ወላጅ እናቷ በኪራይ ቤት ኑሮ ቆሎ እየሸጡ ሲያሳድጓት እንዲከፋት አድርገው አልነበረም። ሁልጊዜ ደስተኛ ሆና እንድታድግላቸው ሲጥሩ ኖረዋል። ተምራ ከቁምነገር እንድትደርሰም የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ይህ ሁሉ ግን ለእርሷ ሰቀቀኗ ነበር። ‹‹መቼ ነው ከዚህ ህይወት የማወጣት››ይሉት ጥያቄ ጭንቀቷ ሆኖ ዓመታት ተቆጥረዋል።
አንድቀን ግን ቆረጠች። ባህር ማዶ ተሻግራ የእናቷን ችግር መፍታት እንዳለባት ወሰነች። ወጣቷ ገነት አበበ በሀሳብ ብቻ አልቀረችም። ያቀደችው ተሳክቶ ወደ አረብ አገር ተጓዘች። ለዓመታት ሰርታ የሰራችበትን ቋጥራ ወደአገር ቤት ተመለሰች።
የመጀመሪያው ህልሟ እናቷን ከኪራይ ቤትና ቆሎ ከመሸጥ ሕይወት ማላቀቅ ነው። እንዳሰበችው ሁሉን ማሟላት አልሆነላትም። ሰርታ ያመጣችውን ገንዘብ ወዲያው ለቤት ግዢ አላዋለቺውም። ለጊዜው በሚል ቤት ተከራይታ የቤት ቁሳቁስ ማሟላቱን ያዘች። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ የነበራትን ገንዘብ ቀነሰው።ገነት ያሰበችውን ቤት ሳትገዛ ብሩ እንደዋዛ ተመዞ አለቀ። እንዲህ መሆኑ ከድንገቴ ችግር ጣላት። የጠዋት ማታ ልፋት ድካሟ ጠብ ከሚል ውጤት ሳያደርሳት ሕይወትን ቀጠለች።
ችግር ያልበተነው ትዳር
ከአረብ አገር እንደተመለሰች ከተዋወቀችው ባለቤቷ ጋር ትዳር መሰረተች። እሱም እንደእሷ በአረብ አገር የቆየ ነበርና ውስጣቸው ለመናበብ አልዘገየም። ከቤተሰቧ ጋር በጋራ በመኖር ዓመታትን በፍቅር አሳልፈዋል። ከቆይታ በኋላ ባል ለስራ ጉዳይ ተመልሶ ወደ አረብ አገር ሄደ።ኑሮን ለመግፋት ህይወትን ለመለወጥ የእሱ ወጣ ማለት ግድ ነበር።
የማታ ማታ ግን ሁኔታዎች መቀየር ያዙ ። ገነት ህይወቷን የሚረብሽ ደስታ ሰላሟን የሚያናጋ ችግር ገጠማት። ለስራ ከአገር የወጣው ባለቤቷ ድንገት መታመሙን ሰማች።ይህኔ ትይዘው ትጨብጠው ጠፋት።በሰው አገር መሆኑ ሲያስጨንቃት ተመልሶ የመምጣቱ እውነት ደግሞ ከራሷ ያሟግታት ያዘ።
ሥራዋ ጥቂት ገቢ ቢያስገኝም ከቤት ኪራይ አልፎ ቤተሰቡን እንዳሻው የሚመገብ አይደለም። ያም ሆኖ የልጆቿን አባት መግፋት አልተቻላትም። ከሄደበት እንዲመጣ ወስና ከእናቷ ጋር ያገኘችውን እየሰራች መንከባከቧን ቀጠለች።
ኑሮ አስጨነቃት፣የቤት ኪራይ ወጪ አንገበገባት። በዚህ መሀል እናቷን በሞት ተነጠቀች። ልቧ ተሰበረ። ሀዘኑ ከበዳት። በዚህ ጭንቅ ጊዜ ባለቤቷ እያጽናና አበረታት።ልጆቿ ተስፋዎቿ ሆኑ። ውላ አድራ ሀዘኑን ተቋቋመች። ከእሮሮ ይልቅ ሮጦ ማደርን መርጣ መልፋቷን ቀጠለች።
ቃልኪዳንን የፈተነ ችግር
