የዓባይ ግድብን የትብብር መንፈስ የሚሻው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ

ኢትዮጵያ የዜጓችዋን የምግብና እና ሥነ-ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያስችላት ዘንዳ በርካታ የልማት መርሃ ግብሮችን ነድፋ እየሠራች ትገኛለች:: በተለይም የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት፤ ቴክኖሎጂና ግብዓቶችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ በማድረግና በመሳሰሉት ሥራዎች ባከናወነቻቸው የልማት ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው::

ለዚህ አብነት ተደርገው ከሚጠቀሱ ውጤታማ የልማት ሥራዎቿ መካከል ሀገሪቱ ከዓመታት በፊት ከምዕራባውያን እጅ ትጠብቅ የነበረውን ስንዴ በበጋ ጭምር በመስኖ ማልማት የቻለችበት ሁኔታ አንዱ ነው:: በዚህም ከስንዴ ጠባቂነት መውጣት ብቻም ሳይሆን ወደ ላኪነት ተሸጋግራለች::

በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነቱን እምርታ ማስመዝገብ የተቻለው የሀገሪቱ መንግሥት ለዘርፍ በሰጠው የተለየ ትኩረትና በቁርጠኝነት በመሥራቱ ነው:: ለአርሶ አደሩ ምርታማነት መጎልበት ደግሞ እንደ የአፈር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን በስፋትና በሚፈለግበት ወቅት ተደራሽ የማድረጉ ባህል እየጎለበት በመምጣቱ ጭምር ነው::

ይህም በመሆኑ ሊታበይ በማይችል መልኩ አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን በመጠቀም ምርታማነቱን እያሳደገ መጥቷል፤ በዚህም የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥና የገቢ አቅሙን ለማሳደግ እየቻለ ነው::

ልማቱን ባስፋፋ ልክ የማዳበሪያ ፍላጎቱም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል፤ በሌላ በኩል በዓለም ላይ በየጊዜው እየናረ ከመጣው የማዳበሪያ ዋጋና ከሌሎችም ችግሮች ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ ግዢው የሀገሪቱን ከፍተኛ ሀብት እየያዘ መሆኑ ሌላ የልማት ማነቆ ሆኗል:: ይህንን ችግር በዘላቂነት ለማስቀረትና የምግብ ዋስትናን ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች በመንግሥት በኩል ታቅደዋል::

ከእነዚህም የልማት እቅዶች መካከል ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ይፋ ያደረጉት የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ አንዱ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በየአመቱ 24 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋታል፤ ለእዚህም በቀን 150 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ታጓጉዛለች፤ ይህንን ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደር እየደረሰ ያለው በወታደር ታጅቦ ነው። ይህም ሀገሪቱ ለሌላ ልማት ልታውለው የምትችለውን ከፍተኛ መዋለንዋይና ጉልበት ይወስዳል::

‹‹ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካን ማቋቋም ነው›› ያሉት ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማምረት አለመቻሏ በርካታ አርሶ አደሮችን የሚነካ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በተደረገው ጥናት ለፋብሪካው ግንባታ ከሁለት ነጥብ አምስት እስከ ሶስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል:: የማዳበሪያ ፋብሪካውን ለመገንባት በትንሹ ሶስት ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል::

‹‹ፋብሪካውን ከተቻለ ከግሉ ዘርፍ ጋር፣ በግለሰብ ኢንቨስትመንት ካልተቻለም መንግሥት በራሱ የሚገነባው ይሆናል›› በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአፈር ማዳበሪያ የኢትዮጵያን ፍላጎት በሚመልስ መልኩ መመረት እንዳለበት አስገንዝበዋል:: ፋብሪካ የማቋቋም ሂደቱ ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚጀመሩም ነው ያስታወቁት::

