የግብርናው ዘርፍ የሰባት ዓመታት ስኬቶች

ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዘርፎች ለውጦችን ማስመዝገብ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ወደ ሥራ በመግባታቸው አያሌ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ግብርና እስከ ለውጡ ጊዜ ድረስም ቢሆን በየዓመቱ ምርትና ምርታማነት እያደገ የመጣበት ሁኔታ አልነበረም ማለት አይቻልም። በዘርፉ ይበልጥ የተሰራበትና የምርትና ምርታማነቱም እድገት እምርታዊ ሊባል የቻለበት ሁኔታ የተመዘገበው ግን ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ስለመሆኑ አሀዛዊ መረጃዎቹን መለስ ብሎ መቃኘት ይቻላል። እነዚህ መረጃዎች ብቻም ሳይሆኑ ገበያም ያመላክታል።

ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ የተቻለው አይነተ ብዙ ሰፋፊ ሥራዎች በመሰራታቸው ነው። የኩታ ገጠም እርሻን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ለቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ለመሳሰሉት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበት ወደ ትግበራ የገባው የኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት ሥራ የአነስተኛ ማሳ ባለቤት በሆኑ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት ላይ ሲደርስ የነበረውን አሉታዊ ተጽእኖ ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያስቻለ ይገኛል።

አርሶ አደሮች ማሳቸውን አቀናጅተው ማረስ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህም መሬቱን በትራክተር ለማረስ፣ አዝመራውንም በኮምባይነር ለመሰብሰብ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በጋራ ለመጠቀምም አስችሏል።

መንግሥት በእዚህ ላይ በሰራው ሥራና በአርሶ አደሩም ዘንድ የነበረው የኩታ ገጠም እርሻ ግንዛቤ እየሰፋ በመምጣቱ በኩታ ገጠም የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥርም እንዲሁም የሚገኘው ምርትና ምርታማነትም በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ከግብርና ሚኒስቴርም ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአጠቃላይ የሚታረስ ማሳን በማስፋፋት ላይም በትኩረት ተሰርቷል፤ ለውጥም ማምጣት ተችሏል። ይህ ማሳ የማስፋፋት ሥራ ለእርሻ ሥራ መዋል ሲገባቸው ክፍት ሆነው የኖሩ ወይም ጦማቸውን ያድሩ የነበሩ መሬቶችን ወደ እርሻ በማስገባት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በባሕር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረን መሬት ወደ እርሻ በመመለስ እና በመሳሰሉት በማሳ ማስፋፋት ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

የሀገሪቱ ግብርና ከቴክኖሎጂ ጋር ብዙም የተቀራረበ ሳይሆን መኖሩ ይታወቃል። እርግጥ ነው ማዳበሪያና ምርጥ ዘሮች ይቀርቡ ነበር። እሱም ቢሆን ግን በሚፈለገው ልክ ነበር ወይ ቢባል አልነበረም ነው መልሱ። ምክንያቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የአመለካከት ችግርም ሊሆን ይችላል።

የምርምር ተቋማት የምርምር ዝርያዎችን ሲያቀርቡ እንደነበርም ይታወቃል። በዚህም በምርምር ጣቢያ በአርሶ አደሮች ማሳና በመሳሰሉት ያመጣው ለውጥ በጉብኝትና በመሳሰሉት ይፋ ይደረግ እንደነበር ይታወቃል። በእዚህ በኩልም ተግዳሮቶች እንደነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሱም ነበር። ቴክኖሎጂ በማስፋት በኩል ውስንነቶች ስለነበሩ የምርምር ውጤቶቹ ግብርናውን ለመለወጥ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዳይወጡ ተደርገው ቆይተዋል።

ቴክኖሎጂ ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፤፤ ትራክተር፣ ኮምባይነር ወደ ማሳዎች በስፋት ካልገቡ ለውጡ ፈጣን ሊሆን አይችልም፤ የሀገሮች ተሞክሮ አንዱ የሚያሳየው ይሄው ነው። እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው ግን የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር እንደነበር ይታወቃል።