በተሻለ ለውጥ ለመራመድ ሥራዋን ማጠንከር ነበረባት ።ይህ ይሆን ዘንድ በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል። በእጇ ያለው የቃልኪዳን ቀለበቷ ነበር። ምርጫ አልነበራትም። ከጣቷ አውልቃ ሸጠችው። የችብስ ማሽን ገዛችና ከበሯ ቆማ ንግዱን አጧጧፈችው። ለዚህ ደግሞ ከደጃፏ ያለው ግሮሰሪ በእጅጉ አግዟታል። ብዙ ደንበኞች እያመጣ ፣ የልጆቿ ወተት እንዳይጓደል አግዟታል። እንዲያም ሆኖ ዕንቅፋት አላጣትም።አከራዮቿ ‹‹ረበሽን›› አሏት። እርሷም ብትሆን የቤት ኪራዩ እንደከበዳት ታውቃለች። ግን የት እንደምትሄድ ጨንቋታል። ባለቤቷ ህመምተኛ፤ ልጆቿ የእርሷን እጅ ጠባቂ ናቸው።
በትዕግስት መኖር ቀጠለች። አንድ ቀን የባለቤቷ ጓደኛ አንድ ጉዳይ ሹክ አላት። ሀሳቡን በዋዛ መተው አልፈለገችም። እሱ በሚኖርበት አካባቢ ሸራ ወጥረው እንዲኖሩ መከራት። አላቅማማችም። ስለቤት ኪራዩ ስትል ተስማማች። እቃዋን ሸክፋ ከባለቤቷና ልጆቿ ጋር ወደ ቦታው አመራች። ሸራዋን ወጥራ ቤቷን ቤት ማድረግ ጀመረች።ህይወት እንደ አዲስ በሸራ ጎጆ ቀጠለ።
ህይወት በሸራ ቤት
ሸራ ወጥራ የምትኖርበት አካባቢ በተለምዶ ‹‹ጌጃ ሰፈር››ይባላል። በተለይ እነሱ ያረፉበት ስፍራ በእጅጉ ስጋት የከበበው ነው ። ማንም ሊኖርበት ቀርቶ ሊያልፍበት የማይደፍር ቦታ ስለመሆኑ ይነገርለታል። ጫካ ስለሚበዛው አውሬ አይጠፋውም።በምሽትም ሆነ በቀን ፍርሀትን ያጋባል።
ገነት መኖርን ሽታለችና ፈተናውን ልትጋፈጥ ግድ ብሏል። አሁን እሷን ከመሰሉት ጋር ተጎራብታለች። ሸራ ወጥራ ኑሮን አሀዱ ብትልም ሁኔታው በቀላሉ የሚገፋ ግን አልሆነም። ሁሌ በሰቀቀን ውላ ታድራለች። የላስቲክ ቤት ከአደጋዎች የራቀ አለመሆኑ ዕንቅልፍ ይነሳታል። ሁሌም ከባለቤቷ ጋር በዕንቅልፍ አልባ ለሊቶች ልጆቻቸውን በንቃት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል ። ፡ ሴት ልጆች ላሉዋት እናት ደግሞ ነገሮች ሁሌም ከባድ ናቸው። እናም ወጣቷ ገነት ይህንን ሕይወት ለአራት ዓመታት እንድታሳልፈው ሆነ።
ክረምት ሲገባ ሁኔታዎች ሁሉ መከራ ይሆናሉ። ብርድና ዝናቡን፤ የመሬቱን ርጥበት ይሁነኝ ብላ ብትቀበልም የበጋ ፀሐይ የበጣጠሰውን ሸራ ለመቀየር ጭምር እጅ ያጥራት ነበር። ይህን ማድረግ ቢቻላት እንኳን ‹‹ሸራውን ልቀይር አትቀይሪም››ይሉት ውዝግብ ሌላ ፈተና ነበር። የክረምቱ ዝናብ ጎርፍ ሆኖ የሚያሰቃያትን ጊዜ ደግሞ ፈጽሞ አትረሳውም ።
ገነት ለሕጻኑ ልጇ አስተዳደግ መፍትሄ የሆነላት ወደ አያቷ ቤት መላኳ ነው። እንዲህ ባታደርግ ኖሮ ከማትወጣው ስቃይ ትገባ ነበር።ልጁ በእሱ አቅም ቅዝቃዜውን የሚቋቋም ባለመሆኑ ልታጣውም ትችላለች። አንዳንዴ እነሱንም ቢሆን የሚታደጓቸው የሰፈር ወጣቶች ናቸው። ብር አዋጥተው፣ ሸራ በመግዛት ችግራቸውን ይጋራሉ። ገነት ለነዚህ ልበ ቀና ወገኖች ምስጋናዋ የተለየ ነው።