እኛም በዛሬው የግብርና አምዳችን ፋብሪካውን እውን ለማድረግና ሀገሪቱ ለተያያዘችው የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ግብ መሳካት ከማን ምን ይጠበቃል ስንል? የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር ዳይሬክተርና ተመራማሪ ታደለ ማሞን (ዶ/ር)ጠይቀናል::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል ማዳበሪያ ዋነኛው ነው:: ማዳበሪያ ብዙ ጊዜ ከውጭ በሚፈለገው ሰዓት የማይመጣ በመሆኑ አርሶ አደሮች ማግኘት የሚችሉትን የምርት መጠን ማግኘት አልቻሉም:: በሌላ በኩል በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች መንገድ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ማዳበሪያ ቶሎ ወደ ሀገር ውስጥ ካልገባ የዘር ወቅት የሚያልፍበት አጋጣሚ ይከሰታል::

‹‹ማዳበሪያ ከውጭ ለማምጣት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልግ መሆኑ ይህም ደግሞ ለሌላ ልማት ሊውል የሚችለውን የሀገርን ሀብት ለማዳበሪያ ግዢ የሚያውለው መሆኑ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል›› ሲሉ አስገንዝበዋል::

በተለይም አሁን አርሶ አደሩ በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት ባህሉ ከማደጉ ጋር ተያይዞ መንግሥት እየጨመረ ካለው ፍላጎት አንፃር ማዳበሪያ ቶሎ ቶሎ በስፋት ማቅረብ እንደሚቸገር ተናግረው፣ በዚህ የተነሳ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ባሰቡት ልክ ማሳደግ እንደሚከብዳቸው ያስረዳሉ:: በሌላ በኩል የማዳበሪያ ግዢ በአብዛኛው በሻጭ ሀገራት ፍላጎት ላይ የሚመሠረት መሆኑንም ጠቅሰው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ማዳበሪያ በስፋት የሚያስገቡ ሀገራት በሻጮቹ ተፅዕኖ ስር የሚወድቁበት አጋጣሚ እንዳለም አመልክተዋል::

ለዚህም አብነት አድርገው የጠቀሱት ከዚህ ቀደም የሻጮችን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ብቻ ጥናት ተደርጓል በሚል ሰበብ ለኢትዮጵያ መሬት የሚያስፈልገው ዳፕና ዩሪያ ፋንታ ኤን.ፒ.ኤስ የተባለ ማዳበሪያ ይሰራጭ እንደነበር ይጠቅሳሉ:: ይሁንና ከአስር ዓመት የጥናት ውጤት በኋላ ይፋ በተደረገው ሪፖርት መሠረት ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ ያላቸው ዩሪያና ዳፕ መሆናቸው መረጋገጡን ያመለክታሉ:: ይህም የግብርና ምርታማነት በሻጭ ሀገራት ጫና ስር እንደሚጥል ተናግረው፣ አርሶአደሩ ማዳበሪያውን በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ማግኘት አዳጋች አድርጎት መቆየቱን ገልጸዋል::

‹‹መንግሥት ከውጭ የሚያስገባውን ማዳበሪያ መጠን እየጨመረ ቢመጣም አሁንም አርሶ አደሮች መጠቀም ከሚገባቸው ግማሹን ያህል እንኳን እየተጠቀሙ አይደለም›› ይላሉ::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ማዳበሪያ ከሚጠቀሙ ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለች፤ ይህም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደጉ ሥራ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል:: በተለይም ደግሞ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ለያዘችው ግብ መሳካት አሁን ከምትጠቀመው ማዳበሪያ ከሶስት እጥፍ በላይ እንደሚያስፈልግም ጥናትን መሠረት አድርገው ተናግረዋል::

ተመራማሪው እንዳስታወቁት፤ ከዚህም ባሻገር ማዳበሪያም ሆነ ሌሎች ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶች ከሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት ከሌለ የሀገር አጠቃላይ እንቅስቃሴ ፈተና ውስጥ የሚወድቅበት አጋጣሚ አለ:: ይህም ሲባል የሚሸጡ ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ማዳበሪያው የሚገባበት ወደብ ሀገራትም ጭምር እጅን የሚጠመዝዙበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፤ ምክንያቱም ምርት ብቻም ሳይሆን የፖለቲካም ጉዳይ ነው:: አንድ አርሶ አደር ማዳበሪያ ማጣቱ የምርታማነትና የምግብ ዋስትና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ችግርም ይዞ ሊመጣ ይችላል ›› ሲሉ አስገንዝበዋል::

አንዳንድ ጊዜ ገዢ ሀገሮች ከተዋዋሉ በኋላ ዋጋ ቢጨምሩ እንኳን በተባለው ዋጋ ከመግዛት ውጪ አማራጭ የማይኖርበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ:: ‹‹በብድርም የሚመጣ ከሆነ አበዳሪዎቻችን ወደ ሚፈልጉት እጅ ጥምዘዛ ሊገቡ ይችላሉ›› ሲሉ ጠቅሰው፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የምታስመጣው ማዳበሪያ በባሕር የሚመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ሀገር እስከሚገባ ድረስ ባሉ መዳረሻ ሀገራትና ወደቦች ሰላም ከሌለ ችግሩ እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችልም ያስገነዝባሉ::

በዚህ አይነት ሁኔታ በወቅቱ ያልደረሰ ሀገር ከፍተኛ መዋለንዋይ መድባ የገዛችውና የብዙዎችን ህልውና የያዘው ማዳበሪያ ከነጭራሹ ጥቅም የማይሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አስታውቀዋል:: ይህም የአርሶ አደሩን ሥራ ከማስተጓጎሉም ባሻገር የማደግ ተስፋውንም እንደሚያጨልምበት ያብራራሉ::

ታደለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ተገንዘቦ ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ የግሉን ዘርፍ በማስተባበር የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ማቀዱ እንደ ትልቅ ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀው፣ ርምጃው የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኑንም ያሳያል ይላሉ::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የማዳበሪያ ፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባቱ ከምንም በላይ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኝና የግብርናውን ሥራ በአግባቡ እንዲያካሂድ ያስችለዋል:: አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ባለመድረሱ ሳቢያ ማግኘት ከሚገባቸው ምርት አምስት በመቶ ያጡ ነበር፤ ይህም ሲሆን ያጡትን ምርት እንዲያገኙ ከማድረጉም ባሻገር ግብርና እንደአጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በዚሁ ልክ ያሳድገዋል::

በሌላ በኩል ማዳበሪያው በሀገር ውስጥ ሲመረት አርሶ አደሩ ዋጋው ሊቀንስለት፣ በዚህም ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ይችላል:: የትራንስፖርትና መሰል ወጪ የሚቀንስለት በመሆኑ ያንን ገንዘብ ለሌላ ማዳበሪያ ግዢ ለማዋል እድል ይፈጥርለታል::

‹‹ይህም ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል:: ከዚህ ባሻገርም ዓመቱንም ሙሉ እንደማንኛውም ሸቀጥ በፈለገው ጊዜ ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታ ስለሚኖርም ያለስጋት የምርት ሥራውን ያከናውናል፤ ድካምም ይቀንስለታል›› በማለት ያብራራሉ::

በተለይ በከተማ ግብርና ላይ የተሰማሩ አርሶአደሮች ከዚህ ቀደም በኤክስቴንሽን ባለመታቀፋቸው ማዳበሪያ እንደልብ ለማግኘት ፈተና እንደነበረባቸው ተመራማሪው ተናግረው፤ ይህ መሆኑ እነሱንም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውና ለሀገራዊ ምርታማነትም ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ግዙፍ የልማት ሥራ ሲሆን፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትንም ይጠይቃል:: እውን መሆን የሚችለውም መንግሥት፤ የግሉ ዘርፍ፤ ለጋሽ ድርጅቶች እና ህብረተሰቡም ጭምር በቅንጅት መሥራት ሲችሉ ነው:: በተለይም ደግሞ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ የሀገርን ልዕልና ከፍ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ በእኔነት ስሜት የየራሱን ዐሻራ ለማሳረፍ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል::

