክቡር ህይወትን ይነጥቃል፣ አካል አዕምሮን አጉድሎ ሀብት ንብረትን ያወድማል። የጦርነት ሂሳብን የቀመሩ ሀገራት መቼም ቢሆን አትርፈው አያውቁም። ህዝባቸውን ለሞትና ስደት ዳርገው፣ ምድራቸውን ለጥፋት ውሀ አሳልፈው ሰጥተዋል።
እስከዛሬ በነበሩ ታሪኮቻችን አንድ የመሆንን ጥቅም ደጋግመን አይተነዋል። ኢትዮጵያዊነት በእኩል ሲጋመድ፤ ክንደ ብርቱነት ያይላል። ዜጎች በሀገር ጉዳይ በእኩል ሲመክሩ፤ ሃሳብ አይነጥፍም፣ ቃል አይታጠፍም። ሁሉም ወገን ‹‹ያገባኛል›› ብሎ ‹‹አለሁ›› ማለትን ሲያውቅ ፈተናዎች ይቀላሉ።
ሀገራችን በባዕዳን ወረራ በተፈተነችባቸው ዘመናት ሁሉ የነጻነቷን ብርሀን ያገኘችው በልጇቿ ብርቱ ትግል ነበር። የዛኔ ከተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ባለፈ ሁሉም በጽኑ አቋም ለሀገሩ ዘብ ቆሞ ደጀን መሆኑን አስመስክሯል። እንዲህ የመሆኑ እውነትም የተገኘውን ድል የመላው አፍሪካ አድርጎታል።
ዛሬም ልክ እንደተፈጥሮ ህግ ውሉን የማይስተው ኢትዮጵያዊ አንድነት በወጉ ተጋምዶ ደጀንነቱን ሊያስመሰክር ይገባል። በህዝብ አንድነትና ህልውና ላይ የተሰካውን የዘመኑን አሜኬላ ከስሩ ለመንቀል የህብረ ብሄራዊነት ጊዜው አሁን ይሆናል።
ኢትዮጵያዊነት ‹‹ የፀና አንድነት›› ነው ስንል አሁንም በምክንያት ነው። የኢትዮጵያዊነት መልክ በብዙ ገጽ ይገለጣል። ህዝቡ ሁሌም ችግር መከራን በአንድ ይሻገራል፣ የጦርነት ወረራን በእኩል ይመክታል፣ ክፉ ወረርሽኙኝ ተደጋግፎ ያልፋል።
የትናንቱ ኢትዮጵያዊነት ዛሬም ቢሆን ነበልባሉ ነዲድ ነው። ህዝቡ በማንነቱ ህብር ለሀገሩ ዘብ ሊቆም ዝግጁነቱን ያሳያል። ደጀን መከታ ሆኖም ወገኑን ከማንኛውም ስጋት ሊታደግ ዘብ ይቆማል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንድነት መገለጫዎቹን በተግባር ሲመነዝር ከልቡ ነው።
ሀገር በጠላት ስትወረር አዋጅ ነጋሪት ጎሽሞ፣ በጽኑ ቃል ተማምሎ ደጀን የመሆን ታሪክ ለአበሻ ህዝብ አዲስ አይደለም። ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ መትመሙ ለሀገሩ ክብር የሚያሳየው ልዩ ምልክት ነው። ይህ እውነታ ደግሞ ዛሬም በቆምንበት ፈታኝ ዘመን ሊታይና ሊመሰከር የግድ ይላል። ሀገር ከሌለች ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም አይታሰብም። ሀገር በክብር ካልቆመች ተምሮ መለወጥ በነጻነት መተንፈስ አይሞከርም። ሀዘንና ደስታ፣ ሰርግና ሞት ይሉት ወግ መነሻ መድረሻው የሀገር በክብር ጸንቶ መኖር ብቻ ነው።
ዛሬም ኢትዮጵያውያን የአንድነታችን ድር ጠብቆ የማንነታችን ስም ደምቆ እንዲዘልቅ ለሀገራችን ዘብ ልንቆም ይገባል። ለወገናችን ክብር፣ ለመኖራችን ህልውና ስንልም የሚጠበቅብንን ግዴታ በተግባር ልናስመሰክር ግድ ይላል። እንግዲህ እኛ ማለት እንዲህ ነን። ስንተባበር እንበረታለን። ስንጠላለፍ እንወድቃለን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም