
መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ የግብርና ዘርፉ ስትራቴጂዎችን ተግብሯል። በዘርፉ ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል በመኸርና በበልግ ወቅት የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከተከናወኑ ተግባሮች በተጓዳኝ ተግባራዊ የተደረገው የመስኖ ልማት በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ይጠቀሳል።
በዚህ ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ስንዴ ከውጭ መግዛት የታደገ ተጠቃሽ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እውን መሆን አርሶ አደሩ በዝናብ ላይ ተመስርቶ ከሚያካሂደው የእርሻ ሥራ በተጓዳኝ የመስኖ ልማትን በማካሄድ ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርት አስችሎታል።
በእዚህ ላይ ለፍራፍሬ ልማት ምቹ ሁኔታ የፈጠረው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ ለፍራፍሬም ለአትክልትም ልማት ምቹ ሁኔታ የፈጠረው የሌማት ቱሩፋት መርሀ ግብሮችም ከመኸርና በልግ እንዲሁም ከበጋ መስኖ ሥራዎች ጋር ተመጋጋቢ ሆነው እንዲከናወኑ በማደረጉ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል፤ እየተመዘገቡም ናቸው።
በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገሪቱ ያስመዘገበችው ምርታማነት የርዳታ ጠባቂነት ትርክትን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እየቀየረ ይገኛል። ሀገሪቱ አሁን የራሷን የስንዴ ፍላጎት ከመሸፈን አልፋ ወደ ውጭ እስከ መላክ የደረሰችውም የግብርናውን ዘርፍ የማምረት ባሕል ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሳደግ በመቻሉ ነው። ለእነዚህ ውጤቶች ዋነኛ አቅም የሆነው ደግሞ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት መሆኑ ይታወቃል።
መንግሥት የምርት መጠኑን ከፍ ለማድረግ በየዓመቱ የመፈፀም አቅሙን እያጎለበተ ከመምጣቱም ባሻገር ልማቱን የዜጎችን ተጠቃሚነት ሊያረጋገጥ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ አድርጓል። የሀገሪቱን ሕዝብ የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማለም ለምርታማነት ማደግ ወሳኝ የሆኑ እንደ ማዳበሪያ፤ ምርጥ ዘር ያሉ ግብዓቶችን አስቀድሞ በማቅረብና የዝግጅት ሥራዎችን ታች ድረስ ወርዶ በመከታተል በቁርጠኝነት መሥራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የሚታረስ መሬትን ሽፋንን በማሳደግ እንዲሁም ለሜካናይዝድ እርሻ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የታመነበት ኩታ ገጠም እርሻ እንዲስፋፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባሮች በሁለቱም ሥራዎች ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች ዘንድሮ ብቻ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ልማት ሽፋን ከነበረበት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማደግ ችሏል።
ይህም እንደ ትልቅ እመርታ እንደሚወሰድ ተናግረው፣ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም መሸፈኑንም አስታውሰው፣ ይህንን አኅዝ ዘንድሮ ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የመሬት ሽፋን ብቻ ሳይሆን ኩታ ገጠምም በከፍተኛ ደረጃ እመርታ ማሳየቱንም አመልክተዋል። መንግሥት ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም፤ አርሶ አደሩን በማስተባበር የተገኘውን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥም እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በተያዘው በ2017 የምርት ዘመን የበልግ ወቅትም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ላይ ያነጋገርናቸው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ እንዳሉት፤ በ2017 የምርት ዘመን የበልግ ወቅት ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 99 ሚሊዮን 235 ሺ 463 ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህ መሠረት በልግ አብቃይ በሆኑ ምስራቅ አማራ፣ ደቡባዊ ትግራይ፣ የኦሮሚያ ታችኛው ክፍል፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብና አብዛኛው የደቡብ ክልል አካባቢዎች ላይ የዝግጅት ሥራዎች የተጀመሩት አስቀድሞ ነው። የሶማሌ ክልል አብዛኞቹ ዞኖች የበልግ ዝናብ ዘግየት ብሎ የሚገባባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ፣ በዝግጅቱ ላይ ግን አርሶ አደሩን በተቀናጀ መልኩ በማስተባበር እየተሠራ ይገኛል።
በዚህ የበልግ ወቅት እስካሁን ድረስ ሁለት ሚሊዮን 441 ሺ 045 ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 222 ሺ 334 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥ 19 ሺ 727 ሄክታር መሬት በክላስተር የተሸፈነ ነው።
የፌዴራል መንግሥት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ቀጣይነት ማረጋገጥ ያስችለው ዘንድ ከክልል መንግሥታት ጋር የተናበበ እቅድ በማውጣትና በማስተባበር ተጨባጭ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል። በተለይም ለምርታማነት ወሳኝ የሆኑትን የማዳበሪያና የዘር አቅርቦትን በተሟላ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረጉ ሂደት ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት አንፃር መሻሻል የታየበት መሆኑን ያስገነዝባሉ።
‹‹ዘንድሮ በተለየ መልኩ ማዳበሪያ የመኸር ወቅትን ብቻ ሳይሆን በልግን ታሳቢ ተደርጎ ቀድሞ እንዲገዛ ተደርጓል፤ ከዚህ ቀደም ማዳበሪያ ቀድሞ የሚገባበት ሁኔታ አልነበረም›› ይላሉ። አሁን ግን ማዳበሪያ በአብዛኛው የበልግ አብቃይና ያደረ ማዳበሪያ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የዘር ወቅታቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲደርሳቸው መደረጉንም ይገልፃሉ፡፡
