የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባለፉት ስምንት ዓመታት 3ነጥብ2 ቢሊዮን ብር መባከኑን አስታውቋል። የባከነውን ገንዘብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከዛሬ ማስመለስ አልቻለም። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ፤ ተሿሚዎች የባከነውን ገንዘብ ማስመለስ ካልቻሉ በህጉ መሰረት እቀጣለሁ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም ለመንግሥት መመለስ ከነበረበት 2ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ጉድለት እስካሁን የተመለሰው 50 ሚሊዮን ብር አይሞላም ብለዋል።
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ 190 ተቋማት የኦዲት ግኝት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። አንድ ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጉድለት 15 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እና 20 ዩኒቨርስቲዎች በድምሩ 35 ተቋማት ወደ ህግ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራም ተሰርቷል ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ኃላፊዎቹ በትኩረት ሰርተው ካላስመለሱ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ገልጸዋል። ይህንን አስመልክቶ ምሁራን አስተያየት እንዲሰጡን አነጋግረናቸዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚስ ኮሌጅ ዲንና መምህር ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ፤ የመንግሥት የሂሳብና የፋይናንስ ስርዓት አሰራርና
ህጋዊ ተጠያቂነት ደካማ ነው። መንግሥት የባከነን የህዝብ ሀብት ለማስመለስ ቁርጠኛ አይደለም። በየተቋማቱ ያሉ ባለሙያዎች ብቁ ካለመሆናቸውም ባለፈ በኃላፊነት እንዲሰሩም ዕድል አልተሰጣቸውም። የተቋማት መሪዎችም የፋይናንስ እውቀት የላቸውም። በፋይናንሱ ብክነት ከፍተኛ አመራሮች እጃቸው ስላለበትና
ስለሚነካኩ ለማስተካከል ቁርጠኝነት የላቸውም። በዚህ የተነሳ ችግሩን ለማስተካካል ያስቸግራል፤ ይላሉ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ተመስገን ሲሳይ (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ የፋይናንስ ብክነቱ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 2 ማንኛውም ተቋምና ኃላፊ በህዝብ ሀብት ላይ ለሚያደርስው ጉዳት ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ ያስቀምጣል። በስነ-ምግባርና በጸረ-ሙስና አዋጁም የኦዲት ግኝት ማስተካከል ካልተቻለ በሙስና እንደሚጠየቅ ይደነግጋል።
በህገ መንግሥቱና በልዩ ልዩ አዋጆች ተጠያቂ ቢያደርግም እስካሁን አልፎ አልፎ በፖለቲካ ውሳኔ የተወሰኑ ሰዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ ህጋዊ መሰረቱ ጠብቆ የተጠየቀ ሰው የለም። ይህ በብዙዎች ዘንድ ቅራኔ ፈጥሯል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የአሁኑ ጠቅላይ አቃቢ ህግ
(የበፊቱ የፍትህ ሚኒስቴር) ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ለዚህም እንቅፋት የነበረው የፖለቲካና የመንግሥት ውሳኔ መደበላለቅ ነው። በህጋዊ አሰራሩ መሰረት መከስስ ያለበትን በፖለቲካ ውሳኔ ያስቀራል። መከስስ የሌለበት በፖለቲካ ውሳኔ ይታሰራል። በዚህ የተነሳ የአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት የተሳከረና ችግር ውስጥ የገባ ሆኖ ቆይቷል ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር አቶ ታረቀ አያሌው፤ ለገንዘቡ መባከን ምክንያቱ ተቋማትንና ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት አለመኖሩ፤ በፋይናንስ ሥራ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፤ ብቃት የሌላቸው ባለሙያዎች መሰግሰግና ለጥፋቱ ድክመታቸውን መደበቂያ ማድረግ፤ ያጠፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተጠያቂ አለመደረጋቸው የመንግሥትን የፋይናንስ አሰራር ሽባ አድርጎታል።
የዚህ ዋና መንስዔ የከፍተኛ አመራሩ እጅ መሰንቀርና ለማስተካከል አለመፈለግ ነው። በዚህ የተነሳ የህዝብ ሀብት እንዲባክን አድርጎታል። ለዚህ ማሳያው ስምንት ዓመት አይደለም በየዓ መቱ እየታረመ መሄድ የሚችለውን ለማስተካከል አልፈለጉም። ያልፈለጉት ከላይ እስከታች ስለተነካኩ ተጠያቂነት ቢጀምር ሁሉንም ስለሚ ያስጠይቅ መሆኑን ያመላክታሉ።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲግና ፋይናንስ ኮሌጅ ዲንና መምህር ዶክተር ለሜሳ ባይሳ፤ ሁሉም ኃላፊዎች ስለተነካኩ ማንም ማንንም ለመጠየቅ አለመፈለጋቸው ወይም አለመድፈራቸው ከመጀመሪያው እየተስተካከለ ላለመምጣቱ ዋናው ምክንያት ነው። በዚህም ከባከነው ገንዘብ በላይ ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት በማጣት መክፈል የሚገባቸውን ግብር እንዳይከፍሉ አድርጓል። እምነት በማጣትም ግብርን እንዲሰውሩ አድርጓቸዋል። በመንግሥትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዲናድ ማድረጉን ከባከነው ገንዘብ በላይ ትልቅ ጉዳት እንዳደረሰ ይገልፃሉ።
