ኢትዮጵያ የቀደምት ዘመን ስልጣኔ ተምሳሌት የራስ ባህል፣ ማንነት እንዲሁም ሉአላዊ ግዛት ያላት ጥንታዊ አገር ነች። ለዘመናት የራሷን አገረ መንግስት መስርታ በማንም ቀኝ ገዢ እጅ ሳትወድቅ አሁን ላይ ከመድረሷም ባሻገር የብዝሃ ባህል፣ ህዝብ፣ ቋንቋ ብሎም የጥበብና እውቀት መፍለቂያ ምንጭ እንደሆነች የታሪክ መዛግብትና እውቅ የዓለማችን ፀሃፍት ይመሰክሩላታል።
አትዮጵያ የኪነ ጥበብ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ፣ ኪነ ህንፃና ስነ ፅሁፍ እውቀት ያበረከተች መሆኗም እሙን ነው። ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ቀደም ያሉ የስልጣኔ አሻራዎች ናቸው። አሁን ላይ በዓለም የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ በቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙ ኪነ ህንፃዎች፣ የስነ ፅሁፍ ውጤቶች፣ ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም ታሪካዊ ክስተቶች አገራችን ለመላው የሰው ልጆች ዛሬ ላይ የመድረስ ምክንያት እንደነበረች ህያው ምስክር ናቸው።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ምድረ ገነት፣ የአባይ ምንጭ መፍለቂያ የ13 ወር ፀጋን የተላበሰች ከመሆኗም ባሻገር ከጉያዋ የወጡ ጥበበኞች ምክንያት በራስ የተቀረፀ ፊደልና የፊደል ገበታን፣ የዘመን መቁጠሪያን፣ በአስትሮኖሚና በክዋክብት ምርምር፣ በሂሳብ ቀመር ምርምር፣ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሁም በርከት ያሉ እሴቶችን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቶችን ለዓለም ማበርከት ችላለች።
ከሁሉም በላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ልምላሜን የምናይበት ከተፈጥሮ ጋር ተሰባጥረን በብሩህ ተስፋ ነገን የምንናፍቅበት፣ በአዲስ እቅድና በንፁህ አእምሮ ለስልጣኔ የምንተጋበት የአዲስ አመት መባቻ አለን። ይህን ወቅት ጠንቅቀን የምንለይበት ከራስ የተቀዳ የዘመን አቆጣጠር ባለቤቶችም ነን። ጥንታዊው የዘመን አቆጣጠር እጅግ የተራቀቀ ነው።
አዲስ ዘመን ለመቀበል የቀናት እድሜ ነው የቀረን። ኢትዮጵያውያን 2014 ዓም ሸኝተን 2015 ዓም አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ነው። ይህ የእኛ ብቻ የሆነና በዓለም ብዙዎችን የሚያስደንቀው ቀመርና አቆጣጠር የማንነታችን መገለጫ፣ የእውቀታችን መለኪያ ከመሆኑም ባለፈ በሌላኛው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ የውጪ አገር ዜጎች ኢትዮጵያንን የበለጠ ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው፣ በዚህም ተነሳስተው እውቀቶቻችንን፣ የስነ ፅሁፍ ሃብቶቻችንን፣ የተፈጥሮና ታሪካዊ የቱሪዝም ሃብቶችን ለመጎብኘት እንዲመጡ ሰፊውን እድል የሚከፍት ጭምር ነው። አዲሱ ትውልድም የአባቶቹን እውቀት ቀደምት ስልጣኔና ሚስጥር መለስ ብሎ እንዲያስተውልና ዳግም እንዲያንሰራራ እድል የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌላው የዓለም ክፍል በተለየ አንድ ዓመትን በ13 ወራት ከፍላ ዘመንን የምትቆጥር አገር ናት። ይህ ለመሆኑ ደግሞ የራሱ ቀመርና እውቀትም አለው። ከሁሉ በላይ 13ተኛው ወር “ጰጉሜን” ልዩ የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር መገለጫንና ሚስጢራትን የያዘች ነች። የዝግጅት ክፍላችን አሮጌውን ያጣናቀቅነውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን 2015 ዓም የምንቀበልበት የጰጉሜን ደጃፍ ላይ መድረሳችን አስመልክቶ ስለአገራችን ዘመን አቆጣጠርና ስለ 13ተኛዋ ወር አመጣጥና ሚስጢር ምሁራንን፣ መዛግብትንና ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን በማጣቀስ ጥቂት ሃሳቦችን ልናቀብላችሁ ወደናል።
ከሁሉ በላይ ለበርካታ አመታት “የ13 ወር ፀጋ” በሚል ኢትዮጵያን ለቱሪዝም ሃብቶቻችን ማስተዋወቂያ ብራንድነት ስንጠቀምበት የነበረውን የዘመን አቆጣጠር ሚስጥራትን የሚገልጡ ማስረጃዎችን እናቀርባለን። ይህን መሰል የራስ ፀጋዎች ያሉንን ሃብቶች እና እውቀቶች በአግባቡ መረዳት እንድንችል ከማድረጉም ባሻገር የአገራችንን መልካም ገፅታ ለመገንባት፣ በቱሪዝም እና መሰል ዘርፎች ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማጎልበት እንደሚረዳ እናምናለን። “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” የሚሉትን ብሂል ለመስበር” እንደሚረዳም እንዲሁ።
“ጰጉሜን” ከ12ቱም ወራት በተለየ መንገድ አንድ ሳምንት የማይሞላ (አምስት እና ስድስት) ቀናትን የምትይዝ ናት። ለመሆኑ የጰጉሜን ወር እና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ምን አይነት ይዘትና ሚስጥራት አለው? ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የኢትዮጵያ ጥበብ እና ሃይማኖታዊ እውቀቶች ላይ ምርምር የሚያደርጉ ምሁር ናቸው። ስለ 13ተኛው ወራትና ስለ ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ሲናገሩ ጰጉሜን የሚለው ስያሜ የመጣው ሊቃውንት “ትርፍ ወይም ተረፍ” የሚለውን ትርጓሜ እንዲሰጥ አስበው መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ተጨማሪ ቀን የሚለውን ፍቺ እንዲይዝ ታስቦ መሆኑን ያስረዳሉ። ከመስከረም እስከ ነሀሴ ያለው ወር 30 ሙሉ ቀናትን የሚይዝ ሲሆን 13ተኛዋ ወር 5 ቀናትን ትይዛለች። በአራት አመት አንድ ግዜ ደግሞ 6 ቀናት ስትይዝ በ600 ዓመት አንድ ግዜ ደግሞ 7 ቀናት ይሆናሉ።
ዶክተር ሮዳስ “የኢዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሊቃውንት አተናተን ወይም አመሰጣጠር አንድ እለት 24 ሰዓትን ይይዛል። 12 ሰዓት ቀን 12 ሰዓት ደግሞ ሌሊት። በዚህ መሃል ትርፍ ደግሞ 52 ካልኢት እና 31 ሳልሲት አሉ” ይላሉ። ይህ ማለት በ12ቱ ወራት ውስጥ ትርፍ ሰከንዶች በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የሂሳብ ቀመር ተደምረው እንዴት 5 እና 6 ቀናትን በ600 ዓመት አንድ ግዜ ደግሞ 7 ቀናትን የምትይዘው ጰጉሜን እንደምትፈጠር ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ “አንድ ካልኢት” ማለት 24 ሰኮንድ ሲሆን” ከመስከረም አንድ እስከ ነሀሴ 30 ድረስ ተደምሮ የሚመጣው 52 ካልኢት እና 31 ሳልሲትን በማባዛት 13ተኛዋን ወር ጰጉሜን እንደምናገኝ ይገልፃሉ። ይህን በትክክለኛው የሊቃውንት የሂሳብ ቀመር ስናስቀምጠው የሚከተለውን ይዘት እንደሚይዝ ይገልፁልናል።