በተመሳሳይ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎችና ከዘር አባዥ አካላት ጋር የተናበበ ሥራ መሠራቱን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። ወቅቱን ባገናዘበና የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ሥርጭቱ መከናወኑንም ይጠቁማሉ። ‹‹በተለይም የግብርና ሚኒስቴር በዘር ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ከክልሎች ጋር በሠራቸው የሶስት ዓመት እቅድ ስራዎች ዘንድሮ የተሻለ የዘር አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የምርጥ ዘር ብዜት ሥራን በተመለከተ የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በ2016/17 ምርት ዘመን በመንግስት ዘር አምራችና በግል አባዢ ድርጅቶች (የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ኮርቲቫ ፣ባየር ላይፍ እና ቫምበር) እንዲሁም በክልሎች (በኦሮሚያ፣ አማራ፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በሶማሌ) 148 ሺ 43 ሄክታር የምርጥ ዘር ብዜት ለመሸፈን ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በዘር ከተሸፈነው 83 ሺ 635 ሄክታር መሬት ላይ አንድ ሚሊዮን 57,ሺ 155 ኩንታል የዘር ምርት ተሰብስቧል።
ከዚህም ባሻገር እንደሀገር ያለውን የምርታማነት አቅም ለማሳደግና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እየተከናወኑ ካሉ የግብርና ሥራዎች መካከል የማዳበሪያ አቅርቦትን ለአርሶአደሩ በወቅቱና በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ የሚለው አንዱ ነው።
በዚህ ረገድም 964 ሺህ 118 ነጥብ አንድ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን በቅርቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህ ውስጥም 836 ሺ 253 ነጥብ ሁለት ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን እና 127 ሺ 864 ነጥብ 9 ሜትሪክ ቶን ደግሞ በወደብ እንደሚገኝ ተመላክቷል። ወደ ሀገር ውስጥ ከተጓጓዘው መካከልም 523 ሺ 375 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን ዳፕ እንዲሁም 312 ሺህ 878 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ መሆኑን ተጠቅሷል።
በበልግ ወቅት በአብዛኛው የአገዳ ሰብሎች እንዲሁም በተወሰነ መልኩ የጥራጥሬና የብዕር ሰብሎች እንደሚመረቱ አመልክተው፤ ዘንድሮም በአርሶ አደሩ ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው የበቆሎ፣ ማሽላ፣ ገብስ፣ ጤፍ ሰብሎች በስፋት እንደሚመረቱ ይጠቁማሉ። ‹‹በተለይ በቆሎ ላይ የነበረውን እጥረት በመፍታት በክልልም በፌደራል ደረጃ ዘር የማድረስ ሥራዎች ተሰርተዋል›› ይላሉ።
የማዳበሪያና የዘር አቅርቦቱንም ሆነ አጠቃላይ የበልግ ሥራውን ሂደት በሚመለከት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በየሶስት ቀኑ ክትትልና ግምገማ እየተደረገበት ስለመሆኑም ጠቅሰው፤ ክፍቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተሰሩ የተሻለ ክንውን ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ያብራራሉ።
በሌላ በኩል የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ዘግየት ብሎ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለማምረት የታሰበው ምርት በታሰበው ልክ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት ከተለያዩ አካላት ይነሳል፤ በዚህም ላይ ምን ያላሉ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኢሳያስ ሲመልሱ፤ ዘንድሮ አብዛኞቹ የበልግ አምራች የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ላይም አርሶ አደሩ ዝናብ ዘግይቷል ብሎ እንዳይዘናጋና ወደ ዝግጅት ሥራ እንዲገባ የመቀስቀስ ሥራ መሠራቱንም አመልክተዋል።
በመጀመሪያው የበልግ ወቅት ሳምንታት ዝናቡ ዘግየት ብሎ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እያገኙ ነው ብለዋል። የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ የሚያሳየውም የተሻለ ዝናብ ሥርጭት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ በሚቀጥሉት ቀናት የዝናብ ሥርጭቱ የሚጨምርበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል። አርሶ አደሮቹ ቀድመው ተዘጋጅተው ዘር እንዲዘሩ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በዘንድሮው በልግ ዝናብ ዘግይቶ ከመጣባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል ተጠቃሽ ነው፤ ከዚህ አንፃር በክልሉ ለቀጣዩ የምርት ወቅት የሚሻገር እቅድ ካለ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተጠይቀው፤ ‹‹በአማራም ሆነ በአብዛኛቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ መደበኛ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እስከ አሁን ባለው ጊዜም በአማራ ክልል ለማረስ ከታቀደው 239 ሺ ሄክታር መሬት ውስጥ 224 ሺ ሄክታሩ ታርሷል›› ይላሉ። የቀረውን እቅድም ያለውን እርጥበት በመጠቀም ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረው፣ ለቀጣይ የምርት ወቅት የሚሻገር ሥራ እንደማይኖር አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ ያወጣው የአየር ትንበያ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተዘሩ ሰብሎች እድገት አመቺ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር ተብሎ ይጠበቃል።
በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀው ርጥበት የአፈር ውስጥ ርጥበትን እንደሚያሻሽል መረጃው ጠቁሞ፣ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን እንደሚኖረውም ያመላክታል። ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የአየር ሁኔታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክቶ፣ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
የዝናብ ወቅቱንና ያለውን እርጥበት ሁሉ በመጠቀም የታቀደውን የምርት መጠን ማሳካት ይቻል ዘንድ ሁሉም በየፊናው የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ነው አቶ ኢሳያስ አሳስበዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም