የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአኀዙ ላይ ስምምነት ባይኖርም ለተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ቆይቷል። ይህም ኢትዮጵያን ከፍተኛ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት መካከል ለመሰለፍ አብቅቷት ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ ተከትሎ ምንም እንኳ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት በባህሪው በአንድ ጊዜ የማይቆም ቢሆንም ከፍተኛ መቀዛቀዝ ታይቶ ነበር። በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ሙስናና ገንዘብ ማሸሽ ሀገሪቷ ከተደቀኑባት ቀዳሚ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች መካከል የሚጠቀሱ ነበሩ።
እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ሳንካዎች በነበሩበት ሁኔታ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን የመጡት። ይሄ እንዳለ ሆኖ ምንም እንኳ የርዕዮተ ዓለምና ሀገሪቱን የሚያስተዳድራት የፖለቲካ ፓርቲ (ኢህአዴግ) ለውጥ ባያደርግም ዶክተር ዐብይ ወደ ሥልጣን በመጡ በወራት ውስጥ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ በቅተዋል።
ከነዚህም መካከል በተለይ በቀደሙት አስተዳደሮች የማይሞከሩ ተብለው የተፈረጁ ሁለት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ውሳኔዎችን ሀገሪቱ ለማስተናገድ ዕድሉን አግኝታለች። የመጀመሪያው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ መሰረት የኢትዮጵያና የኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመርን ተከትሎ ከወደብ አገልግሎትና ከህዝብ ለህዝብ እንቅስቃሴዎች የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩና በቀደሙት መሪዎች ለግለሰብ እንዳይተላለፉ ተወስኖባቸው የነበሩ ድርጅቶችን በተወሰነ ድርሻ ለባለሀብቶች ማስተላለፍ ነበር። የእነዚህን ሁለት ታሪካዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውሳኔን በተመለከተ አዲስ ዘመን የዘርፉ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
ዶክተር ለሜሳ ባይሳ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፋይናንስ ሥራ አመራርና ልማት ኮሌጅ ዲን ናቸው። እርሳቸው እንደተናገሩት፤ እነዚህ ሁለት ውሳኔዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያልታሰበ አዎንታዊ ለውጥ ያመጡ ናቸው። ውጤቱ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩና ከእርሳቸው ጋር ለለውጡ የተንቀሳቀሱ ጥቂት ሰዎች ውሳኔ ነው። ምናልባትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሥልጣናቸው ቀጥለው ቢሆን አልያም ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢመረጥ ኖሮ ሀገሪቷ ይሄንን አጋጣሚ የማግኘት ዕድሏ ጠባብ ይሆን ነበር።
ዶክተር ለሜሳ እንደሚያብራሩት፤ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ኃላፊነት መውሰድ፣ ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች መቋቋምና ተቃውሞን መጋፈጥ የሚጠይቅ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማድረግ ችለዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ከዚህ ቀደም የነበሩት መሪዎች የሞከሩት ነገር ቢኖርም፤ ስኬታማ መሆን አልቻሉም።
እንደ መንግሥትም በተለያዩ አደራዳሪዎች በኢትዮጵያ በኩል ለመታረቅ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ አልነበሩም። ከውጭም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም መንግሥታት ለማስማማት ሞክረው አልተሳካላቸውም ነበር። በመሆኑም ከዚህ ቀደም የነበረውን ‹‹በጦርነት አሸንፈን የያዝነውን መሬት ለምን እንለቃለን›› የሚልን አመለካከት ደፍሮ ኃላፊነት በመውሰድ የሚያሻግር መሪ ያስፈልግ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደሥልጣን በመጡ ጥቂት ወራት ውስጥ ይህንን ማድረግ ችለዋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ላለፉት ሃያ ዓመታት ተኮራርፋ ስትቆይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ነበር። በአንድ ወገን ላለፉት ሃያ ዓመታት ኤርትራ የኢትዮጵያ ስጋት ናት ተብሎ ስለታሰበ በርካታ ወታደር በአካባቢው ተቀምጦ እንዲቆይ ተገዷል።
