በሬ ጠምዶና የክረምት ወቅትን ብቻ ጠብቆ የሚከናወነውን የግብርና ሥራ ለማዘመን እንደሀገር በየጊዜው ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከኋላቀር የአመራረት ዘዴ የመውጣቱ ተግባር ዛሬም የቤት ሥራ ሆኖ ቀጥሏል፡፡በኋላቀር የአመራረት ዘዴና ወቅትን ጠብቆ በሚከናወን የግብርና ሥራ የሚገኘው የምርት መጠን ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ለውጥ ለማምጣት ቀርቶ ዋጋው እየናረ የመጣውን የእርሻ በሬ አርሶአደሩ ለመግዛትም ሆነ የተለያዩ የግብርና መሳሪያዎችን ለማሟላት አቅሙን የሚፈትን ሆኗል፡፡የግብርና ሥራው ምርትና ምርታማነትን በሚጨምር የተለያዩ የአመራረት ዘዴዎች እንዲታገዝ፣የእርሻ ሥራውም ቴከኖሎጂ ባፈራቸው የእርሻ መሳሪያዎች እንዲከናወን እንዲሁም ክረምት ከበጋ የሰብል፣የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲከናወን እንደሀገር አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት ከክረምት እስከ በጋ ልማት እንዲከናወን በተያዘው የግብርና ሥራ የቆላ ስንዴ እና ጎን ለጎን ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ዓለም በተለያየ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በሚገኝበትና እንደሀገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ባጋጠመበት በዚህ ወቅት የምግብ ፍጆታን ከውጭ በማስገባት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ አቅም የለም፡፡የሚታሰብም አይደለም፡፡በዩክሬይንና በሩሲያ መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በስንዴና የስንዴ ውጤቶች ላይ ያጋጠመውን እጥረትና የዋጋ መናር መጥቀስ ይቻላል፡፡እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት በግብርናው ላይ ጠንክሮ መሥራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ነው።
ከውጭ ጠባቂ ከመሆን ለመላቀቅና በምግብ እህል እራስን ለመቻል እየተደረገ ባለው ጥረት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ውስጥ ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ይጠቀሳል፡፡ይህ ዘዴ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው አንስተዋል፡፡አርሶአደሩ በአንድ አካባቢ ያለውን የተበጣጠሰ ማሳ ተመሳሳይ የአስተራረስ ዘዴ፣ተመሳሳይ ግብዓትና የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት እንደሚያስችለውና ምርታማነቱም እንዲጨምር ዕድል ይፈጥርለታል፡፡በአመራረት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥም ብክነትንም ያስቀራል፡፡
በአጠቃላይ የሰብል ምርትን በጥራት ለማሳደግ ዋነኛው አማራጭ ነው፡፡በጥራትና በብዛት ምርት ሲኖር ደግሞ አርሶአደሩ በብዛት ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ያስችለዋል፡፡ገቢ ሲያገኝ ኑሮው ይለወጣል። ሸማቹም በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡እንዲህ ያለው የገበያ ሥርአት ሲፈጠር የዋጋ መናርን በማስቀረት በሸማች በኩል የሚቀርበውን ቅሬታ ያስቀራል፡፡አርሶአደሩም የልፋቱ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር ድረገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣አርሶአደሩ በአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ተሞክረው ውጤታማ ሆኑ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ እያለማ ሲሆን፣የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ወደ አርሶአደሩ በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ሚኒስቴሩ ለአብነት ከሶስት አመት በፊት በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ማልጋ ወረዳ ውስጥ የተከናወነውን ተሞክሮው በድረገጹ በማሳያነት አቅርቧል፡፡በማልጋ ወረዳ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ወደ አርሶአደሩ በማስፋት ኩታገጠም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለቤት ፍጆታ ከማዋል ባሻገር አርሶአደሩ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን አምርቶ በምርቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችሏል፡፡በማልጋ ወረዳ በኩታገጠም እየለሙ ካሉ ሰብሎች አንዱና ዋነኛው የቢራ ገብስ ሲሆን፣በሁለት ኩንታል መስራች ዘር በአንድ ቀበሌ የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከል የተጀመረውን የቢራ ገብስ ዘር ብዜት በማስፋት በ13 የወረዳው ቀበሌዎች መልማት መቻሉን ነው ያስረዳው፡፡ይህ ማሳያ የሆነው የአካባቢው ተሞክሮ የኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የቦራገብስ በሀገር ውስጥ በመተካት ወጪን ማዳን ይቻላል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ለማ፤በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ማልጋ ወረዳ ውስጥ በኩታገጠም በቢራ ገብስ ላይ የተከናወነው ልማት በሀገር ውስጥ በመተካት አርሶአደሩን ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ የሀገር ወጭን በማዳንም ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረውና በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የቢራ ገብስ ልማት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ ኢሳያስ በተያዘው የመኸር ግብርና በኩታገጠም የግብርና ዘዴ ስላለው እንቅስቃሴና የልማቱ ሥራ የሚገኝበትንም እንዳስረዱት፣በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር የእርሻ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡92 በመቶ የሚሆነው ማሳ በዘር ተሸፍኗል፡፡ለምርትዘመኑ የግብርና ሥራ የሜካናይዝሽን የግብርና ዘዴ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡በዚሁ መሠረት በአማራ፣በደቡብ፣በደቡብ ምዕራብ፣በሶማሌ ክልሎች ጥሩ አፈጻፀም ተመዝግቧል፡፡በሜካናይዜሽን የግብርና ዘዴ ለመጠቀም ከተያዘው አጠቃላይ እቅድ 91 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡በሜካናይዜሽን የመጠቀም ልምዱ ከአመት አመት መሻሻል እየታየ ሲሆን፣በማህበር ተደራጅቶ ለመጠቀም ያለው ተነሳሽነት፣ባለሀብቱም በኪራይ በማቅረብ እንዲሁም መንግሥት በሚያመቻቸው የብድር አገልግሎት በመጠቀም የመግዛት አቅም መፈጠሩ፣ከቀረጥ ነጻ እንዲገባም በተፈጠረ ምቹ ሁኔታና በፖሊሲም መደገፉ፣የሜካናይዜሽን ጥቅምን የመረዳት ግንዛቤ ማደግ የተሻለ አፈፃፀም እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ሜካናይዜሽንን መጠቀም ከሚያስገኘው ዘርፈብዙ ጥቅሞች ለምርታማነት የተሻለ የመሬት ዝግጅት እንዲኖር ከማስቻሉ በተጨማሪ የአረም መጠን እንዲቀንስ በማድረግ፣ጥሩ ተክል እንዲኖር ያግዛል ያሉት አቶ ሲሳይ ጥሩ ተክል ሲኖር ጥሩ ምርት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ በሜካናይዜሽን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ቢሆንም የበለጠ በመስራት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክሮ መሥራት ይጠበቃል፡፡
ግብርናው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ጥረቶቹ ቢኖሩም የተስተካከለ ዝናብና ምቹ የአየር ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ለሰብሎች ስጋት የሆኑ ነገሮች አለመፈጠራቸውንም በክትትልና ድጋፍ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ከዚህ አንጻር ስላለው አቶ ሲሳይ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ያለው የአየር ፀባዩና ዝናቡ ለግብርና ሥራው ተስማሚ ነው፡፡በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ መረጃ መሠረት ዝናቡ በመደበኛ መሠረት እንደሚወጣ ነው የሚጠበቀው፡፡ዝናቡ በመደበኛ ሁኔታ ከወጣ የምርት ዘመኑ እቅድ የተሳካ ይሆናል፡፡ለሰብል ስጋት የሚሆኑ በሽታዎችና ተባይ በተመለከተም በክትትልና ቁጥጥር እየተሰራ ነው፡፡ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ሌላው ለግብርናው መዘመን የሚጠቀሰው ሜካናይዜሽን ነው፡፡ሜካናይዜሽን ለኩታገጠም የግብርና ሥራ ምቹ እንደሆነም በአስተያየት ይነሳል፡፡በዚህ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ በረከት ፎርሲዶ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሜካናይዜሽን ለኩታገጠም ምቹ ነው የሚያስብለው በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡በተቆራረጠ ማሳ ላይ ሜካናይዜሽንን ለመተግባር ከአንዱ ማሳ ወደሌላው ማሳ መሸጋገር ይጠይቃል፡፡እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ደግሞ የጊዜ ብክነትን ከማስከተሉ በተጨማሪ ነዳጅና ሌላ ወጭዎችን ለመቆጠብ አያስችልም፡፡በመሆኑም የመሠረተልማት ምቹነትን ይፈልጋል፡፡የግብርና ሥራው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ምቹ መንገድ፣የመስኖ ግድቦች፣ለማሽኑ የሚውል የነዳጅ ማደያና የማሽን ጥገና አገልግሎት ተሟልቶ ሲገኝ በመካናይዜሽን መጠቀም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡በሌላ በኩልም የኩታገጠም የግብርና ዘዴ ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብአቶችን በወቅቱ ለማድረስ ምቹ ነው፡፡