እንደ ዶክተር ሮዳስ ገለፃ 52 ካልኢትን በ24 በማባዛት የምናገኘው ሴኮንድ ወደ ደቂቃ ስንቀይረው 20 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ እናገኛለን። 31 ሳልሲትን ወደ ሴኮንድ (ቅፅበት) በመቀየር የምናገኘውን 12 ነጥብ 2 ሴኮንድ ከ20 ደቂቃ 48 ሴኮንድ (ቅፅበት) ጋር በመደመር 21 ደቂቃ ከ0ነጥብ 4 ሰከንድ እናገኛለን። ይህ ስሌትም ከመስከረም አንድ እስከ ነሀሴ ሰላሳ ባሉት 12 ወራት ውስጥ በሚገኙ እያንዳንዱ ቀናት ውስጥ 21 ደቂቃ ከ0 ነጥብ 4 ሰከንድ (ቅፅበት) ትርፍ እንዳለ ለማወቅ ያስችላል።
ዶክተር ሮዳስ ከእያንዳንዱ እለት ውስጥ የምናገኘው 21 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ ተደምሮ በወር 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በሶስት ወር 30 ሰዓት ከ90 ደቂቃ። በየ ዓመቱ 5 ቀናትን የሚይዝ በየ አራት አመቱ ደግሞ 6 ቀናትን እንዲሁም በ600 ዓመት አንድ ግዜ ደግሞ 7 ቀናትን የምትይዘውን ጰጉሜን ይሰጠናል” ይላሉ። ከስድስት ክፍለ ዘመናት በኋላ የምናገኛት 7 እለታትን የምትየዘው ጰጉሜን እንድትከሰት የሚታደርገው ትርፍን ሴኮንድ (ቅፅበት) ደግሞ ዜሮ ነጥብ አራቷ እንደሆነች ይናገራሉ። እነዚህ ሴኮንዶች (በግእዝ ካልኢትና ሳልሲት በመባል የሚታወቁት) ተደምረው ተካፍለውና ተባዝተው በኢትዮጵያውያን የሂሳብ ቀመር ከሴኮንድ ወደ ደቂቃ ከደቂቃ ወደ ሰአት ከሰአት ደግሞ ወደ እለት ተቀይረው የጰጉሜን እለት እንደሚያመጡ ይገልፃሉ። ይህን ረቂቅ የሂሳብ ቀመርና ጥበብ ላስተዋወቁን ሊቃውንት ክብር ይገባል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሮዳስ ገለፃ በኢትዮጵያ የስነ ፈለክና የዘመን ቀመር ሊቃውንት ጰጉሜን 5 በባህረ ሃሳብ (የኢትዮጵያውያንን የዘመን አቆጣጠር የሚያስረዳ) “እለተ ምርያ አይዋዲት” ወይም የመዳህኒት እለት ወይም አሸጋጋሪት በመባል እንደምትታወቅ ይናገራሉ። ይህ ቀን ከሰኞ እስከ አርብ በአንዱ ቀን ሲውል (ለምሳሌ የ2014 የዘመን መጨረሻ ጰጉሜን 5 ቅዳሜ ቀን ይውላል) የልደት (የገና በአልም) ሁሌም በተመሳሳይ ቀን ላይ እንደሚውል ይናገራሉ።
የስነልሳን እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ባለሙያ ግርማ አውግቸው ደመቀ ካሳተሟቸው መጽሐፎች መሀከል ዘመን አቆጣጠር የቀናትና የወራት ስያሜ ላይ በኢትዮጵያ በርካታ አቆጣጠሮች እንዳሉ ሊቃውንት እንደሚናገሩ ያስረዳሉ። ከሲቪሉ አቆጣጠር በተጨማሪ፣ ባህላዊ እንዲሁም ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ አቆጣጠሮች እንዳሉም ይገልፃሉ። በባህላዊ ረገድ የሲዳማውና በቦረና ኦሮሞ ዘንድ ያሉትን አቆጣጠሮች መጥቀስ ይቻላል። ከሃይማኖታዊ የዘመን ቀመር ወይም አቆጣጠር ውስጥ የእስልምናውን አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል። የእስልምና ተከታዩ ህዝብ የሀይማኖቱን በዓላት፣ አፅዋማትና ባጠቃላይ ከእስልምና ጋር የተያያዙ የእምነት ጉዳዮቹን የሚያከናውነው በእስልምናው አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናም አብዛኛው በዓላት በሲቪሉ አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ የሚከበር ቢሆንም ተንቀሳቃሽ በዓላቱ የሚሰሉበት የተለየ ቀመር አለ።