ይህም መንግሥት ለተለያዩ የልማት ተቋማት ግንባታ ሊያውለው የሚችለውን ከፍተኛ ገንዘብና የሰው ኃይል ሲያባክን እንዲኖር አስገድዶታል። ጦርነቱም ስጋቱም ባይኖር ኖሮ ለዚህን ያህል ጊዜ ለመከላከያው የወጣው ወጪ በርካታ መሰረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል ነበር። በዚህ ረገድ አንዳንዶቹ ውሳኔዎች ለዓመታት ተንጠልጥለው የቀሩት የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ታስቦ ሳይሆን ለግለሰቦችና ለተወሰኑ ቡድኖች ጥቅም ሲባል የተደረገ በመሆኑ ኢኮኖሚውን አንቆት ቆይቷል።
በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስትገለገልባቸው የነበሩትን የአሰብና ምፅዋ ወደቦች መገልገል ያቆመችው በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ነበር። በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ኢትዮጵያ በኤርትራ ያሉ ወደቦችን ለመጠቀም ስምምነት ላይ መደረሷና እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ድርብ ድርብርብ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚያስገኝ ነው።
ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በምትጠቀምበት ጊዜ ጅቡቲ ተደጋጋሚ የዋጋ ጭማሪ እያደረገች አማራጭ ባለመኖሩ የተጠየቀው ሁሉ ሲከፈል ቆይቷል። አሁን ግን አማራጭ ሲኖር እንደ ማንኛውም ገበያ የሀገሪቱም የመደራደር አቅም ይጨምራል።
ከዚህም ባለፈ እንቅስቃሴው እየተሟሟቀ ሲሄድ ስምምነቱ ለሁለቱም ሀገራት ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡ ሁሌም የሰዎች እንቅስቃሴና ዝውውር ካለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ይኖራል። በመሆኑም በተከፈቱት የትራንስፖርት መስመሮች ያሉ በንግድ እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው የቆዩ ከተሞች ይነቃቃሉ። በአካባቢው የሚመሰረቱ አዳዲስ ከተሞችም በተለያየ መልኩ ለዜጎቹ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል። በሁለቱም ሀገራት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑም በሀገራቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ የግድ ነው፡፡
‹‹የወደብ አገልግሎት ለመጠቀም ርቀት ይወስናል፤ ከየት ተነስቶ የት ይደርሳል የሚለውም ይታያል። አማራጭ ሲኖር ለየትኛው ወደብ የትኛው የሀገሪቱ ክፍል ቅርብ ነው ብለህ የመምረጥ ዕድል ይኖርሀል›› የሚሉት ዶክተር ለሜሳ፤ የኤርትራ ወደቦች ሥራ መጀመር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የሚገቡትን ሸቀጦች የበለጠ በተቀላጠፈ መንገድ ለተጠቃሚው እንዲደርሱ የሚያስችሉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ሁለቱም ሀገራት አንዱ ከአንዱ የሚፈልጓቸው ምርቶች አሏቸው። በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል የንግድ ትስስሩን በማቀናጀት ወደ ሌሎች ሀገራት ሲላኩ የነበሩትን የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ኤርትራ በመላክ ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ በቅርበት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ስምምነቱ በር መክፈቱን ዶክተር ለሜሳ ይገልፃሉ።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት አስተዳዳሪ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች መገልገል መጀመሯ ከዋጋ በተጨማሪ ለቅልጥፍናውም እንደሚረዳ ያመለክታሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ 95 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የወጪና ገቢ እንቅስቃሴ በጅቡቲ ወደብ በኩል ይደረግ ስለነበር የወጪና ገቢ እንቅስቃሴው ከፍተኛ መጨናነቅ የነበረበት ነው።
በጅቡቲም ሆነ በሶማሊያ ወደቦች የሚኖረውን የእቃ ክምችትም ብዙ ነበር፡፡ አገሪቱ አዳዲሶቹን ወደቦች መጠቀም ስትጀምር ይሄ መቀነስ ይጀምራል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በወደብ ኪራይ ዋጋ ላይም ተፎካካሪነት ስለሚፈጠር የዋጋ ቅናሽ ለማግኘት ዕድል ይፈጠራል። በተጨማሪም አዲስ የወደብ አማራጭ መከፈቱ ለኢትዮጵያ መርከቦችም የአዲስ የገበያ ዕድልና መዳረሻ ይፈጥርላቸዋል።