ሁሌም የመሬቱ ርጥበት በእፎይታ አያስተኛቸውም። ለሙቀቱ እንጨት ለቅማ ማንደድ ይጠበቅባታል። እንዲህ በሆነ ጊዜም ፈተናው ከባድ ነው። ቤቱ በጭስ ይታፈናል። ልጆቹ በከባድ ሳል ይጨነቃሉ። ግድግዳውም በድንገቴ ፍንጣሪ በእሳት ሊያያዝ ይችላል።
ኑሮ ካሉት…
ገነት ቤት ተከራይታ ስትሰራው የነበረውን ችብስ እዚህም ቀጥላለች። ሁሌም ማለዳ ለእለት ጉርስ ካዘጋጀች በኋላ ችብስ ወደ መስራቱ ትገባለች። የሠራችውን የማከፋፈል ሥራም ተግባሯ ሆኗል። ሁሌም በላስቲክ አሽጋ ‹‹ገኒ ችብስ››በሚል ስያሜ ለሱቆች ታስረክባለች። ይህ ታታሪነቷ ቤተሰቧን ደጉሟል።
ይህ ስራ ግን ቆይቶ ዕንቅፋት አላጣውም። አሁንም ጎረቤቶቿ ተቃወሟት። ‹‹ማታ አምሽተሽ መሥራትሽ ይረብሸናል›› አሏት። ችግሩ በዚህ ብቻ አልቆመም። ሰዎቹ የመብራት ክፍያን ጠየቋት። ምርጫ አልነበራትም። ችፕስ ሽጣ ካኖረችው 2500 ብር አንድም ሳታስቀር ቆጥራ ከፈለች። በእዚህና በሌሎች ምክንያቶች በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ለሊቶችን አሳለፈች።
ገነት ‹‹ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮዋን መደጎም እንዳትችል ሆና ተጎዳች። እንዲህ መሆኑ ግን ብርቱዋን ሴት አልሰበራትም። ሁሌም መሽቶ ሲነጋ ለአዳዲስ አማራጮች ዓይኗን ታማትራለች። ይህ ጥረቷ ከሌላ ስራ አገናኛት። ፈጣን ምግቦችን እያዘጋጀች መንገድ ላይ መሸጥ ጀመረች። ሥራው ከሌሎች የሚያገናኛት አይደለም። ዘወትር ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ማለዳውን ተነስታ ከጌጃ ሰፈር ሜክሲኮ በእግሯ ትጓዛለች። መንገዷ የበዛ ድካም አለው። ምግቦቹን የሚንቀሳቅሱበትን የብረት ጋሪ ያለረፍት መግፋት ይጠበቅባታል።
እርግዝና- በዘመነ ኮሮና
ለገነት ዕለተ እሁድ የእረፍት ቀን ሆኖ አያውቅም። ‹‹ምናለሽ ተራ›› እየሄደች ለቁርስ እንቁላል በሥጋ አዘጋጅታ ትሸጣለች። ሥራው ከእሷ አቅም በላይ አልነበረም። በወቅቱ ሦስተኛ ልጇን ነብሰጡር መሆኗ ግን በእጅጉ ፈትኗታል። ሰባት ወር እስኪሞላት ከራሷና ከስራው ስትታገል ቆየች። ጋሪውን ስትገፋ ትንፋሽ ስለሚያጥራት ኃይለኛ ሳል ያጣደፋት ነበር። ደንበኞቿን ላለማጣት ስትል ሳሉ መለስ እስኪል ያለሥራ ትቀመጣለች። እንዲህ መሆኑ ገበያዋን ካሰበችው በታች አውርዶ ለኪሳራ ይዳርጋታል።ዛሬ አርግዝናዋንና የጋሪ መግፋቱን ስታስታውሰው አስቸጋሪው ጊዜ በዓይኗ ውል ይላታል።
ገነት ሥራዋን እንደ ንግድ ብቻ አይታው አታውቅም።ለእሷ ከእንጀራ በላይ የቤቷን ቀዳዳ ሸፍና ዘመድ ወዳጅ አፍርታበታለች። ምግቡን ስታበስል ተጠንቅቃ ነው። በዱቤ ስትሰጥም ከፍቷት አያውቅም። ሁሌም እርካታዋ በእጇ ላይ ነው። አንዱ በዱቤ ሲበላ ሌላው ደግሞ ትርፍ ገንዘብ ይሰጣታል። ስለሆነው አመስግና ስለነገው ተስፋ ታደርጋለች።