ስለ ኢትዮጵያ የግዜ ስሌትና ዘመን አቆጣጠር በተለያየ ወቅት ሊቃውንት በዙ መዛግብት አስቀምጠዋል። በተጨማሪ በርካታ ምሁራን የጥንት አባቶችን ቀመር በማጥናት አዲሱ ትውልድ እንዲያስተውለው ለማድረግ ሞክረዋል። የውጪ ፀሃፍትም እንዲሁ ጥልቅ ጥናትና ምርምር አድርገዋል ለምሳሌ፣ በአማርኛ ከተፃፉት ውስጥ ጌታቸው ኃይሌ (2006) እና አለቃ ያሬድ (2004) በስራዎቻቸው ላይ ብዙ ብለዋል። በእንግሊዝኛ ከተሰሩት ውስጥ ደግሞ “ኒውጌባወርን” (1964፣ 1979፣ 1988፣ 1989) ማየት ይቻላል።
ኢትዮጵያዊ እሴቶች የቱሪዝም ሀብቶች
በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው ኢትዮጵያ የአያሌ እሴቶች ባለቤት ናት። ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ተፈጥሮ እና በጋራ አብሮ የመኖር ተምሳሌት ነች። ከሁሉ በላይ ግን በአፍሪካ ብቸኛዋ የራሷ ፊደል ያላት፣ በክርስትና እና እስልምና እምነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተከባብረው በጋራ የሚኖሩባት ብዙዎች የምታስደምም ዘርፈ ብዙ እሴት ያላት ነች።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በስፋት መዳሰስ እንደቻልነው ከሌላው ዓለም በተለየ የራሷ የዘመን ሥሌትና ቀመር ያላት ጥንታዊት ሀገር ናት። ለዚህ “የባህረ ሃሳብ ጥንታዊ መዛግብት” እና ሌሎች ማስረጃዎችን ማንሳት ይቻላል። የክረምቱ ወቅቷ የሚፈጥረው ዝናባማ፣ ብርዳማ አየር ሁኔታ ተገልጦ ተስፋ ከብርሃናማ የሰማይ ድምቀት እና ከምድሯ ልምላሜ እና የአደይ አበባ ፍካት ጋር ተደማምሮ በሕዝቧ የአኗኗር ባህል ውስጥ የኖረ፣ ያለና የዳበረ ልዩ የአዲስ አመት ክብረ በዓልም አላት። ባህላዊ ጨዋታዎች፣ ተስፋ የሰፈነበትን የጳጉሜን መጨረሻ እና የመስከረም መጀመርያን ታክኮ የሚገለጠው የሀገሬው ሕይወት በግላጭ ይታያል፣ ይደመጣል ፣ ይሸተታል፣ ይቀመሳልም። ኢትዮጵያዊያን የአዲስ አመት ጅማሮ ወቅታቸውን ሕፃን አዛውንት ፣ ሴት ወንድ ሳይሉ በደስታ፣ በፍቅር ተሰባስበው « እንኳን አደረሰህ፣አደረሰሽ ፣ መልካም አዲስ አመት ፣ የሰላምና የጤና ዓመት ይሁንልን» እየተባባሉ ያልኖሩትን ነገን በጎ ሆኖ እንዲጠብቃቸው እርስ በእርስ መልካም ምኞታቸውን ይገላለፁበታል።
ይህ ሁሉ ያልተመነዘረ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው። ቀሪው ዓለም እነዚህን ውብ ድብልቅ እሴቶች ማወቅ እንዲችልና የአገሪቱ መልካም ገፅታ ጎልቶ እንዲታይ መስራት የሁሉም ድርሻ ነው። በባህላችን፣ በሃይማኖታዊ ስርዓቶቻችን፣ በአመት በአሎቻችንና ሊቃውንት ባስተላለፉልን ጥበብ ለራሳችን ከመፍካት ባሻገር ወደሚመነዘር የቱሪዝም ሃብት ልንቀይረው ይገባል። ከመላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚያማትሩና በጋራ እሴቶቻችን የሚደመሙ አያሌ ጎብኚዎችን አፍርተን ተሻጋሪ ማንነት መገንባት ይኖርብናል። ይህ ሲሆን እራሱን ጠንቅቆ የሚረዳ፣ በስልጣኔ የረቀቀ ትውልድና ጠንካራ አገር ያለጥርጥር መገንባት እንችላለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014