የወደቦች አማራጭ መብዛትና የዋጋ ማሻሻያም መደረጉ የወጪና ገቢ ንግዱን ከማሳለጥ ባለፈ የገበያ ተወዳዳሪነትንም ያሳድጋል የሚሉት አቶ ክቡር ገና፡፡ ምክንያቱን ሲያስቀምጡም ኢትዮጵያ ምርቷን ለውጭ ገበያ ስታቀርብ ቀደም ሲል ለወደብ ትከፍል የነበረው ዋጋ ይቀንስላታል። ይህም በምርቷ ላይ ቅናሽ እንድታደርግና በገበያው ላይም በዋጋ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላታል፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተደራሽ የምትሆንበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ሸቀጥ ዋጋ ስለሚቀንስ በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠርም ይረዳል፡፡
የአማራጭ ወደብ መኖር እንደ ነዳጅ ዓይነት ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት በሚኖር የወደብ መጨናነቅ ወይም አማራጭ ማጣት ምክንያት በአገር ውስጥ የምርት እጥረት ተፈጥሮ ሊከሰት የሚችለውንም ስጋት ያቃልላል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ላለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንቅስቃሴ ትልቅ ገበያ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ባጠቃላይም እነዚህ ጥቅሞች በመገኘታቸው የቀጣናው አገራት ኢትዮጵያን የገበያ መዳረሻቸው እንዲያደርጉ ዕድል ስለሚፈጥር ለኢትዮጵያ የገበያ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሀብቶች በአገሪቱ ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመሳተፍ የወደብ አማራጭ አንዱ መስፈርታቸው በመሆኑ ኢንቨስተሮች በስፋት እንዲገቡ ያደርጋል። በሁለቱም ሀገራት ወደ ወደብ በሚወስደው መስመር ላሉ ነዋሪዎችም ሆነ ኮሪደርን ተጠቅመው ለሚንቀሳቀሱት የሚጠቅሙ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችም ይከፈታሉ። ከትንንሸ የጎዳና ላይ ንግድ ጀምሮ በየመንገዱ ያሉ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በተለይም እንደ ጋራዥና ሆቴል በመሳሰሉት በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ አይቀርም የሚሉት አቶ ክቡር ገና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀጣናው እንደ አንድ ገበያ መዳረሻ የሚታይ በመሆኑ ሠላም ሲሰፍን የበርካታ አገሮች ትኩረት ወደእዚህ መሳቡ እንደማይቀር ይገለፃሉ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተፈራረመው የነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አንዱ ማሳያ ነው፤ ይህ የጅቡቲንም ሆነ የሞምባሳንም በሱዳንም በኩል ያሉትን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። ይህ የሚያሳየው የተወሰነው ውሳኔ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለውን ጠቀሜታ ነው።
የኢንዱስትሪ ግብዓት የእርሻ ምርት ልውውጡ በራሱ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው፤ ይህ ደግሞ በተለይ ለአማራና ትግራይ ክልል እንዲሁም ከፊል አፋር ጥቅሙ የጎላ ነው። የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መዳበር የህዝብ ለህዝብና የመንግሥት ለመንግሥት ትስስሩን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ የመንግሥትና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ ደግሞ በአንፃሩ የተረጋጋና ዘለቄታዊነት ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲፈጠር መሰረት ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።
አቶ ክቡር ገና አክለው እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ወደቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ቀድሞ የነበረው መሰረተ ልማት በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል መታደስ አለበት። ይሄ የሚሆነው ደግሞ በ ሁ ለ ቱ ሀገራት አማካይነት ነው። በተያያዘ የ ታ ክ ስ አከፋፈል፣ የዜጎች እንቅስቃሴ፣ የንግድ ሥርዓቱ ሁሉ በስምምነት ላይ በተመሰረተ የህግ አግባብ ሊሆን ይገባል። እንዲህ አይነት የንግድ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ እንኳን በሁለት ሀገራት መካከል በአንድ ሀገር ውስጥም ቢሆን የተወሰኑ ከተሞች የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ይኖራል፤ የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር የህግ ማእቀፍ ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃ ሚነት ዘላቂ ለማድረግ ግን ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ሊያጠ ናክሩ የሚችሉ ስምምነቶችና አንዳንድ ሥራዎች በስፋት ሊሠሩ ይገባል። ከነዚህም መካከል ታክስንና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በተመ ለከተ ከግምት ውስጥ መግባት ያላቸው ሂደቶች ናቸው። የንግድ ልውውጥ ብቻ ሳ ይ ሆ ን የህዝብ ለህዝብ ትስስሩም አብሮ ስለሚሄድ የማህበራዊ ግንኙነቱም ላ ይ መሠራት አለበት።