አርሶ አደሩ ምርታማነቱን ሊያሳድግ የሚችለው፤ ምርቱም በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ መሆን የሚችለው በሀገር አቅም እንደ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት ሲቻል መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብና ለግድቡ ግንባታ ያሳየውን ተነሳሽነት እዚህ ላይም ሊደግም እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::

‹‹ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ ያንን መንፈስ ሕዝቡ የማዳበሪያ ፋብሪካው የእኔ ነው ብሎ አምኖ በጋራ እንዲሠራ ማነሳሳት ላይ መሥራትም ያስፈልጋል›› ይላሉ:: የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ጥያቄ ሲመለስ የምግብ ፍላጎት ማሟላት እንደሚቻል ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባም ያስገነዝባሉ::

እሳቸው እንዳስገነዘቡት፤ በተመሳሳይ ሁሉም የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የፋብሪካውን መገንባት ለሀገር ያለውን ትልቅ ፋይዳ ተረድተው በግንባታው ላይ የየራሳቸውን አወንታዊ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል:: በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚያደርጉትን ኢንቨስትምንት በማዳበሪያ ፋብሪካው ላይም ቢያደርጉ ዞሮ ዞሮ እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ ለእዚህም በተነሳሽነት ከመንግሥት ጎን መቆም አለባቸው::

ከዚህም ባሻገር ለጋሽ ሀገራትና የፋይናንስ ተቋማት ችግር ከተፈጠረ በኋላ ለዜጎች ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ከሚያስችሉ ወሳኝ የልማት ሥራዎች መካከል አንዱ ለሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እውን መሆን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ታደለ (ዶ/ር) ያስገነዝባሉ::

በተለይ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የምዕራባውያኑ ድጋፍ መቼም ቢሆን የአሕጉሪቱን ዜጎች ከድህነት ሊያወጣ እንደማይችልና ዘላቂ እንዳልሆነ ከሰሞኑ የአሜሪካ ውሳኔዎች መረዳት በቄያቸው እንደሆነ ይናገራሉ:: በመሆኑም ኢትዮጵያም ሆነሌሎች ሀገራት ከድህነት ለመውጣት ለሚያደርጉት ጥረት እስከ አሁን ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ዘላቂ መፍትሔ በሚሆን መልኩ ማገዝ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት::

ህብረተሰቡንም ሆነ የግሉን ዘርፍና ለጋሽ አካላትን በማስተባበር ረገድ መንግሥት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበትም ተመራማሪው ያመለክታሉ:: በተለይም ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ ቦንድ በማዘጋጀት ህብረተሰቡ እንደአቅሙ ለግንባታው የውዴታ ግዴታውን የሚወጣበት እድል ሊፈጥር እንደሚገባ ይመክራሉ::

የግሉ ዘርፍም ቢሆን ልክ እንደ ስኳር ፋብሪካዎች በሽርክና መልክ በጋራ የፋብሪካውን ግንባታ ማካሄድ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ይላሉ:: ‹‹በተለይ ለትላልቅ ባለሀብቶች ልክ እንደገበታ ለሀገር ባሉ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት የሚለግሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል›› በማለትም ያስገነዝባሉ::

ተመራማሪው እንደጠቆሙት፤ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶችንም ቢሆን በመጋበዝ በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባዋል፤ በተለይም በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገራት ለሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች የሚሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል:: የውጭ ባለሀብቶችን በማዳበሪያ ፋብሪካው ማሳተፉ የእነሱን ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ቀስ በቀስ በራስ አቅም ለመቆም እድል ይሰጣል::

የፋብሪካው መገንባት ሀገሪቱን ዘላቂ በሆነ መንገድ ከውጭ ርዳታ ጠባቂነት ሊያላቅቃት የሚችል በመሆኑም ሁሉም የየበኩሉን አስተዋፅኦ በቁርጠኝነት ሊያበረክት ይገባል ሲሉ ተመራማሪው አስገንዝበዋል::

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You