አዲስ አበባ፡- የአሜሪካ ሚያሚ ዴድ ካውንቲ ግዛት የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያግዝና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚረዳ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
በምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ምስግና፤ የአሜሪካ ሚያሚ ዴድ ካውንቲ ግዛት የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ሰሞኑን ውይይቶች እያደረጉ ናቸው። ውይይቶቹና ጉብኝቱም የሚያሚ ግዛት ባለሀብቶች ከኢት ዮጵያውያን ጋር በተለያዩ ዘርፎች በሽርክና ለመ ሥራት ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርገዋል። ሂደቱም ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ይረዳል የጋራ ተጠቃሚነትንም ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱ አገሮች በሽርክና በመሥራት የግብርና ምርቶችን አቀነባብሮ ወደ ውጭ ለመላክ ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጹት አቶ ቢኒያም፤ ጥምረቱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉንም እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል። ከሦስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ምግብና መጠጦች በአሜሪካ ሚያሚ ግዛት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የምግብና የመጠጥ ንግድ ትርዒት በመሳተፍ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ መቻሉን አስታውሰው፤ የግብርና ምርቶች ገበያ ለመፍጠርና ከአገዋ ገበያ ዕድል ተጠቃሚነትን ያሳድጋል በሚል ታሳቢነት ተሳትፎ መደረጉን አክለዋል። በንግድ ትርኢቱ የተሳተፉ ባለሀብቶች የወይን፣ የቢራ፣ የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
የሚያሚ ግዛት ወደብን በወቅቱ መጎብኘ ታቸውንና አብሮ ለመሥራት መነጋገራቸውን በመጠቆምም፤ ልዑካን ቡድኑ በመንግሥት ደረጃ ወስነውና ውይይቱን መነሻ አድርገው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የሚያሚ ግዛት ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ቢሰማሩ ወይንም በሽርክና ቢሠሩ ጥሩ ዕድል እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀው ከተለያዩ ዘርፎች ተወክለው እንደመጡም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአሜሪካ ገበያ ከኬንያና ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ተጠቃሚነቷ አነስተኛ መሆኑንና ከአገዋ እድል ተጠቃሚ እንዳልሆነች የጠቆሙት አቶ ቢኒያም፤ ዘንድሮ የተሻለ ግንኙነት እየተፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እ.ኤ.አ በ2016 በአሜሪካ ሚያሚ ግዛት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የምግብና የመጠጥ ንግድ ትርዒት ላይ በመሳተፋቸው በአገራቸው ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለማወቅ እንዳገዛቸው የሚጠቁሙት የአሜሪካ ሚያሚ ዴድ ካውንቲ ግዛት የንግድ ማህበረሰብ ሊቀመንበር ኦድሪ ኤድሞንሰን፤ በኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነትና መልካም መስተንግዶ እንደተደሰቱ ተናግረዋል።
ጉብኝታቸው ከሦስት ዓመታት በፊት በሚያሚ ግዛት በተካሄደው የንግድ ትርዒት ስለ አገሪቱ የሰሙትን መሰረት አድርገው እንደሆነም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የተሻለ ውጤታማ ግን ኙነት እንደሚያስመዘግብና ለሁለቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነት እና የኢኮኖሚ ትስስር የጎላ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በዘላለም ግዛው