የፋይናንስ ተቋማት ብድር ሲሰጡ የኖሩት ሕንጻ ለሚገነቡ ባለሀብቶች ነበር። ይህም በመንግሥት በተደጋጋሚ ሲተች ኖሯል። ሀገሪቱ ለአርሶ አደሮች የፋይናንስ ቅርቦት ማድረግ የማትችል ብቸኛ ሀገር ሲሉም አንድ የዘርፉ አመራር በአንድ ወቅት የጠቀሱት እዚህ ላይ ሊያዝ ይችላል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ይህን ለመለወጥ ብዙ ተሰርቷል። ይህን ተከትሎም ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮች ብድር ማቅረብ ጀምረዋል።

መንግሥት አርሶ አደሮች ትራክተሮችን ኮምባይነሮችን በብድር ሊገዙ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች አመቻችቷል፤ ከተፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች አንዱ ይሄው የፋይናንስ አቅርቦት ላይ የተከናወነው ተግባር ነው።

በእዚህ በርካታ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች እየገቡ ናቸው። አርሶ አደሮች በግል፣ በሕብረት ሥራ ማሕበሮቻቸው እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በዘርፉ አገልግሎት ለመሰማራት ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን እየገዙ ለግብርናው ሥራ አውለዋል፤ እያወሉም ይገኛሉ።

በእዚህና በመሳሰሉት በተከናወኑ ተግባሮች የሀገሪቱ በትራክተር የማረስ ምጣኔም አምስት በመቶ የደረሰበት ሁኔታ መፈጠሩን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል። አሁን ከሚታረሰው 20 ሚሊየን ሄክታሩ አምስት በመቶው በትራክተር እየታራሰ ነው እንደማለት ነው።

ሀገሪቱ በታሪክ አይታው የማታወቀውን የበጋ ስንዴ መስኖ ልማትም የጀመረችውም፣ በዚህም ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበችበት ሁኔታ የተፈጠረውም በእነዚህ ባለፉት ሰባት ዓመታት ስለመሆኑ መረጃዎችም መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችም ይጠቁማሉ። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እውን መሆን ሀገሪቱ በሁለት የምርት ዘመኖች ብቻ ታርስ የነበረበትን ሁኔታ ዓመቱን በሙሉ ወደ ምታርስበት ሁኔታም ያሸጋገረም ሆኗል።

በአረንጓዴ አሻራና በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችም ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሌሎች የእነዚህ ሰባት ዓመታት ተጠቃሽ ስኬቶች ናቸው። በችግኝ ተከላ፣ በዶሮ እንቁላል ወተት ፍራፍሬና አትክልት ልማት እየታዩ ያሉ ለውጦች በልማቱ የተሳተፉ ዜጎችንም አጠቃላይ ማሕበረሰቡንም በብዙ መልኩ እየጠቀሙ ይገኛሉ።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገራቸውን በቅርቡ የተለያዩ መንግሥት አካላትም አረጋግጠዋል። ኢዜአ በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የአደጋ መከላከል አቅምን በሚመለከት ከግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ጋር ባደረገው ቆይታ እንደተመላከተው፤ ሀገራዊ ለውጡ በግብርናው ዘርፍ ዘርፉ ብዙ ስኬቶች እንደሚመዘገቡ አስችሏል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። በተለይ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና የሜካናይዜሽን እርሻን የማስፋት እንዲሁም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን ግብርና በመቀየር ዓመቱን ሙሉ ወደ ማረስ መገባቱን ጠቅሰዋል። ይህንንም ምርትና ምርማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረ ሲሉ ገልፀውታል።

በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ልማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው መለስ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።

በዚህም ከለውጡ በፊት በመኸር 12 ነጥብ አምስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ይታረስ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህን አሀዝ አሁን ወደ 20 ነጥብ አምስት ሚለየን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል። በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበውን ምርት ከ293 ሚሊየን ኩንታል ወደ 608 ሚሊየን ኩንታል ከፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል በተጀመረው ኢንሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማለት ችሏል።

በ2011 ዓ.ም በ ሶስት ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፥ አሁን ወደ ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን ጠቅሰው፣ ከዚህም 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ስኬት የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመረውን ሥራ እያገዘ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) አስታውቀዋል። ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል በግብርናው ዘርፍም ፖሊሲ ተቀርፆ በሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።