ለምሳሌ በአውሮፓ በስምምነት ያለ ቪዛ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ መንቀሳቀስ ይቻላል፤ በኢትዮጵያና በኤርትራም በኩል እስካሁን የቪዛ ጥያቄ አልተነሳም፡ ፡ ነገር ግን ይህንን በወረቀት ላይ በሰፈረና የሁለቱም ሀገራት ደህንነት በማይነካ እንዲሁም ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ዓለም አቀፍ የንግድ ህግን በመከተል ሆነ በስምምነት በሀገራቱ መካከል ለሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ የመገበያያው ገንዘብ አይነትም መወሰን እንዳለበት አቶ ክቡር አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በተከታታይ ሲያቅዳቸው የነበሩት ሁለቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች ይሄን ያላካተቱ ነበሩ። ከዚህ በኋላ ግን ተገቢው ህጋዊ ስምምነት ተደርጎ ወደቦቹ ሀገሪቱ የምታቅዳቸው እቅዶች አካል ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዶክተር ለሜሳ፣ በመንግሥት ብቻ ተይዘው የቆዩ ድርጅቶች ወደግል እንዲዛወሩ የመወሰኑን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ሲያብራሩ እንደገለፁት፤ የቀደሙት አስተዳደሮች በተወሰኑ ግዙፍ ተቋማት ላይ የነበራቸው አቋም ተመሳሳይ ነበር። አንዳንዶቹ ድርጅቶች ‹‹የሚታለቡ ላሞች በመሆናቸው ለሌሎች አሳልፈን አንሰጥም›› ሲሉም ይደመጡ ነበር።
ነገር ግን ድርጅቶች የሚታለቡ ላሞች ቢሆኑም፤ እስከ መቼ መንግሥት ብቻውን እያለበ ለህዝብ በቂ ነገር ጠብ ሳይል ይቆያል የሚለው መታየት ነበረበት። ይህንንም ኃላፊነት ወስዶ በጥናትና በጥንቃቄ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚወስን መሪ ያስፈልግ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ይህንን ሌሎቹ ደፍረው መወሰን ያልቻሉትንና ያላደረጉትን ውሳኔ በአጭር ጊዜ መፈፀም ችለዋል።
የዝውውሩ ሂደትና መጠን በጥንቃቄ መከናወን አለበት እንጂ መንግሥት እነዚህን ተቋማት ለግል ባለሀብቶች ድርሻ መስጠቱ በርካታ ፋይዳ አለው፡፡ በአንድ ወገን የውጭ ምንዛሪ ክፍተትን ይደፍናል። እስካሁን የነበረውንም የተቋማቱን የተገደበና አማራጭ አልባ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ለሜሳ እንደሚናገሩት፤ ከአንዳንድ ወገኖች ‹‹በመንግሥት ተይዘው የቆዩት ለህዝብ ስለሚጠቅሙ ነው›› የሚለው ነገር በተግባር ሲታይ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ባለፉት ጊዜያት በተግባር እንደታየው በአንድ አቅራቢ መንግሥት በሞኖፖሊ የሚያቀርበው ነገር ሁሉ ራሱ መንግሥትን ይጠቅም እንደሆን እንጂ ህዝብን ሲጠቅም አይታይም። በአንድ ወገን በቂም ባይሆን መንግሥት የሚያገኘው ገቢ በአብዛኛው መንግሥትንና በመንግሥት ዙሪያ የተደራጁ የተወሰኑ ጥቅም አሳዳጆች ብቻ ነበር ሲጠቅም የነበረው። በሌላ በኩል አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ውድድር ባለመኖሩ ህዝቡ ያጣው የዋጋም የጥራትም አማራጭ አለ።
ለምሳሌ ህዝቡ የስልክ ታሪፍ ቢወደድበት ወይንም የመብራት ታሪፍ ቢጨምርበት አልያም አገልግሎቱ ባያረካው ‹‹ከዚህ ወር ጀምሮ እቀይራለሁ፤ ከዚህኛው ተቋም ጋር ያለኝን ግንኙነት መቀጠል አልፈልግም›› የሚልበት ዕድል ስለሌለው እየተቸገረ ለመኖር ይገደዳል። አገልግሎት አሰጣጡም ሆነ ዋጋው ያልተመቸው አካል ቢኖር ያለው ዕድል ያንን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ አለማግኘት ብቻ ነው። በአየር መንገዱም በኩል በሀገር ውስጥ በረራ ያለው እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ወደግል ቢዛወሩ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ይችላል፤ የዋጋና የተለያዩ አገልግሎቶችም አማራጭ ያገኛል።
