ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው አንቂነት ወይም በእንግሊዝኛው አክቲቪስትነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ህዝብን ማሳወቅ፣ መቀስቀስና ማስተማር ነው። ይህም “ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጠንካራ የፖሊሲ ወይም የተግባር ዘመቻ” ከሚለው የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት የአክቲቪስትነት ትርጉም ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ስለሆነም የአክቲቪስትነትን ሥራ የሚሰራ ማለትም በአንድ የተወሰነ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን የሚቀሰቅስና የሚያነቃ ሰው ነው አክቲቪስት የሚባለው።
ይሁን እንጂ “አክቲቪስት” የሚለውን ስም ማግኘት ያለበት ምን ዓይነት ሰው ነው የሚለው የራሱ የሆነ አካሄድ ያለው መሆኑን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ይገልጻሉ። ከዚህ አኳያ ስንመለከተው በተለይም አሁን በእኛ አገር ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው “የአክቲቪስትና የአክቲቪስትነት ጉዳይ” ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን እንታዘባለን። አክቲቪስትነቱ ትክክለኛውን አካሄድ ያልተከተለና ችግር ያለበት ነው። ምክንያቱም አክቲቪስትነት ሃሳብ ነው፤ አንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ፤ ሃሳብ ይዞ የሚደረግ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ ነው።
በእኛ ሀገር ግን በአብዛኛው አንድ ሰው አክቲቪስት የሚባለው ግለሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባለው የተከታይ ብዛት እንጂ በሚያነሳው ሃሳብ አይደለም። ከዚህም ባሻገር አክቲቪስትነት ግለሰቦች ከምንም ተነስተው ለራሳቸው የሚሰጡት ማዕረግ ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት በእኛ ሀገር አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚ መኖሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፣ ሁሉም ራሱን አክቲቪስት ብሎ ስለሚጠራ አራት ነጥብ አምስት አክቲቭስት ተፈጥሯል ማለት ነው።
ተመልከቱ እንግዲህ ትናንትና ማታ እራቱን ምን እንደበላ ለማሳየት የበየ ዓይነት ፎቶ የሚለጥፈውም፣ ፌስቡክ ላይ የስድብ መዓትና የግል ብሶቱን የሚያዥጎደጉደውም፣ ትልቅ ሃሳብ ይዞ ለለውጥ የሚሰራውም ሁሉም አክቲቪስት ሆነዋል። ይሄ ደግሞ ፈጽሞ አንቂ ሊሆን አይችልም፤ በሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ አንቂነት የለም፤ ተከታይ እንጂ የሚያነሳው ሃሳብ የሌለውም አንቂ ሊሆንና ሊባል አይችልም።
የአንድ አንቂ ሃሳብ ለበርካታ ሰዎች የሚዳረስና በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ ጎኑ በብዙሃኑ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ባህርይ ያለው እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከእያንዳንዱ ተግባራቸው ጀርባ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ኃላፊነት አለባቸው። ሆኖም አሁን በእኛ አገር ያለው አንቂነት ከማህበራዊ ኃላፊነት የተነጠለ ነው። ስለሆነም አገር ሁሉ ሊያፈርስ የሚደርስ ጽሁፍ እየጻፉ ራሳቸውን እንደ አክቲቪስት የሚቆጥሩ አካላት አንቂዎች ሳይሆኑ አጥቂዎችና አጥፊዎች ናቸው።
በሰለጠኑ አገራት ያሉ አክቲቪስቶች ለእያንዳንዷ ነገር ይጠነቀቃሉ። አብዛኞቹ የእኛ አገር አክቲቪስቶች ግን የሚጽፉት ይቀስቀስልኛል ያሉትን ነገር ብቻ ነው፤ የሚያነሱት ጉዳይ በሃገርና በህዝብ ላይ ሊያመጣው የሚችለውን ጉዳት አያስቡትም፤ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ረስተውታል፣ አያውቁም ወይም ሆን ብለው እያወቁ አገር ያጠፋሉ።
በዚህ ረገድ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴው በራሱ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳይኖር ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ምክንያቱም አብዛኞቹ በአክቲቪስት ስም የሚለቀቁ መረጃዎች ባለቤታቸው ማን እንደሆነ አይታወቁም። ባለቤት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ማህበራዊ ተጠያቂነትን ለመፍጠር አስቸጋሪ ነው። የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥርዓታችን ነው እንጅ አክቲቪስትነት በእኛ ሀገርም ብዙ መልካም ለውጦችን አምጥቷል። አሁንም ቢሆን በኃላፊነት ከተሰራበት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ነው። ለዚህም በርካታ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል።