ሜካናይዜሽን መሬትን በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ከማረስ ጋር ብቻ በማያያዝ ሀሳብ ለሚሰጡ ሰዎችም አቶ በረከት እንዲህ አስረድተዋል፣ሜካናይዜሽን ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ተጠቃሚው ጋር ለግብይት እስኪደርስ ያለውን ሂደት ያካትታል፡፡ከመሬት ምንጣሮ ጀምሮ መሬት የማረሱ፣በመሳሪያ ተጠቅሞ ውሃ ለእርሻው ማዳረስ ወይንም የመስኖ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ዘር መዝራት፣የመኮትኮቻ መሳሪያን ጥቅም ላይ ማዋል፣አረም ማረምና ፀረተባይ ርጭት በአውሮፕላን፣በድሮን ወይንም በጀርባ በሚታዘል መሳሪያ ማከናወን፣የማጨዱ፣የመውቃቱ፣ምርቱን ሰብስቦ ጎተራ ወይንም ማከማቻ ውስጥ ማስገባቱ የሜካናይዜሽን አካል ነው፡፡ምርቱ ከደረሰ በኃላም አሽጎና አዘጋጅቶ ለገበያ ማውጣቱ የዚሁ የመካናይዜሽን አካል ነው፡፡ይህ ሁሉ የሚከናወነው አቅምን ማዕከል ባደረገ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ልክ እንደሰብል ልማቱ ሁሉ ሜካናይዜሽን ለአሳና ለእንስሳት ሀብት ልማት ጥቅም ይውላል፡፡ለእንስሳቱ የሚሆን መኖ በትራክተር ይለማል፡፡ከማልማቱ ጀምሮ ለእንስሳው መመገብ በሚያስችል መልኩ አዘጋጅቶና ከሌሎች ጠቃሚ ነገሮች ጋር አዋህዶ ምቹ በማድረግ ቴክኖሎጂው ያግዛል፡፡የወተት ማለቢያና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂም የዚሁ የሜካናይዜሽን አካል ነው፡፡ሜካናይዜሽን እጅግ ሰፊና ጥቅሙም ከፍተኛ ነው፡፡አጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ በኢትዮጵያ ሜካናይዜሽን እንዲያድግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሆነም አቶ በረከት ነግረውናል፡፡እርሳቸው እንዳሉት አላጌ፣አርዳይታ ላይ ስልጠና በመስጠት ሚኒስቴሩ ሰፊ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡በሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ የሰለጠነ ባለሙያ ለማፍራት እንዲቻል ሚኒስቴሩ ሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ላይ ይገኛል፡፡እንዲህ ያሉ ተግባራትንም እየተወጣ ያለው ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው። ፍላጎት ያለው በሙያው እንዲሰለጥን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ጎን ለጎን አርሶአደሩ አጫጭር ስልጠናዎችን እንዲያገኝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አመቻችቷል፡፡
ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማደረግ ከማን ምን ይጠበቃል ለሚለው ጥያቄም አቶ በረከት በሰጡት ምላሽ፤አነስተኛ ቴክኖሎጂን የሚያመርቱ የሀገር ውስጥ አምራቾች እየተፈጠሩ ቢሆንም ቴክኖሎጂው በአብዛኛው ከውጭ ነው የሚገባው፡፡የካፖታል ወይንም የገንዘብ አቅም የሚፈልግ በመሆኑ ገዝቶ ለመጠቀም ለማይችለው አገልግሎት ሰጭዎች ተደራጅተው ስልጠና እንዲወስዱና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ማሽን ገዝተው በኪራይ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ነው የተመቻቸው፡፡በዚህ መልኩ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አቅም ያለው አርሶአደር እየተከራየ እንዲጠቀም የተደረገ ነው፡፡መንግሥት እነዚህን ጨምሮ ማሽኖች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡እነዚህ ሁሉ ድጋፎች አርሶአደሩ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡አሁን ላይ በበሬ ከማረስ በትራክተር ማረስ ተመራጭ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሰዋል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ስምንትሺ ትራክተሮች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡እንዲህ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመንግሥት የተያዘው ምርትና ምርታማነት የማሳደግ አቅጣጫ ተጠናክሮ ከቀጠለ ውጤታማ በመሆን ከውጭ ጠባቂነት መላቀቅ ይቻላል።
ሜካናይዜሽን ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ላይ ካልሆነ በአነስተኛ እርሻ ላይ አይተገበርም የሚሉ አስተሳሰቦች እንዳሉ ያነሱት አቶ በረከት፤ ይህን ሀሳብ የሚያቀርቡ ሰዎች መስሏቸው እንጂ ቴክኖሎጂው ለቆላ፣ለሜዳማ፣ለእያንዳንዱ ሥነምህዳር ተስማሚ የሆነና በመሬት መጠኑ ልክ የሚፈለገው አይነት የሰውን ጉልበት መተካት የሚችል አቅርቦት አለ ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም አስፈላጊ ስለሚባሉ ቅድመሁኔታዎችም አቶ በረከት ሲመልሱ፤ አሁን ላይ በአነስተኛ ደረጃ በሀገር ውስጥ አምራቾች እየተፈጠሩ ቢሆንም ቴክኖሎጂው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ ምክንያት የገንዘብ እጥረት ተፈጥሯል።ይህን ችግር ለመቅረፍም አገልግሎት ሰጪዎች እንዲደራጁና ብድርና ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም