ወቅቱ የአብዮቱ ወቅት ነበር። የወጣቶች ደም እንደዋዛ የሚፈስበት፤ ቃታ መሳብ ቀላል የነበረበት። በሰፈሩ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በተለያየ የፖለቲካ አሰላለፍ ተሰልፈው አንዳቸው በሌላቸው ላይ ለመጨካከን የቆረጡበት ወቅት፤ ከመቅደም መቀደም ስሌት የሆነበት። መንግሥት የሆነውን ደርግን ጋር በከተማ ውስጥ ትግል አሸንፎ ሊወጣ የሚታገለው ስብስብ ገናና ሆኖ የብዙዎችን ልብ ያሸፈተበት አሳዛኝ ወቅት።
እንዲህ ባለ ወቅት በሽምግልና እድሜ የሚኖሩ ልጆቻቸውን በፖለቲካ ትኩሳቱ የተነጠቁ አባት ነበሩ። እኚህ አባት ከእዚያ በፊት ሲያለቅሱ አልታዩም ነበር፤ በአንዴ ሁለት ልጆቻቸውን ሲነጠቁ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይናቸው ላይ እምባ ታየ። የልጆቻቸውን ሬሳ ተቀብለው፤ ከቀበሩ በኋላ ዘወትር ማለዳ ተነስተው ቁርስ ሳይበሉ እግራቸው ያደረሳቸው ያህል ቦታ ሄደው ይመለሳሉ። በጉዟቸው የሚያውቁትን ሰው ሲያገኙ አስቁመው የተለመደውን መልእክታቸውን ይናገራሉ፤ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ካገኙም እንዲሁ፤ መልእክታቸው አጭር ነበር “እረፉ” የሚል። አጠር ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ጉዟቸውን ቀጥለው ሲደክማቸው ይመለሳሉ። የእረፉ ጉዞ። “ልጆቼ እረፉ፤ ስታችኋል እረፉ፤ ደም ደምን ይጠራል እረፉ፤ ድካም ድካምን ይወልዳል እረፉ፤ ጥላቻ በጥላቻ ይተካል እረፉ፤ ሞት ሞትን ይወልዳል እረፉ፤ እረፍት ደግሞ ወደ ተሻለ እረፍት ይመራል እረፉ፤ ወዘተ”ይላሉ። እኚህ አባት ከልጃቸው ሞት በኋላ ባለመሰልቻት ለሦስት አመታት “እረፉ” እያሉ ከረሙና እርሳቸውም ሞት ገጥሟቸው አረፉ።
በእኚህ አባት ሞት ምክንያት አካባቢው አዘነ። ድንኳን ተደኩኖ ቤተሰቡም ሃዘን ተቀምጦ ባለበት ወቅት ለቀስተኛው በሙሉ የእርሳቸውን የሦስት አመታት ያለመታከት “እረፉ” መልእክትን እያስታወሰ ብዙ አወጣ አወረደም። የእኚህን አዛውንት ምክር በወቅቱ ለመደመጥ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ያለ ባይመስልም አንዳንዶች ከግርግሩ ወጣ ብለው እረፍትን ለማግኘትና ወደ ቀልባቸው ለመመለስ ተጠቀሙበት። አንድ ገጣሚም “የእረፍቱ ቀመር አረፉ” በማለት ግጥም ጽፎ ጋዜጣ ላይ አስነበበ።
ገጣሚው ግጥሙን ምክንያት አድርጎ በሬዲዮ ቃለምልልስ ሰጠ። ቃለምልልሱም የአዛውንቱ የእረፍት ቀመርን ሰዎች ማሰብ እንዳለባቸው የሚያደርግ እንደሆነም አብራራ። እረፍት ተዘርቶ እረፍት እንዲታጨድ ሁሉም ሰው ሊገኝ የሚገባው ጠቃሚ በሆነ ነገር ውስጥ እንደሆነ ተናገረ። በመግደል ውስጥ በመጨረሻ የሚገኘው የሌላ ሰው መገደል እንጂ ሰላም አይደለምና፤ ይህን ቀመር አዛውንቱ በደንብ አድርገው ተረድተዋል ሲል ምስክርነቱን ሰጠ። የእረፍት ቀመሩም በኢትዮጵያ የዘመናት ጉዞ ውስጥ ቦታ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የትናየት በደረስን ሲልም ተነተነ። ኢትዮጵያ ካጣችው የባህርበር በላይ ያጣችው ብሩህ ጭንቅላት እስከዛሬ አልቆጫትም ሲል ቁጭቱን ገለጹ። አዛውንቱ የሚለውን ሰምቶ በክፉ ፋንታ መልካምን የሚዘራ ሰው ቢኖር ኖሮ በጥቂት ሀዘን ብዙ ደስታ ላይ መድረስ በተቻለ ነበር አለ። አሸናፊ ሆኖ መውጣት ብቻ ግብ ተደርጎ ሲወሰድ የእረፍት ቀመር ይዛባል አለ። እረፍት ቀመር ውስጥ ተሸንፎ ማሸነፍም አለ፤ ግራ ተመቶ ቀኝን በማዞር ውስጥም አሸናፊነት አለ፤ በሌላው ጫማ ላይ ራስን አስቀምጦ ከግብታዊነት በማሰላሰል በመራመድምእንዲሁ አብራራ። በፖለቲካችንም የሆነው ይህ ነው በትላንትም በዛሬም ምናልባትም የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ በነገውምበማለት የልቡን ተናገረ። እኛም ዛሬ በእረፍት ቀመር ውስጥ እንቆይ።
ከግለሰብ ተነስተን እስከ ሀገር ድረስ የምናደርገው ጉዞ ድምር ውጤቱ በይፋ የሚታይ ነው። እንደ ሀገር በኢኮኖሚ ችግር፣ በማህበራዊ ህይወት መስተጓጎል፣ ወዘተ ውስጥ የሚያልፉ የፖለቲካ ህይወት ስብራት መሆኑ ይታወቃል። እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ግለሰብ የያዘው አስተሳሰብ ድምር ውጤት ደግሞ የሀገር ፖለቲካ ቁመና። የእረፍት ህይወትም በህይወታችን ውስጥ ያለው ቦታ ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚታይ ነው።
የእረፍት ቀመር በምድራችን ላይ እንዲሰራ እያንዳንዱ ሰው ከብክነት ወደ ማረፍ፤ ከመባከን ወደ መረጋጋት፤ ከቀማኛነት ወደ መስጠት ይመጣ ዘንድ ነጥቦችን እናነሳለን። አዛውንቱ ዛሬ ባይኖሩም ገጣሚውን ለግጥም ስራ ያነሳሳው መልእክታቸው ጥንካሬ ዛሬ ለሁላችንም መልእክት ይኖረዋል፤ ብዙ ርቀት ሳንሄድ የምናገኘው እረፍትን። በዳንኪራ ቤቶች ህይወት በሙላት ደምቃ የምትታይበት ከመሰለው አብለጭላጭ መብራቶች ወጥቶ እውነታን ሲታይ በውስጥ ያለውን ባዶነት ሊሞላ የሚችል ቀመርን ፍለጋ ለምታስብ ነፍስ የሆነ ምክር። ለወጣቱም ሆነ ለአዛውንቱ ለሁሉም የሚሆን የአዛውንቱ ምክር፤ የእረፍት ቀመር። በትልቁ ምስል ውስጥ ያለው እውነት የተረዱ ሰዎች የሚኖሩት አሁናዊ፤ ዛሬያዊ ኑሮ።
ትልቁ ምስል ውስጥ ያለው እውነት
የተለያየ ስም እየተሰጣቸው የበዙ ዘመቻዎች ምድራችን ላይ ተከናውነዋል። ከዘመቻዎች መካከል አንዱን ዘመቻ እናንሳ። በደርግ ዘመን ውስጥ የተደረገው “ዘመቻ መንጥር” የተሰኘው የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፋቸውን አስተካክለው አሸናፊ ሆነው ለመውጣት የተረባረቡበት ሀገሪቱን ደርግ ተረጋግቶ መምራት እንዲያስችለው በሚስጥራዊነት የተከናወነ ዘመቻ ነው።ዘመቻው እረፍትን ለአገዛዙ ለማምጣት ታስቦ የተደረገ ሲሆን ከዘመቻው አስቀድሞና ከዘመቻው በኋላ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሰዎች ሲያስታውሱ ዛሬ ላይ እንደሆነ የሚከብ ፍርሃትም ይከባቸው ይሆናል። ጥያቄው ዘመቻው ሊያመጣ ያሰበውን የአጭር ጊዜ ግብ ያሳካ ሊሆን ቢችልም፤ በተጨባጭ ግን እንደ ሀገር ያለንበት እረፍት የለሽ የሆነው ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራታችን ግን ባለበት ነው። መልኩ ይለያይ እንጂ እንደ ዘመቻ መንጥር የመሳሰሉ የተለያዩ ዘመቻዎች ሰላምን ሊያመጡታስበው በምድራችን ውስጥ ተከናውነዋል። ዛሬም የሀገራችንን የፖለቲካ መስመር አስተካክሎ ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉ ዘመቻዎች አሉ። አሜሪካ አሸባሪነትን ለመዋጋት የተሰለፈችበትን ዘመቻ ከሀገራችን ውጭ ልንጠቅስ እንችላለን። በሌሎች ሀገራትም የተለያየ ዓላማ የተሰጠው ዘመቻዎች እንዲሁ ይከናወናሉ። የየትኛውም ወታደራዊ ዘመቻ መጨረሻው ሰላምን ማስፈን የራስን ጥቅም ማስጠበቅ ነውና የሰው ልጅ እስካለ ድረስም የሚቀጥል ይመስላል። በተጨባጭ ምድር ሰላምን ማግኘት ቻለች ወይ የሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ አላገኘም፤ የሚያገኝም አይመስልም። ምድር ከቀን ወደ ቀን እረፍት የለሽ እየሆነች የሰው ልጅ ችግርም መልኩን እየቀያየረመሄዱን እናስተውላለን።
ለእዚህም እንደ ምክንያት ልናቀርብ የምንችለው በእሴት ውስጥ ሆኖ የሚፈለገው መፍትሄ ውጤት የሌለው መሆኑን ነው። በህግም፤ በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት በኩል ለሰው ልጆች የተሻለውን ለማምጣት የሚደረገው ስራ ውጤታማ መሆን እንዲችል በሦስት አቅጣጫ የሚፈልግ አንድ ነገር አለ፤ እሴት። ግራው ሲመታ ቀኙን አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ከራሱ በላይ ለሌሎች ጥቅም የሚቆም ስኬትን በእሴት ውስጥ የሚተረጉም። እንዲህ አይነት ሰዎች በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ የሚገኙ ሳይሆኑ በትልቁ ምስል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።የአልበርት አንስታይን ትግልህ ለስኬት ሳይሆን ለ እሴት ይሁን የሚለው አባባል እዚህ ጋር ጥሩ ገላጭ ነው/Strive not to be a success, but rather to be of value.
በማንኛውም ጉዳይ ውስጥ ጥቃቅን ነገሮች አሉ፤ ደግሞም ትልቁ ምስል። ለመፍትሔ የሚሆን ሰው ከትንንሽ ነገሮች ይልቅ ለትልቁ ምስል ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። በትራንስፖርት ዘርፍ ይሁን በገቢዎች፤ በመብራት ኃይል ይሁን በፋይናንስ ዘርፍ፤ በግብርና ይሁን በንግድ ወዘተ የተሰማራ ሰው የእረፍት ቀመርን የራሱ ማድረግ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይችላል፤ የሚያስፈልገው የልብ ፍላጎት ብቻ ስለሆነ። አይደለም በህይወት ያለ ሰው የሞት ፍርድ የተፈረደበትና ሞቱን የሚጠብቅ ሰውም ጋር ቀመሩን መተግበር ያስችላል። ሁሌም ትልቁን ምስል በመመልከት ውስጥ የምንራመድበት መንገድ።
ከታክሲ ረዳት ጋር በሳንቲሞች ምክንያት የተጋጋለ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት የተለመደ ነው። የታክሲ ረዳቱን እንደ አንድ ሙሉ ሰው አክብሮ በአግባቡ በማናገር ውስጥ የሚገለጥ ግለ-ግንኙነት የታክሲ ረዳቱን እንደ ሰው አክብሮ በመመልከት ውስጥ የሚገለጽ ነው። ሰዎች በሚሰሩት ስራ ከእኛ ያነሱ በመሰለን ጊዜ ስሜታችንን ጥግ ድረስ ልቅቅ አድርገን ልንገልጽባቸው እንፈጥናለን። የታክሲ ረዳትን ምሳሌ ማንሳቴ በየእለቱ ከሚገጥመን ገጠመኝ ለመነሳት እንጂ በማንኛውም ስራ ላይ የሚታይ ነው። በዙሪያችን ያሉን ሰዎች አግዝፈን ማየት፤ አክብረን ማየት፤ ከትልልቅ ጉዳዮች በላይ መሆናቸውን መረዳት መቻል ወዘተ የእረፍት ቀመር ውስጥ ይገኛል። ትልቁም ምስል ወደ እረፍት የሚያደርሰን ከሁሉም ነገር ራሳችንን ፈንጠር አድርገን ስናስብ ትክክል እንደሆን የሚሰማን ነው።
ሰውን ማእከል ባለማድረግ በምንሰራው ስራ ውጤት የለሽ የሆነን ጉዞ እየተጓዝን ስኬት አድርገን የምንለካው መለኪያ በሌላው ሰው ሃዘን የሚገኝ መሆኑ እረፍት የለሽ የሆነውን ጉዞ ስፋቱን ያሳየናል። ትልቁ ምስል ውስጥ ያለው እውነት ግን ሰውን በሰውነቱ በመቀበል፤ ሰውን በማገልገል፤ ሰውን በመጥቀም እንጂ በመጉዳት ውስጥ ስሌት የሌለን ሆነን የምንገኝበት ምስል ነው።
በሀገራችን የፖለቲካ መዝገብ ውስጥ ተጽፈው የምናገኛቸው ታሪኮች እንዴት በእዚህ ደረጃ በጭካኔ የሚገለጹ ሆኑ ብለን ልንጠይቅ ያስገድዱናል። በተጨባጭ ለሀገር ለውጥ መልፋት አንድ ነገር ሆኖ ነገርግን አንዳችን በሌላችን ላይ ለመክፈት የምንሄድበት እርቀቱ ረጅም ነው። በዚህም ዘመን በሰፊው እንደተንሰራፋ የሚነገርለት ሙስና አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ የሚገኘው አንዳችን በሌላችን ላይ ለመጨከን በሄድንበት መንገድ እርቀት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።
ጦርነት እየተመላለሰ የሚጎበኘን አግባብ በሆነ መንገድ ቁጭ ብለን መነጋገር ባለመቻላችን እና ዘወትር የምንራመደው እርምጃ አንዳችን በሌላችን ኪሳራ ላይ የመሆኑ ማሳያም ነው። ይህም የእረፍት መንገድ ውስጥ እንዳንገባ አድርጎን ተራ በተራ አስጨናቂ ዋጋ እንከፍላለን፤ ተራ በተራ ድንኳን እንተክላለን።እረፍት ያጣው ኑሯችን እረፍት እንዲኖረው ሰንበትን የህይወት ዘይቤ እናድርግ።
ሰንበትን እንደ ህይወት ዘይቤ
ሰንበት ሲባል ሁሉም የስራ ቦታዎች በራቸውን ዘግተው ሁሉም ወደ እረፍት የሚሄድበትን ቀን ያስታውሰናል። የሰው ልጅ እረፍት የሚያስፈልገው ፍጡር መሆኑ እርግጥ ነው። እረፍት ደግሞ ለነገ አቅምን ሰንቀን የምንወጣበት ነው። ሰንበትን እንደ ህይወት ዘይቤ ስንል እረፍትን እንደ ህይወት ዘይቤመውሰድ ማለት ነው። ራሳችንን አሳርፈን ለሌሎች እረፍት ስለመሆን።
ብዙ ሩጫ ባለባት ምድር ውስጥ እረፍትን እንደ ህይወት ዘይቤ መውሰድን አስበንበት የማናደርገው ከሆነ ስራን እንጨርስ እያልን እራሳችን እናልቃለን። ከምንወዳቸው ጋር ልናጠፋ የምንፈልገውን ጊዜ ከዛሬ ነገ እያልን በገፋነው ቁጥር ክፍተቱ እየሰፋም ይመጣል። አንድ በስራ የተወጠረ አባት ልጆች በልጅነት ለዛ ላይ በሆኑበት ጊዜ ለስራ ቅድሚያ በመስጠት ሚዛን ማስጠበቅ ባልቻለበት የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ ኖሮ በስተመጨረሻ ዞር ብሎ ሲያይ ልጆቹ አድገው ሌላ ሰው ሆኖ አገኛቸውና ልጆቼ አመለጡኝ አለ። ልጆቹም ዛሬም ልጆቹ ሆነው ቤት ውስጥ አሉ፤ ነገርግን እንደ ልጅ ሳይላፋቸው፤ እንደ ልጅ ሊያወሩ የሚፈልጉትን ሳይሰማቸው ያ ዘመን አለፈና ልጆቹን እንዳጣቸው ቆጠረ።