እውነተኛ ንቃት መጠየቅ ነው። እውነተኛ አንቂነትም መረጃን በመጠቀም ሀገርና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት፣ ብሎም አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፊት ሆኖ መምራት ነው። የሃገርና የህዝብን ጥቅም የሚጎዱ አድሏዊ አሰራሮችን መጠየቅ ነው እውነተኛ ንቃትና አንቂነት። ህብረተሰብን በበገንዘብ፣ በስልጣን፣ በሌላም መንገድ ባገኙት አቅም ሌሎችን የሚበድሉ አካላትን መጠየቅ አንባገነኖችን መሟገት ነው ንቃት። ዋነኛ ዓላማውም ለህዝብና ሃገር ጥቅም ዘብ መቆም ነው።
በእኛ ሃገር እንደሚደረገው መረጃንና የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አገርን ለማፍረስ፣ ህዝብን ለማባላት መቀስቀስ ሳሆን እውነተኛ አንቂዎች በተቋም፣ በመንግስትና በግለሰብም ሊሆን ይችላል የሚከናወኑ ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲስተካከሉና ማናቸውም ዓይነት በደል በህዝብ ላይ እንዳይፈጸም ህብረተሰቡ መብቱንና ጥቅሙን እንዲያስከብር ግንዛቤን የሚፈጥሩና ህዝብን የሚያነቁ ናቸው። እውነተኛ አንቂ ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች ሲፈጸሙ ለምን ብሎ ይጠይቃል፣ የመንግስት ባለስልጣናትም ይሁኑ ሌሎች በደል ፈጻሚ አካላትንም በህይወቱ ላይ አደጋ የሚያስከትል እንኳን ቢሆን በፍርሃት አያልፍም፣ ለህግ እንዲቀርቡና በጥፋታቸውም እንዲቀጡ ፍትህ እንዲሰፍን ህይወቱን አደጋ ላይ እስከመጣል ድረስ በጽናት ይታገላል።
አሁን በተጨባጭ እየታየ ያለው ግን የአንቂነት ሥራ ሁሉም እንደፈለገ ዘሎ የሚገባበት አጥር የሌለው ሙያ እየሆነ መምጣቱ ነው። በዚህ የተነሳም ለራሳቸው ጥቅምና ለግል ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው የሚሰሩ አካላት በአንቂነት ስም በአጥቂነት ተሰማርተዋል። ይህም ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያሰቡ በማስመሰል ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ሃሰተኛ መረጃዎች በብዛት እንዲያሰራጩ ዕድል በመፍጠሩ ሥራውን ከፍተኛ የተዓማኒነት ችግር ውስጥ ከቶታል።
ለሕዝብ ጥቅም ከቆመው ትክክለኛው የአንቂነት ዓላማ በተቃራኒው የተሰለፈ በመሆኑ ለአንቂውና ለሙያው ትልቅ ፈተና ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪም የሃሰት አካውንቶችን በመጠቀምና ማንነታቸውን በመደበቅ አክቲቪስት መስለው የፕሮፓጋንዳ ሥራ የሚሰሩ አካላትም መኖራቸውም ሌላው ዘርፉን እየፈተነ የሚገኝ ችግር መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ።
ጠያቂነት ወይም አንቂነት ትልቅ ኃላፊነት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች መጠየቅም ከሁሉም የላቀ ተግባር በመሆኑ አንቂ ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሰራ ማንኛውም አካል አንቂ ሳይሆን “አጥቂ” በመሆኑ በሥራው ሊያፍር ይገባል። ምክንያቱም ጥፋት አያኮራም፣ ክፋት አያስከብርም። ይሁን እንጅ በህዝብ ላይ የሚያሴሩና ራሳቸው አድሏዊ አሰራርን እየተከተሉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ፖለቲከኞችንና የመንግስት ባለስልጣናትን የሚያጋልጡ ትክክለኛ አንቂዎችን ከሃሰተኞቹ ጥቅመኛ አንቂ ነን ባዮች ጋር አንድ ላይ ፈርጆ ሙያውን በጅምላ መኮነንም ሌላው በአሁኑ ሰዓት የምንታዘበው ሃቅ ነው። ስህተትም ነው።
በዚህ ረገድ ህግንና ሥርዓትን ጠብቆ በኃላፊነት የሚሰሩ አንቂዎች መኖራቸው ከምንም በላይ ለሃገርና ለህዝብ፣ ለመንግስትም አስፈላጊ ነውና ማበረታታትም ያስፈልጋል። ከራስ አልፎ ለሌሎች ጥቅም ማሰብ፣ ለመልካም ነገር ከፊት መሰለፍ፣ ዘመኑ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጃችን ላይ እንደ ልብ የሚገኘውን የመረጃንና ዕውቀትን ኃይል ለመልካም ነገር መጠቀም እውነተኛ ጀግንነት ነውና ሁላችንም ልናስብበት ይገባል እላለሁ። ዘመናችን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጃችን ላይ ያለውን የመረጃ ኃይል በከንቱ አናባክነው፣ ለመልካም ነገር እንጠቀምበት፣ ራሳችንን፣ ሃገራችንን እና ዓለማችንን በአዎንታ ለመለወጥ እንጠቀምበት። በተለይም ለትውልድ ተጋሪ አቻዎቼ ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት ነው።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014