በየቀኑ ከ35 ኪሎ በላይ ድንችና ሽንኩርት ፣ አንድ ሊትር ዘይትና ዘጠና ዳቦ ከተጨማሪ ቁሳቁሶች ጋር የጫነውን ጋሪ እየገፋች ትጓዛለች። ይህኔ ነብሰጡር መሆኗን የሚያውቁ ወዳጇቿ ዝም አይሏትም። በተለይ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ያለውን ልብ የሚያፈስ ዳገት ቀድመው ይታገሉላታል። መንገዱን ሳታልፈው እሷን ተክተው ያግዟታል፣ ይገፉላታል።
አሁን ገነት የመውለጃ ጊዜዋ ደርሷልና ስራ አቁማለች።በቀራት ጥቂት ጊዜ ቤቷ አካባቢ መሥራት ፈልጋለች። ወቅቱ ግን ይህን የሚፈቅድላት አልሆነም። በኮቪድ ምክንያት ሁሉም ቤቱ የተከተተ በመሆኑ ማንም እንደማይገዛት ታውቃለች። የዛኔ በእጇ የነበረው 2500 ብር ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ አይደለም ለህመምተኛ ባለቤቷና ለልጆቿ ለእርሷም ቢሆን አይበቃም። እሱንም አብቃቅታ መጠቀም አለባት። እራሷን ከሁሉ እያገለለች ልጆቿንና ባለቤቷን መንከባከቡን ቀጠለች።
ነፍሰጡር ሳለች የ‹‹አማረኝን፣ሸተተኝን›› ልማድ አታውቀውም። ልሞክረው ብትልስ ያሰበችውን ማን ሊያመጣላት? ከወለደች በኋላም አንዲት አራስ መመገብ ያለባትን አላገኘችም። እሱም ቢሆን ከየትም አይመጣም። በቤት ውስጥ ትንሽ ምግብ እንኳን ቢኖር ለቤተሰቧ ታጎርሳለች ። እሷ ለእኔ ይሉት ልምድን አታውቅም። በዚህም ሰውነቷ ተጎድቷል። ጨቅላ ልጇን በበቂ ለማጥባት ተቸግራለች።
ስኳር በሽተኛ የሆነ ባሏንና ልጆቿን የሚንከባከብላት ባለመኖሩ አራስ መሆን እንደማይፈቀድላት ያመነቺው ገነት፤ በሦስት ቀኗ ተነስታ ሥራ ጀመረች። በተለምዶ በክርስትና እምነት ልጅ ክርስትና ሳይነሳ ደጅ አይወጣም። ሁሉም የሚሆነው ሲመቻች በመሆኑ እሷ ህግ አላከበረችም። በዚህም የሰፈር ሰው ጭምር አግልሏት እንደነበር አትረሳም ።
ወልዳ ከተነሳች በኋላ ፈተናዎች ቢከብዱም የራሷን ሥራ ፈጥራ መሥራት ጀመረች። በቤቷ ሆና ልብስ ማጠብን አማራጭ አደረገች። በመተላለፊያ መንገድ ታፒላ ለጥፋ ደንበኞችን ለመሳብ ሞከረች። ወደ ፋብሪካዎች በመሄድ በአንድ ቱታ 50 ብር እየተቀበለች ጎደሎን ለመሙላት ሌት ተቀን ተጋች።
ባለቤቷ ጤነኛ በነበረበት ጊዜ በተለያዩ ሆቴሎች በጽዳት ሥራ ያገለግል ነበር። ዛሬ ግን ህመም ጥሎታል። እንዲያ መሆኑ የቤቱ ሀላፊነት በእርሷ ጫንቃ ብቻ እንዲያርፍ አስገድዷል።
ብዙዎች ባለቤቷ ጭምር ሰርቶ እንደሚገባ ይገምታሉ። በዚህ ምክንያትም ቀርቦ የሚያግዝ የሚረዳት አልተገኘም። ይህ ደግሞ ለአራሷ ገነት በከባድ ፈተና እንድታልፍ አድርጓል። በተለይ አንድ ቀን የገጠማት መቼም አትረሳውም። ለልጆቿና ለባለቤቷ የምትሰጣቸው አጥታ ያለቀሰችበትን ቀን። ደግነቱ ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆኖ በድንገት አንድ ሰው የቤታቸውን በር አንኳኳ። ያልጠበቁት ነገርም እንደመና ወረደላቸው።