ለልጆቻችን መልካም ማድረግን ስናስብ የምናስገባው ዝርዝር ውስጥ ጥሩ ትምህርትቤት ማስተማር፤ ጥሩ እንዲበሉ ማድረግ፤ ጥሩ እንዲለብሱ ወዘተ ብለን ምላሽ እንሰጥ ይሆናል። በተጨባጭ ግን ከእኚህ መሰረታዊ ነገሮች ባለፈ በአይን የማይዳሰስ ነገርግን በእኛ መገኘት የሚሰሩ ለልጆች የህይወት ዘመን ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አሉ። እነርሱም ልጆችን በባህሪ ቀርጾ ማሳደግ፤ በመሳሳት ውስጥ ትምህርት እንዲወስዱ እድል መስጠት፤ በመካከላችን የሚኖር ግንኙነት ፍሬ ያለው ሲሆን እነርሱም ልጆቻቸውን ፍሬ ባለው መንገድ እንዲመሩ እድል መስጠት ወዘተ። እማሆይ ትሬዛ “ዓለምን ለመቀየር ከፈለክ ወደ ቤተሰብህ ሂድ፤ ቤተሰብህንም ውደድ” ያሉትን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው።
የእረፍት ቀመርን ስናስብ በግላዊነት በራችንን ዘግተን የሚያስቅ ፊልም ወይንም ልብ አንጠልጣይ ወይንም አስፈሪ ወይንም ሌላ ፊልም እየተመለከትን በራሳችን አጥር ውስጥ እንገኝ ማለት አይደለም። የእረፍት ቀመር ከራስ በላይ መንፈስን ይጠይቃል። የእኛን ጊዜ በጉጉት ለሚፈልጉ አጠገባችን ላሉት እንቁዎቻችን ጊዜ መስጠት፤ ችግራቸውን ማድመጥ፤ ደስታቸውን መጋራት፤ ጥያቄያቸውን መመለስ፤ ወዘተ ማለት ነው።
ሰንበትን እንደ ዘይቤ ለራሳችን ጊዜ መስጠትንም እንዲሁ ይጨምራል። አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ፤ መጽሐፍት ለማንበብ፤ በቂ እንቅልፍ ለመውሰድ፤ በጥሞና ስለ ህይወታችን ወዘተ ለማሰብ እንዲሁ በእረፍት ቀመር ውስጥ የምናገኘው ነው። ከራስ በላይ መንፈስን በማይከለክል መንገድ የሚሆን ለራስ ጊዜ መስጠት የእረፍት ቀመር አካል ነው። ሚሼል ኦባማ “የተሻለ ሥራ ልንሰራ ይገባናል፤ እርሱም ከስራ ዝርዝራችን በፊት ራሳችን ላይ መስራት” እንዳሉት ማለት ነው።
አንዳንዶቻችን ከሥራ በተረፈው ጊዜ ራሳችን ላይ ብቻ ትኩረት በማደረግ፤ ሌሎቻችን የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ስራን በማድረግ፤ አንዳንዶች ደግሞ ማህበራዊ ህይወት ስራቸውንም ሆነ የግል ኑሯቸውን የሚጎዳ እስኪሆን ድረስ በማድረግ ወዘተ የሚገለጥ ሚዛኑን የሳተ ህይወት ውስጥ እንገኛለን።
መፍትሔው የእረፍት ቀመር ነው። ራስን ማወቅ፤ ውስጥን ማዳመጥ፤ ከሁኔታዎች በላይ መሄድ የሚችል ሆነን በውስጣችን መሰራት፤ ትልቁን ምሰል ለአጠገባችን ላለው ሰው የሚገባውን ትልቁን ቦታ ሰጥተን መመላለስ። የእረፍት ቀመር የጎደለው ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ ጉዟችን እየተስተካከል እንደ ሰው ተከባብረን፤ ተደጋግፈን፤ ከጥቃቅን ነገሮች በላይ ትልቁን ምስል ተመልክተን የምንኖርበት የእረፍት ጊዜ ይገባናል። ነገሮች በሚዛን የሚመዘኑበት በስልጣንም ያለ ሆነ ወደ ስልጣን የሚመጣው የሚኖሩበት ህይወት። በእረፍት ህይወት ውስጥ ስለ ሁሉም እረፍት የሚኖር የተሸለ ህይወት።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014