በሜካናይዜሽን አቅርቦት ላይ በተከናወነው ተግባር ለውጦች ታይተዋል። የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ በትራክተር የማረስ ምጣኔ ከነበረበት 5 ነጥብ ሰባት በመቶ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች አሁን ላይ 25 በመቶ መድረሱን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞት የወጣ ዘገባ ያመላክታል።

የግብርና ሚኒስቴር የግብርና መካናይዜሽን ተወካይ አቶ እሸቱ ሁንዴ ዋቢ አድርጎ በተሰራው በእዚህ ዘገባ ላይ እንደተጠቆመው፤ በኢትዮጵያ በትራክተር የማረስ ምጣኔ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት አምስት ነጥብ ሰባት በመቶ በፍጥነት በማደግ 25 በመቶ ምጣኔ ላይ ደርሷል።

አንድ ኮምባይንር 40 ሚሊየን ብር አካባቢ የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው የግብርና መካናይዜሽንን ለማስፋፋት በባለሀብቶች ወይም በተደራጁ ወጣቶች በኩል መስራት ታምኖበታል።

የግብርና ሜካናይዜሽን ትልቁ ሥራው ቴክኖሎጂን እንዲስፋፋ እና አርሶአደሩ ጋር ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው ሲሉም በኪራይ አገልግሎትም በተደራጁ ወጣቶችም አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂ በመታገዝ የግብርና ሥራው በተከናወነባቸው አካባቢዎች ምርታማነት እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፣ በ2016/17 የምርት ዘመን አርሶአደሩ ምርቱን በግብርና ቴከኖሎጂዎች ታግዞ አየሰበሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ ሰትራቴጂክ እቅድ አሁን ካለበት 20 ሺህ አካባቢ ትራክተር ወደ 65 ሺህ ለማሳደግ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮምባይነር ከቀረጥ ነፃ በፊት ከ500 የማይበልጥ ነበር ሲሉም አስታውሰው፣ አሁን ላይ 2700 መድረሱን ተናግረዋል። እሱንም ወደ 15 ሺህ እንዲደርስ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። አርሶአደሩን በእዚህ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ግብርና ከሌሎች ሀገራት የሚለየው አብዛኛው የእርሻ ማሳ የአነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳ መሆኑን ጠቅሰው፣ እርሻው ወደ ኮሜርሻል እርሻ ያላደገ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት እነርሱን ማዕከል ያደረገ ሥራ ያስፈልግ እንደነበርም አንስተዋል።

በዚህ ላይ ለማምጣት የተከናወነው ተግባር የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ ማድረግ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኩታ ገጠም እርሻም እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን አሀዝ ዘንድሮ ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል። የመሬት ሽፋን ብቻ ሳይሆን ኩታ ገጠምም በከፍተኛ ደረጃ እምርታ አሳይቷል ብለዋል።

ስንዴን ብቻ እንደ አንድ የሰብል ምርት ወስደው ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ በመኸር አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ለምቷል፤ በበጋ መስኖ ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊየን ሄክታር ታርሷል። በድምሩ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ሰብል የሸፈነች ሲሆን፣ ከዚህም ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይጠበቃል። ይህ ስኬት ዛሬ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራች ሀገር እንድትሆን እንዳደረጋትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በግብርናው ዘርፍ በተለያዩ ሰብሎች እየተከናወነ ያለው ተግባር ይበል እንደሚያሰኝ አስታውቀዋል። በቡናው ልማት የተገኘውን ስኬት ጠቅሰው ሲያብራሩም፤ በለውጡ ማግስት 700 ሚሊዮን ገደማ ዶላር በዓመት ከቡና ኤክስፖርት ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፈው ዓመት ብዙ እምርታ የመጣበት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል። ከቡና ኤክስፖርት አንጻር አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የቡና ኤክስፖርት ተብሎ የተመዘገበ ነበር ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በሌማትም፣ በስንዴም፣ በቡናም፣ በሻይም ኢትዮጵያ በቂ የሆነ ሥራ ሰርታለች ብለን ግን አናምንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እውነት ስለሆነ አስደናቂ እምርታ አለ፤ አንክደውም። ከዚያ በላይ ሊሰራ የሚገባው ሥራ ስላለ በቂ ነው ብለን አናምንም ሲሉም አስገንዝበዋል።

በጋዜጣው ሪፓርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You