በአነዋር ሀጎስ የተመሰረተው በጎ አድራጎት ማህበር የቤቷ ጓዳ እንዲሞላ አደረገው። የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት ጊዜ ደርሰው ጎጆዋን የደስታ ብርሃን ፈነጠቁበት። ደስተኛ ሆና እንባዋን በሳቅ ፈገግታ አበሰቺው። በእርግጥ አንዳንድ የሰፈሯ ሰዎች ከጎኗ እንደነበሩ ትመሰክራለች ። አንዳንዴ ‹‹አይዞሽ›› ይሏታል። የተቻላቸውንም ይደጉሟታል ።
ገነት አራስነትን ስታስብ ሁለት ነገሮች ከአዕምሮዋ አይጠፉም። የመጀመሪያው የእናቷ ነገር ነው። ችግርን በመጋራት ሁሌም ከጎኗ ነበሩ። እንደሞት ክፉ የለምና እርሳቸውን ነጠቃት። እንደ ሴት የመታረስ ወጉንም አሳጣት።
ሌላው 160 ብር በማጣቷ ምክንያት ያተረፈችው ቁጭት ነው። ልጇን ክርስትና ስታስነሳ ለእርሷም ሆነ ለሕጻኗ ልብስ አልገዛችም፤ እንዴም ቢሆን አልከፋትም። ከሁሉም ግን በእጇ ገንዘብ ማጠር ሳቢያ የልጇን የፎቶግራፍ ማስታወሻ ያለማስቀረቷ ዛሬ ድረስ ያሳዝናታል።
ትናንት ‹‹ነበር›› ሲሆን
ትውልዷ እዚሁ አዲስ አበባ ቢሆንም በአንዳንዶች ‹‹መጤ›› እየተባለች ተገፍታለች። የልጅነት ወዟ ገርጥቶ ማንነቷ ተቀይሮ ነበር። ከቀናት በአንዱ ግን ይህ ታሪክ ሊቀየር ግድ ሆነ። በሜድሮክ፤ በከንቲባ አዳነች አበቤና በልደታ ክፍለከተማ አስተዳደር ወይዘሮ ፀሐይ ትብብር ዛሬ ካለችበት ሕይወት ደርሳለች። እኝህ በጎ አሳቢ አካላት የልጆቿን ህይወት፣ የእሷና የባለቤቷን የዘመናት ጥያቄ ስለመለሱላት የነገ ተስፋዋ ለምልሟል።
ዛሬ ገነት ከትናንቱ የላስቲክ ቤት ኑሮ ተላቃ የጽዱ ቤት ባለቤት መሆን ችላለች። አሁን የእሷ ክረምት አልፏል፣ ስጋት ፍርሀቷ ተወግዷል።
ይህ ብቻ አይደለም። በጌጃ ሰፈር አካባቢ በተገነባው የተስፋ ብርሀን ምገባ ማዕከል ተቆጣጣሪ በመሆን ተቀጣሪ የወር ደሞዝተኛ ለመሆን በቅታለች።
በአካባቢው መኖሪያቸው ምቹ ላልነበረ አራት የሸራ ቤት ነዋሪዎች ሜድሮክ ቤት ሲሰራላቸው እርሷ አንዷ ለመሆን ችላለች ።
ገነት በአዲሱ ቤት ገብታ መኖር ከጀመረች አንድ ወር አላስቆጠረችም። ያገኘችው ዕንቅልፍና እፎይታ ግን በዓመታት ቆይታ የሚመዘን አይደለም። አዲሱ ዓመት ለእሷና ለመላው ቤተሰቧ አዲስ ህይወትን ይዞ ደርሷል። ዛሬ እሳት ተነሳ፣ ክረምት ገባ ፣ብርድና ዝናብ መጣ ይሉት ስጋት ተወግዷል፡፤
ገነት በተጨማሪ ‹‹ሚሺን›› ከሚባል ድርጅት የአንድ ልጅ እገዛ ታገኛለች። በተለይ ግን ዘንድሮ በተመቸ ዓለም ኑሮን ለመጀመር መዘጋጀቷ በእጅጉ ያስደስታታል። ብርቱዋ ሴት ተስፋ ሳትቆርጥ ፈታኙን ህይወትን መታገሏ ከዛሬው ቀና መንገድ አቁሟታል። ነገ ደግሞ ከትናንት የተሻለ ደማቅ የተስፋብርሀን እንደሚቆያት ታምናለች።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014