በሌላ በኩል በመንግሥት በተያዙ ተቋማት ያሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በኩል በተቋሙ ላይ ‹‹የኔ ነው›› የሚለው ስሜት ብዙ ጊዜ ስለማይታይ መንግሥት ለብክነትና ለሙስና ሲዳረግ በተደጋጋሚ ይታያል። በዚህም የተነሳ የሚያቀርበው አገልግሎት ውድና አዳዲስ ነገር የማይታይበት አማራጭ ባለመኖሩ የሚቀርብ ብቻ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ችግር በግለሰብ በሚመሩ ተቋማት በስፋት ስለማይታይና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ በመሆኑ በአጭር ጊዜም ባይሆንም በረጅም ጊዜ የህብረተሰቡን ፍላጎት የማርካት አቅሙ እየጨመረ የሚሄድ እንደሆነ ዶክተር ለሜሳ አስረድተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው የሚደረጉት ስምምነቶች ግን ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፤ ለጣልቃ ገብነት በር የሚከፍት እንዳይሆን በተለይ በመጀመሪያ ዙር በሚደረጉ ስምምነቶች ለባለሀብቱ የመወሰንና የመቆጣጠር ሥልጣን የሚሰጥ ድርሻ ሊኖራቸው አይገባም። ዘርፉን እንዲነቃቃ ብቻ እንዲሠሩ እንጂ ወደ ፖለቲካው እጃቸውን እንዲዘረጉም የሚፈቅዱ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ መዝጋት ይጠበቃል። እንዲሁም ብዙ ድርሻ ለአንድ ተቋም ከመስጠት ይልቅ የተለያዩ ተቋማት ድርሻ እንዲኖራቸው ቢደረግ ተፅእኖ የመፍጠራቸውን አቅም ይገድበዋል። በዚህም የተደበቀ አጀንዳ ቢኖራቸው እንኳ ወደተግባር ለማውረድ አዳጋች ይሆንባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ክቡር ገናም ዝውውሩ በጥንቃቄና ጠቀሜታቸው እየተፈተሸ እስከሆነ ድረስ በመንግሥት ስር ያሉ ድርጅቶች ባለሀብቶች ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ ያለውን ፋይዳ እንዲህ ያብራራሉ። በአትዮጵያ በመንግሥት ብቻ ተይዘው ያሉ ተቋማትና ለውጭ ባለሀብቶች ያልተፈቀዱ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች እድገት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ቀርፋፋ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በቂ ካፒታልና እውቀት ባለመኖሩ ስለሆነ ይህንን ክፍተት በመሙላት ተቋማቱን የሚያሳድግ አማራጭ መፈለግ ተገቢ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ በበርካታ የዓለም ሀገራት እንደሚደረገው የተወሰነ የድርሻ መጠንን ለሌሎች ልምዱም ካፒታሉም ላላቸው ድርጅቶች መስጠት እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡
አቶ ክቡር ገና፣ ‹‹ባለሀብቶች የሚመጡት ሀገሪቷ ክፍተት ያለባትን እንደ የካፒታል፣ የውጭ ምንዛሪና እውቀትና ቴክኖሎጂ ይዘው ነው። በመሆኑም ይህንን ለመጠቀም ዕድል ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ እነሱ ጥቅማቸውን ብቻ መሰረት አድርገው ስለሚመጡ ስለ ሀገርና የህዝብ ጥቅም ብለው የሚሠሩት ነገር አይኖራቸውም። በመሆኑም እየተመረጠ በመምጣታቸው ሊገኝ የሚችለው ጥቅም ከበፊቱ የተሻለ ለህዝቡም ሆነ ለመንግሥትም እንደሚሆን እየተፈተሸ እንዲገቡ ማድረግ ከተቻለ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ማግኘት ይቻላል›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደምም ወደ ግል የተዛወሩ በርካታ ድርጅቶች ነበሩ። ነገር ግን የተወሰኑት የፋይናንስ ተቋማት፣ ባንኮችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮምን ሳይዛወሩ የቆዩበት ምክንያት አለ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረጅም ጊዜ በህዝብና መንግሥት የተገነባና ከፍተኛ ትርፍ የሚያመጣ ድርጅት ነው። ወደ ግል ይዙር ሲባል ምክንያቱ በግልፅ መቀመጥ አለበት፤ አሁን ከሚሰጠው የተሻለ ትርፍ ማስገኘቱ፣ በአሁኑ ወቅት 100 ከተሞችን ማገናኘቱና መዳረሻ ያለው መሆኑ ሁሉ መታየት አለበት።
‹‹የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቴሌን ለግል ሰጥቶ ውጤታማ ሆኗል፤ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ናይጄሪና ኬንያ ባሉ ሀገራት የባለ ሀብቶች ድርሻ በጣም ሲጨምር የካፒታል ባሪያ ሲያደርጋቸው ታይቷል። በመሆኑም እኛንም ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥመን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ተቋማቱ ውጤታማነታቸው በተገቢው መንገድ ባይሆንም በረጅም ጊዜ በብዙ መስዋዕትነት የተገነቡ መሆናቸው ከግንዛቤ መግባት አለበት። አቅም ባይኖረንም የንብረቱ ባለቤት መሆን በራሱ እንደሀገር የሚያስገኘው ክብር እንዳለም መዘንጋት እንደሌለበት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