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ችግሩ አገሪቱን ወደ አዘቅት ይዟት እንደገባ ተረድቶ ተጠያቂ ወደማድረግ እየሄደ ነው። ህጉን መሰረት አድርጎ አባካኞችን ተጠያቂ ማድረግ አለበት። ገንዘቡን ተመላሽ ከማድረግ ባለፈ ከዚህ በኋላ እንዳይሰረቅ ማስተማሪያ ማድረግም ይገባል። የፋይናንስ አካሄዱ ሙያዊ አሰራራን መሰረት አድርጎ እንዲከናውን ያደርጋል። ይህንን አካሄድም በክልሎችም ጭምር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ያመላክታሉ።
ዶክተር ቀነኒሳ በበኩላቸው፤ መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግ እያደረገ ያለው ዝግጅት አስተማሪም ይሆናል ይላሉ። ከተጠያቂነቱ ጎን ለጎን የፋይናንስ አሰራርን ማስተካከል ዋና ጉዳይ መሆኑን ያመላክታሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የባለሙያዎችንና የተቋማትን አቅም መገንባት፤ ተጠያቂነት መሰረት ያደረገ ነፃነት መዘርጋት፤ የፋይናንስ ሥርዓትና ህግን መሰረት አድርጎ እንዲሰራ መደገፍ፤ ተጠያቂነቱ በጅምላ ሳይሆን አስተማሪና የአገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት አካሄድ በሚያርም መሰረት መሰራት አለበት።
የመንግሥትና የፓርቲ አሰራር መደበላለቅ የችግሩ ማጠንጠኛ ስለሆነ መለየት ይገባል። የፋይናንስን ሥራ በባለሙያ ማሰራት፤ የፖለቲካ ሹመኞች አመራር ከመስጠት ባለፈ በፋይናንስ ሙያ ጣልቃ እንዳይገቡ በማድረግ ሙያን ለባለሙያተኛ መተው አለባቸው። ተጠያቂነቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በማሰፋት በአገሪቱ ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት ማስተካከል እንደሚገባ ይመክራሉ።
በሌላ በኩል አቶ ታረቀም፤ መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግ መወሰኑ መልካም መሆኑን ያነሱና አካሄዱ ሁሉንም በእኩል አይን የሚያይና ህግን መሰረት አድርጎ በአስተማሪነቱ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆን እንዳለበት ያነሳሉ። ሁሉንም አጥፊዎች መጠየቅ ባይቻልም እንኳን የመወሰን ኃላፊነት የነበራቸውንና ያልፈጸሙትን መጠየቅ አሁንና ወደፊት ለማጥፋት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ይገታል፤ ያርማል። ዜጎችም ተጠያቂ ሲሆኑ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያደርጋል። የሚወሰደው ርምጃ ስራው በባለሙያዎች እንዲመራና አሰራር እንዲከበር ያደርጋል። ርም ጃውን ከፌዴራል በተጨማሪ ወደ ሁሉም ክልሎች በማውረድ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠያቂነትን ማስፍን እንደሚገባም ይናገራሉ።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲው አቶ ተመስገን ሲሳይም (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ መንግሥት የጀ መረው የተጠየቂነት አካሄድ የዘገየ ፍትህ ቢሆንም መልካም ነው። ኃላፊዎችና ዜጎች ባጠፉት ጥፋት ተጠያቂ ማድረግ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ያደርግል። የፋይናንስ መባከን ሙሉ ለሙሉ ባያሰቀረውም እንዲቀንስ ያደርጋል።
የፋይናንስ አሰራር እንዲስተካከል ያደርጋል። የተደባለቀው የፓርቲና የመንግሥት አሰራር እንዲለይ ያስ ገድዳል። የጅምላ ፍትህ ውጤት ስለማያመጣ ይህን ያገናዘበ አካሄድ ያስፈልጋል። በተለይም በአንድ ጊዜ ሁሉም ተቋማት የሚጠየቁ ከሆነ መደናገጥ ስለሚፈጥር በስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርጋል። ይህን ከገንዛቤ ያስገባ ርምጃና በቀጣይም በየጊዜው እያስተካከለ መሄድ አለበት ብለዋል።
በእርግጥ በዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ጉድለት የተገኘባቸውም ይሁኑ ሌሎች ተቋማት ከዚህ ጉዳይ ሊቀስሙት የሚገባ ዓይነተኛው ቁምነገር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም ጉዳይ ላይ መቼም ተጠያቂነት ካለ እንደማይቀር ነው። ምክር ቤቱም በዚህ ሪፖርት ላይ ተንተርሶ፤ እንዳለውም ርምጃ የሚወስድ ከሆነ የባከነው የሀገር ሀብት እንዲመለስ የሚያስችል መሆን ይኖርበታል።
ከዚህ ባሻገር፤ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ በተቋማቱም ሆነ በአመራሮቹ ላይ የተጠያቂነት ርምጃ የሚወሰድ ከሆነ ይበልጡኑ አስተማሪ መሆኑ ይገባዋል። ርምጃው የወደፊት መጪዎችንም ይሁን በአሁኑ ወቅት በአመራር ላይ ያሉትን የሚያስበረግግ ሊሆን አይገባም። ይልቁንም በእያንዳንዱ ኃላፊነት ትይዩ/አንጻር ተጠያቂነት መኖሩን የሚያዘክር እንጂ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